Saturday, 13 July 2013 10:33

የሠበታ አካባቢ ገበሬዎች መሬታቸው ተወስዶ እንደተንገላቱ ገለፁ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)

በሰበታ አዋስ ወረዳ ቀበሌ 04 ነዋሪ የነበሩ ከ270 በላይ ገበሬዎች የእርሻ መሬታቸው ለልማት ተወስዶ ካሳ ባለማግኘታቸው ለአራት አመታት ያለስራና ገቢ እንደተንገላቱ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ ነባር የእርሻ ይዞታቸው ለሪል ስቴት፣ ለፋብሪካና ለሌሎች ልማቶች በመፈለጉ ወደ ሌላ ቦታ እንደተዛወሩ ገበሬዎቹ ገልፀው፤ ቦታው ካርታና ፕላን ስለሌለው ስጋት ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡ “ከነባር ይዞታችን አንነሳም ብለን ስንቃወም፤ “የልማት እንቅፋት የሚል ስያሜ ተሰጥቶን ነበር” የሚሉት ገበሬዎቹ፤ ካሳ ይሰጣችኋል ተብለው ከተነሱ በኋላ ላለፉት አራት አመታት ያለ ስራና ያለ ገቢ እንደተቸገሩ ተናግረዋል፡፡

“ጉዳያችንን ለሰበታ ከተማ ከንቲባ፣ መሬት አስተዳደርና ለጨፌ ኦሮሚያ በተደጋጋሚ ብናቀርብም ምላሽ አላገኘንም” ያሉት ገበሬዎቹ፤ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ግን ለካሳ ክፍያ የሚሆን በጀት የለኝም የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ገልፀዋል፡፡ “በወቅቱ የልማት እንቅፋት ተባልን፤ አሁን ደግሞ መጀመሪያውኑ ለምን እሺ ብላችሁ ለቀቃችሁ ይሉናል” ብለዋል አርሶአደሮቹ፡፡ “የ8ኛ እና የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች ትምህርታቸውን እያቋረጡ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማገዝ ወደ ጉልበት ስራ እየገቡ ነው” ያሉት ተወካዮቹ፤ “ስንነሳ በተጠናው መሠረት 16 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ የተመደበልን ቢሆንም ክፍያውን ለአመታት ባለማግኘታችን ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገናል” ብለዋል፡፡

ሌላው ቀርቶ የካሳ ክፍያቸው በ2006 ዓ.ም በጀት ውስጥ እንኳን ታሳቢ አለመደረጉን ገበሬዎች ጠቅሰው፤ አሁን ለተዛወሩበት ቦታም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲዘጋጅላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ ስላላገኙ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሀ/ማርያም ደሳለኝ አቤቱታ ለማቅረብ እንዳሰቡ ገበሬዎቹ ገልፀዋል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተባሉትን የሰበታ ከተማ ከንቲባና የሰበታ ከተማ መሬት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡

Read 17469 times