Saturday, 13 July 2013 11:36

ክኒና

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(4 votes)

አስር አለቃ ጠና ከካፊያው ለመሸሽ ወደ ፋርማሲው በረንዳ ጠጋ አሉ፡፡ «ተናግሬያለሁ ጌታው!... ሰሃት ታለፈ በኋላ ወደዚህ መጠጋት አይቻልም» አሉ የፋርማሲው ዘበኛ ኮስተር ብለው፡፡ «ምን ላርግ ብለህ ነው!?… ስንትና ስንት ብር ያፈሰስኩበት መዳኒት አጉል ሁኖ ሊቀርብኝ እኮ ነው!» ብለው ቆፈን ያደነዘዘው ቀኝ እጃቸውን ወደ ካፖርት ኪሳቸው ከተቱት፡፡ የዘበኛው ተጠራጣሪ አይኖች የካፖርቱ ኪስ በር ላይ ተተከሉ፡፡ አስር አለቃ ጠና ከኪሳቸው ያወጡትን የተጠቀለለ ስስ ፌስታል በጥንቃቄ ፈትተው ተመለከቱት፡፡ አራት አይነት የወረቀት ከረጢቶች… አራት አይነት ክኒኖች… አራት አይነት የአወሳሰድ መመሪያዎች… በትኩሳት ለሚቃጠሉ፣ በራስምታት ለሚሰቃዩ፣ በላብ ለሚጠመቁ፣ በውጋት ለሚቃትቱ… ባዶ ቤት ተኝተው ለሚሰቃዩ ታማሚ ባለቤታቸው የገዟቸው መድሃኒቶች፡፡ «ጉድ እኮ ነው!... እንዴው ምን አጣድፏቸው ዘጉት?» አስር አለቃ ጠና በጭንቀት ተውጠው በረጅሙ ተነፈሱ፡፡ «ሰሃቱንም አላዩት እንዴት?... አራት ሊሞላ እኮ ነው!» ዘበኛው በላያቸው ላይ የደረቡትን ብርድልብስ ሰብሰብ አደረጉ፡፡

«እሱስ ነው… ብቻ እንዲያው… ዘግተው ተወጡ ግን ቆዩ?» «መንገድ ላይ ተላልፋችሁ ይሆናል እንጂ፣ አስር ደቂቃም አይሆናቸው ተወጡ» የፋርማሲው ዘበኛ አሻግረው ወደ ዋናው መንገድ እያዩ መለሱ፡፡ በካፊያ የጨቀየው መንገድ ጭር ብሏል፡፡ «እንዲያው ምናባቴ ይሻለኛል ይሆን አንተየ?...» አስር አለቃ ጠና ወደ ዘበኛው እያዩ በተጨነቀ ድምጽ ጠየቁ፡፡ ዘበኛው በተቀመጡበት ሆነው ወደተዘጋው ፋርማሲ አየት አድርገው፣ መለስ አሉና ወደ አስር አለቃ ጠና ተመለከቱ፡፡ በፌስታል የያዟቸውን መድሃኒቶች በጥንቃቄ እየነካኩ በግርምት አናታቸውን ይወዘውዛሉ፡፡ የሆነ ችግር እንደተፈጠረ ገብቷቸዋል - ዘበኛው፡፡ መጠራጠር አይከፋም ብለው እንጂ፣ ሰውየው ክፉ ነገር አስበው ከመሸ ፋርማሲው በር ላይ እንዳልተገተሩ ያውቃሉ፡፡ ከደቂቃዎች በፊት ከፋርማሲው የገዙትን መድሃኒት ይዘው ሲወጡ አይተዋቸዋል፡፡ ወደ ፋርማሲው ተመልሰው የመጡት የሆነ ችግር ገጥሟቸው መሆን አለበት፡፡ «ለመሆኑ ምን ገጥሞዎት ነው ጌታው?» በማለት ጠየቁ ዘበኛው፡፡ «ኧረ ተወኝ አንተየ!!... ሞላ አልሞላ ብየ፣ ተዚህም ተዚያም አጠረቃቅሜ ገዝቼ በከንቱ ቀረሁ!!» አሉና የተዘጋውን የፋርማሲው በር ገላመጡት፡፡ «መዳኒት ጣሉ እንዴ?» ዘበኛው በሃዘኔታ እያዩ ተናገሩ፡፡ አስር አለቃ ጠና መልስ አልሰጡም፡፡ ቀና ብለው ግድግዳው ላይ ወደተሰቀለው የፋርማሲው ታፔላ ተመለከቱ፡፡

“ጤና አዳም መድሃኒት ቤት 24 ሰዓት ይሰራል” ይላል፡፡ ያነበቡትን ለማመን ቸገራቸው፡፡ መልሰው አነበቡት፡፡ ያው ነው፡፡ «እኔ እምለው… በቀን ዘግተው እየጠፉ ሃያ አራት ሰሃት እንሰራለን ይላሉ እንዴ?» አሉ አስር አለቃ ጠና በንዴት ቱግ ብለው፡፡ «እሱስ አልጠፉም… የማታ ተረኛይቱ ብትዘገይባቸው ግዜ ነው መሰል፣ አሁን ነው ዘግተውት የኸዱ» ዘበኛው ለማስተባበል ሞከሩ፡፡ «እና ግን… ተረኛይቱ ትገባለይ ማለት ነው?» በጉጉት ተውጠው አሻግረው መንገዱን እያዩ ጠየቁ፡፡ «ስራ አይደል እንዴ!... ዝናቡ ይዟት ነው እንጂ እስተዚህም አታመሽ ነበር» እሳቸውም ወደ መንገዱ አማተሩ፡፡ «ምነው ምን አረግኋት አንተዮ!… ዝናብስ ቢሆን፣ የታመመሰው ይመጣል ብላ አታስብም?... ምሽቴ አይሆኑ ሁና እየተሰቃየች፣ እሷ ዝናብ ያበሰብሰኛል ብላ ፈርታ ተቤቷ ተቀመጠች?» አሉና በከፍተኛ ሀዘን ተዋጡ፡፡ “ትንሽ ተጠበቋት መምጣቷ አይቀርም” «አይ አንተ!.. ምሽቴ ከሞተች በኋላ ብትመጣ ምን ታረግልኛለች?» ሳግ ተናነቃቸው፡፡ «ይተው እንጂ ጌታው!... እንዲህማ ደግም አይደል፡፡ ሟቹንም፣ ቀሪውንም የሚያውቀው እሱ መደሃኒያለም ነው!» አሉ ዘበኛው ወደ ጠቆረው ሰማይ በዱላቸው እየጠቆሙ፡፡ አስር አለቃ ጠና ቀና ብለው በዱላው አቅጣጫ ተመለከቱ፡፡

«ቅድም…መዳኒት ገዝተው ሲወጡ አላየሁዎትም ነበር?» ዘበኛው ግራ ተጋብተዋል፡፡ «እሱማ ገዝቼ ነበር… ‘አንድ ልጃችን መክቴን ተአዋሳ ይንበርስቲ ተመርቆ ሲመጣ ድግስ እንደግስበታለን’ ብለን ተሰው የተበደርነውን ብር አንስቸ ስበር መጥቸ ይኸን ሁላ ክኒና ገዝቸ ነበር፡፡ አታየውም?... ያገር ክኒና እኮ ነው ያሸከመኝ!...» ፌስታሉን እየገለጡ ተናገሩ፡፡ «እሷማ ክኒናውን ልግዛ ማለቴን ስትሰማ እምብኝ ብላ ነበር፡፡ ‘ለልጄ ብየ ያስቀመጥሁትን ብር አልነካውም… እነ ደመቀች ልጃቸው ሲመረቅ ድል ያለ ድግስ እንደደገሱት፣ እኛም መክቴ ተመርቆ ሲመጣ አለሙን እናሳየዋለን!’… ብላ፣ ብሩን ነጥቃኝ ነበር» አሉና ሳግ ተናነቃቸው፡፡ «አፈር ልብላ እናቴ!.. እመማቸውን ትተው ስለ ልጃቸው ተጨነቁ!?» ዘበኛው አብዝተው አዘኑ፡፡ «ህመም ቢሉህ ህመም መሰለህ?!... አሳር መከራዋን ስታይ እኮ ነው የባጀችው!... ተትናንት ወዲያ ሲብስባት፣ ተጎረቤቶቼ ጋር አፋፍሰን ጤና ጣቢያ ወሰድናት፡፡ አኪሙ አያትና እንዲህ ነው፣ እንዲህ ነው ሳይል ‘ክኒና ገዝተህ ስጣት’ ብሎ ቁራጭ ወረቀት ሰጠኝ፡፡ ክኒና መግዣውን ገንዘብ ተየታባቴ እንደማገኝ ግራ ገብቶኝ ስጨነቅ ዋልሁ፡፡ ተዚያልህ… ለመክቴ ምርቃት ድግስ ልናዘጋጅበት የተበደርነው ብር ትዝ አለኝ፡፡ እሷ በህመም እየተሰቃየች የምን ድግስ ነው ብየ አሰብሁ፡፡

ብሩን ተቁም ሳንዱቁ ሳወጣው አየችኝና እንደምናምን ታልጋዋ ዘላ ተነሳች፡፡ መዳኒት ልገዛበት ማሰቤን አውቃ ኑሮ እንደ እብድ አርጓት ብሩን ነጠቀችኝ፡፡ ‘የለም! አይሆንም!...’ ብላ ድርቅ አለች…» ንግግራቸውን አቋርጠው ወደ መንገዱ ተመለከቱ፡፡ ዙሪያ ገባው ጭር ብሏል፡፡ ትመጣለች የተባለችዋ የመድሃኒት ቤቱ የማታ ተረኛ ፋርማሲስት አልመጣችም፡፡ «እናልህ… ሁለት ቀን ሙሉ ስትሰቃይ ቆይታ… ዛሬ አመሻሽ ላይ ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ ሆነ… ለልጃችን ማስመረቂያ ብለን የተበደርነው ብር እያለ፣ ክኒና አጥታ ስትሞት ዝም ልበል!?... ሽቅብ ቁልቁል ሲላት ቆይታ በመሃከል እንቅልፍ ሸለብ ሲያደርጋት፣ አንዱን ጎረቤቴን ‘አደራ ክኒና ገዝቸ እስትመጣ ተመልከታትማ’ ብየ ለምኘው፣ ቀስ ብየ ተነሳሁ፡፡ ‘ክኒና ልግዛበት’ ስል ሰምታ፣ ተጄ ላይ ነጥቃ ተሙዳይዋ የደበቀችውን፣ ያንን… ለልጃችን ምርቃት የተበደርነውን ብር አንስቸ፣ ስሮጥ ወደዚህ መጣሁ» አሉና በረጅሙ ተነፈሱ፡፡ «ኧረ ደግ አርገዋል!... ልጁስ ቢሆን እናቱ በሂወት ብትኖርለት አይደል የሚሻለው?... አልደገሳችሁልኝም ብሎ አይቀየማችሁ!…» አሉ ዘበኛው በሃዘኔታ ስሜት ወደ አስር አለቃ እያዩ፡፡

አስር አለቃ ጠና መንገድ መንገዱን ያያሉ፡፡ «እና አሁን… ማለቴ… መዳኒቱን ተገዙ፣ ምን ቀርቶዎት ነው ተመልሰው የመጡ?» አሉ ዘበኛው ግራ በተጋባ ስሜት፡፡ «ሳትሞት ልድረስላት ብየ ስጣደፍ፣ አኪሙ ስለ ክኒናው የነገሩኝን ልብ ብየ አለመስማቴ ትዝ አለኝ፡፡ ‘ተራት በፊት ስጣት’ ይበለኝ፣ ‘ተራት በኋላ’ ተደናገረኝ… እና ደግሞ…» ብለው በእንጥልጥል ተውትና፣ መድሃኒት የያዙትን አራት የተለያዩ የወረቀት ከረጢቶች በጣታቸው እየነካኩ ዝም አሉ፡፡ «አይ የስዎ ነገር!... ለዚህ ብለው ነው ተመልስው የመጡ?... መች መች እንደሚወሰድ ተወረቀቱ ላይ ይጥፉታል እኮ!... እስቲ ያንብቡትማ… » አሉ ዘበኛው በፍጥነት ከተቀመጡበት ብድግ ብለው፡፡ ከማንም አልሻልም ብለው ያስቡ ነበር፡፡ እንደዚህ ማሰባቸው ስህተት እንደሆነ ገባቸው፡፡ ቢያንስ ከአስር አለቃ ይሻላሉ፡፡ «መች አስጨረስከኝ!... እሱማ ተጥፏል… ግን ምንድን ነው… ክኒናውን ሲሰጡኝ፣ ‘ምሽትህ ጨጓራ አለባት ወይ?’ ብለው ጠይቀውኝ፣ ‘የለባትም’ ብያቸው ነበር፡፡ ክኒናውን ይዤ ወደቤቴ እየሮጥሁ እያለሁ፣ ልክ ተደምሴ ስጋ ቤት ላይ ስደርስ፣ ተመስኮቱ ላይ ያንጠለጠለውን ምላስ ሰንበር ተመለከትሁ፡፡ የተንጠለጠለውን ጨጓራ ባየሁበት ቅጥበት፣ መጋኛ እንደመታው ሰው ፈዝዠ ቀረሁ፡፡» ድንገተኛ የመብረቅ ብልጭታ ጥቁሩን ሰማይ ሰነጣጠቀው፡፡

ዘበኛው ጣልቃ ገብተው አማተቡ፡፡ «ተስጋ ቤቱ ላይ ያለውን ጨጓራ ሳይ፣ ምሽቴ አልፎ አልፎ ‘ጨጓራየ ተነሳብኝ’ ትል እንደነበር ትዝ አለኝ፡፡ እግዜር ያሳይህ እንግዲህ!... ለሃኪሙ እኮ ኧረ ጨጓራ እሚባል ህመም አያውቃትም ብየ ወሽክቻለሁ!... » ዘውር ብለው ወደ መንገዱ አዩ፡፡ «ያንት ያለህ!...» ዘበኛው በመገረም አናታቸውን ነቀነቁ፡፡ ደግመው አማተቡ፡፡ «ምናልባት ክኒናው ችግር ይፈጥርባት ይሆን? ብየ ልጠይቃቸው ስመጣ፣ ይሄው ዘግተውት ህደዋል!... አሉና የተዘጋውን የመድሃኒት ቤቱ በር እያዩ ዝም አሉ፡፡ አሸባሪ ነጎድጓድ አስተጋባ፡፡ ዘበኛው ደግመው አማተቡ፡፡ «ወይኔ ምሽቴ!!... እሂን ጊዜማ አንድ ነገር ሁና ነው እሚሆን!!... እኔ እምልህ ወንድሜ… እች ተረኛይቱ ሴትዮ፣ የት አካባቢ ይሆን ቤቷ?… ሮጥ ብየ ህጀ ልጥራት ይሆን?» አይናቸው እንባ አቅርሮ ወደ መንገዱ ተመለከቱ፡፡ ከጨለማው ውስጥ ነጠላ የደረበች ሴት ብቅ ስትል አዩ፡፡ አስር አለቃ ጠና በህይወት ዘመናቸው ሙሉ እንደዚህ አይነት ደስታ ተሰምቷቸው አያውቅም! «እግዜር ይስጣት!!.. መጣች!…» አሉ ደስታ እየተፍለቀለቁ፣ ወደ መድሃኒት ቤቱ የምትመጣዋን ሴት እያዩ፡፡ «ምነው ምን አረግሁህ ጠናየ!... ደብቄ ያስቀመጥሁትን ብር አንስተህ መጣህ? … እኔኮ ተሽሎኛል!!... አታየኝም እንዴ?!… ራስምታቱም ለቀቀኝ!… አሁንማ ህመሙም ለቀቀኝ!...እዚያሄር ይመስገን… መክቴንም ድል ባለ ድግስ ነው እማስመርቀው!!» አሉ ታማሚዋ የአስር አለቃ ባለቤት፣ በብርድ ይሁን በደስታ በማይለይ መልኩ እየተንቀጠቀጡ፡፡

Read 4033 times
More in this category: « ፍርሐት ዘቢብ »