Saturday, 13 July 2013 11:39

የይስማዕከ በአስማት የተሞላው “ክቡር ድንጋይ”

Written by  ተስፋ በላይነህ
Rate this item
(30 votes)

                                 ብላቴናው ቀላል አይደለም፡፡ ሰባት ሥራዎቹን በማይታመነው የእድሜው ቁጥር ጉድ አስብሏል፡፡ ሆኖም ግን ዘመኑ ትውልድን በለጋነት እየቀሰፈ፤የሰብዓዊነትን ሕልውና እያኮላሸ፤የሰውነትን ድርሻ ጥልቅ ሀይል እየቀበረ እያሽካካ ነው እንጂ --- ክርስቶስ በ12 ዓመቱ ስንት የአይሁድ ሊቆችን አስደምሟል? በሀገራችን የነገሱት ነገስታት በሥንት አመታቸው ታሪክ መዝገብ ውስጥ ተከትበዋል? ልጅ ተፈሪ በ13 ዓመቱ ከአባቱ ባገኘው ሥልጣን ወደ ዘውድነት የሚያመራውን ካባ ተከናንቧል፡፡ ነጋድረስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ በምኒልክ ዘመን፣ ለገሰ ዜናዊስ --- ለ“ወገኑ”አርነት ሲል በ19 ዓመቱ አልተሽቀዳደም? ኧረ ስንቱ…! ነገር ግን በአንድ አገር ውስጥ ትኩስ “ወጣት” እያለን ሲኮላሽ ማየት ውርደት ነው፡፡ይህ ብላቴና ከተኮላሸ ትውልድ ውስጥ ገንኖ ቢወጣ ያስመሰግነዋል፡፡ መግነኑ ግን በንኖ እንዳይቀስፈው ወዮለት! የማወራው ስለደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ሰሞኑን ለንባብ ስላበቃው “ክቡር ድንጋይ” የተሰኘ ረዥም ልብወለዱ፡፡ “ክቡር ድንጋይ”ን እንዳነበብኩት በአስማት ቃላት፣ በጥቁር ውሻ እና በድንጋይ የተከበበ ሽፋን የደራሲውን ስም ይዞ ይታያል፡፡

/በአንድ የሆሊውድ ፊልም ላይ ሰው ወደ ውሻነት ሲቀየር ማየቴ ትዝ አለኝ/ ሽፋኑ በአንድነት ተሾመ ቢሰራም “ዲዛይኑ” የራሱ የደራሲው ነው፡፡ ደራሲው በዘመነኛው የስነ-ጽሁፍ ታሪክ ለዚህች አገር ትልቅ ስም አለው፡፡ ይህ መኾኑም ያለንበትን ደረጃ ማሳየት የሚችል መረጃ ነው! /ያለንበት በቂ ነው አይደለም የሚለው ጥያዌ እንዳለ ሆኖ/ የምናምነው የምንጠራጠረውን ነው፡፡ የምትል አንዲት መጽሐፍ የሚወጣላት ዐረፍተ ነገር በገጽ 5 እናነባለን፡፡ ለራሴ ብዙ ጥያቄዎችን በመስጠት አሰላሰልኩ፡፡ በህይወታችን ማንን እናምናለን? ማንን እንጠራጠራለን? ጥርጣሬ ያለበት እምነት ዋጋ ቢስ ነው! የምንጠራጠረውን ካመንን እምነታችን ከንቱ ነው! እምነት የሰናፍጭ ታክል ብትደቅም ምልዕነቷ ግን ዝግ ነው! የቅንጣት ጠብታ ታክል ጥርጣሬ በውስጧ አታስተናግድም፡፡

የዚህ ብላቴና እምነት ግን በትልቅ ጥርጣሬ እንደተሳካች ናት፡፡ ትልቅ ጥያቄ ምልክት በገጽ 5! የዚህ አባባል ንድፍ በገጽ 6 ላይ ቀርቧል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኙትን የአስማት ቃላት በመሞከር ለሚመጣው ችግር ደራሲው ተጠያቂ አይደለም፡፡ ይለናል! አቤቱ… እኛን በማጠራጠር ሊያሳምን የሚሞክር ሙከራ ነው ለማለት ዳዳሁ፡፡ የዚህ “አስማት ቃል” ማሳሰቢያ በገጽ 169 ተደግሟል፡፡ የአስማት ቃሉ ግን ከገጽ 144 በቀር በመፅሐፉ ውስጥ አይገኝም፡፡ ምናልባት ከመጽሐፉ ሽፋን ላይ የተጻፈውን ከሆነ? ነገር ግን ልጁ የዋዛ አይደለም… ሁለተኛ መጽሐፌን ሰረቁኝ ብሎ አስወርቷል… “ሥራዎቹ የበዓሉ ግርማ ናቸው”የሚለው ዱብዳ ዜና …. ሌሎች ሌሎች…አሁንም በዚህ መጽሐፍ ለተደራሲያን ምክንያታዊ አክብሮት እና በስልታዊ ተዘዋዋሪ አጽንዖት እንዲታሰር ያስገድደናል…. በካፒታሊዝም ብልጠት የተነደፈ ጸሐፊ ይህ ነው ትርፉ! ከዚህ መጽሐፍ ተምሬአለሁ፡፡

ብዙም ተማርሬያለሁ! ልብወለድ ነው? ወይስ ታሪካዊ መጽሐፍ? መጣጥፍ? እያልኩ አነበው ጀመር፡፡ የስነ-ጥበብ ጥማቴን ለመወጣት ጊዜዬን ሰጠሁ… በአንድ መጽሔት የወጡ ሃሳቦች ተደግመዋል… ልጁ የፖለቲካ ምሬቱን በልቦለድ ስም ይለጥፋል፡፡ አይተ ስብአት ነጋ ገጸ-ባህሪ ተሰጥቷቸው እናያለን /ገፅ 64/፡፡ ይሄ ልጅ የሰውን የፖለቲካ ጥማት፣ በየመንደሩ የሚወራውን አሉባልታ ስብስብ ለታሪክ ምስክር እንዲሆን እየሞከረ ይኾን? ጠ/ሚኒስትሩ ከህመማቸው ጀምሮ እስከ እለተ ሞታቸው የዜና እወጃ፣ ከዚያም የቀብር ስነ-ስርዓት በኢትዮጵያ የነበረውን ጊዜ ሊያስታውሰን ይሞክራል… ክረምቱን ተገን በማድረግ የሙት አመቱን ሊያሳስበን ይሆን? እያልኩ በግድ ማንበቤን ቀጠልኩ… በአስማት ወደ ውሻነት የተቀየረው መሪ ገጸ-ባህሪ እና ሩጫው፣ ከደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ መሀል ኢትዮጵያ ወደ ቤተ መንግስት ይነጉዳል… በየቦታው የሚሰማውን አሉባልታ ወይንም ምሬት ከዚያም አልፎ በሀገራችን የሚታየውን የገሀድ ገፅታ ሊያሳየን ደፍሯል፡፡ ከአይሱዙ መኪኖች ፍጥነት እስከ የሴቶች መደፈር… ከሥጋ ቆራጭ አስፈሪነት እስከ ትውልድ በጫት፣ በሲጋራና በአልኮል መነደፍ…እንዲሁም የገዢው ቡድን…..አድርባይ የ”ፓርቲው” አባላትን ያስቃኘናል፡፡

አንዳንዴም የሚነግረን ተምሳሌታዊ መረጃ ጸሐፊው ይህንንም አውቃለሁ እያለ ይመስላል፡፡ የብልግናን (ጸያፍ ቃል) በመጠቀም ድርሰቴን በመብረቅ በማጀብ አነጋጋሪነቱን ለማወጅ “ግልጽ ነኝ!” ያክል ድፍረት ነው የተሰማኝ… በገፅ 30 ላይ የተጻፈው አባባል የመጽሐፉን ይዘት በሁለት አሀዝ እንዲዋዥቅ አድርጎብኛል፡፡ ጸሐፊው የጥንቷን ኢትዮጵያ አጥብቆ ይመኛታል፡፡ የነበረንን ታላቅነት በአፈ-ታሪካዊ ሀተታ እያዋዛ ሊያስታውሰን ይዳዳል፡፡ የካፒታሊስትን አሰቃቂ ሸክም ሊያሳየን ይሞክራል፡፡ ለኔ ግን ራሱ ከካፒታሊስት የባሰ ጨካኝ ርዕዮተ ዓለም አራማጅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ካፒታሊዝም “የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው!” አይነት የስግብግብነት ኑፋቄ እንዳለው ሊያስተምረን ይዳዳውና ይህች አገር የምታድገው ህቡዕ ቃል (በአስማት እያለ በሚጠራው) መተት እንደሆነ ሊያሳየን ሲሞክር አይኑን አያሽም፡፡ በገጽ 7 “የእውነቱን የማይኖር የእውነቱን የማይስቅ፣ የእውነቱን የማያለቅስ ትውልድ ይህንን አስቸጋሪ ሀቅ እንዲያይ አይገደድም” ከሚል አባባል ጀምሮ ዘመኑን የሚቃኙ በርካታ ሀተታዎችን በማስቀመጡ መልካም ሆኖ ሳለ፣ በጸሐፊው ፍላጎት ይህ ትውልድ ወደ አስማታዊው “ጥበብ” እንዲመለስ፣ አስማተኛ ትውልድ እንዲፈጠር ይሽቀዳደማል፡፡

ስለ ውሻ፣ ስለ ሰው ባሕርያት፣ የእንስሳን እና የሰውን ወሲባዊ ግንኙነት፣የሰውን ሳይንሳዊ ትንታኔ፣ ስለአመጋገብ እና ታሪክ ከጎግል የቀዳው መረጃ መሆኑን ጠርጥሬለሁ፡፡ የ“ዣንቶዣራ” ዓይነት አፃፃፍ አሳይቶናል፡፡ በዣንቶዣራ ውስጥ ስለ ፍሪሜስን፣ቴምፕላርስ፣ አሉሚናቲ ታሪካዊ አመጣጣቸው እና ምልክቶቻቸው የጎግል ፍብርኮች ነበሩ፡፡ ሰውየው ዓለሙን ሁሉ ልብ-ወለድ አድርጎ፤ምትሃታዊ ትውልድ ፈጥሮ ፈሪ ጸሐፊያንን አበራክቶ አዋቂነቱን በልቦለድ መድረክ ማቅረብ መፈለጉ ምን ነካው አስብሎኛል? እባክህ ተገለጥልኝ! ቻይናዊያን ስለ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን አመለካከት አሳይቶናል፡፡ በገጽ 33 ያ ቻይናዊ የኢትዮጵያኖችን የስራ ጥላቻ ለማስተላለፍ ሞክሯል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ስራ ወዳድ ያልሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? ተብለን ስንጠየቅ ምላሹ ሊቀርብልን ይገባ ነበር፡፡

ገበሬው አመቱን ሙሉ አስቦ፣ ዝናብ ጠብቆ፣ ክረምቷን አርሶ፣ አርሞ፣ ጸሉቶ የሚያገኛትን እህል ላልዘራው እና ላላረሰው ወስዶ ሲገብር ምን ያህል ተስፋው አይታጨድ? ምን ያህል በስራው አይለግም? ዛሬ ልደታ፣ ነገ አቦ ከዛም ስም እየጠራ ስራን ማቅለሉ ታይቶን ይሆን? ፈረሱ ተላልጦ ተሸክሞ፤ መሪውን እና ጋሪውን እየጎተተ የሚታየው የማን ህዝብ ነው? /በገጽ 50 የተገለጸውን ተምሳሌታዊ አቀራረብ አድንቄዋለሁ/ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እለተ ዕረፍታቸው ከታወጀበት ቀን አንስቶ እስከ ቀብራቸው የነበረው ጊዜ ስንት ቀን ነበር? በገጽ 3 ሀተታ ላይ “ይስማዕከ በተፈጥሮ በተለገሰው ክህሎት ሲፈልግ አንዱን ሴኮንድ የዘላለምን ያህል ያረዝመዋል፤ሲያሻው ዘመንን ጠቅልሎ በአንዲት ሰኮንድ ውሥጥ ይከተዋል” በማለት አምልኮታዊ ስብዕናን ያላበሰው አስተያየት ሰጪ----ነሐሴ 2004 ግን ለኢትዮጵያ ዝንት አለም አልነበረችምን? በዚህ መጽሐፍ ላይ ግን በሩጫ ታልፋለች! ደራሲው ወደ ገጽ 191 ለመድረስ ነካ ነካ አድርጎ አልፏታል፡፡

ነካ ነካ ያደረጋት እንደው ፖለቲካዊ ለዛ ለማሳደር እንጂ ሌላው አልመስልህ አለኝ..! ከዚህ መጽሀፍ ምን እንረዳ? የኋላን ታሪክ እንድንማርበት፣ ኢትዮጵያ በመሪዎቿ እንደዋዠቀች፣ ጥቂቶች የሚያወሩባት የሚመራመሩባት ሀገር እንዳለችን፣ የተደበቀ ጥበብ እንዳለ፣ ከህይወት መማር እንዳለብን የሚጠቁሙ አንቀጾች አሉት፡፡ በገጽ 41 የተጠቀሰችውን አባባል እንዳለ ላቅርባት፡፡ “ህይወት እንደ ካርቱን ፊልም ቀለም ዘቅም በሰጣቸው ስዕሎች ተንቀሳቃሽነት ጀብድ የሚፊጸምባት የህልም አለም አይደለችም፡፡ ለመሄድ የራስን ቋንጃ፣ ለመዞር የራስህ ጋንጃ፣ ለመወሰን የራስን ፍርጃ፣ ለመንዳት የራስን አቅም፣ ፍሬን ለመያዝ የራስን ቅልጥም ትጠይቃለች” ሌላም ሌላም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንን ካልክ ለምን ሙሉ በሙሉ አድናቆትህን ችረህ አትዘጋም እንዳትሉኝ፡፡ ልጁ እኮ የ“ዴርቶጋዳ” ጸሐፊ ነው! ሰው እያደገ ሲመጣ፤ እየተሻሻለ ይሄዳል፣ የበለጠ ይጠነክራል፣ የበለጠ ያይላል እንጂ…. ይደበዝዛል? መጽሐፍ በሽያጭ ብዛት፣በገጽ ብዛት ብቻ አይደነቅም፡፡ ምን ተማርኩ? ምን አሳየኝ? ምን የማላውቀውን አስተማረኝ? ምን ለወጠኝ? ምን እንዳስብ አደረገኝ? ምን ጭብጥ አገኘሁበት ተብሎ ይመዘናል…! በቅዠት ብቻ ተለውሶ የሚወራጭ ከኾነ፣ በእኔ እምነት መጽሐፍ ነው ብዬ መጥራት ያዳግተኛል፡፡

ዝና ሊገኝ ይችላል፤ ስምም ሊስፋፋ ይችላል፤ ገንዘብም ሊከማች ይችላል፣ ነገር ግን ሰውን ወደ ተሻለ ስብዕና መቀየር ካልተቻለ የጥበብ ትልቁን ትርጉም ያመክነዋል፡፡ በ“ክቡር ድንጋይ” ውስጥ አስማተኛ እንድንኾን…ሀገራችን “የንጋት ኮከብን” መተት እንድትከተል ጸሐፊው ሊያሳምነን ይሞክራል፡፡ ደራሲው በመጽሐፉ ውስጥ የባዕዳን ርዕዮተአለም ፍልስፍናዎችን ማለትም ካፒታሊዝምንና ሶሻሊዝምን አጥብቆ ይኮንናል፡፡ ታላቅ ክቡር ተብሎ በተገለጸው ቃል አማካኝነት አስማታዊ ሃይልን ይዘን እንድናድግ ይወተውተናል፡፡ ለመኾኑ የንጋት ኮከብ ማን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ የንጋት ኮከብ ተብሎ የተሰየመው የዳዊት ዘር ስር እየሱስ ክርስቶስ ነው! /ራዕይ 21/ ኾኖም ዲያቢሎስንም በንጋት አጥቢያ ኮከብ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡/ኢሳ 14/ ፡፡ በዚህ ደራሲ አገላለጽ የንጋት ኮከብ ማን እንደኾነ የግላችንን መላምት ለመውሰድ እንገደዳለን፡፡ ይኸውም የሰውን ልጅ ከሰውነት ተርታ ወደ ውሻነት ከዚያም ወደ ዘንዶነት እንዲሁም ወደ ፈለግነው ፍጥረት እንድንለወጥ የሚያደርገን የአስማት “ጥበብ” ከዲያቢሎስ እንጂ ከክርስቶስ እንደማይኾን እንተማመናለን፡፡

በአስማት ሃይል ምጣኔ ሃብት ይደግ፤ ሀገርም ትልማ ቢባል ከካፒታሊስቶቹ ፍልስፍና በምን ተለየ? “የክቡር ድንጋይ” ደራሲ ግን ለዚህች ሀገር ከካፒታሊስቶቹ በተለየ በአስማታዊ ጥበብ ሊገዛት ይፍጨረጨራል… የባሰ አታምጣ! የህንጻ ጥበብ አስማት ከተባለ የሰለሞን ጥበብ ከምን ሊመደብ ይችላል? በዲያቢሎስ ተመርቶ መኖር እና ዲያቢሎስን መርቶ ገዝቶ መኖር አንድ አይደሉም፡፡ /ሰለሞን አጋንንትን ገዝቷል/ ውሻው ወደ ቤተ-መንግስት ይሮጣል… ጉዞው ቤተ-መንግስት ላይ አይፈጸምም፡፡ የውሻው ሩጫ ወደ ባለቤቱና ወደ ልጆቹ ይቀለበሳል፡፡ በአስማታዊ ሃይልም ከውሻነት ወደ ዘንዶነት ይለወጣል… “በንጋት ኮከቡም” መሪነት ወደ “ሰውነት” ይቀየራል ---፡፡ሰው ወደ ውሻነት እየተቀየረ ነው….ሰው ወደ አውሬነት እየተለወጠ ነው… ይህ ደግሞ የኾነው “በመሪዎቻችን” ውሻነት ነው…! ጸሐፍት መሪዎቻችን ናቸው! “ውሻ መሪ እና ውሻ ትውልድ ቀስ በቀስ ይታያሉ…!” ይስማዕከ ከውሻነት ወደ ሰውነት እንድንቀየር አጥብቆ ወትውቶናል፡፡ ሰው ከኾንን በኋላ ግን ምን አይነት ሰው እንደምንኾን የወሰደው አማራጭ የሚያስተዛዝብ ነው…. እስቲ መጽሐፉን ያንብቡት እና እንወያይበት፡፡

Read 13268 times