Saturday, 13 July 2013 11:45

የካርታ ጨዋታ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

ሼልፍ አለችኝ፡፡ “አለኝ” ብዬ የምተማመንባት አይደለችም፡፡ እንደ አቅሚቲ የተወሰኑ መጽሐፍት ሰባስቤ ሰካክቼባታለሁ፡፡ ከኑሮ እና ከሌላ አልባሌ ግራ መጋባት የተረፈኝ ገንዘብ ሲኖር አይኔን የሳበውን የመጽሐፍ ሽፋን ተመርኩዤ እገዛና እጨምርባታለሁ፡፡ እንደ ሁላችሁም፤ እኔም የሽፋን አምልኮ ተከታይ ነኝ፡፡ የሰበሰብኳቸው መጽሐፍ ከሁለት የቋንቋ አቅጣጫ የመጡብኝ/ልኝ ናቸው፡፡ አንዱ ያው እንግሊዝኛ መሆኑ ነው፡፡ የተቀሩት፤ አሁን እየፃፍኩ ባለሁበት ቋንቋ የታተሙ ናቸው፡፡ መጽሐፍቱ የተደረደሩት የህትመት ዘመንን ቅደም ተከትለው አይደለም፡፡ እንደዘውጋቸው ወይንም እንደይዘታቸውም አይደለም፡፡

ቅርፃቸውም… ለአደራደራቸው ስምምነት ምክንያት አይሆንም፡፡ ተመለከትኳቸው፡፡ ከመመሳሰል ይልቅ መራራቃቸው አየለብኝ፡፡ ሼልፉ ላይ በተገኘው ክፍተት የተሻጡ፤ ከተገኘው አዟሪ የተሸጡልኝ ናቸው፡፡ አለመመሳሰላቸው፣ በተደረደሩበት… እንደአጋጣሚ የያዙት ተቃርኖ መሰጠኝ፡፡ ልጽፋቸው ተነሳሁ፡፡ አይኔ በመጀመሪያ ያረፈበት መጽሐፍ የእኔ የትኩረት ምርጫ ነው፡፡ መፅሐፉማ ምርጫ የሌለው ግዑዝ ነው፡፡ “ኦሮማይ” ይላል፡፡ “ኦሮማይ” ከሚለው አርዕስት ጋር የሚተሳሰሩ ለዘመናት፣ የተከማቹ መረጃዎች ትዝ አሉኝ፡፡ በዓሉ ግርማ…ሀዲስ፣ ከአድማስ ባሻገር…በደብረ ዘይት መንገድ ላይ ቆማ የተገኘችው ቮልስ ዋገን…የተሰወረው እና የደረሰበት ያልታወቀው ደራሲ… ሁሉም ትዝ አለኝ፡፡ ከኦሮማይ ጐን የተሰካው መጽሐፍ ግን መሆን ያልነበረበት ነው፡፡ “ዘ ማይንድ” የሚል በዶ/ር አቡሽ የተፃፈ ራስን ለማነቃቃት (motivation) ይጠቅማል ተብሎ የተፃፈ… “የአንቃ-አሩጥ” መጽሐፍ ነው፡፡

ራስን ለማነቃቃት ተብሎ የተፃፈ መጽሐፍ ከ”ኦሮማይ” ጋር መዳበሉ ለበአሉ ግርማ ምን ይፈይድለታል? ብዬ በጠማምኛ አሰብኩ፡፡ የበአሉ መነቃቃት፤ ወይንም ከሞት ተመልሶ መምጣት… ለማን ብልጽግና ይፈጥራል? ብዬ በዳኛቸው ወርቁ’ኛ “ፈደስኩ”፡፡ አዲስ መጽሐፍ ጠረጴዛ ላይ ሼልፉ መሃል ቦታ አጥቶ ሲጠብቅ አየሁ፡፡ በይስማይከ ወርቁ የተፃፈ ከማተሚያ ምጣድ ወደ አንባቢ አይን በቅርቡ ማእድ የተቀላቀለ፣ ያጨናነቀ መጽሐፍ፡፡ “ክቡር ድንጋይ” ይላል አርእስቱ፡፡ “በአሉ ከተሰወረበት ተመልሶ የመጣው ይስማዕከን ሆኖ ነው” የሚል ጭምጭምታ የሰማው ጆሮዬ… በአፌ በኩል ወደ ፈገግታ ሲለወጥ ተሰማኝ፡፡ መጽሐፉን አንስቼ ከዶ/ር አቡሽ መፅሐፍ አስከትዬ አስቀመጥኩት፡፡ “ኦሮማይ” ራሱን የብልጽግና ጥበብ ካስተማረ በኋላ “ክቡር ድንጋይ” ሆኖ መሸጡን አመልካች ይሆን ድርጊቴ?...ሊሆን ይችላል፡፡ በተርታው ወደ ግራ በመቀጠል የተሰተረው መጽሐፍ ላይ ላተኩርበት በማነጣጠር ላይ ሳለሁ መጽሐፉ ቅርፊት (ሽፋን) የሌለው ሆነብኝ፡፡ አውጥቼ ከምመለከተው… የትኛውን መጽሐፍ ሊሆን እንደሚችል በአቦ ሰጡኝ ብገምት ለጨዋታዬ ብዙ አማራጭ እንደሚከፍት ገመትኩኝ፡፡

ሽፋን አልባውን መጽሐፍ እንደ “ጆከር” ቆጠርኩት፡፡ እንደ ፍልስፍና መጽሐፍ የጆከርን ባህሪ በደንብ አድርጐ የሚላበስ የለም፡፡ መጽሐፉ በገጽ ብዛትም በቁመትም አጭር ነው፡፡ የፍልስፍና መጽሐፍ ከሆነ/ ቢሆን የምዕራባዊያን ፍልስፍና ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና መሆኑ አያጠራጠርም፡፡ የኢትዮጵያዊ ፍልስፍና በዘረ-ያዕቆብ ተጀምሮ እዛው ዘረ-ያዕቆብ ላይ ይጠናቀቃል፡፡ በአጭሩ… በጥቂት ገፆች፡፡ ጆከሩን መዝዤ ውስጥ ገፁን ስመለከተው የአቤ ጉበኛው ታዋቂ መጽሐፍ “አልወለድም” ሆነና አረፍኩት፡፡ የገዛሁት ከአሮጌ ተራ ነው፡፡ ተራው ራሱ አሮጌ አድርጐታል፡፡ “አልወለድም” ከሚለው ተጨባጭ አርዕስት ጋር ስፋጠጥ፤ ቅድም በምናቤ የሳልኩትን የፍልስፍና መጽሐፍ ቢሆንልኝ የሚለውን ምኞቴን መርሳት ቢኖርብኝም፣ መርሳት ግን አልቻልኩም፡፡ ተጨባጩ እና የማይጨበጠው ተደባልቀው ሌላ ትርጉም በውስጤ መሳል ወይ ማሳል ጀመሩ፡፡ ፍልስፍናና ዘረ - ያዕቆብ በኢትዮጵያ “አልወለድም” አሉ፤ የሚል ትርጉም፡፡ ትርጉሙን ወዲያው ረሳሁት፡፡

ጨዋታው ቁማር ነው፡፡ በሳንቲም ወይንም በካርታ ወይንም በDice የሚደረግ ቁማር ሳይሆን… በመጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍቶቹ እንደ ካርታ ተደርድረዋል፡፡ ውልግድግድ ያሉ ጥርሶች ቢመስሉም፤ እኔ እንደ አሻኝ አስተካክዬ በጽሑፍ መልክ እወርዳቸዋለሁ፡፡ ቁማሩ የሃሳብ ነው፡፡ ተጫዋቹ እና የጨዋታው ህግ ከእኔ… መጫወቻው ግን ከመጽሐፍት መደርደሪያው… የመጡ ናቸው፡፡ ጨዋታው ይቀጥላል፡፡ ከ”አልወለድም” ጐን የሰለሞን ዴሬሳ “ዘበት እለፊቱ” አለ፡፡ ዘመናዊ ጥበብ እንዲወለድ አስተዋጽኦ በማድረጉ ከአቤ ጉበኛው ጋር መቀመጡ ተገቢ መሰለኝ፡፡ አልወለድም ያለውን እንቢተኝነት “በልጅነት” ያዋለደው ዶክተር እሱ ስለሆነ፡፡ በአንድ ተርታ መቀመጥ ይችላሉ፡፡ አንዱ “ኤ” ጦር ሌላው “ኬ” ጦር ቢሆኑም፤ ንጉሱ እና ጦር መሳሪያው ከተገናኙ ጦርነት መፍጠሩ አይቀርም፡፡

በአልወለድም እና ትወለዳለህ መሐል የጥበብ ጦርነት ተከስቶ ነበር ይላሉ፤ የስነፅሁፍ ታሪክ ዘካሪዎች፡፡ ከሁለቱ ተቃራኒ ሃሳቦችን አንድ ለመምረጥ ሶስተኛ ሀሳብ ያስፈልጋል፡፡ ሶስተኛው የለም፡፡ ከሁለቱ መፅሐፍት በመቀጠል በሼልፌ ላይ ተደርድሮ ያገኘሁት የደስቲዮቪስኪ “crime and punishment” የተባለው ገናና ድርሰት ነው፡፡ በ”አልወለድም” መፅሐፍ እና በ”ልጅነት” መሃል ለተፈጠረው የጥበብ አቋም ግጭት ማን ወንጀለኛ እንደሆነ ማወቅ ካልተቻለ እንዴት “ወንጀለኛውን መቅጣት” ይቻላል?... ዘመነኛ መፅሃፍ “የመኝታ ቤት ሚስጥር” በሚል አርዕስት ስፍራውን ይዞ ተሸጉጧል፡፡ ከዚህ መፅሃፍ ጋር የሚሄድ ነገር መፈለግ እንዳለብኝ አመንኩ፡፡ የመኝታ ቤት ሚስጥር የሚያጋልጠው ምንድነው? ብዬ የመፅሃፍቱን ጠርዝ በዓይኔ እንደ ፒያኖ መምታት ጀመርኩ፡፡ ትክክለኛ ድምፅ በሌላ ረድፍ ላይ መፅሐፍን ተመስሎ አገኘሁ፡፡ የመኝታ ቤትን ሚስጥር የሚያጋልጥ “big brother” ነው፡፡ ቢግ ብራዘር የሚለውን መፅሃፍ ያነሳሁት ከአባቴ ሼልፍ ነበር፡፡ የመኝታ ቤትን ሚስጥር የሚገልፀውም ሆነ የሚያደንቀው ቢግ ብራዘር ነው፡፡ ጎን ለጎን አስደግፍኳቸው፡፡ የናዚ ወንጀለኞችን የከሰሰው የኑረንበርግን ፍርድ ሂደት የሚያትት “the “Nuremburg Trial” ከሚለው መፅሃፍ ጎን ብደረድረው “ትሪስ” የሚሰራ… የመፅሀፍ ካርታ በዓይኔ ማሰስ ነበረብኝ፡፡ “ኢህአዴግን እከስሳለሁ” የሚል መፅሃፍ ገዝቼ እንደነበር ትዝ አለኝ፡፡ ሁለቱን አንድ ላይ ለማስቀመጥ ግን ደበረኝ፡፡ አይመጣጠኑም፡፡

በክስም በክስ አወቃቀርም፡፡ በገፅም፡፡ የማይረባ ክስ የያዘው መፅሃፍ፣ የረባ የገፅ ብዛት አለው፡፡ እና ተገላቢጦሽ፡፡ የናዚ ወንጀለኞችን የፍርድ ሂደት ከሚዘግበው መፅሃፍ ጎን የገስጥ ተጫኔን “ነበር” መደርደር የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የተሻለ ካርታ ከወጣልኝ አደራደሬን መለወጥ እችላለሁ፡፡ “ነበር” የሚለውን መፅሃፍ የሚመስሉ ብዙ “ነበረኝነትን” የሚተርኩ መፅሐፍት አየሁ፡፡ ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ፣ትግላችን፣ አጥፍቶ መጥፋት፣ የደራሲው ማስታወሻ…፣… የተደጋገመ ካርታ (ዶፒዮ) ይመስላሉ፡፡ … ብከምራቸው ሰማይ የሚነካ ማማ አክለው (tower in the sky) ሳይቆለሉ አይቀሩም፡፡ “ነበር”ን በየፈርጁ ከመደጋገም… “ሆኗል” የሚል አዲስ ካርታ በመፅሃፍ መልክ ብስብ ምናለበት ብዬ ፀለይኩ፡፡ ፀሎቴ “እንቅልፍ እና እድሜ” የተቀላቀለበት እንዲሆን በእውቀቱ ሥዩምን አስከተልኩት፡፡ አስገባሁት፡፡ በ“ነዋሪ አልባ ጎጆዎች” በኩል፤ አስገባሁት፡፡ በመፅሐፍ ካርታዎቼ መሃል፡፡ አስገባሁት፤ ዳግመኛ “መግባት እና መውጣት” እንዳይችል አድርጌ፡፡መፅሐፍቱ ካርታ ናቸው፡፡ እየታዩ የሚደረደሩ እንጂ የሚነበቡ አይደሉም፡፡

የሚነበቡ ቢሆን እንኳን፤ እርስ በራሳቸው ግን አይናበቡም፡፡ አይስማሙም፡፡ መፅሐፍቱ በይዘት ወይንም በቅርፅ ወይንም በገፅ ብዛት የማይለኩ፣የማይሰካኩ ከሆነ የምንመዝናቸው በኪሎ መሆን አለበት፡፡በኪሎም ቢሆን ያን ያህል ኪሎ የሚያነሳ መፅሃፍ አላየሁም፡፡ ከ16-100 ሉክ ደብተር ናቸው፡፡ እንደ ፈረንጆቹ (hard cover) ቅርፊት ያለው እንኳን ለአመል አይገኝም፡፡ በዋጋ ተመናችሁ መተማመንም ዋጋ የለውም፡፡ በኪሎ ወፍራም የሆነ መፅሐፍ ድሮ በታተመበት ወቅት የተሰጠው ዋጋ አሁን ላይ ሲታይ ቀልድ ይመስላል፡፡ ዝም ብዬ ካርታውን መጫወት ይሻለኛል፡፡ መበወዝ እና መደርደር፡፡ ተደርድሮ አልስማማ ሲል ማሰባጠር፡፡ ሲሰባጠሩ እና በአርዕስቶቻቸው አማካኝነት ሲቀባጥሩ መመልከት፡፡ ያልተናገሩትን… እንዲናገሩ ማድረግ፡፡

በውስጣቸው የያዙት ይዘት ከፍ ያለም… ዝቅ ያለም ዋጋ የለውም፡፡ ለማመዛዘኛነት አይጠቅምም፡፡ በካርታ ጨዋታው፤ ይዘትም ሆነ ቅርፅ ብዙም ሳይኖረው በሆነ ተአምር “ልብ” “ጦር” “ጦሩ” “ዳይመንድ” ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ “ልቡ” ካህሊል ጂብራን (ከሆነ) በተበወዘው አደራደር “ልቡ” “የጦርነት ጥበብ” መፍጠሪያ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ ወይንም “የጦርነት ጥበቡ” ክቡር ድንጋይ ሊሆን ይችላል፡፡ ክቡር ድንጋይ፤ ድንጋይም ሆኖ የሚከበረው በገበያ ላይ ዋጋ ስላለው ነው፡፡ እየበወዝኩ የደረደርኳቸው የመፅሐፍት ካርታዎቼ እርስ በራስ ባይስማሙም… ለቅጽበት ግን ከትርጉም አልባ የተናጠል ማንነታቸው ያለፈ የእጣ ፈንታ፣ የአጋጣሚ ትስስር እና ዝምድና የፈጠሩ ይመስላሉ፡፡ ስራ መፍታት ለፈለገ የእኔ አይነት የማጣረዝ ፍቅር ላዛለው ሰው ምናቡን በማዝናናት ሰበብ የካርታ ጨዋቶቹ ስራ ያሸክማሉ፡፡ ሰፊ ያልሆነ ስራ፡፡

Read 2750 times