Saturday, 13 July 2013 11:29

በፊልሞች እየጠፉ ያሉትን ህፃናት ማን ይታደጋቸው?

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(14 votes)

በክረምት ወራት ህፃናት በቀን ከ4-6 ሰዓት ፊልም በማየት ያሳልፋሉ

                     ስፍራው እዚሁ አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለከተማ ውስጥ ነው፡፡ ድርጊቱ ከተፈፀመ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአንድ የውጭ ድርጅት ውስጥ በኃላፊነት ደረጃ በጥሩ ደመወዝ ተቀጥሮ የሚሠራው የቤቱ አባወራ ከሆስተስ ባለቤቱ ጋር ትዳር ከመሰረቱ 15ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡ አሁን የሚኖሩበትን ቤት ሰርተው ከጨረሱ ወደ አራት ዓመት ግድም ይሆናል፡፡ በ15 ዓመት የትዳር ዘመናቸው የአስራ አራትና የአስራ ሁለት ዓመት ወንድና ሴት ልጆችን አፍርተዋል። ልጆቻቸው በጥሩ እንክብካቤ እንዲያድጉና ጥሩ ትምህርት ቤት እንዲማሩ የተቻላቸውን ያህል ጥረት አድርገዋል፡፡ ባልና ሚስቱ ለሥራ ወደተለያዩ አገራት የሚጓዙበት ጊዜ በርከት ስለሚል፣ ልጆች ናኒ ከሚሏት የቤት ሠራተኛቸው ጋር አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ ልጆቹን ከቤት ወደ ትምህርት ቤት፣ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት የሚያመላልስ ሰርቪስ መኪናም ተቀጥሮላቸዋል፡፡ አባትና እናት አገር ውስጥ በሚሆኑባቸው ጊዜያት በተቻላቸው መጠን ከልጆቻቸው ጋር ለማሳለፍ ይሞክራሉ፡፡ ልጆቻቸው አንዳችም ነገር ሳይጓደልባቸው የፈለጉት ሁሉ ተሟልቶላቸው እንዲያድጉ የማያደርጉት ጥረት የለም።

ወቅቱ እንዲህ እንደ አሁኑ ት/ቤቶች አመታዊ የትምህርት ጊዜያቸውን አጠናቀው የተዘጉበትና ተማሪዎች ረጅሙን የሁለት ወራት የእረፍት ጊዜ የተያያዙበት ወቅት ነበር፡፡ እንደተለመደው የእነዚህ ታዳጊዎች ወላጆች በአገር ውስጥ የሉም፡፡ የቤት ሠራተኛዋ ናኒም ልጆቹ የሚበሉ የሚጠጡትን በአግባቡ አዘጋጅታ ከማቅረብ፣ ንፁህ መልበሳቸውን፣ ምቾታቸው መጠበቁንና እቤት ውስጥ በቲቪ ስክሪን ላይ አፍጥጠው መዋላቸውን ከማየት ውጪ፣ ልጆቹ እያከናወኑት ስላለው ነገር የምታውቀው ጉዳይ የለም። የተባረኩ ልጆች ናቸው - ለእሷ፡፡ ከቤት አይወጡ፣ አይረብሹ፣ ሥራዋን አያስተጓጉሉ… የተባረኩ ልጆች! እሷን ከተጨማሪ ስራ ስለአዳኗትና ጊዜዋን ስለአልተሻሙባት ፍፁም ደስተኛ ነች፡፡ ይህ ሁኔታ ለቀናት በዚሁ መልኩ ቀጠለ፡፡ ታዳጊዎቹ በዲኤስቲቪ የሚሰራጨውን ፊልም ቻናል እየቀያየሩ ማየቱ አልሰለቻቸውም። በሠፈራቸው ከሚገኘው የፊልም አከራይ ዘንድ እየተከራዩ የሚያመጡትን ፊልም ወንድምና እህት ከምቹው ሶፋ ላይ ጋደም ብለው ማየቱን ለምደውታል፡፡ ፊልሙ ደግሞ ለእነሱ ዕድሜና ደረጃ ሊመጥን የማይቻል የወሲብ ፊልም ነው፡፡

ታዳጊዎቹ በፊልሙ በሚያዩት ትዕይንት እጅግ ተመስጠዋል፡፡ ቀስ እያሉ መጠጋጋት፣ቀስ እያሉ መሳሳብ፣ቀስ እያሉ መደባበስና መተቃቀፍ ጀመሩ፡፡ በፊልሙ ውስጥ የሚመለከቷቸው ሰዎች የሚተውኑትን በተግባር ለመፈፀም እጅግ ጓጉ፡፡ በመሀላቸው ያለው ትልቅ ጉዳይ ለአፍታም አልታሰባቸው፡፡ እየፈፀሙ ያሉት ተግባር አንዳች ስህተት ያለበትም አልመሰላቸው፡፡ የአስራ አራት ዓመቱ ታዳጊ፣ የእህቱን ያጎጠጎጡ ጡቶች በፊልም ትዕይንቱ ላይ እንደተመለከተው እያደረገ እህቱን ይበልጥ ተጠጋት፡፡ ትንፋሹ ደከመ። ታዳጊ ህፃናቱ በቲቪ ስክሪን ውስጥ የሚያዩዋቸውን የወሲብ ተዋንያን ተግባር እዚያው ጋደም ባሉበት ሶፋ ላይ ተወኑት፡፡ የልጅቱ ጩኸት ካለችበት ወጥቤት ድረስ ዘልቆ የተሰማት የቤት ሰራተኛዋ ናኒ፤ በድንጋጤ ወደ ሳሎን ሮጠች፡፡ ሳሎን ደርሳ የተመለከተችው ነገር መሀል አናቷን ነደላት፡፡ እዛው በቆመችበት ደርቃ ቀረች፡፡ የአስራ ሁለት ዓመቷ ታዳጊ በደም ተነክራ ሶፋው ላይ በጀርባዋ ተንጋላለች፡፡

ወንድሟ በሁኔታው እጅግ ተደናግጧል፡፡ እርቃን ገላውን የሚሸፍንበት ጨርቅ ፍለጋ ይውተረተራል፡፡ ሰራተኛዋ ኡኡታዋን አቀለጠችው፡፡ የድርጊቱን ምንነትና የተፈጠረውን ጉዳይ ለማወቅ ጥቂት ደቂቃዎች አስፈልገዋት ነበር፡፡ በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ የሚታየው የወሲብ ትዕይንት ታዳጊዎቹ ምን እንደፈፀሙ አረዳት፡፡ እንደምንም ራስዋን አረጋግታ ለህፃናቱ አክስት ደውላ ሁኔታውን አሳወቀች፡፡ የእነዚህ ታዳጊ ወላጆች ከውጭ አገር ቆይታቸው ሲመለሱ የጠበቃቸው እጅግ የሚሰቀጥጥ እና “የወላድ ጆሮ አይስማው” የሚያሰኝ ዜና ነበር። ለችግሩ መከሰትና ለጥፋቱ መፈፀም ተጠያቂ ያደረጓትን የቤት ሰራተኛ ከቤታቸው አባረሯት። ጉዳዩ በሚስጥር እንዲያዝ ለማድረግም ወሰኑ። ከቤት ያባረሯት ሰራተኛቸው ጉዳዩን አደባባይ ልታወጣው እንደምትችል አልጠረጠሩም፡፡

የሁለቱ ታዳጊዎች ምስጢራዊ ድርጊት ከአካባቢያቸው አልፎ ት/ቤታቸው ለመድረስ ግን ጥቂት ቀናት ብቻ ነበር የፈጀበት፡፡ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውና የአካባቢው ነዋሪዎች መጠቋቆሚያ የሆኑት ህፃናቱ ለከፍተኛ የስነልቦና ችግር በመዳረጋቸው ለጊዜውም ቢሆን ትምህርታቸውንም እንዲያቋርጡ አስገደደቸው፡፡ ይህ ከአመታት በፊት በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የተከሰተ ጉዳይ በወቅቱ በርካቶችን አስደንግጦ ነበር። ድርጊቱን ፈፀሙ የተባሉትን ታዳጊዎች “አይናችሁ ላፈር” ለማለት ያልተጣደፈ አልነበረም፡፡ ወላጆቻቸው ሳይቀሩ ልጆቹ በፈፀሙት ስህተት ውስጥ የእነርሱ ቸልተኝነት አስተዋፅኦ እንደበረው ማሰብ እንኳን አልፈለጉም፡፡ ህፃናቱ ዕድሜያቸውንና ዕውቀታቸውን የሚመጥኑ ፊልሞችን ብቻ እንዲመለከቱ አልተቆጣጠሯቸውም፡፡ በዚህ የግሎባይዜሽን ዘመን ከባህልና ከዕምነታችን ውጪ የሆኑና “ውጉዝ” ያልናቸው የወሲብ ፊልሞችን ቤታችን ድረስ የሚያመጡልን የቴሌቪዥን ቻናሎች በርክተዋል፡፡ ፊልሞቹ በዲኤስቲቪና በዲሽ አማካኝነት ቤታችን ይመጣሉ፡፡ ልጆቻችንም እነዚሁኑ ቻናሎች ያለአንዳች ከልካይና እንደልባቸው ከመመልከት የሚያግዳቸው ምንም ነገር የለም፡፡

ህፃናት ደግሞ ከማንኛውም አዋቂ በተሻለ ፍጥነት ነገሮችን የመቀበልና ወደ ተግባር የመለወጥ ተፈጥሮአዊ ባህሪይ አላቸው፡፡ ሕፃናቱ ብዙ ጊዜያቸውን በቴሌቪዥን ላይ አፍጥጠው ሲያጠፉ በባህሪያቸውና በአመለካከታቸው ላይ የሚደርሰው ስነልቦናዊ ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ እንደዚህ ያሉ ጉዳዮችን የሚከታተልና የሚያጠና ተቋም በአገራችን እምብዛም ባይኖርም፣ ህፃናቱ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለዚህ ችግር ሰለባ እየሆኑ መምጣታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ ፊልሞች የህፃናትን ባህሪይ በመቀየር ረገድ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በቴሌቪዥንና በፊልም ስክሪን ላይ የሚቀርቡ ሀይል የተቀላቀለባቸው አክሽን ፊልሞች፣ግጭት የበዛባቸው ፊልሞችና የወሲብ ፊልሞችን የሚመለከቱ ህፃናት በባህሪያቸው አስቸጋሪዎችና የወሲብ ሱሰኞች ይሆናሉ፡፡ ጥናቱ እንደሚያመለክተው፤ በቀን ውስጥ ከ4-6 ሰዓት ጊዜያቸውን ቴሌቪዥን ላይ አፍጠው የሚውሉ ህፃናት ለተለያዩ ወንጀሎች፣ ያለዕድሜ ለሚፈፀሙ ወሲቦችና፣ራሳቸውን ለማጥፋት ይጋለጣሉ፡፡

ግጭትና ድብድብ የበዛባቸውን የመገዳደል ትዕይንት ያለባቸውን ፊልሞች ለብዙ ጊዜ የሚመለከቱ ህፃናት፤ በባህርያቸው አስቸጋሪዎች፣ በፊልሙ የተመለከቱትን ተግባራት በገሃድ ለመፈፀም የሚፈልጉና የሚሞክሩ ይሆናሉ፡፡ ህፃናቱ እነዚህን ትዕይንቶች በብዛት ከተመለከቱ፣ ባህሪይውን በቀላሉ በመላመድ በፊልሙ ውስጥ ያዩትን ገፀባህርይ አይነት ሰብዕና ለመላበስ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ የወሲብ ትዕይንቶችን በግልጽ የሚያሳዩና ሥርዓት አልባ የወሲብ ተግባራት የሚስተዋልባቸው ፊልሞችን የሚመለከቱ ህፃናት፤ ያለዕድሜያቸው የወሲብ ሱስ ተጠቂ ከመሆናቸውም በላይ በፊልሙ ውስጥ እንደሚመለከቱት አይነት ወሲብ ለመፈፀም ከፍተኛ ጉጉት ያድርባቸዋል፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክተው የሥነልቦና ባለሙያው ዶ/ር የኔ ሰው ብርሃኑ ሲናገሩ፤ በየቤታችን የተቀመጡት ቴሌቭዥኖች በልጆቻችን ባህርይ ላይ የሚያስከትሉት ተጽዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ለህፃናት ባህርይ መቀያየር አራት መሠረታዊ ምክንያቶች አሉ።

እነዚህም ወላጆች (ቤተሰብ)፣ ፊልሞችና ጌሞች፣ ባህልና ህብረተሰብ እንዲሁም ት/ቤቶች ናቸው ይላሉ - ባለሙያው፡፡ ቤተሰብ (ወላጆች) የልጆቻቸውን ባህሪይ በማረቅ፣ከባህል ፣ከስርዓትና ከመስመር ያልወጡ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችሉ የሚናገሩት ዶክተሩ፤ ይህ ትልቅና መሰረታዊ ጉዳይ እየተረሳ ወላጆች ለልጆቻቸው መስጠት የሚገባቸውን ነገር ባለመስጠት የልጆቻቸው ባህሪይ የተበላሸ እንዲሆን ያደርጋሉ ይላሉ። ህብረተሰቡ ለህፃናቱ ማሳየት የሚገባውን ነገር ለማሳየት ባለመቻሉ፣ ህፃናቱ ትክክል ያልሆነውን ጉዳይ ትክክል ነው ብለው ለማመንና ድርጊቱን ለመፈፀም ይገደዳሉ፡፡ ት/ቤቶች ከተለያዩ አካባቢዎች፣ ቤተሰብና ባህል የሚውጣጡትን ህፃናት በአንድ ቦታ በማሰባሰብ የሚያገናኝ እንደመሆኑ መጠን፣ ተማሪዎች እርስበርስ በሚያደርጉት ግንኙነትና አብሮ በመቆየት የባህሪይ መወራረስ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ህፃናቱ እያዳበሩ የሚያድጉት ባሕሪይ ደግሞ በሚያዩት፣ በሚሰሩትና በአቅራቢያቸው በሚያገኙት ጉዳይ ላይ የተወሰነ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ህፃናቱን ለመታደግና ብልሹ ባህሪያትን ይዘው እንዳያድጉ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ የየራሱን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል፡፡

በፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል የወጣቶች ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ሲስተር ወርቅነሽ ኬሬታ በበኩላቸው፤ ለህፃናቱ ባህሪይ መቀየር በየቤታችን በሚገኙት ቴሌቪዥኖች የሚተላለፉ ፊልሞች ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ጠቁመው፣ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው ከቤት ሳይወጡ መዋላቸውንና ከሌሎች አልባሌ ቦታዎችና ድርጊቶች መታቀባቸውን ብቻ በማየት፣ ህፃናቱ የፈለጉትን ጊዜ ያህል የፈለጉትን አይነት ፊልም እንዲያዩ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ስለሚያዩት ፊልም ምንነት፣ ልጆቻቸው ቴሌቪዥን ስር ስለሚያጠፉት ጊዜ ፈፅሞ አይጨነቁም፡፡ ልጆቹ በሌሎች ቤተሰባዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው እንኳን ይዘነጉታል፡፡ ይህ ጉዳይ በአደጉ አገራት በአንድ ወቅት እጅግ በጣም ከባድ ችግር ነበረ፡፡ አገራቱ ጉዳዩ በልጆቻቸው ላይ ያስከተለው ችግር ምን እንደሆነ የተገነዘቡት ዘግይተው ነው፡፡ ልጆቻቸው የእነሱ አልሆኑም፤ ሙሉ በሙሉ ፊልሙ ወስዷቸዋል፡፡

ጉዳዩ ያስከተለውን አገራዊ ቀውስ በመገንዘባቸው ምክንያትም በአሁኑ ወቅት እያስቀሩት ነው፡፡ ልጆቻቸው እንዲመለከቱ የሚፈቅዱላቸውን ቻናል ብቻ እንዲያዩ በማድረግና የህፃናቱን የቴሌቪዥን መመልከቻ ሰዓት በመወሰን ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህ ነገር ግን በእኛ አገር ተስፋፍቶ ህፃናት ረዥም ጊዜያቸውን በቲቪ ላይ አፍጥጠው እንዲውሉ እያደረጋቸው ነው፡፡ ልጆቹ በቤት ውስጥ ማከናወን የሚገባቸውን ነገር እንዳያከናውኑ፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀራረብና መጫወት እንዳይችሉ ፊልሙ አስሮ ቁጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በቤተሰብ ውስጥ መዳበር የሚገባው የመናገር፣ የመግባባትና የመከባበር ልምዶች እንዳይዳብሩ ያደርጋል ብለዋል። የወሲብ ፊልሞች በህፃናቱ ህይወትና በባህሪያቸው ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አስመልክተው ሲናገሩም፤ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከሚፈፀሙ መደፈሮች ውስጥ በቁጥር በርከት የሚሉት በቅርብ ቤተሰብ ማለትም በአባት፣ወንድምና አጎት የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ ለዚህ ጉዳይ መባባስ በየቤቱ ያለገደብ እየተከፈቱ የሚታዩት የወሲብ ፊልሞች አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ይላሉ፡፡

በክረምት ወራት ልጆች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በቤት ውስጥ በመሆኑ በርካታ ፊልሞችን ይመለከታሉ፤ ፊልሞቹ ደግሞ ለአዋቂ የተሰሩ ናቸው። ልጆቹ የወደዱትን ፊልም ተከራይተው እንዲመጡ ቤተሰብ ገንዘብ ይሰጣል። ቤተሰብ ልጆቹን ከተለያዩ የውጪ ነገሮች ጠብቆ ቤት ውስጥ ማቆየቱን ብቻ ነው የሚያየው፤ ነገር ግን ልጆቹ እጅግ የከፋና አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ይህን ጉዳይ ቤተሰብ አትኩሮ ሊያስብበት የሚገባና ትልቅ ችግር የሚያመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ልጆች ያለ ዕድሜያቸው ወይንም ያለጊዜያቸው የወሲብ ፊልሞችን በነጻነት እያዩ ነው፡፡ ይህንን ፊልም ባዩ ቁጥር ድርጊቱን መፈፀም ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ልጆቹን ለወሲብ ሱሰኝነት እያጋለጠና ልጆቹን ከማይወጡበት ገደል ውስጥ እየከተታቸው ነው። ስለዚህም ቤተሰብ ልጆቹ የሚመለከቱትን ፊልም ማወቅ፣ መምረጥና አንዳንዴም አብሮ መመልከት አለበት ብለዋል፡፡በዚህ የክረምት ወቅት ቤተሰብ የልጆቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መከታተልና ማወቅ ይገባዋል፤ ህፃናት ነገ የወንጀል፣ የሃሺሽ እና የሱስ ተጠቂ እንዳይሆኑ ከወዲሁ ጥበቃና ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል ሲሉ ባለሙያዎቹ ያሳስባሉ፡፡

Read 20313 times