Saturday, 22 June 2013 11:16

‘ለ20/80 ቤት፣ 50/50 ትዳር…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

                  እኔ የምለው…ለቤት ምዝገባው ተብሎ የፈረሱ ትዳሮች አሉ የሚባለው ነገር…የምር እውነት ነው እንዴ? አሀ… ግራ ገባና! እውነት ከሆነ እኮ…አለ አይደል…የትዳርና የአዳር ልዩነት ሊጠፋ ነው ማለት ነው! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ባልና ሚስት ለሽ ብለው ተኝተዋል፡፡ ሚስት ሆዬ ለካ የሆነ ህልም አይታ ኖሮ ብድግ ብላ ማልቀስ ትጀምራለች፡፡ ባልም ደንግጦ ይነቃል፡፡ “ምን ሆንሽ፣ በውድቅት ሌሊት እንዲህ የሚያስለቅስሽ ምንድነው?” ይላታል፡፡ እሷም…“አንድ መልከ መልካምና ሀብታም ሰውዬ ከአንተ ነጥቆ ሲወስደኝ አየሁ…” ትለዋለች፡፡ ባልም እያጽናናት... “የእኔ አበባ፣ በቃ አታልቅሺ፡፡ ህልም እኮ ነው” ይላታል፡፡ እሷ ሆዬ ምን ብትል ጥሩ ነው…“ታዲያ የሚያስለቅስኝ ህልም መሆኑ አይደል!” ልጄ… ልብ ያለው ልብ ቢል አሪፍ ነው፡፡ አሀ…ባሏ 10/90 የተመዘገበው ሚስት “40/60 የተመዘገበ ከአንተ ነጥሎ ሲወስደኝ በህልሜ አየሁ…” ልትል ትችላለቻ! ነገርዬው…አለ አይደል… “ለድካም የጣፈኝ ብነግድ አይተርፈኝ” ነው፡፡ ነገራችን ሁሉ ‘ህልም’ ሆኖ እየቀረ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

እና ገና “ሁለታችን ለየብቻችን ተመዝግበን ሁለት ቤት እናገኛለን…” በሚል ትዳር የሚፈርስበት ዘመን ከተደረሰ የምር ያሳስባል፡፡ እኔ የምለው…ይሄ ቢግ ብራዘር ምናምን የሚሉት ነገር ላይ ልጅቷ “እነሆ በረከት…” ተባብላ ትንሽ አንዳንዶችን ደማቸውን ከፍ፣ ስኳራቸውን ዝቅ አደረገችው አይደል! እኔ ግራ የሚገባኝ ምን መሰላችሁ…ልጅቱ ሠራችው የተባለው በምንም መለኪያ ‘ብራቮ’ የሚያሰኝ አይደለም፡፡ መጀመሪያ ላይ በኤፍ.ኤሞች ላይ “ቮት አድርጉላት” ስንባል የነበረው ግራ ይገባኛል፡፡ መጀመሪያ ‘ቢግ ብራዘር’ የሚባለውን ነገር የሚከታተለው ህዝባችን አንድ በመቶስ ይሞላል? በማያውቀው ነገር፣ ወክሎ ላልከው ሰው ድምጽ ስጥ ተብሎ ‘ሎቢ’ የሚካሄድበት ለምን እንደሆነ ግራ ይገባኛል! ብዙዎች ተበሳጭተው አስተማሪዋ ላይ ያንን ሁሉ ያወረዱባት እኮ ከመሬት ተነስተው ላይሆን ይችላል፡፡ ድምጽ ሰጡ፣ ድምጻቸው ግን ያላሰቡትን አመጣባቸው፡፡ ‘ፎርቹን’ ጋዜጣ ላይ አንድ ቋሚ ጸሀፊ “እንደ ማህበረሰብ፣ ለገንዘብና ለዝና ሲሉ ምንም ወደሚያደርጉ ህዝቦች ዝቅ ብለናል…” ብሎ ያሰፈረው የእውነትም የዘንድሮ አከራረማችንን የሚገልጽ ይመስለኛል፡፡ ትዳር አፍረስው እያንዳንዳቸው በየራሳቸው ቤት ለማግኘት የሚሞክሩ ካሉ ዞሮ፣ ዞሮ ጥቅም (‘ገንዘብ’) ፍለጋ ነው፡፡

እነሱ ትዳራቸውን ‘በጊዜያዊነት’ አፍርሰው ‘ሁለት ቤት’ ሲፈልጉ የሌሎችን አንድ ቤት እንኳን የማግኘት ዕድል እያበላሹ እንደሆነ ዘወር ብለው አለማየታቸው ያሳዝናል፡፡ እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የባልና የሚስት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ፡፡ ባል ሆዬ ቤተክርስትያን ስብከት ሲሰማ ውሎ ይመጣል። ቤት እንደ ደረሰ ወዲያውኑ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው… ሚስቱን ብድግ አድርጎ ይሸከማትና ቤቱን መዞር ይጀምራል፡፡ ሚስትም ነገርዬው ያልተለመደ ይሆንባትና… “ቄሱ ሚስቶቻችሁን ተሸክማችሁ ፍቅራችሁን አሳዩ አሉ እንዴ?” ብላ ትጠይቃለች፡፡ ባልም ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“የራሳችሁን ሸክም ራሳችሁ ቻሉ ነው ያሉን…” ብሏት አረፈው፡፡ እኔ የምለው…ይሄ ሁሉ ባል ጂም ቁና፣ ቁና ሲተነፍስ የሚያመሸው ለካ ቤት ሲገባ ሸክም ስለሚጠብቀው ነው! ቂ…ቂ…ቂ… ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይሄ የኳሳችን ነገር…እንዲሁ “አሁንስ መልክ ያዘ…” ስንል ‘በግልባጩ’ እየሄደ አስቸገረን፡፡ ይሄ በተጫዋች ተገቢነት የተፈጠረው ነገር ለእኔ በምንም መለኪያ “የፈሰሰ ውሀ…” የሚባል አይመስለኝም፡፡ ‘ውሀ እንዳይፈስ’ ማድረግ ካልተቻለ እኮ…አስቸጋሪ ነው፡፡

ስሙኝማ… ካነሳነው አይቀር…ከበቀደሙ ጨዋታ ጋር በተያያዘ…አለ አይደል፣ ቆም ብለን ልናስባቸው የሚገቡ ነገሮች ያሉ አይመስሏችሁም? የምር እኮ… ገና ለገና የአባይ ጉዳይ የጦፈበት ጊዜ ነው ተብሎ… ዳኞቹ ግብጻውያን መሆናቸው ያንን ሁሉ የአየር ሰዓት ይዞ ‘ዓቢይ ጉዳይ’ መሆኑ ግራ ያጋባል፡፡ ምን መሰላችሁ…ይሄ የ‘ኮንስፒሬሲ ቲዮሪ’ ነገራችን…አለ አይደል… ሁሉም ነገር ላይ “ምን ተንኮል ቢያስቡብን ነው?” እያስባለን ጠላት ፈላጊ አድርጎናል፡፡ ዳኞቹ የሚመጡት ከግብጽም ሆነ ከፊጂ የሚያጫውቱባቸው ህጎች እነዛው ናቸው፡፡ እኛ የምንዳኛቸው በዘር ግንዳቸው ሳይሆን በእግር ኳስ ህጎቹ አተረጓጎማቸው መሆን አለበት፡፡ አንዳንድ ሜዲያ ላይ ግን ከዳኝነት ብቃታቸው ይልቅ ዜግነታቸው ‘ሰበር ዜና’ ነገር እየሆነ ብዙዎች ጨዋታውን ከጅምሩ በጥርጣሬ እንዲያዩ አድርጓቸዋል፡፡ (እግረ መንገድም…በስፖርት ፕሮግራሞችም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች የአሌክትሮኒክስ ሜዲያው ራሱን በጥንቃቄ ማየት ያለበት ጊዜ አሁን ይመስለናል፡፡ አንዳንድ ‘እያመለጡ’ ያሉ ነገሮች የምር አሳሳቢ ናቸው፡፡

በነገራችን ላይ በስፖርት ሚዲያው አሪፍ እየሠሩ ያሉ እንዳሉ መጥቀስም አሪፍ ነው…ከእነጥቃቅን ስህተቶቻቸው፡፡) እናላችሁ…የኳሳችንን ነገር በተመለከተ ሚዲያ ውስጥ ያለን ሰዎች ከ‘እኛ ውጪ’ ያለውን ዓለም ብቻ ሳይሆን ‘የራሳችንን ዓለም’ ማየት ያለብን ይመስለኛል፡፡ አንደኛ ነገር መልካም መመኘት እንዳለ ሆኖ ህዝቡ… “ወይ ማሸነፍ ወይ ሞት!” አይነት ስሜት እንዲያድርበት የሚያደርጉ አቀራረቦች አሪፍ አይደሉም፡፡ ደግሞላችሁ…ከጨዋታው በኋላ ታየ የተባለው የ‘ደስታ ስሜት’ አንዳንድ ነገሮች እንዴት መልካቸውን እየለወጡ እንደሆነ ደስ የማይል ምልክት ነው፡፡ ዋናውን እውነተኛ ደስታ በተጓዳኝ የታዩ ጥፋቶች ነገሮች ላይ ጥላ እያጠሉባቸው ነው፡፡ እዚቹ ከተማችን ውስጥ በርካታ ቦታዎች ላይ የታዩ አላስፈላጊ ምግባሮች የምር ሊያሳስቡን ይገባል፡፡ ሰው የለፋበት ንብረቱ ለምን ይወድማል? ሰዎችስ ደስ ሊላቸው በሚገባ ሰዓት ለምን ለራሳቸው ደህንነትና ለንብረታቸው እንዲሰጉ ይሆናል? ሰዎች ተጎድተዋል፣ ንብረቶች ወድመዋል፡፡ “ለምን?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ወዳጄ የአንድ ትልቅ ሆቴል በር ላይ የነበሩ የጥድ ዛፎች እየተነቀሉ መወሰዳቸውን ሲነግረኝ ነበር፡፡ ለምን? በጣም ልቅ የሆኑ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡

በደስታ ስም ሰዎች መኪናቸው የሚሰበር ከሆነ፣ የማህበራዊ አገልገሎት መስጫዎች የሚወድሙ ከሆነ፣ ሰዎች ጉዳት የሚደርስባቸው ከሆነ… ምናልባት ወደፊት ደስታችንን በተወሰነ ክልል እንድንወስን የምንገደድበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡ ሰዋችን ‘ደመ መራራ’ ሆኗል፡፡ በትንሽ ነገር ሆድ ይብሰዋል፣ ይቆጣል…ዓለም ሁሉ በእሱ ላይ የሚያሴር ይመስለዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ስሜቶች እንዲገነቡ በማድረግ የሚዲያው ሚና አለ፡፡ በቢጫና ቀይ ካርድም ይሁን በሌላ ምክንያት ያልተገባ ተጫዋች ማሰለፍ ቅጣት ያስከትላል፡፡ አለቀ፡፡ የፊፋ የኳስ ህጎች የማናውቅ ሰዎች እንኳን ይህን በ‘ተራ ሎጂክ’ ልናውቀው የምንችለው ነው፡፡ ጥፋት ይነስም ይብዛም…ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የፊፋ መግለጫ ሲወጣ ወዲያውኑ ለህዝቡ መግለጽ ያለብን የሚዲያ ሰዎች ነን፡፡ የኳስ ህጎችን የማናውቅ የስፖርት ጋዜጠኞች አለን ለማለት ያስቸግረኛል፡፡ ሁኔታውን ወዲያውኑ ለህዝቡ ማስረዳት ያለብን እኛ ነን፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ምን መሰላችሁ…አንዳንድ አቀራረባችን “ፊፋ እኛን ጥሎ ደቡብ አፍሪካን ለማሳለፍ ፈልጎ ነው…” አይነት ስሜት የሚያሳድሩ ነበሩ፡፡

እና የኳስ ተመልካቾች ቢቆጡና የመጠቃት ስሜት ቢያድርባቸው በአብዛኛው ከ‘ባዶ ሜዳ’ ተነስቶ የመጣ አይደለም፡፡ ቃላቶቹ በጥንቃቄ ካልተመረጡ በስተቀር አብዛኛውን ጊዜ በቅንነት የሚቀርቡ ነገሮች እንኳን አላስፈላጊ ችግር ያስከትላሉ፡፡ ጥፋት ተሠርቷል? አዎ፣ ጥፋት ተሠርቷል፡፡ እናማ…እኛ የሚዲያ ሰዎች ይህንን ለማለት የጥፋቱ ሶርስ የሆነው ክፍልን መግለጫ የምንጠብቅበት ምክንያት ትንሽ ግራ ይገባል! ጥፋቱን ደግሞ ‘አለባብሶ ለማረስ’ ማድረጉ አለ አይደል…ትክክል አይመስለንም፡፡ ስሙኝማ…ይሄ የባልና የሚስት ‘ጊዜያዊ ሰማንያ ቀደዳ’ እውነት ከሆነ ሀሳብ አለን፡፡ የጋብቻ ሰርተፊኬት ላይ… “ይህ ስምምነት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁለቱ ተጋቢዎች ለሚስማሙት ጊዜ ተቋርጦ እንደገና ሊቀጥል ይችላል” የሚል ይከተትበትማ፡፡

እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ… ባልና ሚስት በመንገድ ሲሄዱ አንድ የእኔ ቢጤ ያዩና ሚስት “ይህንን ለማኝ አልወደውም…” ትለዋለች፡፡ ባልም “ለምን? ምን አደረገሽ?” ይላታል፤ ምን አለችው መሰላችሁ…“ከትናንት ወዲያ ቤት መጥቶ ሲለምን እንጀራ በወጥ ሰጠሁት፡፡ ትናንትና ምን ይዞልኝ መጣ መሰለህ?” “ምን ይዞልሽ መጣ?” “የምግብ አሠራር ጥበብ’ የሚል መጽሐፍ፡፡” አሪፍ አይደል! እናማ…ለቤት ምዝገባ ትዳር ‘ኦን ሆልድ’ የሚሆን ከሆነ… ሰርተፊኬቱ ላይ ‘ቋሚ’… ‘ኮንትራት’… ‘ፍሪላንስ’ የሚሉ ሰንጠረዦች ይካተቱልን፡፡ ልክ እኮ ‘ለ20/80 ቤት፣ 50/50 ትዳር’ የመጣ ነው የሚመስለው! ቂ…ቂ…ቂ… ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5114 times