Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 November 2011 08:41

ለሚኒስትር የሚዘጋጅ መኪና ተቀንሷል - ኦባማ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአገራችን ባለስልጣናትስ የግድ የሚሊዮን ብር መኪና መያዝ አለባቸው?
ዘመኑ፤ የሶስኛው መንገድ (የቅይጥ ኢኮኖሚ) ቀውስ የሚተረክበት ዘመን ነው
በእዳ ተዘፍቀው በቀውስ እያታመሱ ያሉት የአሜሪካ እና የአውሮፓ መንግስታት፤ ወጪዎቻቸውን ለመቀነስ እዚህም እዚያም እየተውተረተሩ ናቸው። ነገር ግን፤ ብዙዎቹ ጊዜያዊ እፎይታን ለማግኘት እንጂ፤ የችግሩን ስረ መሰረት ነቅለው ለመጣል የተዘጋጁ አይመስሉም። መንግስታት በየአገሩ እጆቻቸውን ኢኮኖሚ ውስጥ ከማስገባትና ከማማሰል ተቆጥበው፤ በስር ነቀል ለውጥ ወደተሟላ የነፃ ገበያ ስርአት ካልተራመዱ በቀር፤ ወጪዎቻቸውን በአግባቡ መቀነስና ከእዳ መውጣት አይችሉም። የባራክ ኦባማን ሙከራ ተመልከቱ።

ወጪ ቅነሳ - የባለስልጣን መኪና
ለመንግስት ሰራተኞች የሞባይል ስልክ እና የላፕቶፕ ኮምፒተሮችን ለመስጠት የሚውል ወጪ እንዲቀነስ ትእዛዝ የሰጡት ባራክ ኦባማ፤ የባለስልጣናት የመኪኖች ቁጥርም ዝቅ ማለት አለበት ብለዋል - ረቡእ እለት። ለበታች ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆን፤ ለሚኒስትር ጭምር የሚዘጋጅ የመኪና አገልግሎትም ከአንድ መብለጥ የለበትም ተብሏል። “ምነው ይሄን ያህል?” ያሰኛል። በድሃዋ አገር በኢትዮጵያ፤ የመንግስትና የባለስልጣን መኪኖች ብዛት ብቻ ሳይሆን በጣም ውድ መሆናቸው ሲታይ፤ የአሜሪካ ባለስልጣናት አያሳዝኑም?
ግን፤ የአገራችን ባለስልጣናትም ቅያሬ መኪኖችን ከመደርደር ይልቅ፤ አንድ መኪና ብቻ ቢኖራቸው... በዚያ ላይ፤ ሚሊዮን ብር የሚያስወጣ መኪና ከሚገዛላቸው ይልቅ፤ በተመጣጣኝ ዋጋ (ትንሽ ገንዘብ ባይሆንም ለምሳሌ በ200ሺ ብር) የተገዙ መኪኖችን እንዲጠቀሙ ቢደረግስ? እንኳን በድሃ አገር ውስጥ ይቅርና በአሜሪካም፤ የመንግስት ወጪ ኡኡ የሚያሰኝ ሆኗልኮ። ኦባማ፤ የባለስልጣናትን መኪኖች ከመቀነስ በተጨማሪ፤ ሌሎች ተመሳሳይ ትእዛዞችንም አስተላልፈዋል።
የአገር ውስጥ ገቢ መስሪያ ቤት ሰራተኞች፤ ግብር ለመሰብሰብ ሲሰማሩ ለመጓጓዣ የሚያወጡት ገንዘብ ከፍተኛ እንደሆነ በመጥቀስ፤ ጉዞዎቹ በ30 በመቶ ገደማ ይቀነሳሉ ተብሏል - ስራቸውን በኢንተርኔትና በቪዲዮኮንፈረን ዘዴዎች በማከናወን። ህጎችና ሰነዶች በወረቀት ከማተም ይልቅ፤ ያለ ወጪ በኢንተርኔት ለሁሉም ዜጋ እንዲሰራጭም ተወስኗል።
በባራክ ኦባማ የወጪ ቅነሳ ትእዛዝ በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ የሚድን ቢሆንም፤ ከጠቅላላ የመንግስት ብክነት ጋር ሲነፃፀር ኢምንት ነው። ለምሳሌ፤ ባለፉት ሁለት አመታት “ፋኔ ሜይ” እና “ፍሬዴ ማክ” የተሰኙ መንግስታዊ ተቋማት፤ 170 ቢሊዮን ዶላር ብክነት እንደታየባቸው አሶሼትድ ፕሬስ በሰሞኑ ዘገባው ገልጿል። በተለይ፤ “ፋኔ ሜይ” አሁንም በሶስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ7 ቢ. ዶላር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበትና ተጨማሪ 8 ቢ. ዶላር ድጎማ ከመንግስት ጠይቋል። ለመሆኑ የተቋሞቹ ስራ ምንድነው? በመንግስት የሚተዳደሩ የብድር ዋስትና ተቋማት ናቸው - ፋኔ ሜይ እና ፍሬዴ ማክ።
ከባንክ ተበድረው ቤት መግዛት የሚፈልጉ ሰዎች፤ ለዋስትና የሚያስመዘግቡት ንብረት ወይም ቋሚ የገቢ ምንጭ ሊኖራቸው ይገባል አይደል? አዎ፤ አበዳሪዎች በየመንገዱ ገንዘባቸውን መበተን እስካልፈለጉ ድረስ፤ የተበዳሪውን አቅም መርምረው ለማረጋገጥ ይጥራሉ።
መንግስት፤ “ድሆችን ለመርዳት” በሚል ሰበብ ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ ግን፤ ነገሩ ሁሉ ይለወጣል። ተበዳሪዎች ንብረትም ሆነ ገቢ ባይኖራቸውም ችግር የለውም፤ ማንም ሰው ከባንክ ተበድሮ ቤት መግዛት ይችላል - ፋኔ ሜይ እና ፍሬዴ ማክ ዋስትና ይሆኑለታል። ተበዳሪው እዳውን መመለስ ባይችል፤ ሁለቱ ተቋማት እዳውን ይከፍላሉ ማለት ነው። በዚህ መንገድ ነው፤ ሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ ኪሳራና ብክነት የሚደርሱት። በሚቀጥሉት ሁለት አመታትም ብከነቱ 220 ቢ. ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት ኤፒ ዘግቧል።
መንግስት እጆቹን ኢኮኖሚ ውስጥ እስካስገባ ድረስ፤ የገንዘብ ብክነት ማቆሚያ የለውም። የአሜሪካ መንግስት፤ “ኢኮኖሚውን ለማነቃቃትና የስራ እድሎችን ለመፍጠር” በሚል ሰበብ፤ ጄነራል ሞተርስ ለተሰኘው ኩባንያ የሰጠው ብድርም ተመላሽ የሚሆን አይመስልም። የኩባንያውን የአክሲዮን ድርሻ በከፊል በመያዝ ነው፤ 52 ቢ. ዶላር ብድር ለኩባንያው እንዲለቀቅ የተወሰነው። ነገር ግን በመንግስት የተያዘው የአክሲዮን ድርሻ ዋጋ፤ ሰሞኑን ወደ 12 ቢ. ዶላር ወርዷል - 40ቢ ዶላር ኪሳራ መሆኑ ነው።
በየትኛውም አገር ቢሆን መንግስት ሲባል፤ ገንዘብ እጁ ውስጥ አይግባ እንጂ ከገባ፤... የየትኛውም ፓርቲ ቢሆን መንግስት ሲባል፤ ኢኮኖሚ ውስጥ አይግባ እንጂ ከገባ... በቃ፤ መንግስትን የሚፎካከር ገንዘብ አባካኝ የለም ማለት ይቻላል። መንግስት፤ እንዲህ ኢኮኖሚን ለማነቃቃትና ለስራ አጦች የስራ እድል ለመፍጠር በሚሉ ሰበቦች፤ ወይም ለጤናና ለትምህርት በሚሉ ምክንያቶች የሚያባክነው ገንዘብ ከመብዛቱ የተነሳ፤ የአሜሪካ መንግስት የ14 ትሪሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ ገብቷል።
ባራክ ኦባማ፤ ለወሬ ለይስሙላ ያህል ካልሆነ በቀር፤ ጥቃቅን ወጪዎችን በመቀነስ የእዳ ቀውሱን ማቃለል እንደማይችሉ የሚጠፋቸው አይመስሉም። ለምሳሌ፤ በዚህ አመት ብቻ፤ የመንግስት ወጪ ከገቢው በላይ በመሆኑ፤ እንደገና በሃይለኛው እየተበደረ ነው - እናም አንድሮ የአሜሪካ መንግስት እዳ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። ታዲያ የጥቂት ሚሊዮን ዶላሮችን ወጪ መቀነስ ምን ዋጋ አለው?
ባራክ ኦባማ፤ ትልልቅ ወጪዎችንም ለመቀነስ እንደሚፈልጉ መግለፃቸው አልቀረም። ለምሳሌ፤ በመቶ ቢ. ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የባከነባቸውን፤ ፋኔ ሜይና ፍሬዴ ማክን ለማፍረስ አቅድ አዘጋጅቻለሁ ብለዋል። ነገር ግን፤ ይህም በቂ አይደለም።
በየአመቱ የ1500 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ጉድለትን ለማሟላት፤ በቦንድ ሽያጭ ብድር እያከማቸ የሚገኝ መንግስት፤... ከ14 ትሪሊዮን በላይ የብድር እዳ የተወዘፈበት መንግስት፤ ጥቃቅን ወጪዎችን በመቀነስ ወይም ሁለት ተቋማትን በማፍረስ ብቻ ከውድቀት ሊድን አይችልም። አመታዊ በጀቱን ወይም አመታዊ ወጪዎቹን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ይኖርበታል - መንግስት ከኢኮኖሚው ውስጥ እጆቹን በማስወጣትና ካፒታሊዝምን በማስፋፋት። አለበለዚያ ከቀውስ የመገላገል እድል አያገኝም።

የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ
የአሜሪካና የአውሮፓ የኢኮኖሚ ቀውስ፤ ከካፒታሊዝም (ከነፃ ገበያ) ስርአት ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስመስለው የሚናገሩ ሞልተዋል። እውነታው ግን፤ የየአገሮቹ የቀውስ ጥልቀት ሲለካ፤ ከካፒታሊዝም ያፈነገጡበትን ርቀት የሚያሳይ ነው። ከነፃ ገበያ ስርአት በማፈንገጥ፤ ኢኮኖሚውን ይበልጥ በሶሻሊዝም በመረዙት ቁጥር፤ የቀውሱ ስፋትም ይጨምራል። ለነገሩማ በቀውስ የታመሰችውን ግሪክ መመልከት ብቻ በቂ ነው - የመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኘው ፓርቲ ሶሻሊስት ፓርቲ ነው።
የአሜሪካም ሆኑ የአውሮፓ መንግስታት፤ ከጠቅላላ የዜጎች አመታዊ ምርት ውስጥ ቢያንስ 30 በመቶ ያህሉን ይነጥቃሉ፤ ይወስዳሉ። አንዳንዶቹም እስከ 50 በመቶ ያደርሱታል። በዚያው መጠንም፤ ኢኮኖሚው ውስጥ እጃቸውን ያስገባሉ ማለት ነው። ከዜጎች የዚህን ያህል ሃብት በየአመቱ የሚዘርፉና ኢኮኖሚውን እያማሰሉ የሚያደፈርሱ መንግስታት፤ የካፒታሊዝም ወይም የነፃ ገበያ አርአያ ሊሆኑ አይችሉም።
ደረጃቸው ይለያያል እንጂ፤ ባለንበት ዘመን ውስጥ በሶሻሊዝም ያተበረዘ ካፒታሊዝም በየትኛውም አገር የለም። ቅልቅል ስርአት ነው በአለማችን የነገሰው። ሶስተኛው መንገድ ይሉታል። ሙሉ ለሙሉ ካፒታሊዝምን ያልተከተለ፤ ሙሉ ለሙሉ ሶሻሊዝምን ያልተከተለ፤ የቅይጥ ኢኮኖሚ ስርአት እንደማለት ነው። ግን፤ ያዋጣል?
የሶሻሊዝም ውድቀት ያን ያህልም አከራካሪ አይደለም። ከኢትዮጵያ እስከ ሶቭዬት ህብረት፤ ከኩባ እስከ ሰሜን ኮሪያ፤ ሶሻሊዝም በረገጠበት መሬት ሁሉ፤ ዜጎች በድህነትና በረሃብ ለእልቂት ተዳርገዋል። ታዲያ መርዛማውን ሶሻሊዝም፤ ከካፒታሊዝም ጋር በማደባለቅ መልካም ውጤት መጠበቅ ሞኝነት አይደል? የተበረዘውንና የተመረዘውን ያህል... በዚያው መጠን ቀውስ መፈጠሩ አይገርምም።
የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት፤ ሶስተኛው መንገድ የተሰኘው ቅይጥ የኢኮኖሚ ስርአት የነገሰባቸው ቢሆኑም፤ ከብዙዎቹ የአፍሪካ፤ የኤስያና የደቡብ አሜሪካ መንግሰታት ጋር ሲነፃፀሩ፤ ሻል ያሉ ናቸው። ለዚህም ነው እንደ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት በድህነት የማይሰቃዩት። ለዚህም ነው፤ ለበርካታ አመታት በቀውስ ሳይንበረከኩ የዘለቁት። ግን የጊዜ ጉዳይ ነው። በሶሻሊዝም የተመረዘ ኢኮኖሚ፤ በጊዜ ካልተስተካከለ፤ ወደ ቀውስ ማምራት አይቀርለትም። እንዴት?
ሙሉ ለሙሉ የሶሻሊዝም ስርአት የነገሰባቸው አገራት፤ ከዳር ዳር በኢኮኖሚ ውድቀት እየተመቱ ሲንኮታኮቱ አይተናል። ከሶሻሊዝም ውድቀት በኋላ፤ ከ1990ዎቹ ወዲህ የነገሰው ቅይጥ ኢኮኖሚስ?
የሶሻሊዝም አሰራር በብዛት ጎልቶ የሚታይባቸው የቅይጥ ኢኮኖሚ ተከታዮች፤ (እንደ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት) ከድህነት መውጣት እያቃታቸው ወይም በማያቋርጥ ቀውስ ከአመት አመት እየተመቱ ይተራመሳሉ - ሌላው ሌላው ቀርቶ በብድር ለጥቂት አመታት እየተንገታገቱ መቀጠል አልቻሉም። ባለፉት አመታት ለድሃ አገራት የብድር ስረዛ የተደረገው ለምን ሆነና? ብድራቸውን መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ስለደረሱና፤ መውጣት የማይችሉበት ቀውስ ውስጥ ስለተዘፈቁ ነው ብድር የተሰረዘላቸው። እናም፤ ህልውናቸውን ለመጠበቅ የማያቋርጥ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ከኢትዮጵያ አመታዊ በጀት መካከል፤ 30 በመቶ ያህሉ ከውጭ እርዳታ የሚመጣ ነው። ሶሻሊዝም በጣም የገነነበት ቅይጥ ኢኮኖሚ፤ ያለ ቀውስ ለረዥም አመታት መቀጠል አይችልም።
የአውሮፓና የአሜሪካስ? የእነዚህኛዎቹ ኢኮኖሚ፤ በአፍሪካ ከሚታየው ይለያል። በአውሮፓና በአሜሪካ የሰፈነው ቅይጥ ኢኮኖሚ፤ ሶሻሊዝም በጣም የገነነበት አይደለም። ለዚህም ነው፤ በአጭር ጊዜ ሳይንኮታኮቱ እስካሁን መቀጠል የቻሉት። እንዲያም ሆኖ ከቀውስ አላመለጡም፤ አያመልጡምም - ቅይጥ ኢኮኖሚን (በሶሻሊዝም የተመረዘ ካፒታሊዝምን) እስከተከተሉ ድረስ። የመርዙ መጠን አነስ በማለቱ፤ ጉዳቱን ለበርካታ አስርት አመታት ተቋቁሞ መዝለቅ ቢቻል እንኳ፤ ከአመት አመት እየጠራቀመ ሲንከባለል ቆይቶ፤ ይሄውና ዛሬ እንደምናየው በቀውስ ታምሰዋል።
አሁን ያለንበት ዘመን፤ “የሶስተኛው መንገድ (የቅይጥ ኢኮኖሚ) የውድቀት ዘመን” ልንለው እንችላለን። ከ1970ዎቹ ጀምሮ እስከ 1990 የነበሩትን አመታት፤ በጥቅሉ “የሶሻሊዝም ውድቀት ዘመን” ናቸው። ከ2008 ወዲህ ያሉት አመታት ደግሞ፤ የቅይጥ ኢኮኖሚ ውድቀት ዘመን።

 

Read 4711 times Last modified on Saturday, 12 November 2011 08:51