Saturday, 06 July 2013 10:50

ምክኒያታዊነት እና እንባ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(7 votes)

ወደ ለቅሶ ቤትም ሆነ ሠርግ ቤት አዘውትሮ መሄድ አልወድም፡፡ ሠርግ ቤት የግብዣ ካርድ ሲደርስህ ብቻ መሄድ ትችላለህ፡፡ ለለቅሶ ቤት የግብዣ ካርድ አያስፈልግም፡፡ የዳሱም ሆነ የድንኳኑ አዘጋጆች የገንዘብ ወጪ (ጣጣ) አለባቸው፡፡ ታዳሚውን ለማስደሰትም ሆነ ለማሳዘን ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡
እኔ ሁለቱንም አላዘወትርም፡፡ ግዴታ ሲሆኑብኝ ብቻ ጐራ እላለሁ፡፡ ስለ ደስታ ቤቱ ለጊዜው ልተውና ለቅሶው ላይ ላተኩር፡፡ ምናልባት፤ ለቅሶ ቤት መሄድ የምፈራው የለቅሶን ትርጉም ስለማላውቅ ይሆናል፡፡ አልቅሼ አላውቅም አይደለም ያልኩት፡፡ ለቅሶ ራሱ ለሰው ልጆች ምናቸው እንደሆነ ነው ያላወኩት፡፡
The Logic of the Moist eye የምትል ምዕራፍ ከአርተር ኮስለር መፅሐፍ ላይ አገኘሁ፡፡ መረጥኳት፡፡ ጨመቅኳት፡፡ ጠብ የሚል ካለ እንደ እንባ ጨው ጨው ባይልም እስቲ ቅመሱት፡፡
ለቅሶ ለሰው ልጆች የመጀመሪያ ቋንቋ ነው፡፡ በተወለድንበት ቅፅበት አለምን የምናናግርበት፡፡ ለቅሶ የመጨረሻም ቋንቋ ነው፡፡ ከእንግዲህ ላለመናገር/ላለመኖር አለምን ጥሎ የሚጓዝ ሰውን እንሸኝበታለን፡፡ የመጀመሪያና የመጨረሻ ብቻ ሳይሆን የእድሜ ልክም ቋንቋ ነው፡፡ ያልተወለደ እና በህይወት ያልኖረ… ማልቀስ አይችልም፡፡
ለምንድነው የምናለቅሰው? ብለን ስንጠይቅ አንድ ሳይሆን ብዙ መልሶች እናገኛለን፡፡ ለቅሶ ሀዘንን ብቻ ገላጭ አይደለም፡፡ ለቅሶ ማለት የእንባ ከረጢት የሚያመነጨው ፈሳሽ ማለት ብቻም አይደለም፡፡ ለቅሶ ያለው በሞት አለም ውስጥ ሳይሆን ህይወት ባለበት አለም ላይ ነው፡፡ የለቅሶ መኖር የሰው ልጅን የስሜት ሙቀት ከታችኛው እርከን እስከ ከፍተኛው ጥቅል ፍቅር አንድነት መድረስ እና መመለስ መቻልን አመልካች ነው፡፡ለቅሶ ለፈረንጆቹ ሁለት ስያሜ አለው Crying & Weeping.
ህፃን ልጅ ጡት ፈልጐ ሲያለቅስ ለቅሶው ማስጠንቀቂያ ወይንም ፍላጐቱን ማሟያ ነው፡፡ ፍላጐቱ እንዲሰጠው በመሻት ሲወራጭ ድርጊቱ መፍጨርጨርን… እልህን… ትግልን ያሳያሉ፡፡ ህይወት ላይ ለመቆየት ከሚያስፈልጉ ትግሎች ጋር የሚያነሳሳ ምክንያት ሲደነቀርበት ሰው አፀፋውን በአፀፋ መመለሱን የሚገልጽባቸው (Self asserting) አንዱ ነው፡፡ ራስን ከተፈጥሮአዊ ህልውና ጋር ለማመሳሰል ለማፎካከር የሚጠቅም ስሜት ነው፡፡
ይህ ስሜት እንዲመነጭ የሚያነሳሳ ምክንያት ሲደነቀርበት ሰው አፀፋውን በአፀፋ መመለሱን የሚገልጽባቸው መቆጣት፣ መፍራት፣ መታገል፣ ረሐብ፣ በሰውነት አካል ላይ የሚሰሙት ህመሞች… የተወሰኑት ናቸው፡፡
እነዚህ ምክኒያቶች የሚፈጥሩት ስሜት Self asserting እርምጃዎች በሰውየው አማካኝነት እንዲተገበሩ ያስገድዳሉ፡፡ ሁሉም ስሜቶች፤ በጡንቻ አማካኝነት ወደ ተግባር የሚቀየሩ ናቸው፡፡ ጡንቻ የሚያበረታው፣ እንዲፈጥን… እንዲቀለጥፍ የሚረዳው ሆርሞን (አድሬናሊን) አጋራቸው ነው፡፡ ያለዚህ ሆርሞን ሰው የተፈጥሮን ጫና መቋቋም አይችልም፡፡
ለምሳሌ፤ ሴትየዋ ባሏ መሞቱ ሲነገራት፤ በመጀመሪያ ደንዝዛ ትደርቃለች፡፡ የሰማችውን ማመን ያቅታታል፡፡ …የተከሰተውን ነገር መገንዘብ ስትጀምር ጨርቋን ጥላ ልትሮጥ ሁሉ ትችላለች… ከተከሰተው መከራ በስነ ልቦናዋ ላይ የደረሰውን ስቃይ በአካሏ አማካኝነት ተወራጭታ ለማምለጥ ትሞክራለች፡፡ ህመሙ እና ስቃዩ በእሷ መፍጨርጨር ጥሏት እንደማይሄድ ስትገነዘብ ወደ ቅስም ስብራት ታመራለች፡፡ ወደ መቀበል፡፡
እዚህ ላይ እንባ የተሰበረ ቅስምን በሚያሻማ መልኩ የሚጠቁም ማረጋገጫ አይደለም፡፡ ሀዘኑን በተሸከመው ሰው ሰውነት ላይ የሚገለፁ የእንቅስቃሴ ምልክቶች ግን የሚያሻሙ አይደሉም፡፡
በሳቅ ምክንያት የሚፈስ እንባ እና በሀዘን ምክንያት የሚፈሰው በመጠንም ሆነ በሌላ መለኪያ አንድ ቢሆኑም… በሳቅ ወቅት ሰውነት ከመጠን ያለፈ ይፍታታል፡፡ ጭንቅላት ወደ ማጅራት ከንበል ይላል፡፡ ሰውነት አይጨበጥም፡፡
በሀዘን ወቅት (ሀዘንን መቀበል ከመጣ በኋላ) ጭንቅላት በጉልበቶች ላይ ወይንም ወደ ደረት በትከሻ መሀል ይጣላል፡፡ ራስን በራስ… እጅን በወገቡ አዙሮ መታቀፍ፣ በሰው ትከሻ ሀዘንተኛው ራስን ለድጋፍ ማሳረፍ፣ ሰው ላይ ተጠምጥሞ መንሰቅሰቅ… ሀዘንን ለማምለጥ የተደረገው የአካላዊ መወራጨት እንደተቻለ በሰውነት መፍጨርጨር… ሳይቻል ሲቀር በፋንታው “መቀበል” መተካቱን የሚያሳዩ አካላዊ የእንቅስቃሴ መግለጫ ናቸው፡፡ ድጋፍ፣ ሀዘኔታ እና ፍቅር እንሻለን ማለታቸውም ነው፡፡
በደስታ ምክንያት ከሳቅ የፈለቀ እንባን ሳቂው ይቋቋመዋል፡፡ ድጋፍም አይሻም፡፡
ሌላ ምሳሌ፡- ህፃኑ ልጅ አሁን አድጓል፡፡ ወደ እናቱ እቅፍ እየሮጠ… ድንገት ደንጋይ ቢያደናቅፈው እና ቢወድቅ፤ ልክ ድንገተኛ ሞትን እንደተረዳችው የቅድሟ ሴትየው መጀመሪያ ይደነግጣል፡፡ ድንጋጤው ፊቱ ላይ የሚስተዋለው… በመውደቅ ላይ ባለበት ቅጽበት ነው፡፡ መሬቱ አጉል ቦታ እንዳይመታው በደመነብስ በሚወራጭበት ሰከንድ፡፡ ለመትረፍ የሚያደርገው መፍጨርጨር እስኪያከትም የድንጋጤ ገጽታ በፊቱ ላይ መታየቱን ይቀጥላል፡፡ እሱን ለማትረፍ የቀለጠፉት ጡንቻዎቹ መሬት ከተንከባለለ በኋላ… እና ተጨማሪ አደጋ አለመኖሩን ሲገነዘቡ መልሰው ይላላሉ፡፡ የጡንቻ መላላት፤ የአድሪናሊን ሆርሞን መመንጨት ማቆሙን ገላጭ ነው፡፡ የመጀመሪያው የፍርሐት ክፍለ ጊዜ አልፏል፡፡ ፊቱ ላይ ያለው ገፅታ ከፍርሐት ወደ ሐዘኔታን መሻት ይለወጣል፡፡ ይኼኔ፤ ያለቅሳል፡፡
ግን የሚያለቅሰው፤ ሀዘኔታን የሚሰጠው ሰው ካለ ነው፡፡ እናቱ ወይንም ሌላ “አይዞህ ባይ” በአቅራቢያ ከሌለ ሀዘኔታ መሻቱ ስለማያዋጣው… ሌላ የሚያዋጣ አማራጭ ይፈልጋል፡፡ ግራ መጋባት ፊቱ ላይ ከድንጋጤው በኋላ የሚከተል ይሆናል፡፡ ግራ ከመጋባት ሲያገግም፤ ከት ከት ብሎ ይስቃል፡፡
የእናቱ ማባበል… ወይንም የአይዞህ ባይ ሆይ ሆይታ ካየለ ግን በተቃራኒው ሀዘኔታን መሻቱ ወይንም ፍቅር ይገባኛል ባይነቱ ይባባሳል፡፡ ለቅሶው በቀላሉ ላይቆም ይችላል፡፡ ብቻውን ያለ “እኔ ልውደቅ” ባይ እንቅፋቱ ሲጥለው፤ ለፍርሐቱ እና በወቅቱ ለተሰማው ስሜት ምክንያታዊ አማራጭ በደመነፍሱም ቢሆን ይፈጥራል፡፡
ወደፊት ሲያድግ፣ ሀዘኔታ ፈላጊ አዝማሚያውን በአጭሩ የቀጨ፣ ቆፍጣና ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ለፍርሃቱ በሙሉ “ለቅሶ እና ማባበያ” የማይፈልግ መሆኑ ጥሩ ቢሆንም፤ በአግባቡ ሰአት እና ሁኔታ አለማልቀስ ግን በስሜት ተሸካሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ያመጣል፡፡
የተወጠሩ፣ የደነገጡ፣ በስቃይ የደከሙ ስሜቶች እና የጡንቻ አውታርን… በለቅሶ እንዲያርፉ ካልተደረጉ ባለስሜቱ ጉዳት ይጠበቅዋል፡፡
ምናልባት የሞተባቸው ሰውን ተከትለው የሚሞቱ ሀዘንተኞች…የሞታቸው ምክንያት ቅስማቸው መሰበሩ ሳይሆን፤ የተሰበረውን ቅስም በማሳረፉ በለቅሶ አማካኝነት… ሃዘናቸውን ከራሳቸው አቅም ውጭ ለሆነው ሙሉኤ ኩሉው ህግ (Cosmic justice) በእንባ መልክ አሳልፈው መስጠት ባለመቻላቸው መሆኑ ይታመናል፡፡ ህይወት ላይ ራሳችንን ለማጠንከር፣ ጫና ለመፍጠር ለማስከበር… የምናለቅሰው ለቅሶ crying ሲሆን … ይህ ከራስ አቅም ውጭ ለሆነ የበላይ፣ ልዕለ አንድነት ሀዘናችንን አሳልፈን ስንሰጥ የሚወጣን እንባ ግን “Weeping” (በአማርኛ ትርጉሙን አላቀውም) ተብሎ ይጠራል፡፡
ባለቅኔው ቴኒስን፣ የጀግናው አስከሬን ከጦር ሜዳ (?) ሲመጣ በሀዘንዋ መብዛት ሳቢያ ማልቀስ ስላልቻለችው (በግጥሙ ለሟቹ ያላት ቅርበት ግልጽ ባይደረግም) ሚስት እንደሚከተለው ይቀኛል?
Home they brought the warrior dead she nor swooned nor uttered cry/
All her maidens, watching said/
“She must weep or she will die.”
ለቅሶ ቤት ውስጥ ከገጠሙኝ ለቀስተኞች (በበለጠ የተጐዳው ማን እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡
የበለጠ የተጐዳው ያልተቀበለው ነው፤ የሟቹን ሞት ያልተቀበለው፡፡ ወደ መፍጨርጨር ወደ ደረት መምታት፤ ወደ “ጉርጓድ ተከትዬ ልግባ” የሚያደላው እሱ ወደ “መቀበል” ደረጃ ያልደረሰ ነው ብዬ ከእንግዲህ የምመዝን ይመስለኛል፡፡
እንባ ከሳቅም ጋር ዝምድና እንዳለው ሁሉ ከምክንያት አልባው ደመነፍስም ጋር ይዛመዳል፡፡ በሪፍሌክስ አክሽን (reflex action) ጠለቅ ያላለ የስሜት ፍቺ ከማይፈልጉ የነርቭ መዋቅሮችም ጋር የእንባ ስሜት ይጣመራል፡፡
ለምሳሌ አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል ማለት…ባል ሲሞት ሚስት ታለቅሳለች እንደማለት ያህል ጠለቅ ያለ ውስጣዊ የስሜት ጉዳት ደረጃን ወይንም የአእምሮ የፍቺ ተሳትፎን አይጠይቅም፡፡ ባል ሲሞት ሚስት የምታለቅሰው…ከፍ ያሉ መረዳቶችን በስሜት አማካኝነት…ከድንጋጤ እስከ መቀበል በተለያየ ደረጃ አስተናግዳ ሲሆን፤ “አፍንጫ ተመትቶ አይን የሚያለቅሰው” ግን ስሜትም ሆነ ምክንያታዊነት የሌለው ደመ ነብስ በመሆኑ ነው፡፡
ሁሉም የተፈጥሮ ፍጡር እጣፈንታ ከውልደት እስከ ሞት የሚያስተሳስረው እንቆቅልሽ በሞት ቋጠሮ ሲጠናቀቅ ለሚመለከት ሁሉ የስሜቱን ውጥረት በእረፍት ለማደስ፣ ለመቀበል…ተቀብሎም ለመቀጠል፤ ለቅሶ ብቸኛ አማራጩ ነው፡፡
እንደኔ እይታ ሞትን በጭፈራ፣ በፉከራ እና በዘፈን የሚሸኙ ማህበረሰቦች መቀበል ደረጃ ላይ የደረሱ አይመስለኝም፡፡ ገና ፍርሐት ላይ ናቸው፡፡ እንደኔ እይታ ሞት የሚሞተው በሀዘን ነው፤ ሀዘን ደግሞ የሚሞተው በመቀበል ብቻ ነው፡፡ በለቅሶ፡፡

Read 4358 times