Saturday, 22 June 2013 10:13

“…Puberty...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(13 votes)

በአለማችን የተለያዩ ሰነዶች እንደሚያረጋግጡት ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ከታዳጊነት እድሜያቸው ጀምሮ የፈጸሙቸው የወሲብ ታሪኮች አሉ፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ ከ1939-2012 ዓ/ም ድረስ ከተመዘገቡት መረጃዎች ውስጥ ሁለት ታሪኮችን እናስነብባችሁ ዋለን፡፡ አንዱ በፔሩ የተፈጠረ ሲሆን ታሪኩ እንደሚከተለው ነው። .....ሕጻኑዋ የአምስት አመት ከ7 ወር እድሜ አላት፡፡ የልጅቱዋን ጤንነት በተመለከተ ወላጆችዋ ክትትል በሚያደርጉበት ወቅት እየዋለ እያደረ ሆድዋ እያደገ እየተወጠረ ይመጣል፡፡ ይህች ልጅ የተለየ ሕመም ወይንም ደግሞ እጢ በሆድዋ ውስጥ ተፈጥሮአል በሚል ወደሆስፒታል ይወስዱአታል፡፡ መልሱም ለማመን የሚያስቸግር ነበር፡፡ ለወላጆችዋ የተነገራቸው ልጅትዋ የሰባት ወር እርጉዝ እንደነበረች ነው፡፡

ወላጆች ዋም እጅግ ቢደናገጡም ቀጣዩ እርምጃ አባትየውን በአስገድዶ መድፈር ወንጀል ጥርጣሬ ወደ እስር ቤት ማስገባት ነበር፡፡ ሆኖም ግን እየተጣራ ሲሄድ ድርጊቱ የተፈጸመው ምንም በማያውቀውና የሁለት አመት ከ6 ወር እድሜ ባለው ሕጻን ወንድሙዋ መሆኑ ታውቆአል፡፡ ይህ አጋጣሚ እጅግ የሚገርም ወይንም የሚያስደነግጥ ቢሆንም እርግዝና ውን ጊዜውን ጠብቆ በሕክምና ከማዋለድ በስተቀር ምንም አማራጭ አልነበረም..... .....ሌላወ ታሪክ በራሽያ የተፈጠረ ነው፡፡ በራሽያ እርጉዝ ሆና የተገኘችው የ6 አመት እድሜ ያላት ልጅ ናት፡፡ ይህች ልጅ ያረገዘችው በአያትዋ ተደፍራ ነበር፡፡ ይህንን ድርጊት የፈጸሙት ሰው በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ሲደረግ ጽንሱ ግን እንዲቋረጥ ተደር ጎአል። በአለም አቀፍ መረጃ መሰረት ሴቶቹም ሆኑ ወንዶች እድሜያቸው ከሁለት አመት ከስድስት ወር እስከ 12/አመት የሚጠጉ ከ1939 -2012 ዓ/ም ድረስ በቁጥር ወደ 250 የሚጠጉ ህጻናት ከላይ ለተጠቀሰው ድርጊት ተጋልጠዋል፡፡ ሴት እና ወንድ ህጻናቱ አስር አመት እንኩዋን ሳይሞላቸው የማርገዝና የማስረገዝ ድርጊት መፈጸማቸው ተፈጥሮ በምትሰጠው ካለእድሜ ኮረዳነትና ወይንም ጉርምስና ባህርይ ምክንያት መሆኑን ለዚህ ንባብ ማብራሪያቸውን የሰጡን ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ኢሶግ፡ Puberty... ኮረዳነት...ጎረምሳነት እንዴት ይገለጻል? ዶ/ር ድልአየሁ፡ ኮረዳነት ወይንም ጎረምሳነት ከልጅነት ወደ አዋቂነት መሸጋገሪያ የሆኑ የእድሜ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በእድሜ ሴቶች ወደ 8 ወይንም ከ 10-11 አመት ሲደርሱ ወንዶች ደግሞ ወደ 11 አመት ሲደርሱ የሚታዩ የእድሜ ለውጦች በእንግሊዝኛው Puberty ይባላል ፡፡ በሰውነት ላይ የሚታዩ ለውጦችን በሚመለከት፡- ሴቶች ፡- የጡት መጠን መጨመር፣ በብልትና በብብት ላይ ጸጉር ማብቀል፣ የወር አበባ መታየት፣ የሰውነት ቅርጽ መቀየር፣...ወዘተ ወንዶች፡- የዘር ፍሬ ማመንጫና የብልት ማደግ፣ የብልትና ብብት ጸጉር መብቀል፣ የድምጽ መጎርነን ፣ ፐርም ማፍሰስ...ወዘተ የመሳሰሉት ነገሮች ይታያሉ፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ የሰውነት መግዘፍ ፣ቁመት መጨመር ፣ከፊት ላይ ቡጉር ማውጣት... በፍጥነት የሚታይ ለውጥ ከመሆኑ በተጨማሪ የስነአእምሮ ወይንም የስነተዋልዶአዊ ለውጦች በታዳጊዎቹ ላይ ይታያል፡፡

እነዚህ ለውጦች የሚታዩት እድሜውን ተከትለው በሚመነጩ አዳዲስ ሆርሞኖች ምክንያት ነው፡፡ ኢሶግ፡ ለውጡን የሚያመጡት ሆርሞኖች አስቀድሞውኑ የተፈጠሩ ናቸው ወይንስ አዲስ? ዶ/ር ድልአየሁ፡ ይህንን ለውጥ የሚያመጡትን ሆርሞኖች አፈጣጠር በሴቶች ላይ ስንመለከት ከእንቁላል ማኩረቻው ወይንም ከኦቫሪ የሚመነጩ ሆርሞኖች ናቸው ፡፡ እነዚህን ሆርሞኖች የሚያመነጨው ክፍል ሴቷ ስትወለድ ጀምሮ አብሮ የሚፈጠር ነው፡፡ ነገር ግን ሆርሞኖች ስራቸውን መስራት የሚጀምሩት በአብዛኛውን ጊዜ እድሜያቸው ከ8-11 ባለው ጊዜ ሲደርስ ነው፡፡ ይህንንም እንዲያደርጉ የሚታዘዙት ከአእምሮ በሚመነጩ ሆርሞኖች አማካኝነት ነው፡፡ ኢሶግ፡ Puberty... ኮረዳነት...ጎረምሳነት የሚያስከትለው ባህርይ ምን ይመስላል? ዶ/ር ድልአየሁ፡ በኮረዳነት ወይንም ጉርምስና እድሜ ላይ የሚኖረው ባህርይ ትንሽ ለየት ያለ ነው፡፡ በመጀመሪያ ስለጉዳዩ እውቀቱ ከሌላቸው በሰውነታቸው የተለያዩ ክፍሎች እና በድም ጻቸው በሚኖረው ለውጥ ምክንያት ግራ የመጋባት ሁኔታ ይታይባቸዋል፡፡ከዚህ ውጪ ግን በዚህ እድሜ የሚታየው ...ነገሮችን የመሞከር ወይንም ፍተሻ የማድረግ ዝንባሌ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተለዋዋጭ ደስተኛና ብስጩ የመሆን ባህርይ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ በባህሪያቸው መለዋወጥ እና በሚኖራቸው ተገቢ ያልሆነ ፍላጎት ምክንያትም ከቤተሰቦቻቸው ጋር መስማማት ሲያቅታቸው ይታያል፡፡

በእንደዚህ ያለው አጋጣሚ ቤተሰብ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ በግልጽነት ከልጆቹ ጋር መወያየት እና ስለሁኔታው በግልጽ ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡ ልጆቹ ይህንን ተፈጥሮአዊ ሁኔታ በሚገባ አውቀው ዝግጁ ሆነው እንዲጠባቁ የሚያስችላቸውን እውቀት ሊያገኙ ይገባል፡፡ ከቤተ ሰብ ውጪም ትምህርት ቤቶች በበኩላቸው ተገቢውን ነገር ለህጻናቱ ማስረዳት አለባ ቸው፡፡ ኮረዳነት ወይንም ጉርምስና ወሲብ ለመፈጸም ፍላጎታቸው የሚነሳሳበት ወቅት እንደመሆኑ ቤተሰብ ወይንም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው ህጻናቱን ከተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ኤችአይቪን ጨምሮ ለመከላከል በሚያስችል መልኩ ምክሩን መለገስ ይገባዋል፡፡ ልጆቹ ከዚህ ድርጊት እንዲዘገዩ ወይንም ደግሞ እራስን መጠበቅ የሚቻልባቸው መንገዶች መኖራቸውን በግልጽ ከወላጆቻቸው ወይንም ከሚያምኑዋቸው ሰዎች ማግኘት አለባቸው፡፡ ይህ ካልተፈጸመ ልጆቹ ጉዳት ላይ ሊወድቁ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡

ኢሶግ፡ የኮረዳነት ወይንም ጉርምስና እድሜ የሚጀምረው ከ8/አመት በሁዋላ ሲሆን ከዚያ በፊት ባለው እድሜ ወሲብ የመፈጸም ፍላጎት ሊኖር ይችላልን? ዶ/ር ድልአየሁ፡ ይህ እድሜ ከልጅነት ወደ አዋቂነት የሚሸጋገሩበት እንደመሆኑ አንዱ የሚኖረው ለውጥ የስነተዋልዶ አካላት ሁኔታ ነው። አልፎ አልፎ ግን ከዚህ እድሜያቸው አስቀድሞም ወሲብ የመፈጸም ፍላጎትም ሆነ የማርገዝ አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከተጠቀሱት እድሜ በታች ሆነው የወሲብ ሙከራ እና የእርግዝናው አጋጣሚም መፈጠሩን ያሳያሉ፡፡ ይህ ገጠመኝ ቅድመ ኮረዳነት ወይንም ጉርምስና የሚከሰት ይባላል ፡፡ ኢሶግ፡ በአሁኑ ዘመን የወር አበባ መምጫ እድሜ ስንት አመት ነው ? ዶ/ር ድልአየሁ፡ በአሁኑ ጊዜ በተለይም በአገራችን የወር አበባ መምጫው እድሜ እንዲህ ነወ ተብሎ በግልጽ መናገር ባይቻልም ባደጉ አገሮች ግን ከ10-11 አመት ባለው እድሜ ሴቶች ልጆች የወር አበባ ያያሉ፡፡ የወር አበባ የመምጫው እድሜ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ደረጃው ይለያያል፡፡

የወር አበባ ከቤተሰብ በሚወረስ ዝርያ ምክንያት የመምጫው ጊዜ ሊረዝም ወይንም ሊያንስ ይችላል፡፡ የወር አበባ መምጫን የህብረተሰቡ የእድገት ደረጃ እና የአኑዋኑዋር ባህርይም ሊወስነው ይችላል፡፡ ባደጉት አገሮች ባለፉት ሃያ እና ሰላሳ አመታት በተደረገው ጥናት እንደታየው ከእድገት ጋር በተገናኘ የወር አበባ የመምጫው ጊዜ በየአስር አመቱ በአማካይ ሶስት ...ሶስት ወር እየቀነሰ አሁን ካለበት ደርሶአል። ስለዚህ ዋናው የቤተሰብ ውርስ ሲሆን ከዚህ ውጪ ግን የአኑዋኑዋር ሁኔታ ...ምቾት የመሳሰሉት ነገሮች ይወስኑታል፡፡ ምቾት ማጣት ወይንም ድህነት የወር አበባ መምጫውን ሊያዘገዩት ይችላሉ የሚል ግምት አለ፡፡

Read 25424 times