Saturday, 29 June 2013 09:43

የፌስቡክ ‘ፕሮፋይል ፒክቸር’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(18 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ይኸው ሰኔም ልትወጣ ነው…ሐምሌም ሊገባ ነው…ዓመቱም ሊያልቅ ነው! ይለቅማ! ስሙኝማ…ዘንድሮ ራስን ሆኖ ከመገኘት ይልቅ የታየዘው ምን መሰላችሁ…‘ኢምፕሬስ’ ማድረግ፡፡ (‘ኢምፕሬስ’ የምትለው የገባችው ጨዋታ ለማሳመር እንደሆነ ልብ ይባልልን…) እናላችሁ…የነገሮችን ስሞች እንደቀለበት መንገድ ማሽከርከር፣ በተለይ ሁሉ ነገር ውስጥ የ‘ፈረንጅ አፍ’ ሸጎጥ ማድረግ የተለመደ ‘ኢምፕሬስ’ ማድረጊያ ዘዴ ሆነውላችኋል፡፡ ‘የምናምን ድርጅት የሰው ሀይልና የፕሮጀክት ትግበራ የሥራ ሂደት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር…’ አይነት “ትንፋሽ እየወሰዳችሁ…” የምትጠሩት ስም አይሰለቻችሁም! ኮሚክ ነገር እኮ ነው…ከሰውየው የሥራ ሀላፊነት ዝርዝር ይልቅ እኮ የማዕረግ ስሙ ሊረዝም ምንም አይቀረው! (ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አንዳንድ የሥራ ሀላፊዎች ጠረዼዛ ላይ ፊት ለፊታቸው የሚቀመጠውንና ስማቸውንና ሀላፊነታቸውን የሚገልጽ ጽሁፍ አይታችሁልኛል! የምር እኮ… ግዙፍነቱ …አለ አይደል…“ተሳስተው የመሥሪያ ቤቱን መጠሪያ ከዋናው በር ነቅለው አምጥተውት ነው እንዴ!” ያሰኛል፡፡

አሀ… ከመተለቁ የተነሳ አንዳንዴ የሀላፊውን ከረባት እርፍናና ቅሽምና ማየት አልቻልንማ! ቂ…ቂ…ቂ… እኔ የምለው… ሥራ ይቀላጠፍ፣ ዙሪያ ጥምጥም ነገር ይቅር በሚባልበት ዘመን አንድ መስመር ጨርሶ ሁለተኛ መስመር የሚያጋምስ የማዕረግ ስም አጻጻፍ ከየትኛው የበለጸገ አገር የወሰድነው ተሞክሮ ነው! (ስሙኝማ…ይሄን ሁሉ ነገር ከበለጠጉ አገሮች ተሞክሮ እየወሰድን በ‘ፎቶኮፒ’ ለራሳችን እንደምናውለው…“ምን አለ እኛ የኮረጅነውን ነገር የፈጠሩበት አእምሯቸውን በወሰድን…” አያሰኛችሁም! ‘ቦተሊከኞች’ ሆይ… “ከበለጸጉ አገሮች የወሰድነው…” ማለት ‘ደረት እንደማይስነፋ’ ልብ ይባልሉንማ! እናማ…“ከበለጸጉ አገሮች የወሰድነው…” ማለት ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ‘ኢምፕሬስ’ ለማድረግ! ስሙኝማ…አሁን አንዳንድ ፊልሞቻችንን ነገሬ ብላችሁ እንደሆነ በአማርኛ ቋንቋ ተሠርተው ፖስተሮቻቸው በእንግሊዝኛ የተሞሉ ናቸው፡፡ አማርኛው ኖሮ እንግሊዝኛው በተጓዳኝነት ቢኖር ይገባችኋል…ግን ፊልሙ ውስጥ..አለ አይደል…ከቦሌ እስከ ጉለሌ ሁላችን የምንሞክራት ‘ሁዋሳ’ፕ’ የምትለዋን የ‘ፈረንጅ አፍ’ በሌለችበት ፊልም የእንግሊዘኛ ድርድር… ግርም አይላችሁም! ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ጠጋ ብላችሁ ፖስተር ላይ የተጻፈውን ስታነቡ…አለ አይደል…“ይቺን እንኳን ያለስህተት መጻፍ አይቻልም!” ያሰኛችኋል፡፡

እናማ…ይሄ ሁሉ ለምን መሰላችሁ… ‘ኢምፕሬስ’ ለማድረግ! ስሙኝማ እግረ መንገዴን…ፊልሞች የአማርኛ ቃለ ምልልሶችን በእንግሊዝኛም በግርጌ ጽሁፍ ማቅረባቸው (‘ሰብታይትል’ የሚባለው) አሪፍ ነው፡፡ ግንማ… የ‘ፈረንጅ አፏ’ ኘላይ ባትሆን እንኳን መሰረታዊ ስዋሰው ምናመን ነገር ይታሰብበት! አንዳንዴማ በየፖስተሩና በየ‘ሰብታይትሉ’ ላይ ያሉትን ስህተቶች ስታዩ…አለ አይደል…“ከሼክስፒር ትያትሮች ወዲህ እንግሊዝኛ ላይ ስር ነቀል ለውጥ የተካሄደው በፊልሞቻችን ፖስተሮችና ‘ሰብታይትሎች’ ነው…” አይነት ነገር ያሰኛችኋል፡፡ እናማ ይሄ ሁሉ ለምን መሰላችሁ…‘ኢምፕሬስ’ ለማድረግ! ስሙኝማ…ይሄ የ‘ፈረንጅ አፉን’ በሆነ ባልሆነው ቦታ በመሸጎጥ ‘ኢምፕሬስ’ ማድረግ የእኛ የተራዎቹ ነገር ብቻ ሳይሆን ‘ወደላይም’ ከፍ፣ (ኧረ ‘በጣም ከፍ’!) ይላል፡፡ ይኸውና… ኧረ እባካችሁ ‘ትራንስፎርሜሽን’ ለሚለው አቻ አማርኛ ቃል አይጠፋም እያልን ባለንበት ሰዓት…‘ሌጌሲ’ ተጨምራ አረፈችው! (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በየቦታው ‘ሌጌሲ’ የምትለዋን በየመፈክሩ ላይ የሚከቱ ሰዎች አንዳንዶቹ “ለመሆኑ ሌጌሲ የምትለዋ ቃል ትርጉሟ ምንድነው?” ቢባሉ የሚሰጧቸው መልሶች ለቲቪ ዝንቅ ፕሮግራም የሚሆኑ አይመስላችሁም! ከሚሰጡት መልስ አንዱ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…“ሂድና የበላይ አካልን ጠይቅ!) እናማ ይሄ ሁሉ ለምን መሰላችሁ…‘ኢምፕሬስ’ ለማድረግ! እናላችሁ…ይሄ ‘ኢምፕሬስ’ የማድረግ አባዜ ማለቂያ ያለው አይመስልም፡፡ በየመንደሩ እየተቋቋሙ ያሉት የማህበረሰብ ቢጫና ጥቁር ኮንቴይነር ቤቶች ላይ የተጻፈውን ልብ ብላልችሁልኛል? ‘…ፖሊስ ጣቢያ…’ ከማለት ይልቅ የተጻፈው ‘…ፖሊስ እስቴሽን…’ የሚል ነው፡፡ (ሀሳብ አለን…‘…ፖሊስ እስቴሽን…’ የሚለው ቃል የማይቀርልን ከሆነ ‘እስቴሽን’ የምትለዋ ቃለ ውስጥ ‘እ’ የምትለው ፊደል ወይ ትወገድልን… ወይም “ማን የጻፈውን ማን እናቱ የወለደችው ያስወግዳል!” ከተባለ ‘ትዋጥልንማ’! ቂ…ቂ…ቂ… እናማ ይሄ ሁሉ ለምን መሰላችሁ…‘ኢምፕሬስ’ ለማድረግ! እኔ የምለው…የስም መርዘም ወይም የ‘ፈረንጅ አፍ’ መክተት እኮ ለነገርዬው ተጨማሪ ‘ክብደት’ አይሰጠውም፡፡ አባቶቻችን ‘መልከ ጥፉ በስም ይደገፉ…’ የሚሏት ነገር አይነት ነው፡፡ አሁን ደግሞ ይሄ የፌስቡክ ዘመን አይደል…ፌስቡክ የሌለው ሰው ልክ እኮ በ‘ድንጋይ ዘመን’ እንዳለ ሰው ሊቆጠር ምንም አይቀረው፡፡

እናላችሁ… ኤፍ ኤሞች ላይ በርካታ ፕሮግራሞች “ፌስቡክ ገጻችን ላይ ላይክ አድርጉን…” ሲሉ እየሰማን ነው፡፡ ‘ላይክ’ እንድናደርጋችሁ የሁላችሁንም ፎቶ ለጥፉልንማ! አሀ…‘ላይክ’ የሚደረገው ገጹ ይሁን ወይም ከገጹ ጀርባ ያሉት ሰዎች ግልጽ ይደረግልና! ስሙኝማ…እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ… ልጅቷና ሰውየው የተዋወቁት ፌስቡክ ላይ ነው፡፡ እና በአካል ሊገናኙ ይቀጣጠራሉ፡፡ ታዲያላችሁ…እሷዬዋ አሪፍ እንትናዬ ሆና ቀጠሮው ቦታ ስትጠብቅ የሆነ ሰው ይመጣል፡፡ እናማ… “እንዴት ነሽ?” ምናምን ሲላት እሷ ሆዬ በልቧ “ምን አይነቱ ደረቅ ሰው ነው?” ምናምን እያለች ሳለች…ሰውየው ማን መሰላችሁ…የፌስቡከ ጓደኛዋ! ለካስ በፌስቡክ ‘ፕሮፋይል ፎቶው’ ሸበላና የብራድ ፒትን የቶም ክሩዝ ‘ሪሚክስ’ የሚመስለው ሰውዬ በአካል ሲታይ የእኔ ቢጤ ዘፍዝፈው ያሳደሩት በቤተሰቡ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአልጋ ልብስ ይመስላል! እናላችሁ…እሷዬዋ “ፕሮፋይል ፒክቸርህ ላይ ሌላ ነህ?” ትለዋለች፡፡ እሱዬው ምን ቢል ጥሩ ነው… “በፎቶሾፕ አሳምሬው ነዋ!” እናማ…እንትናዬዎች… የፌስቡክ ‘ፕሮፋይል ፒክቸር’ ሁሉ እውነት መስሏችሁ እንዳትታለሉማ፡፡ የእኔ ቢጤዎቹ “ሰው ቢጠይቀን ምን ብለን እንመልሳለን?…” በሚል ፌስቡክ ገጽ የከፈትን ፎቶ የማንለጥፈው እኮ ፎቶ ስለሌለን ሳይሆን…“ማን እጅ ይሰጣል!” በሚል ነው፡፡

ልጄ አንዳንዴ ብልጥነት እኮ ወንዝ ያሻገራል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የብልጥነት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ… በጋብሮቮ መንገድ ላይ ሲያለቅስ የነበረ አንድ ልጅ የገጠመው አንድ ለጋስ ሰው ልጁን “ለምንድነው የምታለቅሰው?” ይለዋል፡፡ ልጁም “አንድ ብር ጠፋብኝ” ሲል ይመልሳል፡፡ ሰውየውም “በቃ፣ አታልቅስ” ብሎ አንድ ብር ይሰጠዋል፡፡ ልጁ ግን ብሩን ከተቀበለ በኋላ ማልቀሱን ይቀጥላል፡፡ ሰውየውም “አሁን ደግሞ ምን ሆንኩ ብለህ ነው የምታለቅሰው? ብር ሰጠሁህ አይደል እንዴ!” ይለዋል፡፡ ልጁ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው...“አንዷ ብር ባትጠፋ ኖሮ ሁለት ብር ይሆንልኝ ነበር፡፡” ልጁ ጋብሮቮያዊ ነዋ! እናላችሁ…በየቦታው የምታዩት ‘ኢምፕሬስ’ የማድረግ ሙከራ ወደ ኮሜዲነት እየተለወጠ ነው፡፡ እናማ…የፈረንጅ አፍ መክተት፣ ስምን “መንገዱ ረዘመ፣ ረዘመ…” አይነት ማስረዘም…“ሂድና ሞኝ ቱሪስት ብላ!” የሚሉ ‘ነቄ’ ሰዎች እንዳሉ ማወቁ አሪፍ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ‘ኢምፕሬስ’ የምትለዋን የ‘ፈረንጅ አፍ’ ደጋግሜ በመጠቀም የምርም ‘ኢምፕሬስ ካላደርግኋችሁ’… አለ አይደል…‘ነቄ’ ብላችኋል ማለት ነው፡፡ እንደ ፌስቡክ ፕሮፋይል ፒክቸር መሆኑን ነቅታችሁብኛል ማለት ነው፡፡ ‘“ማሞ ሌላ መታወቂያ ሌላ…” እንደተባለው፡፡ ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 7346 times