Saturday, 15 June 2013 10:56

የኢትዮጵያ ሱማሌ ለካ ፍቅር ነው!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

እንደ ዓለት የጸና ታሪክ፣ እንደ ፏፏቴ የሚፈስስ ዜማ የሚያፈስሱ ከንፈሮች፣ የልብ አፍንጫ የሚነቀንቅ የፍቅር መዓዛ ያለውን የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ለመጎብኘት ወደ ኦጋዴን ስንበርር፣ አውሮፕላኑ በሁለት ክንፎቹ ሲበር፣እኛም ሺህ ክንፎች ያወጡ ልቦች ነበሩን፡፡ ኦጋዴን ገብተን ፈንጂ አየር ላይ ከነወንበራችን ሲያንሳፍፈን፣ኦብነግ መንገድ ላይ ቆርጦ ሲማርከን…እና ሌሎችም ሃሳቦች ነበሩብን፡፡ ኋላ እንደሰማሁት ብዙዎቻችን በዚህ ቅዠት ውስጥ ነበርን። ደሞ ታሪክ የማወቅ ጉጉትም አድሮብናል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሶማሌዎች፤ ውሳኔ ህዝብ የሰጡበትን ታሪካዊ ቦታ ማየት፡፡ አውሮፕላኑ ሲበርር እኔ አጠገብ ከተቀመጡት የአማራ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊ ጋር ጥቂት አወራን፡፡ እኔ የነበርኩበት አውሮፕላን የመጀመሪያው ዙር በራሪ ሲሆን የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለብርሃንም ነበሩና እያንዳንዳችንን በየመቀመጫችን እየመጡ ሰላምታ ሰጡን፡፡

አፈ ጉባዔው ከሰው ጋር ያላቸው ቅርርብ አስደማሚ ነው፡፡ ጎዴ ስንደርስ የኢትዮጵያ ሶማሌ ሰማይ፣ በጥቁር አድማሳት አይኖቹን ኩሎ ነበር የጠበቀን። ከአውሮፕላን ስንወርድ ህዝቡ የናፍቆት ዓይኖቹን እንደ ችቦ እያበራ…እንደወንዝ በሚፈስስ ዜማ…እንደ ቄጠማ እየተወዛወዘ ተቀበለን፡፡ እኛም ሲቃ በተሞላ ደስታ እጆቻችንን እያውለበለብን አጸፌታውን መለስን፡፡ እውነትም የኢትዮጵያ ሶማሌ ፍቅር ነው። እውነትም ይወዱናል፡፡ በአይኖቻቸው ላይ ያነበብነው ፍቅር ሌላ ፍቅር በልባችን ወልዶ ብዙዎቻችን በተመስጦ ውስጥ ወደቅን፡፡ “ይህን ህዝብ ለምን በኪናዊ ስራዎቻችን አላየነውም

” በሚል ራሳችንን ወቀስን፡፡ ሰዓሊው እጁ ነደደ፤ደራሲው በአርምሞ ውስጡ ታመመ፤ሙዚቀኛው ነፍሱ ታመሰች፡፡ የሁሉም ልብ በየመስመሩ ፈሰሰ። የሁሉም ሰው ነፍስ በኢትዮጵያ ሶማሌዎች ፍቅር ተጎረሰ፡፡ ሶማሌ የሚለው መጠሪያ “ሶሜ” በሚል ቁልምጫ እስኪለወጥ የከያኒውን ልብ ወሰዱት፡፡ በመጀመሪያው ቀን የጎዴ አዳር ብዙዎቻችን ፈራን፤ በተለይ እባብና ጊንጡን፡፡ ከፊላችን ያደርነው ቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ ነበር፡፡ በተለይ ለተጓዡ ሁሉ የሳቅ ምንጭ ከነበረው ሽመልስ አበራ (ጆሮ) ጋር ልዩ ጊዜ አሳልፈናል። ጊንጥና ጃርት የየራሳቸው ታሪክ ነበራቸውና ሰው በሳቅ አልቆ ነበር፡፡ ያ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ፕሮግራሞችና የጥበብ ዝግጅቶች የሚታወሱ አስቂኝ ነገሮች በሙሉ ተዘርግፈዋል፡፡ ሽሜ ዋናው ኮሜዲያን ይሁን እንጂ ታገል ሰይፉና ሌሎቹም ማለፊያ መዝናኛ ፈጥረውልን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ዜማዎችን ሳንረሳ ነው ታዲያ፡፡ እነዚህ ሰዎች በሙዚቃቸው ሃይል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤውን በተደጋጋሚ ከመቀመጫቸው አስነስተው አስጨፍረዋል፡፡

ትከሻ-ለትከሻ ገጥመው አብረው ጨፍረዋል፡፡ በጎዴው አዳራችን እባብና አይጥ ፈርተን አንዳንዶቻችን ፍራሾቻችንን ወደ መሃል ለመሳብ ሞክረናል፡፡ ታዲያ ሽመልስ አበራ በሳቅ ሆዳችንን እያቆሰለው ሸሽተን ወደመኝታችን ሄድን፡፡ ግና አላመለጥንም፤ እየተከተለ ኮረኮረን፡፡ ማምሻውን እንናፈስ ብለን ወደከተማ ስንወጣ ሰው ሁሉ ዝነኛ አርቲስቶችን በስማቸው ይጠራ ነበር። ሽመልስ አበራ፣ ጥላሁን ጉግሳና ሌሎቹ ከየአቅጣጫው ይጠሩ ነበር፡፡ እንደ አበበ ባልቻ መከራ ያየ፣ የተከበበና ፎቶ በመነሳት የተጨናነቀ ግን አልነበረም፡፡ ሁሉም ከተማ፣ ሁሉም ሰው ቀድሞ የሚጠይቀው አስናቀ መጥቷል እያለ ነው፡፡ እንዲያውም ደገሀቡር ከተማ ምሳ በልተን የቡና ወረፋ ስንጠብቅ፣ አንድ ጠንከር ያሉ አዛውንት እንዲህ አሉ፤ “ያ አስናቀ መጥቷል?” እኛም “አዎ መጥቷል” አልናቸው፡፡ ሰውየው ተቆጥተው “…እርሱ’ኮ ነው የድግሳችንን ወጥ ያሳረረብን… የ40 ቀን መታሰቢያ ድግሳችንን ያበላሸው!” አሉ፡፡ ስለሁኔታው ሌሎችን ጠየቅን “ሰው ለሰው በኢቴቪ ሲጀመር አስናቀ መጣ፣ አስናቀ መጣ!” ተብሎ ሴቶቹ ሁሉ ቴሌቪዥን ሊያዩ ወጡ፡፡

በዚህ መሃል ነው ወጡ አረረ የተባለው፡፡ ሰውየው ግን “ቆይ” ብለው እየዛቱ ወደ መሀል ከተማ ሄዱ፡፡ “አበበ ባልቻ እግዜር ይሁንህ!” አልን፡፡ በማግስቱ ጧት ወደ ታሪካዊቷ ከተማ ካሊ ነበር የተጓዝነው፡፡ እኛ መኪና ውስጥ ድምፃዊው ሞገስ ተካ፣ የሙዚቃ ሃያሲው ሠርፀ ፍሬስብሀት፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና ሁለት የአፋር ክልል፣ ሁለት የጋምቤላ ክልል ጋዜጠኞች አሉ፡፡ አልፎ-አልፎም ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ አብሮን ይሆናል፡፡ አርቲስት አለለኝም ብቅ-ጥልቅ ይላል፡፡ ካሊ ስንሄድ ትንሽ አቧራ ነገር ነበር፡፡ ይሁንና ታሪኩ ለብዙዎቻችን የሚያጓጓ ነው፡፡ ያ ቦታ የኢትዮጵያ ሶማሌዎች፤ “ውሳኔ ሕዝብ” የሰጡበት ነው፡፡ እንግሊዛዊያን የሀገር ሽማግሌዎችን ሰብስበው “ከኛ ጋር ትሆናላችሁ ወይስ ከኢትዮጵያ?” ብለው ምርጫ የሰጧቸው ቦታ ነበር፡፡ አንድ የጉዟችን አባል ሲናገር እንደሰማሁት፤ እንግሊዞች እሾህ ላይ ነጠላ አንጥፈው ነጠላውን እሾህ ሲነክሰው “ኢትዮጵያ ማለት እንዲህ ናት!” ብለው አስጠንቅቀዋቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌዎች ግን በዚያችው አደባባይ፣ ሰማይና መሬት እያዩ፣ ፀሐይ እየታዘበች፣ ቁጥቋጦው እያሸበሸበ “እኛ ኢትዮጵያዊያን ነበር፤ አሁንም ነን፣ ወደፊትም በኢትዮጵያዊነታችን እንዘልቃለን” በማለት ቁርጡን ተናገሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌዎች ኢትዮጵያዊ የሆኑት በመወለድ ብቻ አይደለም፡፡ በምርጫም ነው፡፡ ምንም እንኳ ይህንን የጠራ ባህር ሕዝብ ታሪክ ለማበላሸት አፈር ቢበትኑም ዛሬም ግን ሕዝባችን ከማናችንም በተሻለ የሀገር ፍቅር በልቡ የሚነድድ፣ ነድዶም የማያባራ ሕዝብ ነው፡፡

ለዚህም ነበር እርጥብ ቅጠል ይዞ በፍቅር ነበልባል በታጀቡ አይኖቹ የተቀበለን፡፡ ከጐዴ ከወጣን በኋላ የደናን ከተማ ሕዝብ ግራና ቀኝ ተሰልፎ ነበር፡፡ ቀብሪደሀር ስንሄድ ወጣቶቹ በፉጨትና በአድናቆት ተቀበሉን፡፡ በሚገባ ባላጣራም አንድ ከሙቀቱ ጋር በቢራ ሞቅ ያለው አርቲስት “አምላኬ ሆይ! እንደታቦት በሕዝብ ታጅቤ በእልልታና በሆታ እሸኝ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?” እያለ በአድናቆት ደረቱን ይደቃ ነበር፡፡ በዚህ ጉዞ የኔ ትዝታም ደማቅ ነው፡፡ ቀብሪደሀር ከተማ አንድ ሱቅ ገብቼ ደብተር ልገዛ ስል፤ ሻጩ ወጣ የያዝኩትን ብር ወደ እኔ ገፍቶ በነፃ ሊሰጠኝ ሲል ገፍቼ መለስኩለት። ቀጥሎም የታሸገ ለስላሳ መጠጥ ለመግዛት መቶ ብር የሰጠሁት መስሎኝ ሁለት መቶ ብር ሰጥቼው ኖሮ መቶ ብሩን ሲመልስልኝ አንጀቴ ተላወሰ፡፡ ወገኔ ባይሆን፣ ባይወድደኝ መች ይህን ያደርግልኝ ነበር? የሚለው ነገር ለሕዝቡ ያለኝን ፍቅርና ክብር ጨመረው። ታዲያ በየከተማው መሀመድ ጠዊል፣ ሀብተሚካል ደምሴ፣ ዘውዱ በቀለ (ወላይትኛ) በባህላዊ ዜማቸው ሕዝቡን እንደማዕበል ነቅንቀውታል፡፡ ቀብሪደሀር ስንገባ 12ኛ መተማ ክፍለ ጦር ግቢ ነበር የተስተናገድነው። የሠራዊቱ አባላት ዳስ ተክለውልን በሚደንቅ መስተንግዶ፣ በሀገራዊ ፍቅር የምንገባበት እስኪጠፋን ተቀብለውናል፡፡ ይህ ክፍለ ጦር ግቢ፣ በገበየሁ አየለ “ጣምራ ጦር” መፅሐፍ ውስጥ የተጠቀሰ ሲሆን በየመንገዱ ያየናቸው ኩይሳዎች፣ መንገዶችና መልከዐ ምድራዊ አቀማመጦች ሁሉ ወደኋላ መለስ ብለን ገፆቹን በትዝታ እንድንገልጥ አድርገውናል፡፡

ከከተማ ወጥተን ደገሀቡር ስንገባ፣ የደገሀቡር ሕዝብም በሚገርም ሁኔታ ተቀበለን፡፡ መቼም ደገሀቡር የሸጋዎች ሀገር ናት፡፡ እንደ ቄጠማ የሚወዛወዙ ቆነጃጅት ነበሩ፣ ጣፋጭ ዜማ የሚያሰሙት፡፡ ወንዶችም ቁመናቸው የሚያምር፣ ፈገግታቸው ልብ የሚነካ ለዛ የተሞሉ ነበሩ፡፡ ታዲያ እዚህ ግቢ መኝታ ክፍሎች ስለነበሩ የቡድናችን አባል ሽመልስ አበራ ጡንቻም ስላለው ሁለት ክፍል ይዞ ጠበቀን፡፡ እኔ፣ ተስፋዬ ገ/ማርያም (ብሔራዊ ቴአትር) መልካሙ ዘሪሁን (ፀሐፌ ተውኔት) አንድ ክፍል፣ ውድነህ ክፍሌ፣ ታገል ሰይፉና ሽመልስ ከኛ ትይዩ ገቡ፡፡ የምሽቱን ደማቅ የበአል አከባበር ተቀላቅለን ተመልሰን ሻወር ከወሰድን በኋላ ወደየመኝታችን ገብተን ተኛን፡፡ ለካ ሦስት ሰዎች መኝታቸው ከመግባታቸው በፊት በአካባቢው ስለነበረው አራዊት ጠይቀዋል፡፡ የጠየቁት መኮንንም ምንም የሚያስፈራ ነገር እንደሌለ ይነግራቸዋል፡፡ ይሄን ብሎ ግን አላበቃም፡፡ “ብ…ቻ አንድ… ነገር አለ” አላቸው፡፡ ሳሚና ታገል ጆሮ ሰጡት። ተረከላቸው፡፡ “በአርጃም ይባላል፡፡ አዞ የመሰለ ሆኖ አራት እግሮች አሉት፤ ርዝመቱ ሁለት ሜትር ያህል ይሆናል፡፡ እንቅልፍ ካልወሰዳችሁ አይናካም፣ ግን ሰው እንቅልፍ እንዲወስደው የሚያደርግ መላ አለው - በፊት እግሮቹ ደባብሶ እንቅልፍ ያመጣል፡፡ አይናከስም፣ ብቻ ሁለት ምላሶች አሉት፤ እንቅልፍ የወሰደው ሰው ሲያገኝ ሁለቱን ምላሶቹን አፍንጫ ውስጥ ሰድዶ አንጐልን ይመጥጣል፡፡

ልክ ደም መምጣት ሲጀምር ግን ትቶ ይሄዳል” ይላቸዋል፡፡ ጭንቅ በጭንቅ እንደሆኑ ይመጣሉ፡፡ ሙቀት ስለነበር በረንዳ አንጥፈው ለመተኛት ቢፈልጉም “አርጃኖ” ትዝ ይላቸውና ወደ ክፍላቸው ይገባሉ፡፡ ክፍላቸው ሲገቡ የሆነች ተባይ ታሳድዳቸውና መኝታ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይሄኔ የመኪናው ረዳት ወደ መግቢያው ላይ፣ ቀጥሎ ታገል ሰይፉ፣ ከዚያ ውድነህና ሽመልስ በተከታታይ ይተኛሉ፡፡ ታገል ጧት እንደነገረን፤ ከውጭ ንፋስ ሲያንቋቋ እርሱ አርጃኖን ያስባል፤ ተኝቼ እያለ አንጐሌን ይመጠው ይሆን? ሲል ያስብና “አይ ከኔ ቀድሞ ረዳቱ ስላለ እርሱን ሲገድል እሰማለሁ!” እያለ ሲያብላላ ይነጋል፡፡ ሽመልስ አድምቆ ያወራልን ሌላው ወሬ አብረን የሰማነው የአለምዬ ሶራ ዘፈን ተወዛዋዥ ነው። የሰቆጣው ልጅ ግንባሩ ላይ ትልቅ መስመር ነገር ጠባሳ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ስለዚያ ሲተርክልን ከነብር ጋር ተናንቆ ታግሎ በመጨረሻው ነብሩን እንደገደለው ሲነግረን፣ ሁላችንም በግርምት ፈዝዘን ነበር፡፡ በማግስቱ ግን ሽሜ ምርጥ አድርጐ ተወነበት፡፡ ያ ሁሉ በመቀመጫው የፈሰሰ አርቲስት፣ ሆዱን እየያዘ ሳቀ፡፡ ሽሜ ምርጥ ኮሚዲያን ሆኖ ነበር፡፡

በዚህ ሁሉ ውስጥ ታዲያ የኢትዮጵያ ሶማሌዎች ፍቅር የሚረሳ አልነበረም፡፡ ሁላችንም ይህ ሕዝብ ፍቅር ነው! ውለታ አበዛብን! ፎንቃ አስያዘን እያልን ተገረምን። አትታዘቡኝና እኔ አሁን የኢትዮጵያ ሶማሌዎችን ሳይ እቅፍ አድርገህ “ሳማቸው ሳማቸው” ያሰኘኛል፡፡ እኔ ብቻ አይደለሁም፤ አጠገቤ የነበሩት ሁሉ ከጅጅጋ ስንወጣ በስደት ወደሌላ ሀገር እንደምንሄድ ተሰምቶን ነበር፡፡ ያ ፈገግታ… ያ… ዜማ… ያ ፍቅር እንዴት ሊረሳ ይችላል? በምን? ናፈቁን! ጅጅጋ ከተማ ገብተን በመጨረሻው ቀን መስተንግዶ ላይ የተሰማንን ገለጥን፣ ግጥሞች አቀረብን፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እጅግ ውብ የሆነ ወግ አቀረበልን! …እያጣፈጠ አሳቀን፡፡ ጅጅጋ፣ የክልሉ እንግዶች ማረፊያ (Guest house) ግቢ ውስጥ ሦስት ነብሮች ታስረው ነበር። ታዲያ እነዚህን ነብሮች ያየ ሁሉ አብሯቸው ፎቶ መነሳት፣ ቪዲዮ መቅረፅ ጀመረ፡፡ ታገል ሰይፉ የአንዱን ነብር አንገት ደባበሰ፣ ሌሎችም አብረውት ፎቶግራፍ ተነሱ፡፡

ፀሐፌ ተውኔቱ ውድነህ ክፍሌ ግን ከሌሎች የተለየ እጣ ደረሰው፡፡ ነብሩ ሳያስበው ሁለት እጁን ቧጠጠው፡፡ ይሁን እንጂ በራሱ አንደበት እንደገለጠው፤ በሚያስደንቅ ጥበብና ስትራቴጂ ተጠቅሞ ራሱን አዳነ፡፡ ይህም በሳቅና ፌሽታ ተመንዝሮ ተሳቀበት፡፡ በጅጅጋ የማይረሳው ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ሶማሌ ፕሬዚደንት ንግግር ነበር። ሰውየው የማይቀመሱ እሳት፣ የሚጥሙ ጣፋጭ፣ የሚያስቁ ኮሜዲያን ነገር ናቸው፡፡ በመጨረሻው ቀን ስንብት አዳራሽ በገባን ቀን ሰውየው ንግግር ሊያደርጉ ነው ሲባል ሁላችንም ፈራን። አሰልቺ ንግግር ይሆናል ብለን ሃሞታችን ፈሰሰ። እንዳሰብነው ግን አልሆኑም፡፡ ያገር አርቲስት ልቡ እስኪፈርስ እየሳቀ እርስ በርስ እየተያየ፣ እጁ እስኪቃጠል እያጨበጨበ፣ ስብሰባው ተፈፀመ፡፡ የመጨረሻው ጭብጨባ ድምፅም እስካሁን በውስጤ ያስተጋባል። ሰውየው የዋዛ አይደሉም፤ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ሶማሌ መልክ ለማምጣትም ዋነኛው ተዋናይ፣ ደማቁ ቀለም እርሳቸው ናቸው ይባላል፡፡ ጉዟችን ወደ ሐረር ሲቀጥል የአቀባበል ውበት፣ የዜማው ሃይል የፈገግታው አቅም እየቀነሰ ሄዷል፡፡ ብዙ ነገሮች እየተዝረከረኩ አሰልቺ እየሆኑ መጡ፡፡ አብረውን የነበሩ ታዋቂ ሰዎች እጃቸውን እያነሱ ትርኪ ምርኪውን ሲያወሩ የብዙዎችንን ልብ ሰበሩት፡፡ መታወቅና ማወቅ ይለያያልና! ብዙ ዘባርቀው አንገታችንን አስደፉን፡፡ ጥሎ የማይጥል አምላክ፣ ሰርፀ ፍሬ ሰንበትን አስነስቶ “ኧረ እንደዚህ ብቻ አይደሉም፤ እንደዚህም ናቸው” የሚያሰኝ ምርጥ ሀሳብ፣ በሳይንስ የተደገፈ ጥበብ አወራ፡፡ ስለ አርአያነትም ረገጥ አድርጐ ገሰፀ፡፡ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይም “ማሳሰቢያ” ብሎ በድሬዳዋው አዳራሽ አፈጉባኤው በተገኙበት አፋቸው እንዳመጣላቸው የሚናገሩ ሰዎችን አደብ ግዙ አለ፡፡ ድሬዳዋ ከተማ ሌላው ያየነው ነገር ሕፃናት ተሰብስበው ጥላሁን ጉግሳን “ዘሩ…ዘሩ…ዘሩ!” እያሉ ሲከብቡት ነው፡፡

መሄጃ ከልክለውት ነበር፡፡ ሳላጋንን ፖሊሶች ልጆችን እስኪለከልሉ ደርሷል፡፡ ይህ ነገር ያሳየኝ ልጆች የእሱን “ቤቶች” ድራማ የሚመለከቱት ከሆነ ለቀጣዩ ትውልድ መልካም ዘር መዝራት እንደሚገባው ነው፡፡ በመጨረሻው የጅጅጋ ሽኝት ቀንም ዘነበ ወላ፣ ሠራዊት ፍቅሬ፣ ሰርፀ ፍሬሰንበት፣ ዳንኤል ወርቁ፣ ንግግር አድርገዋል፡፡ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራና እንዳለ ጌታ ከበደ ግጥም ያቀረቡ ሲሆን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም ምርጥ ወግ አቅርቧል፡፡ ደስ የሚሉ ቀናት አሳልፈናል፡፡ በትዝታ የሚታተሙ ዜማዎች አድምጠናል፡፡ ስቀጥል ፍቅር ወድቀናል ኢትዮጵያ ሶማሌ ፍቅር ነው ብለናል፡፡ ለሴት ልጆች ባላቸውም ክብር ተደምመናል ሴት ክቡር ናት!

Read 4490 times