Saturday, 29 June 2013 09:13

የሙስና ተጠርጣሪዎች ጉዳይ እየተራዘመ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

ምርመራው እየተጠናቀቀ ነው ብሎ እንደሚያምን ፍ/ቤቱ ገልጿል

የገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤትን በሚኒስትር ማዕረግ የሚመሩ ዳሬክተርና ምክትላቸውን ጨምሮ በርካታ ስራ አስኪያጆችና የስራ ኃላፊዎች በተጠርጣሪነት የታሰሩበት የሙስና ምርመራ በዚህ ሳምንት እንደገና እንዲራዘም ፍ/ቤት ፈቅዷል፡፡ ቢሆንም ምርመራው መቋጫ እንዲኖረው ማሳሰቢያ አዘል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ምርመራውን በትጋት እያካሄደ መሆኑን የገለፀው የፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በመግለጽ ለአራተኛ ጊዜ ቀጠሮ እንዲራዘምለት የጠየቀ ሲሆን የታሳሪ ጠበቆች በበኩላቸው፤ የኮሚሽኑ ምርመራ እልባት የሚያገኘው መቼ ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ ሰሞኑን ፍ/ቤት ቀጠሮ የነበራቸውም በአምስት መዝገቦች ምርመራ የሚካሄድባቸው 37 ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ ሦስቱ በዋስ ተለቀዋል፡፡

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ዳሬክተር አቶ ገ/ዋህድንና ባለቤታቸውን ጨምሮ 11 ተጠርጣሪዎች የተካተቱበት የምርመራ መዝገብ ባለፈው ሰኞ እለት በፍ/ቤት የታየ ሲሆን፣ የአቶ ገ/ዋህድ ባለቤት ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋዬ የዋስ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የልጆች እናት እንደሆኑና ልጆቻቸው ትምህርታቸውን ለመከታተል እንደተቸገሩ ለፍርድ ቤቱ የገለፁት ኮ/ል ሃይማኖት፤ በዋስ ከእስር ወጥተው ጉዳያቸውን ለመከታተል እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተቃውሞውን ሲያሰማ፣ ኮ/ል ሃይማኖት ቀደም ሲል ሰነድ በማሸሽ ከመጠርጠራቸውም በተጨማሪ፣ “ሞኒት” በተሰኘ ኩባንያ ተቀጥረው የባለቤታቸውን ስልጣን ተገን በማድረግ ግብር የመሰወር ተግባር ፈጽመዋል ተብለው እንደተጠረጠሩ ገልጿል፡፡ ፍ/ቤቱ የኮ/ል ሃይማኖትን የዋስትና ጥያቄ ሳይቀበለው ቢቀርም፣ ከሌላ የምርመራ መዝገብ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሦስት ተጠርጣሪዎች በዋስ ተለቀዋል፡፡

ማክሰኞ ሰኔ 18 ቀን በሚኒስትር ማዕረግ የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን ዳሬክተር የነበሩ አቶ መላኩ ፋንታን ጨምሮ 11 ተጠርጣሪዎች በተያዙበት የምርመራ መዝገብ ፍ/ቤት ቀርቧል፡፡ አቶ መርክነህ አለማየሁ 1.3 ሚ. ብር ለመደበቅና ለመቅበር ሲሞክሩ ተባብረዋል የተባሉ ወንድማቸው አቶ ብርሃኑ አለማየሁ እና ዘመዳቸው አቶ ገተፎ መታሰራቸው የሚታወስ ሲሆን በዋስ ተለቀዋል፡፡ ረቡዕ ሰኔ 19 ቀን ደግሞ አቶ ጥጋቡ ግደይ ጨምሮ፤ 5 ተጠርጣሪዎችን የያዘው መዝገብ ፍ/ቤት ሲቀርብ ወ/ሮ ሶፊያ ሱሌማን የዋስ ጥያቄ አቅርበው የፀረ ሙስና ኮሚሽን ተቃውሞ እንደሌለው በመግለፁ በ2ሺ ብር ዋስ ተለቀዋል፡፡ ከሰኞ እስከ ሐሙስ ድረስ በፍ/ቤት የተመለከታቸው አምስት የምርመራ መዝገቦች ላይ ዋናው አከራካሪ ጉዳይ የነበረው ግን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ ነው፡፡

ሦስቴ የ14 የጊዜ ቀጠሮ እያስፈቀደ ምርመራ ሲያካሂድ የቆየው የፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ ያከናወናቸውንና ቀሪ ስራዎችን በመዘርዘር ተጨማሪ የሁለት ሳምንት ቀጠሮ ጠይቋል፡፡ የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው፤ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለ4ኛ ጊዜ የ14 ቀን ቀጠሮ መጠየቁ፣ ተጠርጣሪዎች ያለ በቂ ማስረጃ እንደታሰሩ ያሳያል ብለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎች ክስ ሳይመሰረትባቸው ለ45 ቀናት መታሰራቸው ተገቢ አይደለም በማለት የተከራከሩት ጠበቆች፣ እየተጓተተ የመጣው ምርመራ ማብቂያው የት ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ስራውን በትጋት እንዲሰሩ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ይስጥልን ሲሉም አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

ፀረ ሙስና ኮሚሽን በትጋት እየሰራ መሆኑን በመጥቀስ በሰጠው ምላሽ፣ ምርመራው ሠፊና ውስብስብ በመሆኑ ጊዜ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከተመለከተ በኋላ፣ ምርመራው በአብዛኛው እንደተከናወነ መገንዘቡን ጠቅሶ፤ ከምርመራው ውስብስብነትና ስፋት አንፃር ለቀሪ ስራዎች የጊዜ ቀጠሮ መፍቀዱን ገልጿል፡፡ ነገር ግን ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራውን እንዲቋጭ የሚገፋፋ ማሳሰቢያ አዘል ትዕዛዝ ፍ/ቤቱ ሰጥቷል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በቀጣይ ቀጠሮ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ ምን ያህል የሰነድና የምስክር ቃል እንዳዘጋጀ በግልጽ ዘርዝሮ እንዲያቀርብ በፍ/ቤቱ ታዟል፡፡

Read 12983 times