Thursday, 27 June 2013 08:52

“ከተጠያቂነት መሸሽ አንችልም”

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(5 votes)

አቶ አሸናፊ እጅጉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ በመሆን ለበርካታ አመታት የሰሩ ሲሆን የፊፋ “ኮሚኒኬ” (መረጃ) ሲመጣ በመጀመሪያ የሚደርሰው ለእሳቸው ነው፡፡ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከደቡብ አፍሪካው ጋር በአዲስ አበባ ስቴዲየም ባደረገው ግጥምያ ያገኘውን ድል ተከትሎ በተሰማው አሳዛኝ ዜናና በተከሰቱ ችግሮች ዙርያ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው ከአቶ አሸናፊ እጅጉ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

አቶ አሸናፊ እጅጉ

****

“ኮሚኒኬ” ምንድነው? “ኮሚኒኬ” ማለት በጨዋታ ጊዜ ለሚከሰቱ ጥፋቶች የሚሰጡ የቢጫ እና የቀይ ካርድ ቅጣቶች የሚገልፅበት ደብዳቤ ነው፡፡ ፊፋ ኮሚኒኬን ለእኛ ይልካል፡፡ ከዚያም በፅ/ቤቱ በኩል ለቡድን መሪና ለአሰልጣኙ ይሰጣል፡፡ የሚመጣውን “ኮሚኒኬ” መነሻ በማድረግ ውይይት ታደርጋላችሁ? ውይይት አይደረግም፡፡ ደብዳቤው እንደደረሰኝ ለብሄራዊ ቡድኑ አስተላልፋለሁ፤ ለሴቶች ብሄራዊ ቡድን እና ለዋናው ቡድናችንም ደብዳቤው በአፋጣኝ እንዲደርሳቸው አደርጋለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ማሳረፍ የሚገባቸውን ተጫዋች የማሳረፍ ግዴታ ያለባቸውና የሚገባቸው እነሱ በመሆናቸው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ “ማን ቢጫ አየ” ማን ቀይ አየ” ብለን የምንወያይበት ነገር የለም፡፡ ይሄ ጉዳይ መፈፀሙን የሚከታተል ሰው አለ? ማንም የለም፡፡ በአሰልጣኙ የስራ ዝርዝር ተራ ቁጥር 20 ላይ በኢንተርናሽናል ውድድር ወቅት ቀይና ቢጫ የሚያዩ ተጫዋቾችን መዝግቦ መያዝና በውሳኔው መሰረት ተግባራዊ ማድረግ የአሰልጣኙ ዋና ስራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ አሰልጣኙም ይህን ሃላፊነት ፈርመው የወሰዱት ነገር ነው፡፡ ይህንን ማየት ይቻላል፡፡

እኔ ከቡድኑ ጋር ቦትስዋና ድረስ አልሄድኩም፡፡ ማን ይግባ የሚለውን አላውቅም፡፡ አንዳንዴ ቅጣት እያለባቸው በህመም የማይሳተፉትን ለሞራል እያሉ ይወስዷቸዋል፡፡ ስለዚህ ማንን ማሰለፍ እንዳለባቸው ማወቅ የሚገባቸውና በትዕዛዙ መሰረት መፈፀም የነበረባቸው እነሱ ናቸው፡፡ እንጂ ጉዳዩን የሚከታተል ሰው የለንም፡፡ ደብዳቤውን ስትሰጧቸው ጉዳዩን በትኩረት እንዲመለከቱ አልተናገራችሁም? እስካሁን እንዲህ አይነት አሰራር አልነበረም፡፡ ደብዳቤው ሲመጣ ተረክበን እንሰጣቸዋለን፤ ዝርዝር ጉዳዩን የሚመለከታቸው አካላት አንብበው የሚረዱ ስለሆነ፣ እንደዚህ ነው ብለን የምናስረዳበት ሁኔታ የለም፡፡ አቶ ብርሃኑ ወረቀቱን መውሰዳቸውን አምነው ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ሰውነት አለመውሰዳቸውን ይናገራሉ፣ እዚህ ጋ ክፍተት አለ? በትክክል ክፍተት አለ፡፡

የመጣውን ኮሙኒኬ ለቡድኑ መሪ እና ለአሰልጣኙ ይሰጥ ብዬ ነው የምመራው፡፡ እዚህ ጋ ጉዳዩ ትልቅ ስለሆነ አቶ ብርሃኑ ጊዜ ስለነበረው ፈርሞ ወሰደ፡፡ መዝገብ ቤት ሰራተኛዋ አቶ ሰውነትን ጠርታ እንዲወስድ ጠየቀችው፡፡ “ቆይ ስራ አለኝ” አላት፡፡ ከዚያም ተመልሶ መጥቶ ሁለት የመዝገብ ቤት ሰራተኞች ባሉበት ወሰደ፡፡ ፀሃፊዋም በወቅቱ ወስደዋል በማለት ፈረመችበት፡፡ አልፈረሙም ነበር፡፡ አለመፈረማቸው ክፍተት ነው፤ ነገር ግን አቶ ሰውነት ማንኛውንም ደብዳቤ በሙሉ በእምነት ሳይፈርሙ ነው የሚወስዱት፡፡ ለምን ሳይፈርሙ እንደወሰዱ የጠቅኋቸው ፀሃፊዎች፤ ከዚህ ቀደምም ደብዳቤ ሳይፈርሙ እንደሚወስዱ ነገሩኝ፡፡ እኔ ግን ይሄን አላውቅም ነበር፡፡ ከደሞዝ ጭማሪ እና ከስራ ዝርዝር ደብዳቤ ውጪ ፈርመው አያውቁም፡፡ ይሄ በጣም ያሳዝናል፡፡ እንዲህ ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ስለዚህ ክፍተት አለ፡፡ የህክምና እና የቪዛን ክትትል በተመለከተ የሚመለከተው ማነው? የህክምና ሳይሆን የቪዛና የአየር ትኬት ጉዳይ ማጠናቀቅ ያለበት ጽ/ቤቱ ነው፡፡ ቀደም ሲል የክለብ ማናጀር ነበር፡፡ በአንዳንድ ምክንያቶች እንዲነሳ ተደረገ፡፡

መልሰን መቅጠር አልቻልንም፡፡ እንዲህ ሲነገር ለህዝብ ሌላ ነገር ይመስላል፡፡ ግን አንደኛ የተጫዋቾች ዝርዝር የደረሰን በጣም ዘግይቶ ነበር፡፡ በፓስፖርት አሰጣጥም ላይ ችግር ነበር፡፡ ፓስፖርት የሚያሠራ ፕሮቶኮል ሹም አለ፡፡ በአውሮፕላን ጉዞ ችግር ፓስፖርት የሌላቸው፣ ቪዛቸው የተቃጠለ፣ ሦስትና አራት ሲቀረው ነው አሰልጣኙ የሰጠን። ከጊዮርጊስም ሲመጡ ፓስፖርታቸው የሚታደስ ነበር፡፡ ያንን ለማሳደስ ኢምግሬሽን ተባብሮን በሁለት ቀን ነው የጨረሰልን፡፡ ትልቅ ባለውለታችን ናቸው። ከዚህ በኋላ ትኬት ለመቁረጥ አስመዝግበን፣ መሄጃ እንጂ መመለሻ የለም ተባልን፡፡ የእኛን ችግር እንዲያይ ለማድረግ የቡድኑን መሪ አቶ ብርሃኑን ይዘን ነበር የሄድነው፡፡ አቶ ብርሃኑ በጣም ቀናና ለማንኛውም ነገር ተባባሪያችን ነው፡፡ ይሄ ነገር ገጠመው እንጂ ጉዳዩ የአገር ጉዳይ ስለሆነ ተንሸራቶ እኛ ጋር እንዳይመጣና ችግር እንዳይፈጠር የራሳችንን ስራ ተሯሩጠን ሰርተናል፡፡ ሌላው የቢጫ ወባን ህክምና በተመለከተ ልጆቹ ካርዱን እየጣሉ እንደገና ነው የምናወጣው፡፡ እዚህም ላይ ጤና ጥበቃ ስለሚተባበረን ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ሲባል እንደገና እናወጣለን፡፡

ስለዚህ አገርን የሚጐዳ ነገር እየሸፈንን ነው የምንሰራው፡፡ ውጤታማ ስለሆኑ ደግሞ ያስቸግራል፡፡ ሉሲዎችም ከናይጄሪያ አቻቸው ጋር ሲጫወቱ ከማሊያ ጋር በተያያዘ ችግር ተፈጥሮ ነበር ይባላል፡፡ ምን ነበር የሆነው? እኔ ማሊያ ይሰጣቸው ብዬ ስመራ፣ የናይጄሪያ ማሊያን ተቀራራቢ እንዳይለብሱ በማለት ሌላ ማሊያ እንዲሰጧቸው ገልጬ ነበር፡፡ ነገር ግን እታች ያሉት የተባለውን ሳይሆን ሌላ ማሊያ ሰጧቸው፡፡ እነሱም ማሊያውን ያዩት እዛ ከደረሱ በኋላ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር የሚፈጥሩት ላይ ለምን እርምጃ አይወሰድም? የቡድን መሪውም ሆነ አሰልጣኙ በጥድፊያም ላይ ይሁን በምንም ማየት አለባቸው፡፡ እያንዳንዱን ነገር ተደረገ አልተደረገ ብዬ ለመከታተል አልችልም፡፡ ሲወስዱ ገልጦ መመልከት የተረካቢው ፋንታ ነው፡፡ “ካፍ” የሚል የተፃፈበትን ማሊያ ለአለም ዋንጫ ይዘው መሄድ የለባቸውም፡፡ እንደዚህ አይነት ስህተት ይታያል፡፡ እኔ እያንዳንዱን ወርጄ ጫማ ቁጥሩ ድረስ መከታተል ደረጃዬም አይደለም፡፡ ችግሩ ገፍቶ እንዳይሄድ እርምጃ አያስፈልገውም? እያንዳንዱ ሠራተኛ ሃላፊነቱን ተጠንቅቆ መወጣት ይገባዋል፡፡

ትጥቅንም የሚረከብ አካል ተጠንቅቆ መረከብ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ቦትስዋና ሲሄዱ ሁለት ማሊያ ነው የሰጠናቸው፡፡ አንዱ ማሊያ ላይ የካፍ ምልክቶች አሉ፡፡ በእጃቸው ላይ የሚለጠፉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች አልቀውብናል፡፡ አንድ ማሊያ ላይ ብቻ ነበር የተሰራው፡፡ ችግሩ እንግዲህ ተጫዋቾቹ ማሊያዎችን አይመልሱም፡፡ ስለዚህ በየጊዜው አዳዲስ ማሊያ ነው እያሳተምን የምንሰጠው፡፡ ፊፋ የሰጠንን ደግሞ ጨረስን፡፡ ከዚህ በፊት እንደዚህ አይነት ችግር ገጥሟችሁ አያውቅም? አጋጥሞን አያውቅም፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲከሰቱ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ አይገባም? አሁን ችግሩ ስለተከሰተ ነው እንጂ ሁላችንም ተረባርበን ነው የሠራነው፡፡ የአገር ጉዳይ በማለት ሌት ተቀን የደከምነው ለአገራችን ውጤት እንዲመጣ ነው፡፡ የደጋፊውን ፍላጐት ለማሳካት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ችግር እንዳይከሰት የራሳችንን ውሳኔ እየሰጠን ነው በጽ/ቤት በኩል፡፡

ለምሳሌ ማንም ሰው ደብዳቤ ሳይፈርም እንዳያወጣ ወስነናል፡፡ የፊታችን ሰኞ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተናል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ የሚያስፈልገውን ነገር መውሰድ ይቻላል፡፡ ለፌዴሬሽኑ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ያስገባ አለ? እስካሁን ያስገባ የለም፡፡ ከተጠያቂነት መሸሽ አንችልም፡፡ በስራው ላይ ስህተት ተፈጽሟል፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀናል፡፡ ከዚህ በኋላ ምንም ማድረግ ያለብን አይመስለኝም፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው የሚሰጠውን ውሳኔ መጠበቅ ነው የሚሻለው።

Read 2132 times