Saturday, 29 June 2013 09:09

ተቃዋሚዎች የቤት ልማት ፕሮግራሙ አይሳካም የሚል ጥርጣሬ አላቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

ዜጐች ራሣቸው ሊሠሩት በሚገባው የቤቶች ልማት ፕሮግራም ውስጥ መንግስት መግባቱ ተገቢ አለመሆኑን የተናገሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ከአገሪቱ አቅም አንፃር ፕሮግራሙ በተባለው ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ገለፁ፡፡ የባንክ ባለሙያ የሆኑት የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሠሙ፤ ማንኛውም ዜጋ ቤት ማግኘት ያለበት በራሱ ጥረት እንጂ እንደ ሎተሪ እጣ እየወጣለት አይደለም ብለዋል፡፡ መንግስት በማይመለከተው ተግባር ላይ መሠማራቱን የጠቀሱት አቶ ሙሼ፤ ፕሮግራሙን ለማስፈፀም የሚውል ፈንድ ለማግኘት ገንዘብ ካላተመ በስተቀር አቅም እንደሌውም ተናግረዋል፡፡

የቤት ግንባታውን ለማከናወን በሚሊዮን የሚቆጠር የሠው ሃይል እንደሚያስፈልግ በመጠቆምም እነዚህ ሁሉ ተደማምረው የተባለው የቤት ፕሮግራም በተባለው ጊዜ ይሣካል የሚል ግምት እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡ የፓርላማ አባልና የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ግርማ ሠይፉ በበኩላቸው፤ መንግስት የዜጐች ቤት ሠሪ ሊሆን እንደማይገባውና ከዚያ ይልቅ ለግለሠቦች ሁኔታውን አመቻችቶ እንዲሰሩ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የቤት ልማት ፕሮግራም የተባለው ነገር ትርጉም የማይሠጥ ነው ያሉት አቶ ግርማ፤ መንግስት ይህን እቅድ የዘረጋው የቁጠባ ባህልን ለማሣደግ እንደሆነ ጠቁመው፤ እንደተባለው ሁሉም ተመዝጋቢ የቤት ባለቤት ይሆናል ብለው እንደማያምኑ ገልፀዋል፡፡ የፖለቲካ ሣይንስ ምሁሩ እና የመድረክ አመራር አባል ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ የቤት ፕሮግራም ተብሎ የተቀመጠው ቢሣካ ጥሩ እንደነበር ገልፀው፤ ነገር ግን መንግስት ብዙ ድስቶችን ጥዶ የሚንቀሣቀስ በመሆኑ የመሣካት እድል ያለው አይመስለኝም ብለዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ግርማ በማከልም ፕሮግራሙ የፖለቲካ ጨዋታ ያለበትና በዋናነት ቀጣዩን ምርጫ ታሣቢ ያደረገ እንደሚመስላቸው ገልፀዋል፡፡ ለረጅም አመታት በተለያዩ አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሠሩት የመድረክ አመራር አቶ ቡልቻ ደመቅሣ በበኩላቸው፤ መንግስት የዘረጋውን የቤት ልማት ፕሮግራም አጥብቀው እንደሚቃወሙ ገልፀው፤ መንግስት በነጋዴ ሥራ ውስጥ እየገባ ነው ብለዋል፡፡ “መንግስት ነጋዴ እንዲሆን አይደለም የሚመረጠው፤ የሃገር ሉአላዊነትን እንዲጠብቅ፣ ፍትህን እንዲያሠፍን እና ግብር እንዲሠበስብ እንጂ” ሲሉ የመንግስትን ሚና አስረድተዋል፡፡

Read 12487 times