Saturday, 22 June 2013 11:59

“የአበበ መለሰን ህይወት ለመታደግ ጥረታችንን እንቀጥላለን” ድምፃዊ ይሁኔ በላይ

Written by 
Rate this item
(7 votes)
  • የኢትዮጵያ ህዝብ ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር የሚደንቅ ነው---
  • ዘፈኑ ለሚቀጥለው የእግር ኳስ ድል እንደሚደመጥ ተስፋ አለኝ--
  • ለህዝብ መንደርደሪያ እና ቀብድ ሰጥቼ ከአስር ቀን በኋላ እሄዳለሁ---

ኑሮውን በአሜሪካ ቨርጂኒያ ያደረገው ድምፃዊ ይሁኔ በላይ፣ ለዜማ ደራሲው አበበ መለሰ የመታከሚያ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ኮንሰርት ላይ ለመሳተፍ ባለፈው ሰሞን ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣው፡፡ የመጣበትን ጉዳይ ከፈፀመ በኋላ ያገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው፣ ከድምፃዊው ጋር በሙያው በትምህርቱ፣ በአሜሪካ ኑሮውና በኢንቨስትመንቱ ዙሪያ ሰፊ ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡
እንድታነቡት ተጋብዛችኋል;

 በህመም ላይ ለሚገኘው የዜማ ደራሲ አበበ መለሰ የመታከምያ ገንዘብ ለማሰባሰብ ባለፈው ቅዳሜ በላፍቶ ሞል በተዘጋጀው “ውለታ ኮንሰርት” ላይ ተሳትፈሃል፡፡ ቀደም ሲልም በአሜሪካ ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር ኮንሰርት እንደሰራችሁለት ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ጨዋታችንን በዚህ እንጀምር--- 

እስራኤል አገር ለኮንሰርት ሄጄ ነው ‹‹አቤ ታሟል›› የሚል ወሬ የሰማሁት፡፡ እኔ ካየሁት በኋላ የአቤን ጉዳይ ሌሎች አድናቂዎቹና የኢትዮጵያ አርቲስቶች እንዲሰሙና የአቅማቸውን እንዲያደርጉ ሚል እንደ ጓደኛም፣ እንደ ጋዜጠኛም አድርጎኝ --- በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በቪዲዮ ቃለመጠይቅ አደረግንለትና በዩቲዩብ ለቀቅነው፡፡ ያኔ ነው እነ ሃይልዬ ለአቤ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ማሰባቸውን የነገሩኝ፡፡ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ለሚሹ ወገኖች የባንክ አካውንት ከፍተው ስለነበረም የአካውንቱን ቁጥር ከቃለምልልሱ ጋር አካተትኩት፡፡ ሌሎች ሚዲያዎችም መረጃውን እየወሰዱ ማስተላለፍ ጀመሩ፡፡
ከዛ በኋላ አሜሪካ ያሉትን አርቲስቶች አቀናጅተን ትንሽ ገንዘብ ማሰባሰብ ነበረብን፡፡ እዛ ያለው የስራ ጫናና ኑሮ ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በአሜሪካ ከራስ አልፎ ጊዜን ለሰው መስጠት ትንሽ ይከብዳል፡፡ ሆኖም እንደምንም ብዬ አርቲስቶች በማሰባሰብ ኮሚቴ አቋቋምንና ተወያይተን ‹‹መዓዛ ሬስቶራንት›› ውስጥ የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ ተስማማን፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች ሲኖሩን እዚያ ሬስቶራንት ውስጥ ነው የምንሰራው፡የሬስቶራንቱ ባለቤት እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ሲኖሩ ትተባበራለች፡፡
በእዚህ ኮንሰርት ላይ የተሳተፉት እነማን ነበሩ? ምን ያህል ገቢስ ተገኘ?
የመግቢያ ዋጋው 25 ዶላር ነበር፡፡ እሱን ለመርዳት ብለው ትኬት ቆርጠው የገቡም በጥሪው ገንዘብ የሰጡም አሉ፡፡ አበበን ለመርዳት የተቻለውን ያህል ተረባርበናል፡፡ በዝግጅቱ አርቲስት መሃሙድ አህመድ ነበረበት፡፡ ሌሎችም በርካታ ሙዚቀኞች ተሳትፈዋል፡፡ ከኮሚቴው አባላት መካከል ገጣሚ አለምጸሃይ ወዳጆ፣ ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ፣ ፀሃይ ካሳ፣ ደሳለኝ መልኩ፣ ዳምጠው(ተወዛዋዥ) ወደ አስር ገደማ ይሆናሉ፡፡ ከቦታው ጥበት አንፃር ብዙ ታዳሚዎች አልነበሩም፡፡ ኮንሰርቱን ትልቅ አዳራሽ ውስጥ ብናደርገው ኖሮ …ችግሩ ግን አሜሪካ ሰፊ አዳራሽ ለመከራይት ክፍያው ብዙ ነው፡፡ እንደውም ገቢውን በሙሉ እንዳይወስደው በመፍራት ነው በዚያ መልኩ እንዲሆን የመረጥነው፡፡ ከኮንሰርቱ 12 ሺ 500 ዶላር (212 ሺ 500 ብር ያህል) ተገኝቷል። የገንዘብ ማሰባሰቢያ ኮንሰርቱ አሁንም ይቀጥላል። አበበ ህክምናውን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ገንዘብ እስኪያገኝ ድረስ ህይወቱን ለመታደግ ጥረታችንን እንቀጥላለን፡፡ አርቲስቶች በዚህ ተስማምተን ነው የተለያየነው፡፡
ከሳምንት በፊት ደግሞ ከዚሁ አርቲስት ገንዘብ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀው ‹‹ውለታ ኮንሰርት›› ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መጣህ–
አዎ ስመጣ ሙዚቀኞች ጥናት ላይ ነበሩ። ፖስተር ሁሉ ተዘጋጅቷል፡፡ እኔ እንደምኖር ስላልታወቀ ለህዝብ አልተገለፀም ነበር፡፡ ሆኖም በሰዓቱ ደርሼበታለሁ፤ እናም ሙዚቀኞች የ‹‹ዘገሊላ ዕለት›› የሚለውን ሙዚቃዬን አጠኑልኝና ደስ ብሎኝ ኮንሰርቱ ላይ ተጫወትኩ፡፡
ከአሁኑ ኮንሰርት ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ኮንሰርት ሰርተህ አታውቅም--- ለምንድን ነው?
በአሁኑ ኮንሰርት እንደ ሰርፕራይዝ ነው የቀረብኩት፡፡ ህዝቡ ናፍቆኝ ስለነበረ በዚያች አጭር ጊዜ ውስጥ ከእስክስታውና ከዘፈኑ ጋር ተዳምሮ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አድርጎልኛል፡፡ በእውነቱ በጣም ነው የተደነቅሁት---እንዴት ደስ አለኝ መሰለሽ---የኢትዮጵያ ህዝብ ሰው ማዳን የሚችል..ፍቅር የሆነ… አንቺ ምን ዓይነት ህዝብ ነው፡፡ በጣም ነው የተደሰትኩ---.ለሙዚቃ ያለው ፍቅር..እንባዬ ሁሉ ነው የመጣው..ቦታው ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር፡፡ ታዳሚው ይጫወታል --- ይጨፍራል-- ይደሰታል…ይሄ እንግዲህ በአዲስ አበባ የመጀመሪያዬ ኮንሰርት ነው፡፡ መቼም ያየሁት ድባብ ልዩ ነበር፡፡ ህዝቡ ከእኔ ጋር በጣም ሲዘል፣ ሲጨፍር ነው ያመሸው፡፡ አይተሽው አይደል--
አዎ አይቼዋለሁ፡፡ እኔ የምለው-- አበበ መለሰ ለአንተ ዜማ ሰጥቶሃል እንዴ?
አልሰጠኝም፡፡ ግን አበበ ይሄ ሲያንሰው ነው። ከዚህ በላይ ሊደረግለትና፣ ብዙ መስዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባው አርቲስት ነው፡፡..
እንግዲህ ‹‹ውለታ ኮንሰርት›› አስፈንድቆኛል ብለሃል፡፡ ወደፊትስ እዚህ መጥተህ ኮንሰርት ለማቅረብ አላሰብክም?
ለአዲስ አመት አዲሱን ሙሉ አልበሜን ለማድረስ ዝግጅቴን አጠናቅቄአለሁ፡፡ በአገኘሁት አጋጣሚ ቀን ማታ ሳልል ግጥምና ዜማዎችን እያሰባሰብኩ ነው፡፡ በነገርሽ ላይ ባለፈው እሁድ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ ተመልክቼ በጣም ነበር ደስ ያለኝ፡፡ ከድሉ በኋላ ስቱዲዮ ገብቼ ከአዲሱ ስራዬ ውስጥ ለአንድ ጉዳይ ያዘጋጀሁት ዘፈን ነበር --- ከእርሱ ላይ ቆረጥ ቆረጥ አድርጌ ለኢትዮጵያ ህዝብ ‹‹የእንኳን ደስ ያላችሁ›› ዜማ ሰርቼአለሁ፡፡
እስኪ ከዘፈኑ ግጥም ቀንጨብ አድርገህ ንገረን--
‹‹ዛሬ ነው ዛሬ ፋሲካ ነው ደስታ ነው ዛሬ
እንኳን ደስ አለሽ ኢትዮጵያ ሃገሬ››
የሚልና ተጫዋቾቹን የሚያወድስ ነው፡፡ ይሄን ዜማ ሌሊቱን ስንሰራ አድረን ነው የጨረስነው፡፡ የሙዚቃ ባለሞያዎች እንቅልፍ አጥተው ከእኔ ጋር አድረዋል፡፡ ግጥሙ የፀጋዬ ደቦጭ ሲሆን ዜማው የእኔ ነው፡፡ እነ አበበ ብርሃኔ፣ ሄኖክና ሌሎች ጓደኞቼ አብረውኝ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለኳስ ያለው ፍቅር የሚደንቅ ነው፡፡ በባህላችን ደግሞ ድል ሲገኝ ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ ›› የመባባል ነገር ስላለ ነው ያንን ሙዚቃ የሰራሁት፡፡ እና ሌሊት ስንሰራ አድረን..ጠዋት ሲዲውን ለሚዲያ ልንሰጥ ስንል ግን ሌላ ነገር ተፈጠረ፡፡ አስደንጋጭ ዜና ሰማን። የእኛም ዘፈን ለጆሮ ለመብቃት ሳይታደል ቀረ፡፡ ዞሮ ዞሮ ውጤቱ ቡድናችን ለወደፊቱ ያለውን ተስፋ ጠቋሚ ነው፡፡ በተጨዋቾቻችንም እንኮራለን፡፡ ዘፈኑ ለሚቀጥለው ተመሳሳይ ድል እንደሚደመጥ ተስፋ አለኝ፡፡
አንድ ጊዜ ስትናገር--- ዘፈኖቼ ሳላስበው ከባህላዊ ወደ ዘመናዊነት እየወሰዱኝ ነው ብለህ ነበር፡፡ በአዲሱ ስራህስ?
በአዲሱ አልበም ባህላዊም ዘመናዊም ዘፈኖች ይካተታሉ፡፡ ‹‹የዘገሊላ እለት››፣ ‹‹አውማ››፣ ‹‹ዘንገና››--ሁሉም ነገሮች አሉበት፡፡ አቅሜ የፈቀደውን ያህል ጣፋጭ ዜማዎች ለህዝብ ለማድረስ እየሰራሁ ነው፡፡ ባህላዊ ነገሩ ቅድሚያ ተሰጥቶት ነው እየተሰራ ያለው.. አድማጮቼ በአዲሱ ስራዬ ትደሰታላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስራዎቹ ባህላዊም ዘመናዊም ናቸው። ለአዲስ ዓመት የሚወጣ ሙሉ ካሴትና በቅርቡ የሚለቀቅ ነጠላ ዜማ አለኝ፡፡ መንደርደሪያ እና ቀብድ ሰጥቼ ከአስር ቀን በኋላ እሄዳለሁ፡፡
አባትህም ድምፃዊ ነበሩ ይባላል---እንደውም የአንድ ዘፈን ግጥም እንደሰጡህ ሰምቻለሁ---
አባቴ ከገጠር እየተመላለሰ ነበር የሚያየን፡፡ አባቴንም ሆነ ትልልቅ ሰዎች ወደ እኛ ቤት ሲመጡ መጠየቅ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ አባቴንም እጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹ለፍቅር…ለወደዳችኋት ልጅ፣ ለፋሲካም ሆነ ለገና በዓል ምን እያላችሁ ነው የምትዘፍኑት›› ብዬ ስጠይቀው፤
‹‹የዛሬን እኔ አለሁ አሳድርሻለሁ፣
ደግሞ ለነገው ይፈለጋል ሠው›› ነው የምንላት ብሎ ነገረኝ፡፡ ይሄንንም ‹‹እህና ናና ሆይና›› በሚለው ዘፈኔ ላይ ተጫውቼዋለሁ፡፡ በእኔ ሙዚቀኝነት ውስጥ የአባቴ ድርሻ ጉልህ ሥፍራ አለው። በአጠቃላይ የገጠሩ ህብረተሰብ አካል ነኝ። መሆን የምፈልገው፤ ይዤ የተነሳሁትም የአገሬን ባህል፣ቋንቋውን ማሳወቅ፣ ማስከበር ነው፡፡ ባህሌን ማሳወቅ የእኔ ግዴታ፣ ውዴታም ነው፡፡
እንደ ‹‹እህና ናና ሆይ እና››፣ ‹‹ሎጋው ሽቦ››፣ ‹‹የማይ ውሃ›› የመሳሰሉ የህዝብ ዜማዎች ትርጉማቸው ጠጠር ይላል የሚሉ ወገኖች አሉ----
በቃ እኮ ከህዝብ የሚፈልቅ ስሜት ነው፡፡ የፈጠራ፣ የጥበብ ሰው እኮ ነው ባላገር፡፡ የገጠሩ አካባቢ ሰው ሁሉም ዘፋኝ፣ አቀንቃኝ፣ ገጣሚ ነው፡፡ ቋንቋው የበሰለና ጥበብ የታከለበት ነው። በቃ ቅኔ ነው--- የህዝብ ህብረ ቀለም ያለው ቅኔ፣ የሚጣፍጥ--ከውስጥ ጥልቅ የሚል ቋንቋውና ፍሰቱ የሚያስደንቅሽ…ድንቅ ህዝብ፣ ድንቅ የባህልና የፈጠራ ባለቤት ነው ባላገር.. እኔ ይሄ ነኝ---የዚህ ህዝብ አካል፡፡
የአሜሪካ ኑሮህ እንዴት ነው?
አሜሪካ ስኖር ጎደለኝ የምለው ነገር የለም፤ እግዚአብሄር ይመስገን ሁሉ ሙሉ ነው፡፡ እኔ ደስ የሚለኝ በሃሳብ ወደ ኋላ ተመልሼ፣ የልጅነት ጊዜዬን፣ አገር ቤትን በትዝታ ስቃኝ ነው፡፡ በተለይ…ፍኖተ ሠላምን-- ያደኩበትን ሠፈር፣ጓደኞቼን አይቼ ስመለስ ስራዬን እንዴት እንደምሰራ አታውቂም! በተረፈ ግን..ብዙ ነገሮች ለእኔ ድግግሞሽ ናቸው። ልጆቼን ገጠር የአባቴ አገር ይዣቸው ሄጄ ደበሎ አልብሻቸዋለሁ፡፡ ሴትዋን ልጄን ባለገመዱን ቀሚስና መቀነት አልብሻታለሁ፡፡ ባህላቸውን አውቀው እንዲያድጉ ከከብቶች ጋር ፎቶ አንስቻቸዋለሁ፡፡ እንደውም ‹‹እምዬ ኢትዮጵያ አገረ ገነት›› የሚለው ዘፈኔ ቪድዮ ክሊፕ መፅሐፍ ቅዱስ እያነበብን ነው የሚጀምረው፡፡ ልጆቼ ይህን እንዲያገኙ፣ እንዲያውቁ፣ እንዲኮሩበት ስለምሻ ሁሌም አስተምራቸዋለሁ፡፡. ደበሎ ለብሰን አድገን በአሜሪካ የምንወልዳቸው ልጆች ባህላችንንና እኛን አያውቁንም፡፡ መሠረታችንን አመጣጣችንን አያውቁም… ብናግዛቸው መልካም ነው፡፡
ትምህርት እንደጨረስክ ነው ”ጊሽ ዓባይ” ኪነት ቡድንን የተቀላቀልከው?
ከዛ በፊት ለአንድ ወር በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ላይ ተሳትፌአለሁ፡፡ ባከል ገብርኤል ላይ ነበር የዘመትኩት፡፡ ገበሬው ደስ ይለው ነበር። ለአስተማሪ ትልቅ ክብር ስላለው ቤቱ አግብቶ ያበላል ያጠጣል… እንዴት ሰው ያከብራሉ መሰለሽ፡፡ በጣም ፍቅር ነው የገጠሩ ህብረተሰብ፡፡
ወደ “ጊሽ ዓባይ” እንግባ…
በ1979 ዓ.ም ነበር፡፡ ‹‹አንቱየዋ እነሱ እኮ ልጆች ናቸው ይጫወቱ በጊዜያቸው›› የሚለውን የሙዚቃ ፕሮግራም እኔ ነበርኩ ይዠው የሄድኩት፡፡ ፈጠራው የእኔ ነው፤ እኔ ነኝ የትርኢቱን ንድፍ (ስኬለተን የሰራሁት) ይሄ አለኝ ብዬ ስሰጣቸው የ “ጊሽ ዓባይ” ትርዒት ኃላፊ እሱባለው ጫኔ ..ሰማኸኝ በለው/አባት ፣ ሀብቱ/እረኛ፤ አለምወርቅ አስፋው/እናት፣ ብዙአየሁ ጎበዜ/ልጅ ሆኑና--ወዲያው ተቀነባበረ። እዛ ከደረሰ በኋላ እየተቀየረ መጣ..ሁሉም ሰው የራሱን ፈጠራ ይጨምራል..አንዱን ቀን የሰራነው ሌላ ቀን ሌላ ይጨመርበታል..እያደገ መጣ..ያን ከሰራን በኋላ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጠሩን፡፡ እድገቴ ፈጣን ነበር፡፡ በ1981 ዓ.ም ካሴት አወጣሁ..‹‹የአገሬ ልጅ ባለጋሜ ትውልደ ጎጃሜ›› የሚለውን፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ስትመጣ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብህ?
ከክፍለ ሃገር ለሚመጣ ሰው ደስ የምትል ከተማ ናት፡፡ መኪና ውስጥ ሆኜ--አዲስ አበባ ደረስን እስኪባል ድረስ አቀነቅን ነበር፡፡ የመጀመሪያው የህብረት ጉዞ ነበር፡፡ በየቦታው አብረን ነበር የምንቀሳቀሰው፡፡ ሁለተኛ ካሴት ለማሳተም ስመጣ ብቻዬን ስለመጣሁ--ትንሽ አደናግሮኝ ነበር፡፡ ከጎጃም የሚመጣ ሰው ማረፊያው ጎጃም በረንዳ ነው፡፡ ጎጃም በረንዳ ሆኜ በፊት ስመጣ ለተዋወቅኋቸው ጓደኞቼ ደወልኩላቸው፡፡ ማሲንቆ ተጫዋች አበበ ፈቃደ የሚባል አሁን ካናዳ ነው … ሁለት ቀን ከሆነኝ በኋላ ደወልኩለትና መጣ፡፡
‹‹ምን ሆነህ መጣህ›› አለኝ፡፡
‹‹ካሴት ላወጣ›› አልኩት፡፡
‹‹እና እዚህ ሆነህ ነው የምታወጣ›› አለኝ፡፡
የአዲስ አበባን የኑሮ ውድነት ስለሚያውቅ ነው እንደዚህ ያለኝ፡፡ ከዛ ይዞኝ ሄደ፡፡
የምሽት ክበብ ውስጥ አስቀጠረህ?
ጓደኛዬ ማታ ማታ ክለብ ውስጥ ይሰራ ነበር… እሱን ተከትዬ እሄድኩ ሲጫወት እሰማዋለሁ። ነገሮችን አጤናለሁ፡፡ ካሴት ካወጣሁ በኋላ ነው ካራማራ የተባለ ናይት ክለብ ውስጥ መስራት የጀመርኩት፡፡ ለአንድ ዓመት ከሰራሁ በኋላ አይቤክስ ሲከፈት፣ ሙዚቀኞችን አሰባስቤ ኮንትራት ወስጄ እየሰራሁ ሳለሁ ነው ወደ አሜሪካ የመሄድ እድል የገጠመኝ፡፡
አሜሪካ ከገባህ በኋላ በሙዚቃው ብቻ ሳይሆን በንግዱም ተሳክቶልሃል ይባላል…
አሜሪካ ሰፊ እድል አጋጥሞኛል፡፡ እንደሄድኩ ያላሰብኩት ጥሩ ፍቅር ገጠመኝ - ከአሁኗ ባለቤቴ ጋር። የባለቤቴ ራዕይና መልካም አቀራረብ ገዛኝና ጋብቻ መሰረትን፡፡ በትዳሬና በልጆቼ ደስተኛ ስለሆንኩ--በምሄድበት ቦታ ሁሉ ይቀናኛል። የመጀመሪያ ልጄ ፍቅር ይሁኔ ይባላል፡፡ ሴትዋ ሰላም ይሁኔ ትባላለች፡፡ ባለቤቴ ደግሞ የሺእመቤት ተስፋዬ፡፡ በአሜሪካ የሺእመቤት በላይ ነው የምትባለው፡፡ “ዘ በላይ ፋሚሊ” ተብለን ነው የምንጠራው፡፡ ባለቤቴ በቢዝነስ ነው የተመረቀችው---የእኔ ስራ እየዞሩ ኮንሰርት ማቅረብ ነው፡፡ በኋላ “ኢትዮጵያን የሎው ፔጅስ” የሚባል የመረጃ መጽሐፍ ማሳተም ጀመርን፡፡ እንደ ቢቢስ እና ሲኤንኤን ያሉ አለማቀፍ ሚዲያዎች ስለመጽሐፉ ብዙ ዘግበዋል፡፡ በዋሺንግተን ዲሲ የሎው ፔጅ በጣም የታወቀ ካምፓኒ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ፈጥሮልናል - ጥሩ መረጃ ነው የምንሰጣቸው፡፡ አሜሪካን አገር የሎው ፔጅ የሚባል ትልቅ የመረጃ መስጫ መፅሃፍ አለ - አሜሪካኖች በስፋት የሚጠቀሙበት፡፡ ባለቤቴ ያንን አይታ ነው ለምን ለኢትዮጵያ ተመሳሳይ ነገር አንጀምርም ብላ የጀመርነው፡፡ በየዓመቱ የሚወጣ ነው…በዚህ ስራ ላይ ለአስራ ዘጠኝ ዓመት ሰርተናል፡፡
በካምፓኒያችሁ አማካኝነት ከአሜሪካውያን ታዋቂ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ሙዚቀኞችና ተዋንያኖች ጋር ግንኙነት መፍጠር እንደቻላችሁ ሰምቼአለሁ--
አዎ--- ሂላሪ ክሊንተን፣ ጆን ማኬን፣ ዴንዝል ዋሽንግተን፣ ኤሪክ ቤኔ፣ ዳጊ ፍሬሽ/ራፐር/…እንዲሁም ከበርካታ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ሙዚቀኞችና ተዋንያኖች ጋር በሰፊው እንገናኛለን..በቅርቡ እንደውም አንዲት ኢትዮጵያዊት ከጥቁር አሜሪካዊ ጋር ተጋብታ እኔ ነበርኩ የሰርጉን ሙዚቃ የሰራሁላት፡፡
በፌስ ቡክ ፔጅህ ላይ የምርቃት ፎቶ አይቻለሁ። በምንድነው የተመረቅኸው?
ላለፉት ሁለት ዓመታት ትምህርት ቤት ነበርኩ፡፡ በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ነው የተመረቅሁት፡፡ የኮምፒዩተር ጤንነትን በተመለከተ፣ ኮምፒዩተርን ቢዩልድ ማድረግ--ኔትዎርክ፣ ኢንተርኔት ሴኪዩሪቲ ተምሬአለሁ፡፡ ከአራት ወር በኋላ ደግሞ በ“አርት ኤንድ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ” እመረቃለሁ፡፡ ወደፊትም መማሬን እቀጥላለሁ፡፡
በአገር ውስጥስ ኢንቨስት ለማድረግ አላሰብክም?
ብዙ ሃሳቦች አለኝ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት መጥቼ ፍኖተ ሠላምን ሳያት እየተለወጠች ነበር፡፡ አዳዲስ ግንባታዎች አሉ…በፍኖተ ሠላም ትልቅ ባዛር የተካሄደ ጊዜ “አንተም ልጃችን ነህ፤ የበኩልህን አስተዋፅዖ አድርግ” ተባልኩ፡፡ አፋጣኝ ምላሽ ነበር የሰጠሁት፡፡ ሁሉን ነገር ትቼ በሶስት ቀን ውስጥ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ከዛም ወደ ፍኖተ ሠላም ሄድኩ፡፡ እንደ ጠዋት አዲስ አበባ ገብቼ ወዲያው በመኪና ተሳፍሬ ፍኖተ ሠላም ከምሽቱ አራት ሰዓት ነው የገባሁት፡፡
ህዝቡ፣ ከችኳንታ እስከ አውቶብስ፣ ባጃጁ ሳይቀር… ከፍኖተ ሠላም ተነስቶ ጅጋ የምትባል 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቦታ ድረስ መጥቶ እንደ ሙሽራ አጅቦ፣ እየፎከረ እየሸለለ አጅቦ አስገባኝ---ይህን ሳይ በጣም ነው ያለቀስኩት፡፡ ስደርስ የባዛሩ መዝጊያ ደርሶ ነበር፤ ሁለት ቀን ኮንሰርት ሰርቼ ተመለስኩ፡፡ ምን ያህል ገቢ እንደተገኘ ባላውቅም ገቢው ለከተማዋ የሚውል ነበር፡፡ ኢንቨስትመንቱን በተመለከተ ግን የጀመርኩት ነገር ጥሩ ደረጃ ሲደርስ እነግርሻለሁ፡፡
በባዛሩ ኮንሰርት ላይ አንተን ይተካል ተብሎ የሚጠበቀው የአካባቢህ ልጅ ሰለሞን ደምሴ “ነይማ ላሳይስ ነይማ ጎጃም ፍኖተ ሠላም” እያለ ሲያቀነቅን የእጅ ሰዓትህን አውልቀህ ሸልመኸዋል ይባላል--
የሚገርም ድምፃዊ ነው፡፡ በጣም የሚያድግ ልጅ ነው፡፡ እኛም ድሮ እንደዚህ የሚያበረታታን ስናገኝ ደስ ይለን ነበር፡፡ ለዚህ ነው ሲጫወት ሳየው ስላስደሰተኝ የእጄን ሰዓት ፈትቼ የሸለምኩት፡፡
ቀረ የምትለው ካለ…
እግዚአብሄር ያክብራችሁ፡፡ ጎተራውን ሙሉ…አገሩን ጥጋብ ያድርግላችሁ..አይለየን..አለማችሁን ያሳያችሁ…ፍቅር፣ ሰላም፣ ደስታ ከእናተ ጋር ይሁን!

Read 4950 times