Saturday, 13 July 2013 11:48

ሞት የናፈቃቸው የ99 ዓመት አዛውንት!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ለአገራቸው ነፃነት ከጣልያን ጋር የተዋጉ አርበኛ ታሪክ
ሁለት ልጆቻቸው በቀይ ሽብር ተገደሉ፡፡
ልጆቼን ልቅበር ሲሉ እስር ቤት ተወረወሩ፡፡
ሚስታቸው በሃዘን ብዛት ህይወታቸው አለፈ፡፡
አንድ የቀረቻቸው ልጅ የት እንደገባች አያውቁም፡፡
ስድስት ዓመት ታስረው ሲወጡ ቤታቸው ፈርሷል!

አቶ መኮንን ብሩ ይባላሉ - የ99 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ በወሎ ክፍለሀገር አማራ ሳይንት ውስጥ የተወለዱት አቶ መኮንን፣ አምስት መንግስት አይቻለሁ ይላሉ፡፡ በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲወር የ20 ዓመት አፍላ ወጣት እንደነበሩ የሚያስታውሱት አዛውንቱ፤ በደርግ ዘመ ሁለት ወንድ ልጆቻቸው በቀይሽብር እንደተገደሉባቸው ይናገራሉ፡፡ ይሄም ሳያንስ ግን “ሬሳቸውን ወስጄ ልቅበር” በማለታቸው በማዕከላዊ እስር ቤት ለስድስት ዓመት ታስረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚኖሩት “የወደቁትን እናንሳ” በተባለ አዛውንትን ሰብሳቢ ማህበር ውስጥ ሲሆን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ስለ ጣሊያን አርበኝነታቸው፣ ስለኖሩባቸው አምስት መንግስታትና ስለህይወታቸው ቃለምልልስ አድርጋላቸዋለች፡፡ ከ15 ዓመት በፊት የተመሰረተው “የወደቁትን እናንሳ” የተሰኘ ማህበር በበጐ ፈቃደኞች የሚደገፍ ሲሆን በአሁን ሰዓት 46 ሴትና እና 34 ወንድ አረጋዊያንን በመጠለያ፣ በምግብ፣ በህክምናና በእንክብካቤ እየደገፋቸው ይገኛል፡፡ በማህበሩ ከሚረዱት አዛውንቶች መካከል ከ25 ዓመት በላይ በመምህርነት ያገለገሉ፣ የፖሊስ ኦርኬስትራ የሙዚቃ አባል የነበሩ፣ በአርበኝነት ዘምተው የጣልያንን ወራሪ ኀይል የተፋለሙና በህግ ባለሙያነት ያገለገሉ ይገኙበታል፡፡ ለዛሬ ከ99 ዓመቱ አርበኛ አቶ መኮንን ብሩ ጋር ያደረግነውን ጨዋታ እነሆ፡፡

 በጣሊያን ወረራ ወቅት አርበኛ እንደነበሩ ሰምቻለሁ ---

እንዴታ! አምስት አመት ሙሉ ተዋግቻለሁ፡፡
እንዴት ነው የዘመቱት?
አባቴ ቀኝአማች ብሩ ሀይለኛ አርበኛ ነበሩ፡፡ በጦርነቱ ጣሊያኖች አባቴን ሲገድሉብኝ እጅግ ተቆጣሁ፣ ደሜ ፈላ፡፡ በወቅቱ የ20 ዓመት ወጣት ነበርኩ፡፡ ማቄን ጨርቄን የምለው አልነበረኝም፡፡ ጫካ ገባሁና መዋጋት ጀመርኩኝ፡፡
ከየት አካባቢ ነው ወደ ጦርነቱ የሄዱት?
የተወለድኩት ወሎ ውስጥ አማራ ሳይንት ነው፡፡ ጦርነቱን የተቀላቀልኩትም ከዚያ ሄጄ ነው፡፡
በላይ ዘለቀን ያውቁታል ይባላል፡፡ እውነት ነው?
አሳምሬ አውቀዋለሁ እንጂ እንዴት አላውቀውም!
አብራችሁ ዘምታችኋል እንዴ?
አብረን አልዘመትንም፡፡ እኔ እራያ አዘቦ፣ መሆኒ፣ ሸዋ፣ መንዝ፣ መራ ቤቴ፣ አህያ ፈጅ ዶባ እየተዘዋወርኩ ራያው ከፈለ ከተባለ የጦር መሪ ጋር ነው የተዋጋሁት፡፡ ጐበዝ የጦር መሪ ነበር፡፡ በላይ ዘለቀ ግን አባይ በረሃ ላይ ነበር፡፡ ግን ተገናኝተን እናውቃለን፡፡ በደንብ ነው የማውቀው!
ድል ካደረጋችሁ በኋላ ስለነበረው ሁኔታ ያጫውቱኝ-----
ጃንሆይ “አገርህን ለመጠበቅ በጫካ ያለህ ወደ እኔ ተሰብሰብ” ብለው ሲጣሩ፣ ከነበርኩበት ተነስቼ ከጓደኞቼ ጋር መጣሁ፡፡ እርሳቸው ውጭ አገር ከርመው መምጣታቸው ነበር፡፡ እናም አርበኛው ሁሉ በጠቅላላ አዲስ አበባ ገባና ተሰበሰበ፡፡ ጃንሆይ ጃን ሜዳ መጡ፣ በሬው ሁሉ ታረደ፣ ተደገሰ፡፡ ድግሱ ሲያልቅ እዚሁ ለትንሽ ጊዜ ቆዩ ተባልን፡፡ ግን ማንም የሰማቸው የለም፣ ሁሉም በየሀገሩ ሲበታተን እኔም አማራ ሳይንት ገባሁ፡፡
በወቅቱ ጡረታ ምናምን አልነበረም ? ከድል ስትመለሱ ማለቴ ነው---
ደሞ የዛን ጊዜ ጡረታን ማን ነገሬ ይለዋል! መሬት ሞልቷል፣ ገንዘብ ሞልቷል፣ ከብት እንዳፈር ነው፡፡ አሁን እኮ ነው ሁሉ ነገር ችግር የሆነው፡፡ እናም ዝም ብለን አገራችን ገባን፡፡
ታዲያ እንዴት አዲስ አበባ ተመለሱ?
ከተማ ልኑር ብዬ ነው የመጣሁት፡፡ ከዚያም ሚስት አገባሁ፣ ሁለት ወንድና እና አንድ ሴት ልጆች አፍርቼም በሜካኒክነት ሙያ እየሰራሁ ልጆቼን ማስተማር ጀመርኩኝ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ --- ሁለቱ ወንዶች ልጆቼ 12ኛ ክፍልን ጨረሱ፣ ደረሱልኝ ስል ተቀጠፉብኝ፡፡
እንዴት?
በቀይሽብር ጊዜ ከጨርቆስ አምጥተው ከጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አለፍ ብሎ ባለው እራስ እምሩ ቤት አጠገብ በሚገኘው ሜዳ ላይ አምጥተው ገደሏቸው፡፡ እያበድኩኝ ሄጄ የልጆቼን እሬሳ አንስቼ እቀብራለሁ ብል ተከለከልኩኝ፡፡ ከዚያም ሙግት ገጠምኩኝ፡፡ እምቢ ካልክማ አሉና --- ማዕከላዊ የሚባል ፖሊስ ጣቢያ ያለጠያቂ ለስድስት ዓመት ታሰርኩ፡፡
ባለቤትዎና ሴት ልጅዎስ?
ባለቤቴ በልጆቿ ሞት ሀዘን ገብቷት እህህ… ህ ስትል፣ እኔ እስር ቤት እያለሁ ሞተች፡፡ እናቷንና ወንድሞቿን በሞት፣ አባቷን በእስራት የተነጠቀችው ሴት ልጄ የት እንደገባች፣ ምን እንደበላት አላውቅም፡፡ በህይወት ትኑር ትሙት የማውቀው ነገር የለም፡፡ እስከዛሬም የእግር እሳቴ ናት፡፡ ስድስት አመት ታስሬ ስወጣ እንኖርበት የነበረው ቤት በመንገድ ስራ ምክንያት ፈርሶ አገኘሁት፡፡ መውደቂያ አጣሁ፣ ችግርና ቁስቁልናው ተስፋ አስቆርጦኝ ሜዳ ላይ ወደቅሁኝ፡፡ ለረጅም ጊዜ ሜዳ ላይ ዝናብና ፀሐይ ሲፈራረቅብኝ ነው የኖርኩት፡፡
አሁንስ? ወደ እዚህ ማህበር ከመጡ በኋላ ኑሮ እንዴት ነው ?
እዚህማ አለም ነው፡፡ እበላለሁ አጠጣለሁ፣ እታጠባለሁ፡፡ ሁሉም ነገር ጥሩ ነው፡፡ በደንብ ይንከባከቡኛል፡፡
አሁን እርግጠኛ 99 ዓመት ሞልቶዎታል?
እንዴ ምን ትላለች! ጣሊያን ሲወረን 20 አመቴ ነው እያልኩሽ! አምስት መንግስት አይቻለሁ እኮ ነው የምልሽ፡፡
አምስት መንግስት ሲሉ--- ከምኒልክ ጀምሮ ነው?
ከዘውዲቱ ጀምሬ አለሁ፡፡ ንግስት ዘውዲቱን አውቃታለሁ፡፡ የስፌት ባርኔጣ ነበር የምታደርገው፡፡ በጣም አደገኛ ሴት ነበረች፡፡
አደገኛ ናት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አይ የዛሬ ልጆች! በቃ አደገኛ ናት አልኩሽ አደገኛ ናት፡፡
አምስት አመት ሲዋጉ በጥይት ተመተው ያውቃሉ?
አንድም ቀን አልተመታሁም፡፡ ጥይቱ በግራ በቀኝ ሲያፏጭብኝ አንድም ቀን ተመትቼ አላውቅም፡፡
ኃይለኛ ውጊያ ውስጥ አልነበሩም ማለት ነው? እንዴት ሳይመቱ ቀሩ?
እኔ ምን አውቃለሁ፡፡ እየነገርኩሽ --- በደረቴ ላይ እየሄደ አይመታኝም ነበር፣ ይስተኛል፡፡ ምክንያቱን ግን አላውቀውም፡፡
እርስዎስ ይስታሉ ወይስ አልሞ ተኳሽ ነበሩ ?
ኧረረረ…ስለኔ አልሞ ተኳሽነት ጓደኞቼ በነገሩሽ እንዴት ጥሩ ነበር! (ከንፈራቸውን በተረፉት ጥርሶቻቸው እየነከሱ) ስሜ መኮንን ብሩ ነው ብዬሻለሁ፡፡ በኋላ ጓደኞቼ ቃኘው መኮንን የሚል ስም አወጡልኝ፡፡ ለምን አወጡልህ ብትይኝ --- ጦርነት ከመጣ ወደ ፊት መሄድ እንጂ ድል አርገናል ብዬ ወደ ኋላ አልመለስም፡፡ በቃ ወደ ፊት መግፋት ነው፡፡ ጥይቱ እየተንፏፏ እንኳን ቢሆን ዝም ብዬ እሄዳለሁ፡፡
ካዩዋቸው መንግስታት ጥሩ ነው፣ አስደስቶኛል የሚሉት የትኛው ነው?
እሱን አትጠይቂኝ! (በኃይለቃል) ይህን ቢያወሩት ምን ይሠራል! በቃ ወደ ሌላ ጨዋታ --- ወሬ ታለሽ!
አብዛኛዎቹ እርስዎ ያሉበት ክፍል ውስጥ ያሉት አረጋዊያን ራሳቸውን ችለው አይንቀሳቀሱም ፡፡ እርስዎ ግን ብቻዎን ይንቀሳቀሳሉ ---
እንዲህ ናትና--- በደንብ ነዋ! (ከተቀመጡበት አልጋ ላይ ተስፈንጥረው ወረዱ) አታይም እንዴ! ገና ጐረምሳ እኮ ነኝ! እንዴት ትቀልዳለች ይቺ ልጅ!
ድሮ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ስትዋጉ ፉከራ፣ ሽለላና ቀረርቶ በሽበሽ ነበር፡፡ አሁን ካስታወሱት እስኪ ትንሽ ይፎክሩልኝ ----
ምን እባክሽ ---- ፉከራና ቀረርቶ ሞልቷል፡፡ ግን አሁን ምን ያደርግልኛል? ጉሮሮዬ ገጥሟል-- ሰውንም መረበሽ ነው--- ይቅር
ለእርጅና እጅ አልሰጥም--- ጐረምሳ ነኝ አላሉም እንዴ?
ታዲያ ያልኩ እንደሆነሳ! በቃ ፉከራና ሽለላ አሁን ይቅር ነው ያልኩት---የተኙትን ሰዎች እረብሻለሁ፡፡ ጉሮሮዬም ትንሽ ችግር አለው፡፡
ከዚህ በኋላ ስንት ዓመት መኖር ይፈልጋሉ?
አሁን ሞት መጥቶ ቢወስደኝ ደስታውን አልችለውም፡፡
ለምን?
ተይ የኔ ልጅ--- ከዚህ በላይ መኖር አይረባም፡፡ ምንም እንኳን አሁን የጎደለብኝ ነገር ባይኖርም እሰው እጅ ላይ ወድቆ አንሱኝ ጣሉኝ ማለት ትንሽ ደስ አይልም፡፡ እንዲሁ ቅልጥፍ እንዳልኩ ብሄድ ደስ ይለኛል፡፡
ግን ለምን ተስፋ ቆረጡ?
በቃ ቆርጫለሁ፡፡ ሞት ግን እኔን አልፈልግም አለ፡፡ መሬት ላይ ወድቄ እንዲህ እንደማያቸው ሰዎች (እርሳቸው ክፍል ውስጥ ያሉትን ተረጂዎች ማለታቸው ነው) ሳልሆን ብሞት ብዬ ፈጣሪን ብለምነው እምቢ አለ፡፡ ከዚህ በላይ ምን እንደምሠራለት አላውቅም፡፡ በቃ ሰው ራሱን እንደቻለ ነው መሞት ያለበት፡፡

 

Read 7238 times Last modified on Monday, 15 July 2013 13:02