Saturday, 22 June 2013 10:53

የወሊድ መከላከያዎች ምን ያህል ይከላከላሉ?

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(21 votes)

                 የዘር ቱቦ መቋጠር ህክምና ከተደረገም በኋላ እርግዝና ሊከሰት ይችላል

“ትዳር ከያዝኩ 10 ዓመት አልፎኛል፡፡ የስድስትና የአራት አመት ወንድና ሴት ልጆችም አሉኝ፡፡ ልጆቻችንን በጥሩ ሁኔታ ለማሣደግና ለማስተማር እንድንችል ቤተሰባችንን መመጠን እንደሚገባንና ተጨማሪ ልጅ መውለድ እንደሌለብን ከባለቤቴ ጋር ተመካከርንና የወሊድ መከላከያ መድሃኒት መውሰድ ጀመርኩ፡፡ በየሶስት ወሩ የሚሰጠውን መርፌ እየወሰድኩ አንድ አመት ያህል በሠላም ቆየሁ፡፡ መድሃኒቱ በሰውነቴ ላይ አንዳንድ ለውጦችን ማሳየት ሲጀምር ሃሣብ ያዘኝ፡፡ አይኔ ብዥ ይልብኝ ጀመር፣ ከፍተኛ ራስ ምታትና ትኩሳት በየጊዜው ያጋጥመኝ ጀመር፡፡ ኪሎዬ እየጨመረ ሄደ፡፡ ጉዳዩ በጣም ስላሣሰበኝ በአካባቢዬ ወደሚገኝ አንድ ክሊኒክ ሄጄ ስለ ሁኔታው አማከርኳቸው፡፡ ሰውነትሽ መድሃኒቱን በደንብ ሲለማመደው ይተውሻል አሉኝ፡፡

ህመሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ቢታወቀኝም መርፌውን አቋርጬ ከባለቤቴ ጋር ተመካክረን የወሰንነውን ተጨማሪ ልጅ ያለመውለድ ውሣኔ ለማፍረስ አልፈለኩምና ቀጠልኩበት፡፡ እያደር የሚሰማኝ ስሜት እየተለወጠና እየጨመረ መምጣቱ እጅግ አሣሰበኝ፡፡ ማቅለሽለሽ፣ የምግብ ፍላጐት ማጣትና ራስ ምታት የየዕለት ህመሞቼ ሆኑ፡፡ ግራ ቢገባኝ ወደ ሆስፒታል ሄጄ ምርመራ አደረግሁ። የምርመራውም ውጤት የሁለት ወር ነፍሰጡር መሆኔን አረዳኝ፡፡ ሁኔታውን ማመን አልቻልኩም፡፡ እንዴት ይሆናል? “በመርፌ የሚሰጠውን የእርግዝና መከላከያ መድሃኒት በአግባቡና በሥነስርዓት መውሰድ ከጀመርኩ አንድ ዓመት ሆኖኛል፤ እንዴት አረግዛለሁ?” ብዬ ከሃኪሙ ጋር ሙግት ገጠምኩ። ግን ሆኗል፡፡ ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡

ማርገዜን ለባለቤቴ ስነግረው ሊያምነኝ አልቻለም፡፡ ሆን ብለሽ መድሃኒት መውሰዱን (መርፌ መወጋቱን) አቁመሽ ነው እንጂ እንዴት በመድሃኒት ላይ ይረገዛል ብሎ ሞገተኝ፡፡ ስለ ጉዳዩ እንዲያስረዱት ወደ ሆስፒታል ይዤው ሄድኩ፡፡ ሐኪሞቹ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ሊፈጠር እንደሚችሉ ቢነግሩትም ሊዋጥለት አልቻለም፡፡ ጊዜውን ጠብቆ ህፃኑ ተወለደ፡፡ ባለቤቴ ከእሱ ፍላጐትና ፍቃድ ውጪ በተወለደው ልጅ እምብዛም ደስተኛ አልሆነም። ምን ማድረግ እችላለሁ፡፡ የወሊድ መከላከያ እየተባለ በመርፌና በኪኒን የሚሰጡን መድሃኒት እርግዝናን አይከላከልም ማለት ነው? እንዲህ ከሆነ ደግሞ መከላከል የማይችለውን ይከላከላል እያሉ በቴሌቭዥኑና በሬዲዮ የሚጨቀጭቁን ለምንድነው?” በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ልጃቸውን ለማሣከም መጥተው ያገኘኋቸውን የአንዲት እናት ቅሬታ ነው ለፅሁፌ መግቢያ ያደረግሁት፡፡

ወ/ሮ ተናኜ ታደሰ የተባሉት እኚህ እናት፤ ለእርግዝና መከላከያነት ለአንድ ዓመት ያህል የተጠቀሙበትን መርፌ በየጊዜው እየሄዱ የሚወጉት በአካባቢያቸው በሚገኝ የጤና ጣቢያ ውስጥ ነበር፡፡ ወ/ሮ ተናኜ መከላከያው በእርግጠኝነት እርግዝና እንዳይፈጠር ሊያደርግላቸው እንደሚችል በማመናቸው ሌሎች ተጨማሪ የእርግዝና መከላከያዎችን አይጠቀሙም፡፡ ሆኖም ባላሰቡትና ባልጠበቁት ጊዜ ያለ ዕቅድ ለሚከሰት እርግዝና ተጋልጠዋል፡፡ ይህ ሁኔታም ወ/ሮ ተናኜ ሙሉ በሙሉ በወሊድ መከላከያ መድሃኒቶች ላይ ያላቸውን እምነት እንዲሽሩ አድርጓቸዋል፡፡ አሁን አሁን ለወ/ሮ ተናኜ የተሻለውና ተመራጩ የወሊድ መከላከያ ዘዴ ባህላዊ ወይንም ተፈጥሮአዊ መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ሆኗል፡፡ እናም ጡት ማጥባት፣ በወር አበባ ሁደት መጠቀም እና አንዳንዴ ደግሞ ከግብረሥጋ መታቀብን መርጠው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡

የወሊድ መከላከያ መድሃኒቶች በባህላዊ፣ በተፈጥሮአዊና በሰው ሠራሽ መንገዶች እየተዘጋጁ ለተጠቃሚዎች የሚሰጡና ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚረዱ ናቸው። በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጁ የእርግዝና መከላከያዎች አሠራራቸውና አጠቃቀማቸው ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ በአገራችን በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጁ የእርግዝና መከላከያዎች በተለይም በደቡባዊው የአገራችን ክፍል በስፋት የተለመደ ነው፡፡ በሐመርና በሱርማ ብሔረሰብች ባህል አንዲት ሴት ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ፣ የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ ይፈቀድላታል፡፡ ከጋብቻ በፊት ማርገዝ ግን በብሔረሰቦቹ ዘንድ እጅግ የተወገዘ ጉዳይ ነው። ኮረዳዋ ከጋብቻ በፊት እንዳታረግዝ ከዕፅዋት የተዘጋጀ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት ይሰጣታል፡፡ ይህ ባህላዊ የወሊድ መከላከያም ኮረዳዋ ትዳር ይዛ ልጅ ለመውለድ ዝግጁ እስከምትሆን ድረስ እርግዝና እንዳይፈጠር በአስተማማኝ ሁኔታ ይከላከልላታል፡፡ የኮረዳነት ዘመኗን ጨርሳ ትዳር ስትይዝ በባህላዊ መድሃኒት ቀማሚዎች የተዘጋጀው የመድሃኒት ማርከሻ ይሰጣታል፡፡ ይህም መድሃኒቱን ስለሚያረክስላት ማርገዝ ትችላለች፡፡

ይህ አይነቱ ባህላዊ የወሊድ መከላከያ መድሃኒት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተለመደ ነው፡፡ ተፈጥሮአዊ የወሊድ መከላከያ የሚባሉት ደግሞ ምንም አይነት ኬሚካል ያላቸው መድሃኒቶችን ወደ ውስጥ ሣያስገቡ በተለያዩ ተፈጥሮአዊ መንገዶች እርግዝናን መከላከል የሚያስችሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መንገዶች መካከልም በወር አበባ ሁደት መጠቀም፣ የሰውነት ሙቀትንና ፈሳሽን በመቆጣጠር ግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም፣ ግንኙነት ካደረጉ በኋላ የወንዱን ዘር ወደ ውጪ እንዲፈስ ማድረግና ጡት ማጥባት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የወር አበባ ሁደትን ለመጠቀም የሴቷ የወር አበባ መምጫ ያልተዛባና ጊዜውን በአግባቡ ጠብቆ የሚመጣ መሆን አለበት፡፡ የሰውነት ሙቀትንና ፈሳሽን በመለካት ለመጠቀም ሴቲቱ ንቁና የሰውነቷን ለውጦች በየጊዜው የምትረዳና የምትከታተል መሆን ይኖርባታል፡፡ በግንኙነት ወቅት የዘር ፍሬን ከሴቷ ማህፀን ውጪ በማፍሰስ እርግዝና እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚያስችለው ዘዴ ሁልጊዜም አስተማማኝ ነው ማለት አይቻልም። ለዚህ ምክንያት ደግሞ የወንዱ ዘር ወንዱ ለወሲብ ከተነቃቃበት ጊዜ ጀምሮ በብልቱ ጫፍ ላይ በሚገኝ እርጥበት ውስጥ ስለሚኖርና ይህም ወንዱ የእርካታ ጫፍ ላይ ደርሶ ዘሩን ሙሉ በሙሉ ከመርጨቱ በፊት ወደ ሴቷ ማህፀን ዘሩ እንዲገባ ስለሚያደርግ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የማህፀንና የፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪሙ ዶ/ር ፍፁም ተወልደ ብርሃን እንደሚናገሩት፤ በዚህ ዘዴ ከሚጠቀሙ ሴቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እርግዝና ይከሰትባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ዘዴ ለመጠቀም ወንዱ በግንኙነት ወቅት ንቁና ስሜቱን በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ በህመም፣ በሃይማኖት ጉዳዮችና በተለያዩ ምክንያቶች ሰው ሰራሹን የወሊድ መከላከያ መጠቀም ለማይችሉ ሰዎች ተፈጥሮአዊው የወሊድ መከላከያ ዘዴ ተመራጭ እንደሆነም ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ ሠው ሠራሹ የወሊድ መከላከያ ዘዴ ደግሞ በሁለት አይነት መንገዶች የሚዘጋጅ ነው። ይህም ቋሚ የእርግዝና መከላከያና ጊዜያዊ የእርግዝና መከላከያዎች ተብሎ ይገለፃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በስፋት ገበያ ላይ የሚገኙት የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ሆርሞኖች እንደሆኑ የሚናገሩት ዶ/ር ፍፁም፤ የሆርሞኖቹ አሠራር በሴቶች ውስጥ ካለው ሆርሞን ጋር ተመሳሳይነት እንዳለውና ይህም የሆርሞኖቹን መጠን በማመጣጠን እርግዝና እንዳይከሰት ለማድረግ እንደሚያስችል ይገልፃሉ፡፡

ቋሚ የእርግዝና መከላከያዎች ተብለው ከሚገለፁት መካከል የዘር መተላለፍያ ቱቦዎችን መዝጋት፤ መርፌ፣ በክንድ የሚቀበሩ መድሃኒቶች፣ በማህፀን ውስጥ የሚገባው ሉፕ ሲጠቀሱ በየቀኑ የሚዋጡ ክኒኖች፣ ኮንዶም፣ ፎምና ጄሎች ደግሞ ጊዜያዊ የእርግዝና መከላከያ መድሃኒቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች እርግዝና እንዳይፈጠር ለመከላከል ያስችላሉ ቢባልም ውጤታቸው መቶ በመቶ አስተማማኝ ነው ለማለት ግን እንደማያስደፍር ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት መድሃኒቶችን በአግባቡና በትክክለኛው ጊዜ እየወሰዱ እርግዝና ሊያጋጥማቸው የሚችሉ ሴቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ፍፁም ይህ ግን በቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል። መከላከያውን በአግባቡ ከወሰዱ ሴቶች መካከል 0.1 በመቶ የሚሆኑት እርግዝና ሊያጋጥማቸው መቻሉ እንግዳ ነገር አይደለም ሲሉም ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሚዋጥ ክኒን የሚወስዱ ሴቶች በአብዛኛው ለዚህ ችግር እንደሚጋለጡ ጠቅሰው፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የሚዋጥ ክኒኖችን በየዕለቱ የሚወሰዱ ሴቶች መድሃኒቱን ሳያወስዱ መርሳት፣ ከወሰዱ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ማስመለስ አይነት አጋጣሚዎች የመድሃኒቱን የመከላከል ብቃት በመቀነስ ለእርግዝና እንደሚያጋልጥ ጠቅሰዋል።

የወሊድ መከላከያ መድሃኒቶች እርግዝናን ለመከላከል ከሚሰጡት ጠቀሜታ ጐን ለጐን የሚያስከትሏቸው የጐንዮሽ ጉዳቶች መኖራቸውን የሚገልፁት ዶ/ር ፍፁም፤ ከነዚህ ችግሮች መካከልም የወር አበባ መዛባት፣ ክብደት መጨመር፣ የደም መርጋትንና ስትሮክ የደም ግፊትን፣ የካንሰር ህመሞችን ማባባስ (በተለይም የጉበትና የጡት ካንሰሮችን) ጡት አካባቢ ማወፈር፣ የወር አበባ እንዳይታይ ማድረግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መድሃኒቶቹ የማህፀንና የማህፀን ካንሰርን መከላከል፣ ከማህፀን ውጪ እርግዝናን መከላከል፣ የአጥንት ጥንካሬን እንዳይቀንስ ማድረግ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የወሊድ መከላከያ መድሃኒቶች መውሰድ አደገኛ ከሚሆንባቸዉ ሴቶች መካከል የቲቢ በሽታ ያለባቸው፣ የሚያጠቡ እናቶች፣ የቆዳ ችግር ያለባቸው ሴቶች ይጠቀሳሉ፡፡

የእርግዝና መከላከያ መድሃኒቶች መቶ በመቶ እርግዝና ያስቀራሉ ማለት አይደለም በሚለው ሃሣብ በአዲስ ህይወት ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ካሣሁንም ይስማማሉ፡፡ እርግዝናን 100% መከላከል ያስችላል የሚባል መድሃኒት አለመኖሩን የሚናገሩት ዶክተሩ፤ በኦፕራሲዮን የዘር መተላለፊያ ቱቦዎችን እንዲቋረጡ የሚደረገው የመከላከያ ህክምና ከተሠራላቸው በኋላ እንኳን ማርገዝ የቻሉ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። እርግዝናን ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለማስቀረት የሚያስችለው ዘዴ ከግብረ ሥጋ ግንኙነት መታቀብ እና ማህፀንን ማስወጣት መሆኑንም ዶክተር ካሣሁን አክለው ገልፀዋል፡፡ የወሊድ መከላከያ መድሃኒቶች መቶ በመቶ እርግዝናን መከላከል እንደሚችሉ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተናገሩ ህብረተሰቡን ከማሣሣት የመከላከል አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ በግልፅ ማሣወቁ ተገቢነት ያለው ተግባር መሆኑን ባለሙያዎቹ ይጠቁማሉ፡፡

Read 18263 times