Saturday, 06 July 2013 11:14

ስደት የከፋ ማህበራዊ መዘዝ እያስከተለ ነው!

Written by  ኤልሳቤት እቁባይ
Rate this item
(3 votes)
  • ለትዳር ሽምግልና ሲላክ “አረብ አገር ትልካታለህ ወይ” ተብሎ መጠየቅ ተጀምሯል
  • መምህራን፣ ፖሊሶችና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ጭምር እየተሰደዱ ነው

የማህበራዊ ­ጥናት መድረክ ሰሞኑን “የወጣቶች ስደት” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ፕሮግራም ወደ ደቡብ አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ የሚደረጉ የስራ ጉዞዎች ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ከመደረጋቸውም በላይ ውይይቶችም ተካሂደዋል፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን ጉዞ አስመልክቶ ጥናት ያቀረቡት ዶክተር ዘርይሁን በጥናታቸው መግቢያ ላይ፤ ፍልሰት በአገሪቱ ረጅም ታሪክ ያለው እንደሆነ ጠቅሰው፤ የቅርብ ጊዜውን የፍልሰት ታሪክ በሶስት አበይት ክፍሎች በመለየት አስቀምጠዋል፡፡
የመጀመሪያው ዘመን ቅድመ 1966 አብዮት ሲሆን፤ በጣም ውሱን ፍልሰት የታየበት እንደነበርና ይሄ ዘመን ህብረተሰቡ ተምሮ ወደ አገር የመመለስ ሁኔታው የጎላበት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሁለተኛው ከ1966 እስከ 1983 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚያካልል ሲሆን በአብዛኛው ወደ ምእራቡ አለም የፖለቲካ ስደት የበዛበት፤ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረገውም የስራ ፍልሰት የጀመረበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ፍልሰትን በአሉታዊነት የሚመለከት ፖሊሲ እንደነበረም በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
ሶስተኛው ድህረ 1983 ሲሆን የመንቀሳቀስ ይሄ ወቅት መብት የተከበረበት፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስደት እንዲሁም ከፍተኛ የስራ ፍልሰት የታየበት እንደሆነ አጥኚው አመልክተዋል፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ፍልሰት ከ1990ዎቹ ወዲህ እንደተስፋፋ የጠቆመው ጥናቱ፣ ለዚህም ምክንያቱ በአገር ውስጥ አና በደቡብ አፍሪካ የታዩ ለውጦች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በአገር ውስጥ ከታየው የመንቀሳቀስና ሰነዶችን በቀላሉ የማግኘት የመብት ለውጥ ባሻገር በደቡብ አፍሪካም የአፓርታይድ ስርአት መውደቅ ያመጣው ምቹ ሁኔታ እንዲሁም በኬኒያ እና በኢትዮጵያ የተደረሰው የቪዛ ስምምነት ተጠቅሰዋል፡፡
ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረገውን ፍልሰት ታሪካዊ ዳራ አስመልክቶ ጥናት ያቀረቡት ዶክተር አስናቀ በበኩላቸው፤ ጉዞው ከ1970ዎቹ አንስቶ ቢጀመርም ኢትዮጵያዊያን በብዛት ወደ ሥፍራው መጓዝ የጀመሩት ግን ከ1983 ዓ.ም ወዲህ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሴት ተጓዦች ቁጥር በከፍተኛ መጠን በማሻቀብ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በሁለቱም ጥናቶች ላይ የፍልሰቱ ዋነኛ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን በመዳረሻ አገሮች ያለው ሰርቶ የማግኘት እድልም ሳቢ ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመሄድ የሚገፋፉ ምክንያቶች ተብለው ከተጠቀሱት መካከል፣ በአገር ውስጥ የስራ እድል አለመስፋፋት፣ በተለይ ለገጠር ሴቶች ከግብርና ስራ ውጪ ያሉ የስራ አማራጮች ውሱን መሆንና የጓደኛና የቤተሰብ ተጽእኖ ይገኙበታል፡፡ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ከሚፈልሱት የህብረተሰብ አባላት መካከል በስራ ላይ ያሉ መምህራን፣ ፖሊሶችና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ጭምር እንደሚገኙበት ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
በጉዞ ወቅት የሚገጥሙ ችግሮችን አስመልክቶ በጥናቱ ላይ እንደቀረበው፣ የደቡብ አፍሪካ ጉዞ በአብዛኛው የሚደረገው በህገወጥ መንገድ በመሆኑ ዋናው ችግር ያለው ደቡብ አፍሪካ እስኪገባ ባለው የጉዞ ሂደት ውስጥ ሲሆን በህጋዊ መንገድ የሚደረገው የመካከለኛው ምስራቅ ጉዞ ችግር የሚጀምረው ደግሞ መዳረሻ አገር ላይ ነው፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገው ጉዞ ከአገር ውስጥ እስከ ደቡብ አፍሪካ የተዘረጋ ጠንካራ ኔትወርክ ባላቸው ደላሎች የሚካሄድ ሲሆን በመንገድ ላይ ለሚደርስ እንግልት፣ ስቃይና ሞት ማንም ተጠያቂ አካል እንደሌለ ተጠቁሟል፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ ጉዞ ከአገር ከተወጣ በኋላ በህጋዊ መንገድ በሄዱት እና በህጋዊ መንገድ ባልሄዱት መካከል ልዩነት እንደሌለ ያመለከተው ጥናቱ ፤ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ወደ ሳኡዲ የሚደረገው ጉዞ በቀጣሪ ኤጀንሲዎች ስምምነት ብቻ የሚከናወን በመሆኑ ተቀጣሪዎች ወደ ተቀባይ አገሮች የሚሄዱትና የሚኖሩት በአሰሪው መልካም ፈቃድ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ኤጀንሲዎች ህገወጡንና ህጋዊውን ቀላቅለው ይሰራሉ የሚል ጥርጣሬ ማረበቡም ተጠቅሷል፡፡
ፍልሰቱ በአገር ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እያስከተለ መሆኑ በጥናቱ የተገለፀ ሲሆን ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚደረገው ጉዞ በተለይ በደቡብ ክልል ባሉ አካባቢዎች በመንግስት ስራ ላይ ያሉ ሳይቀሩ በመፍለሳቸውና አብዛኞችም ለጉዞው ያኮበኮቡ በመሆናችው የተማረ የሰው ሀይል ላይ የሚያስከትለው መመናመን በአፅንኦት ሊታሰብበት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
ፍልሰቱ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች ከስደት ይልቅ በአገሩ ሰርቶ መኖር የሚመርጥ ግለሰብ ቢገኝ እንኳን ከህብረተሰቡ ያለበት ጫና ቀላል አለመሆኑን የጠቀሱት አጥኚዎቹ፤ ጎረምሳ ልጅ ያለ ስራ ተቀምጦ ከታየ “ከአንተ የደቡብ አፍሪካ ሬሳ ይሻላል፤ ቢያንስ ሞባይል ይዞ ይመጣል” መባሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ሰው ሞቶ አስከሬኑ ሲላክ ንብረቶቹ አብረው ስለሚላኩ ቢያንስ ሞባይል ከንብረቱ መሀል ስለማይጠፋ እንደሆነ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
በአማራ ክልል ሴቶች በብዛት ወደ አረብ አገሮች በሄዱባቸው አካባቢዎች ማህበራዊ ለውጦች እየታዩ እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን እናቶች በብዛት በመፍለሳቸው የተነሳ ትንንሽ ሴት ልጆች ላይ ከፍተኛ የስራ ጫና እየተፈጠረ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ልጆቹ በትምህርታቸው እየደከሙ እንደመጡ ታውቋል፡፡
ባሎች ደግሞ ከዚህ በፊት የማይሰሯቸውን የቤት ውስጥ ስራዎች መስራት እንደጀመሩ ጥናቱ ይጠቁማል - ለምሳሌ ወሎ ውስጥ እንደ ሮቢት ባሉ ሴቶች በብዛት ወደ አረብ አገሮች በሄዱባቸው አካባቢዎች፣ ወንዶች የቤት ውስጡን ስራ ሚስቶቻቸውን በመተካት እየሰሩ ይገኛሉ ተብሏል - እንጀራ በመጋገርና ወጥ በመስራት፡፡
በጥናቱ ላይ ከተጠቀሱት ሌሎች ለውጦች መካከልም ህብረተሰቡ ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ እየጨመረ መምጣቱ አንዱ ሲሆን የሴቶች ከቤተሰብ ቁጥጥር ውጪ መንቀሳቀስ፣ ሴቶች በተለይ አንደኛ ደረጃን ጨርሰው ትምህርታቸውን ማቋረጥ፣ ዕድሜያቸው 18 ያልሞላ ልጆች ፓስፖርት በማውጣት ፍልሰቱን መቀላቀላቸው እና በሚላከው ገንዘብ የተነሳ በቤተሰብና በትዳር ጓደኛ መሀል ግጭት መፈጠር እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች ለትዳር ሽምግልና ሲላክ “አረብ አገር ትልካታለህ ወይ” የሚል ጥያቄ መቅረብ መጀመሩ ይጠቀሳሉ፡፡
የጥናት ጽሁፎቹ ከቀረቡ በኋላ በተደረገው ውይይት፤ የሁለት ጎራ ሀሳቦች ከተሳታፊዎች የተሰነዘረ ሲሆን አንደኛው አገር ወስጥ ሰርቶ መለወጥ ይቻላል የሚል ሲሆን ሁለተኛው በአገር ውስጥ መለወጥ ከባድ ነው የሚሉ ናቸው፡፡ መንግስት ለወጣቶች ምቹ እድል መፍጠር አለበት የሚለው ጎልቶ የወጣ ሀሳብ ሲሆን በውይይቱ ላይ ልምዷን ያካፈለች ወጣት ስትናገር፤ “እኔ ውጤት አምጥቼ ዩኒቨርሲቲ ስገባ የጎረቤት ልጆች ውጤት ስላላመጡ ወደ አረብ አገር ሄዱ፤ እኔ ተማሪ ሆኜ እነሱ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለውጠዋል፤ እኔ ከተመረቅሁ በኋላ ስራ አላገኘሁም፤ የሚወጣው ማስታወቂያ በሙሉ ከአምስት አመት በላይ የስራ ልምድ ይጠይቃል፤ ሌላ ትምህርት እንዳልማር ወጪ መጋራት በሚለው አሰራር ክፍያ አላጠናቀቅሁም፤ ደቡብ አፍሪካ እህት አለችኝ፤ በየቀኑ እኔም የምወጣበትን መንገድ እንድታመቻችልኝ ነው የምጠይቃት” ብላለች፡፡ እንግዲህ በግልፅ እንደቀረበው ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም ትውልዱ ልቡ ለስደት አሰፍስፏል፡፡ አሳዛኙ ደግሞ ሃይ ባይ ተቆጭ እንኳን አለመኖሩ ነው፡፡ ጎበዝ! ትውልድ ተሰዶ ከማለቁ በፊት ብንወያይበትና መላ ብንዘይድ አይሻልም፡፡

Read 4717 times