Saturday, 13 July 2013 10:35

450 ሚ.ብር ሙስና ተጠርጣሪዎች ፍ/ቤት ቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

በኤሌክትሪክ እቃዎች ግዢ ላይ ሙስና በመፈፀም መንግስትን (ከ450.ሚ ብር) በላይ አሳጥተውታል ተብለው ሰሞኑን የታሰሩ ዘጠኝ የኤሌትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን የስራ ሃላፊዎች ላይ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተጨማሪ ምርመራ እንዲያካሂድ ተፈቀደለት፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በሁለት የምርመራ መዝገብ ተካተው የቀረቡ ሲሆን፤ በአንደኛው መዝገብ የኮርፖሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ብርሃኔ አበበ እና የቴክኒክ ክፍል ቡድን መሪ አቶ መኮንን ብርሃኔ ተሰማ ተመዝግበዋል፡፡ በሁለኛው መዝገብ ስር የተካተቱት 7 ግለሰቦች በኮርፖሬሽኑ የሃገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ፕሮግራም ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፣ የኢንጂነሪንግ ክፍል ሃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቱሳላ፣ የሠፕላይቼይን ሃላፊ አቶ ዳንኤል ገ/ስላሴ፣ የኢንጅሪንግ ፕሮሰሲንግ የስራ ሂደት ተወካይ አቶ ሠመረ ሃሳቤ እንዲሁም የጨረታ ኮሚቴ አባላት አቶ ፋሪስ አደም፣ አቶ ብሩክ ተገኘ እና አቶ ጌታቸው አዳነ የተሰኙ ግለሰቦች ናቸው፡፡

የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን፤ ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ለፍርድ ቤቱ እንዳቀረበው፤ በአንደኛው መዝገብ የተካተቱት አቶ መስፍን ብርሃኔ፣ የስልጣን ውክልና ሳይኖራቸው እና የኮርፖሬሽኑን ይሁንታ ሳያገኙ ከሪዘርቭ ባንክ ኦፍ እንዲያ እ.ኤ.አ ሚያዚያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ፤ የግዢ ውሉን ተቀባይነት ማረጋገጫ በመስጠታቸው እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ 3520 ትራንስፎርመሮች ለሀገሪቱ የሃይል አቅርቦት መገዛት አለበት ብሎ ቢያቅድም አሮጌና ያገለገሉ ትራንስፎርመሮች ባልተገባ የግዢ አካሄድ እንዲገዙ ማድረጋቸው የሚለው ነው፡፡ በአቶ መኮንን ብርሃኔ ላይ የቀረበው የወንጀል ጭብጥ ደግሞ የተገዙትን ትራንስፎርመሮች መመርመር ዋነኛ ተግባራቸው ሆኖ ሳለ፣ በአቶ መስፍን ብርሃኔ የተዘጋጀውን ግዢና ውል እንደወረደ በመቀበል ኮርፖሬሽኑ ወይም መንግስት ከ17 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲያጣ አድርገዋል የሚል ነው፡፡ በሁለኛው መዝገብ የካተቱት አቶ ሽፈራው ተሊላ እንዲሁ የስልጣን ውክልና ሳይኖራቸው እና የኮርፖሬሽኑን ፍቃድ ሳያገኙ በሪዘርቭ ባንክ ኦፍ ኢንዲያ እሣቸውም የውሉን ማረጋገጫ ደብዳቤ ጽፈዋል የሚል የወንጀል ጭብጥ ቀርቦባቸዋል፡፡

በዚህ መዝገብ የተካተቱት አቶ ሚሊዮን ማቱሳላ ደግሞ ደረጃቸውን ያልጠበቁ አሮጌ ትራንስፎርመሮች አዳዲስ ናቸው ተብለው ሲቀርቡላቸው ውድቅ ማድረግ ሲገባቸው ስራ ላይ እንዲውሉ አድርገዋል፡፡ ከሳቸው በተጨማሪም አቶ ዳንኤል ገ/ስላሴም በዚህ ድርጊት ተሣታፊ ናቸው ተብሏል፡፡ አቶ ሠመረ ሃሣቤም የቀረበላቸው ሰነድ ግድፈት አለበት ብለው ውድቅ መሆን አለበት ማለት ሲገባቸው ለቀጣዩ ክፍል ትክክል ነው ብለው አስተላልፈዋል የሚል የወንጀል ጭብጥ ቀርቦባቸዋል፡፡ የጨረታ ኮሚቴ አባላት የሆኑት አቶ ፋሪስ አደም፣ ብሩክ ተገኝ እና ጌታቸው አዳነ ደግሞ ኮንትራክተሩ አቀርባለሁ ካለው ውጪ ሲያቀርብ ትክክል ነው ብለው ተቀብለዋል የሚል ነው፡፡ ግለሰቦቹ ኮርፖሬሽኑ ሊገዛ ያሰበው የትራንስፎርመር አይነት ሄርማቲባል ሲልድ የሚባል ቢሆንም ገዝተው ያቀረቡት “ጉድ ላክ ስቲል ትዩብስ” ከተባለ ኩባንያ ትራንስፎርመር ዋዝ ኮንሰርቫቲቭ ዩኒት የተባለውን እንደሆነ በማመልከቻው ላይ ተጠቁሟል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ግዢውን ሰነዱ ላይ ከተቀመጠው መስፈርት ውጪ ነው ብለው በቴክኒክ ግምገማ ውድቅ ማድረግ ሲገባቸው የፋይናንስ ግምገማው ያለአግባብ እንዲያልፍ በማድረግ፣ ኮርፖሬሽኑ 1950 አዳዲስ ትራስፎርመሮችን ሲጠባበቅ አሮጌና ያገለገሉትን አቅርበው ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የሚል ነው፡፡ በሁለቱ መዝገቦች የተካተቱት ተጠርጣሪዎችም በአጠቃላይ ኮርፖሬሽኑን ወይም መንግስትን ከ24 ሚሊዮን ዶላር በላይ አሳጥተውታል ተብሏል፡፡ የምርመራ ቡድኑ ባለፈው ማክሰኞ በቁጥጥር ስር በዋሉት ዘጠኙም ግለቦች ላይ ማስረጃዎችን እያሰባሰበ መሆኑን፣ እስካሁንም የኦዲት ሪፖርትና የትራንስፎርመር ግዢ የተፈፀመባቸው ሰነዶች መሰብሰባቸውን፣ የምስክሮችን ቃል መቀበሉን አስረድቶ፤ በቀጣይም ቀሪ ማስረጃዎችን መሰብሰብ፣ በእንግሊዝኛ የተፃፉ ሰነዶችን ወደ አማርኛ መተርጐም፣ የተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው አመልክቷል፡፡

ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው፤ የኦዲት ሪፖርቱ ከተሰበሰበ ከአንድ አመት በላይ ሆኖታል፤ ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ ማሰባሰብ አስፈላጊ አይደለም፤ ከ6 አመት በፊት የተካሄደ ጨረታ ስለሆነ ሁሉም ማስረጃ በእጃቸው አለ፣ የቤተሰብ ሃላፊነት አለብን የሚሉ ምክንያቶችን በማቅረብ የዋስ መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ ችሎቱም ቀሪ የምርመራ ስራዎች እንዳሉ በመገንዘብ፣ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ባለመቀበል፣ የመርመሪ ቡድኑ የጠየቀውን የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ፣ ለሃምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

Read 20968 times