Saturday, 13 July 2013 11:52

ድምፃዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ እና ስጦታው!

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ከአስራ አምስት ዓመት በፊት ወደ ሙዚቃ ሙያ የገባው ድምፃዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ፣ ባለፈው ሳምንት “ስጦታሽ” የተሰኘውን ሁለተኛ አልበሙን ለአድማጭ ጆሮ አድርሷል፡፡ “ስቅ አለኝ” በተባለው የመጀመርያ ስራው ከህዝብ ጋር የተዋወቀው አርቲስቱ፤ እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው “ኮራ” የሙዚቃ ውድድር ላይ እጩ ሆኖ ለመመረጥ በቅቷል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው በአዲሱ አልበሙና በሙዚቃ ህይወቱ ዙሪያ አነጋግራዋለች፡፡

ስቱዲዮ በሄድኩ ቁጥር መብራት እየጠፋ ያስቸግረን ነበር
ስታይላችን ቢቀራረብም እኔም ራሴን ነኝ፣ ቴዲም ራሱን ነው
ፎቶውን ያነሳኝ አንቶኒዮ ፊዮሬቴ ነው፤ ተሰቅሎ ሳየው ደስ ብሎኛል

 አዲሱ አልበምህ ገበያው እንዴት ነው? 

የአገር ውስጥ ሽያጩን በተመለከተ አልበሙን አሣትሞ የሚያከፋፍለው ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ነው፡፡ ባለቤቱ እንደነገሩኝ የመጀመሪያው ሕትመት ወዲያውኑ በመጠናቀቁ ሁለተኛውን አሣትመው ከስር ከስር እያከፋፈሉ ነው፡፡
የመጀመሪያው እትም ምን ያህል ቅጂ ነበር?
25 ሺህ ቅጂ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ያለው ግን ከስር ከስር ስለሚሰራጭ ምን ያህል እንደታተመ የተጣራ መረጃ የለኝም፡፡
አልበምህ በወጣ በሦስተኛው ቀን በአዟሪዎች እጅ አልነበረም፡፡ እጥረት መፈጠሩ ጉዳት የለውም?
እጥረቱ የተከሰተው ለአንድ ቀን ቢሆንም ጉዳት ይኖረዋል፡፡ ይህን ያህል ጊዜ አልበሜን ለመስማት የጓጓው አድማጭ ሊገዛ ፈልጎ ገበያ ላይ በማጣቱ የመጀመሪያው ተጎጂ እኔ ነኝ፡፡ አሣታሚው የመጀመሪያውን ሕትመት ቁጥር ሲወስን በሦስት ቀን ውስጥ ያልቃል ብሎ አልገመተም፡፡ የሆኖ ሆኖ አሁን ችግሩ የተስተካከለ ይመስለኛል፡፡ የታተመው ከስር ከስር እየተሰራጨ ነው፡፡ እኔም ገበያው እንዲህ በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
ማስተሩን ለኤሌክትራ ለመሸጥ ተዋውለህ የቅድሚያ ክፍያ የተቀበልከው ከስድስት ዓመት በፊት መሆኑን ሰምቻለሁ…
የመጀመሪያ አልበሜ አሣታሚና አከፋፋይ ዜድ ሙዚቃ ቤት ነው፡፡ አልበሙ በጣም በመወደዱ ውጭ አገር ኮንሰርት እንዳቀርብ ብዙ ግብዣዎች እየመጡልኝ ነበረኝ፡፡ አልበሜ በወጣ በዓመቱ ከረጅም የኮንሰርት ጉዞ ስመለስ ደግሞ የኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ተሾመ ጸጋዬ ጠርቶኝ፣ ያለምንም የጊዜ ገደብ ሁለተኛ አልበሜን ሠርቼ ማስተሩን እንድሰጠው የቅድምያ ክፍል ከፈለኝ። አልበሙ ቢዘገይም የወጣው ግን በዚህ ውል መሠረት ነው፡፡
ከሰባት ዓመት በፊት የተዋዋልክበት ክፍያ ከአሁኑ ጊዜ አንፃር አነስተኛ በመሆኑ ውልህን አፍርሰህ ሌላ ውል እንድትገባ ጥያቄዎች ቀርበውልህ እንደነበርና አንተም ፈቃደኛ እንዳልነበርክ መረጃ ደርሶኛል፡፡ ከቀድሞ ውልህ ከፍ ያለ ክፍያ አግኝተህ ነበር?
እንዳልሽው ውሉን ከፈጸምኩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እንደሚታሰበው የሚያረካ ባይሆንም የሙዚቃ ኢንዱስትሪው አካባቢ ትንንሽ ለውጦች አሉ፡፡ በተጨማሪም በዛን ግዜ የነበረው የገንዘብ መጠን ከአሁኑ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የተሻለ የሚባሉ ክፍያዎችን የያዙ ጥያቄዎች ቀርበውልኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ቃል ከገንዘብ የላቀ ዋጋ ስላለው ውል ለማፍረስ አልፈለግሁም፡፡ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ደግሞ የማስታወቂያ ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ወጪ በሙሉ ስፖንሰር በማድረግ ደግፎኛል፡፡ ለዚህም በጣም ላመሰግነው እፈልጋለሁ፡፡
ሁለተኛውን አልበም ለማውጣት ብዙ የዘገየህ ትመስላለህ …
በትክክል ሥራ የጀመርኩት የመጀመሪያውን አልበም ካወጣሁ ከሁለት ዓመት በኋላ ነው- የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ፡፡ የመዘግየቴ ምክንያት ደግሞ ሁሌም አዲስ ነገር ለማውጣት ከመጓጓትና በምሠራው ሥራ ካለመርካት የመነጨ ነው፡፡ የተለያየ ዜማና ግጥም እመርጥና ወድጄው ሠርቼ አስቀምጠዋለሁ፡፡ ሌላ ሠርቼ ደግሞ የቀደመውን መልሼ ሳዳምጠው አላስደስት ይለኛል፤ እንደገና ፈርሶ ሌላ ይሠራል፡፡ እኔ ጥቂት ድርሻ ቢኖረኝም ይህ ሁሉ የሚሆነው ከተለያዩ ዜማ እና ግጥም ደራሲዎች ጋር ነበር፡፡ ይልማ ገ/አብ፣ ሞገስ ተካ፣ቴዲ አፍሮ፣ ጌትሽ ማሞ፣ አለማየሁ ደመቀ፣ ብስራት ጋረደው፣ መሰለ ጌታሁን፣ ታደሰ ገለታ፣ አማኑኤል ይልማና ጌቱ ኦማሂሬ --- በአጠቃላይ አሥር የግጥማና የዜማ ደራሲያን በአልበሙ ላይ ተሳትፈዋል። የጠቀስኳቸው በአልበሙ ላይ አሻራቸውን ያሳረፉትን ነው፡፡ ሠርተውልኝ ያላካተትኳቸው ደግሞ በርካታ ናቸው፡፡ ሃያ አምስት ዘፈን ሠርቼ ነው አሥራ አምስቱን የመረጥኩት፡፡
አልበሙን ሠርቼ ካጠናቀቅሁ በኋላም በቅጂ መብት መከበር ዙርያ ችግር ነበር፣ በዚህ ሳቢያም በአሣታሚዎች ላይ የተፈጠረው ስጋት ቀላል የማይባለውን ጊዜ ወስዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዛሬ ስድስት ዓመት ከሁለት ጓደኞቼ ጋር በከፈትነው “ፋራናይት ናይት ክለብ” ሙሉ ለሙሉ የአስተዳደሩን ሥራ የምሠራው እኔ ነኝ፡፡ በዚህ የተነሳም የጊዜ እጥረት ነበረብኝ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ለአልበሙ መዘግየት ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሌላው መታወቅ ያለበት ሙዚቃ የስሜት ሥራ ነው - የተመቻቸ ጊዜና ቦታ ይፈልጋል፡፡ ምቹ ጊዜ እና ቦታ ማግኘት ደግሞ ራሱን የቻለ ሥራ ነው፡፡ በዚህ በዚህ ነው የዘገየው፡፡
በአልበም ሥራህ ከሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር የነበረህ የሥራ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ሥራው አድካሚ፣አስደሳችና አስጨናቂም ነበር። ከባለሞያዎቹ ጋር የነበረኝ ግንኙነት የሥራ ብቻ ሳይሆን የጓደኝነትም ጭምር ቢሆንም ይመሩን የነበሩት የሚፈጠሩት ስሜቶች ናቸው፡፡ አልመጣ ሲለን ድካምና መሰላቸት ይኖራል፡፡ ጥሩ ስንሠራ ደግሞ ደስታና ጨዋታው አለ፤ በቃ በጣም ደስ የሚል ጊዜ እናሳልፋለን፡፡ በተሠራው ስራ ሳንግባባ ስንቀር ደግሞ ልዩነቶች ይፈጠራሉ፤ እንጣላለን፤ ለሌላ ጊዜ እንቀጣጠራለን፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ ለምሳሌ አንድ ሰሞን አበጋዝ በሰጠኝ የጊዜ ሰሌዳ ሥራውን ለመሥራት ጓጉቼ ስመላለስ፣ እኔ እግሬ ስቱዲዮ በረገጠ ቁጥር መብራት ይጠፋ ነበር። ጠብቄ ጠብቄ ወደ ቤቴ ስመለስና ልክ እቤት ስገባ ይመጣል። አንዳንድ ግዜ ደግሞ ተመልሼ ልክ መንገድ ስጀምር መጣ ይባላል፡፡ ይህ በጣም አብሻቂ እና አስጨናቂ ጊዜ ነበር፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ ስሜቶች ጋር በመጨረሻ በፍቅር ሠርተን አጠናቀናል፡፡ ሁሉም ባለሞያዎች ጎበዞችና ጥሩ ባህሪ ያላቸው ነበሩ፡፡
የአድማጩ ምላሽ ምን ይመስላል?
እንግዲህ ከወጣ ገና አንድ ሣምንቱ ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የበርካታ ሰዎችን አስተያየት ማግኘት ባይቻልም ከዘመድ ጓደኞቼ፣ከአድናቂዎቼ፣ከአድማጮቼና ከፌስቡክ ጓደኞቼ ከተሰጡኝ አስተያየቶች፣ እንደ ዩቱዩብና ድሬ ቱዩብ ባሉ የምስል ማሳያ ዌብሳይቶች ላይ ከተጻፉ አስተያየቶች እንዳነበብኩት ከሆነ፣ እስካሁን ጥሩ አስተያየት እየተሰጠኝ ነው፡፡ በግጥምና ዜማ እንዲሁም በቅንብሩ ‹‹ጥሩ ነው የሰራኸው›› ተብያለሁ። በድምፅም እድገት አሳይተሃል ብለውኛል፡፡ እስከ አሁን ያለው የሚያበረታታ ቢሆንም ትክክለኛውን አስተያየት ለማግኘት አልበሙ በደንብ እስኪሰማ በቂ ጊዜ ሰጥቶ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
“የሸዋንዳኝ ድምፅ ውስጥ የቴዲ አፍሮን ድምፅ ማድመጥ ይቻላል” የሚሉ አድማጮች አሉ፤ አንተ ምን ትላለህ?
እኔ እና ቴዲ በሥራ ብቻ ሳይሆን የልብ ጓደኞችም ነን፡፡ ሥራዎችን የምንሰራው ተማክረን ነው፡፡ የቴዲን የግጥምና ዜማ ችሎታ እኔ መናገር ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ በተለይ በመጀመሪያው አልበሜ ከጓደኝነትም ባሻገር ዘጠና በመቶ የሚሆነውን የግጥምና ዜማ ሥራ ሠርቶልኛል፡፡ በሁለተኛው አልበሜም ተሳትፎው እንደ መጀመሪያውም ባይሆንም ቆንጆ የሚባሉ ሥራዎችን ሰጥቶኛል፡፡
እኔና ቴዲ ስታይላችን ተቀራራቢ ነው እንጂ እኔም እራሴን ነኝ ቴዲም ራሱን ነው፡፡ እንዳልኩሽ በመጀመሪያው አልበሜ ላይ ቴዲ በርካታ ግጥምና ዜማ ስለሰጠኝ ሥራዎቼ በእርሱ ዓይን የመታየት ዕድላቸው ሰፊ ነበር፡፡ ለዚህ ነው እንደዚህ ዓይነት አስተያየት የሚሰጠው፡፡ በአዲሱ አልበሜ ከተለያዩ ደራሲዎች ዜማና ግጥም በመውሰድ ስሎው፣ ቺክቺካ፣ ሮክ፣ ሬጌ---የተካተቱበት አዳዲስ ስታይሎችን ሞክሬያለሁ፡፡ ወደ አማርኛ ሥራም የበለጠ ተጠግቻለሁ፡፡
አድማጭ ብትሆን ከአዲሱ አልበም ደጋግመህ ማድመጥ የምትመርጠው የትኛውን ዘፈን ነው?
ሁሉንም (ሳቅ) ለምሳሌ በጣም በተጣበበ ጊዜ ውስጥ ሁለት ዘፈኖች ብቻ ይከፈትልህ ከተባልኩ--- ከስራዎቼ ውስጥ ‹‹ስጦታሽ›› እና ‹‹ስለኔ››ን ልመርጥ እችላለሁ፡፡
ለአልበምህ ማስተዋወቂያ ከተማ ውስጥ የተሰቀለውን ቢልቦርድ ሰዎች ሲያደንቁት ሰምቻለሁ…
ባይገርምሽ ከብዙ የፎቶግራፍ ድካም በኋላ በአጋጣሚ የተገኘ ፎቶ ነው፡፡ ፎቶውን ያነሳኝ አንቶኒዮ ፊዮሬቴ ነው፡፡ ዲዛይኑ ‹‹ላይቭ ዲዛይን›› የሚባል ነው፡፡ ተሰቅሎ ሳየው ለእኔም ደስ ብሎኛል።
ለሙዚቃህ የቪዲዮ ክሊፖች አልሠራህም..
‹‹ስጦታሽ›› ለሚለው ዘፈን የቪዲዮ ክሊፕ ተሠርቶ ተጠናቋል፡፡ የሁለት ወይም የሦስት ዘፈኖች ቪዲዮ ክሊፖች ደግሞ በቅርቡ ተሰርቶ ይለቀቃል፡፡
ከአልበም ሥራዎች ውጭ ኮንሰርቶች የት አቅርበሃል..
የውጭ ጉዞ የጀመርኩት የመጀመሪያውን አልበም ከማውጣቴ ቀደም ብሎ ነው፡፡ ሙዚቃ ስጀምር የእንግሊዘኛ ዘፈን እና ጥቂት አማርኛ እጫወት ስለነበር ከአገር ውስጥ የመድረክ ሥራዎች በተጨማሪ ጣልያን፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ እና ዱባይ ተጉዤ ሠርቻለሁ፡፡ አልበሙ ከወጣ በኋላም በአገር ውስጥ የተለያዩ የመድረክ ሥራዎችን አቅርቤአለሁ። ከኢትዮጵያ ውጪ ደግሞ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ባህሬን፣ ዱባይ፣ አቡዳቢ፣ እስራኤል፣ ስዊድን፣ እንግሊዝ፣ ኖርዌይ፣ ሆላንድ እንዲሁም በአሜሪካ ከአሥራ ሁለት ግዛቶች በላይ እና በሌሎች አገሮች በተደጋጋሚ ለኮንሰርት እየተጋበዝኩ ሠርቻለሁ፡፡ “ፋራናይት”ን ከከፈትኩ በኋላም በየሣምንቱ ሐሙስ እየተጫወትኩ ነው፡፡
ናይት ክለብ የምትጫወተው የራስህን ሥራዎች ብቻ ነው?
አይደለም፡፡ ከራሴ አልበም ውጪ በዋናነት የአርቲስት መሐሙድ አህመድን፣ የአርቲስት ንዋይ ደበበን፣ የአርቲስት ጌታቸው ካሣና ሌሎች ዘፋኞችን ሥራዎችም እጫወታለሁ፡፡
የዩኒቨርስቲ ትምሕርትህን አቋርጠህ ነው ወደ ሙዚቃ የገባኸው፡፡ ቤተሰብ አልተቃወመም?
ስሜቴ ወደ ሙዚቃ የተሳበው አስረኛ ክፍል ስደርስ ነበር፡፡ ያን ግዜ አሁን በሕይወት የሌለው አባቴ ከፍቶት ነበር፡፡ ዩኒቨርስቲ ስገባ ግን ዶርም ውስጥ አድር ስለነበር ነገሮች ምቹ ሆኑልኝ፡፡ እየተደበቅሁ በመውጣት ሙዚቃውን ገፋሁበት። እንዲህ እንደማደርግ አባቴ ባወቀ ጊዜም ደስተኛ አልነበረም፤ ሊደግፈኝም ፈቃደኛ አልሆነም። በመጨረሻ ቆርጬ ወደ ሙዚቃው መግባቴን ሲያውቅ ግን ምንም ሊለኝ አልቻለም፡፡
አዲሱ አልበም ከወጣ በኋላ የውጭ ኮንሰርቶች ግብዣ አልመጣልህም?
ውጭ አገር ከሚገኙ ፕሮሞተሮች ጋር ትውውቁም ጓደኝነቱም ስላለን ገና አልበሙን እንዳገኙ ነው መደወል የጀመሩት፡፡ በእኔ በኩል ግን ኮንሠርት ለመሥራት አልበሙ በደንብ መሰማቱን እና መወደዱን ማረጋገጥ አለብኝ፡፡
አሁን ደግሞ የሙስሊም ፆም ገብቷል (በዚህ አጋጣሚ ለእስልምና እምነት ተከታዮችና ለጓደኞቼ መልካም የፆም ጊዜ እመኛለሁ) ፆሙ ሲወጣ የአዲሱ አልበም ምርቃት ይኖረኛል፡፡ ኮንሠርት የመሥራት ዕቅዴም ከዚያ በኋላ የሚወሰን ይሆናል፡፡
ቤተሰብ አልመሰረትክም፤ ትዳርን ፈራኸው እንዴ?
ኧረ አልፈራሁም! አሁን የምር እያሰብኩበት ነው፡፡ በቅርብ አዲስ ነገር ይኖራል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

Read 5253 times