Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 19 November 2011 14:09

ጦጢት ራሷ ሳትገረዝ የሌላውን ዐይን ትይዛለች - (የወላይታ ተረት)

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አንበሳ፣ አንድ በሬ ሰፊ መስክ ላይ ሣር ሲግጥ ያያል፡፡ በጣም የሰባ በሬ በመሆኑ ጭኑን፣ ሽንጡን፣ ሻኛውን እያየ ምራቁን ይውጥ ጀመር፡፡ ከዚያም፤
“ይሄንን በሬ ከፊሉን ለቁርሴ፣ ከፊሉን ለምሣዬ፣ የቀረውን ደግሞ ለእራቴ ሳደርግ አቤት ጥጋቤ አቤት ደስታዬ! አቤት እርካታዬ!” እያለ ክፉኛ በመጐምዠት ሲቋምጥ ቆየ፡፡
አንድ ነገር ግን ደፍሮ በሬውን እንዳይነካው አስፈራው፡፡ በጉልበት ላርገው ካለ አይችለውም፡፡

ምክንያቱም እጅግ በጣም ሹል የሆኑት የበሬው ቀንዶች ያስፈራሉ፡፡ ስለዚህ፤ 
“ይሄ በሬ በእነዚህ ሹል ሹል የሆኑ ቀንዶቹ የወጋኝ እንደሆነ አልተርፍም፡፡ ስለዚህ በሆነ ጥበብ ቀንዶቹ የሚቆረጡበትን መላ መፍጠር አለብኝ” አለ፡፡ ብዙ ካወጣ ካወረደ በኋላ ወደ በሬው ተጠግቶ :-
“አያ በሬ ሆይ እንደምን ከርመሃል” አለው፡፡
“ደህና ነኝ አያ አንበሶ፡፡ ዛሬ ምን እግር ጣለህና ወደ እኛ ሠፈር መጣህ” ሲል በሬው ጠየቀው፡፡
አያ አንበሶም፤
“ከደን ወጥቼ እዚህ አንተ የምትግጥበት መስክ ድረስ የመጣሁት አንድ ትልቅ ጉዳይ ላዋይህ ነው፡፡ ከሩቅ ሆኜ ስመለከትህ በአካባቢህ የሚያማክርህ ወዳጅ አጥተህ ነው እንጂ እስከዛሬ ይህን ችግርህን አውቀህ ዝም አትልም ብዬ አሰብኩኝ”
አያ በሬም፤
“ስላሰብክልኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ይሄ አለብህ ያልከኝ ችግር ምን ይሆን” ሲል ጠየቀው፡፡
አያ አንበሶም በሚያማልል ቅላፄ ድምፁን አሳምሮ፤
“ያንተን የአካል ቅርጽ እንደኔ በጥሞና ላስተዋለ እዚህ ቦታ ይሄ ጐደለህ ለማለት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ እንዴት ያለ ጭንቅላት እንዳለህ ለማመን አይቻልም! የፈረጠመው ታፋህና ጭንህ ምን ቢበላ ነው እንዲህ ያማረው ያሰኛል፡፡ የሻኛህ ነገርማ አይነሳ - ወደግራ ወደቀኝ ሞንደል ሞንደል ሲል ላየ “ከሰቡ አይቀር እንደ በሬ ነው” እያለ እንስሳው ሁሉ እንዲቀና ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን ይሄን ሁሉ ውበትህን ዋጋ እንዳይኖረው የሚያደርግ አንድ እንከን ብቻ ይታየኛል” አለና ዝም አለ፡፡
አያ በሬ ስለውበትና ጥንካሬው የተሰጠው አስተያየት በጣም አማለለው፡፡ አለብህ የተባለው እንከን ምን እንደሆነም ለማወቅ ጓጓና፤
“ምን እንከን ነው ያየህብኝ አያ አንበሶ” ሲል ጠየቀ፡፡
አያ አንበሶም፤
“እነዚህ ሁለት ቀንዶችህ በጭራሽ ከሚያምረው አካልህ ጋር አይሄዱም፡፡ ውበትህን ቅርፀ ቢስ አድርገውታል፡፡ እነሱን ቆርጠህ ብትጥል ፍፁም የሆነ ቅርጽና የተመጣጠነ አካል ይኖርሃል” አለው፡፡
አያ በሬ ውበቱንና የአካል ቅርፁን ለማስተካከል ወሰነ፡፡ ሁለቱን ቀንዶቹን ቆርጦ ጣለ፡፡ ዋናውን የመከላከያና የማጥቂያ መሣሪያው የሆነውን ቀንዱን አጣ፡፡
አንበሳም በቀላሉ በክርኑ ደቁሶ፤ እንደተመኘው የቁርስም፤ የምሳም፣ የራትም ፌሽታ አደረገው፡፡

* * *
በማናቸውም የህይወት መንገድ ብልህነትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ አቅምን በትክክል መለካት የብልህነት ትልቁ አንጓ ነው፡፡ መጐምዠት ብቻውን የዕለት እንጀራ እንደማያመጣ ሁሉ፤ መመኘት ብቻውንም ፍሬ አያፈራም፡፡
በፖለቲካው ዓለም መበላላት፣ መጠላለፍና ስም ማውጣት ባህል ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ምናልባት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ፍሬ የማያፈሩት ለዚህ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ አዛውንት ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ፤
“ወዴት ነው የሚሄዱት” ተብለው ቢጠየቁ፤ “ለበሽታዬ ስም ላስወጣ” ብለው መለሱ አሉ፡፡ የበሽታችን ስሙ ጠፋን እንጂ መታመማችንንማ እናውቃለን፤ ነው ጨዋታው፡፡ ልዩ ልዩ ስም ማውጣት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የተለመደ ነው፡፡ እርግጥ በሩሲያም፣ በጀርመንም፣ በፈረንሳይም አብዮት ታሪክ ይሄው ተከስቷል፡፡ (የእኛ ቅኔው ሳይበዛ አይቀርም፡፡) ለምሳሌ የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት “የታህሳስ ግርግር” ነው ስሙ፡፡ “ቀኝ መንገደኞች”፣ “አምስተኛ ረድፈኞች”፣ “ግልገል ፋሽስቶች”፣ “በጠብታ ውሃ ውስጥ ጉማሬ አየን የሚሉ”፣ “የእንጀራ ጠርዝ እጃቸውን የሚቆርጣቸው ንዑስ ከበርቴዎች” “በሠፊው ህዝብ የጥቅም ገመድ ሲላሲሎ የሚጫወቱ ፀረ - ህዝቦች” ወዘተ የስም፣ የቅጽል መዓት ይዥጐደጐዳል፡፡
ይሄ ባህል ሁሌም አለ፡፡
ከስም ምን አተረፍን ተብሎ ሲጠየቅ እልቂት፡፡ ሰላም ማጣት፡፡ ሀገርን ማቆርቆዝ፡፡ ከስም ማውጣት ይሰውራን፡፡ ሀሳብን ከማንሸራሸር ይልቅ እገሌ እንዲህ ነው ከማለት ይሰውረን፡፡ በሽተኛውን ለማዳን በሽታው ላይ እናተኩር፡፡
አብርሃም ሊንከን እንዲህ አለ አሉ :-
“የምታቀርብልኝ ሻይ ከሆነ ቡና አድርግልኝ፡፡ የምታቀርብልኝ ቡና ከሆነ ሻይ አድርግልኝ፡፡ የሚሉ ሰዎች ዓላማቸው መጠጣት ሳይሆን መቃወም ነው”
ከዚህም ይሰውረን፡፡ የምትናገረው ሁሉ አይጥመኝም በመባባል ልናተርፍ የምንችለው ጥላቻን ብቻ መሆኑን አንርሳ፡፡
አንድ ያልታወቀ ደራሲ እንዳለው በህይወት ውስጥ ሁለቱ አዳጋች ነገሮች ውድቀትንና ስኬትን ማመን ናቸው፡፡
ውድቀታችንን አምነን ካላረምን፣ ሌላ ውድቀት ይጠብቀናል፡፡ ስኬታችንንም አምነን መጪውን ካላዘጋጀን ወደ ውድቀት እንጓዛለን፡፡ ዋናው ቁምነገር እንግዲህ በመመሪያና በመግለጫ ሳንሸፋፈን በግልጽ ራሳችንን መመርመሩ ላይ ነው ማለት ነው፡፡ ሳናድግ አደግን አንበል፡፡ እየሞሰንን ንፁህ ነን እንበል፡፡ ትክክለኛ ፍርድ ሳንሰጥ ፍትሕ ርትዕ አለ እንበል፡፡ ሠራተኞቻችን ታማኝ ስለሆኑ ብቻ ታታሪዎች ናቸው አንበል እኛ ስለፈለግነው ብቻ የምናወጣው ደንብ በግድ ለህዝብ ጠቃሚ ነው አንበል፡፡ ከሁሉም በላይ አንድ ታዋቂ ደራሲ ያለውን ልብ እንበል
“ቤት የምንሠራበት፣ ሪል ስቴት የምንለው ጠንካራ መሬት፤ በዓለም ላይ ያሉት ወንጀሎች ሁሉ የሚፈፀሙበት ጠንካራ መሠረት ነው”
ይህንንም አላየንም፣ አልሰማንም አንበል፡፡ በራሳችን ላይ ያለውን ጉድፍ ማየት ሳንችል በሌሎች ላይ ጥፋት የምንደርት ከሆነ ፍፃሜያችን አያምርም፡፡
ወደ ራስ ማየት፣ ወደ ውስጥ ማየት እጅግ ጠቃሚው መንገድ ነው፡፡ “ጦጢት ራሷ ሳትገረዝ የሌላውን ዓይን ትይዛለች” የሚለው የወላይትኛ ተረት የሚያስገነዝበን ይሄንኑ ነው፡፡

 

Read 5880 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 14:12