Saturday, 13 July 2013 12:02

‹‹...የጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት ለእድሜልክ...››

Written by 
Rate this item
(3 votes)

• እናቶች ለእርግዝና ክትትል ወደጤና ተቋም በሚቀርቡበት ጊዜ ተመርምረው ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ከሆኑ ወዲያውኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መድሀኒቱን አንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ • ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ይበልጥ የሚመረጠው እናቶቹ የእድሜ ልክ የጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደልጅ እንዳይተለሰለፍ ለመታደግ ሲባል የአለምአቀፉ የጤና ድርጅትን ጨምሮ በየአህጉሩ ያሉ ብሔራዊ ተቋማት እና ሌሎች አለምአቀፋዊ ድርጅቶችን ጨምሮ የተለያዩ ጥረቶች መደረግ ከጀመረ ሰንበትበት ብሎአል፡፡ የሚወለዱ ሕጻናት ከእናቶ ቻቸው የኤችአይቪ ቫይረስን እንዳይወስዱ ለማድረግ የሚያስችሉ ግኝ ቶች እና አሰራሮች በመዘርጋታቸው ከቫይረሱ ነጻ የሆኑ ሕጻናትን ማዋለድ ተችሎአል፡፡ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈው የቫይረሱ ስርጭት በእርግዝና ፣በምጥ ፣በመው ለድ ወይንም ጡት በማጥባት ሲሆን ስርጭቱም ከ25-45 % የሰፋ ነው፡፡

የኤችአይቪ ቫይረስን ስርጭት ለመግታት አስቸኩዋይ እቅድ የማወጣት ፕሮግራም ወይንም ደግሞ pepfar (ፔፕፋር) ተብሎ የሚጠራው ሰፊ ፕሮግራም ባወጣው መረጃ መሰረት የዛሬ አራት አመት ገደማ በአለም ላይ ወደ 390,000- (ሶስት መቶ ዘጠና ሺህ) የሚጠጉ ህጻናት ከቫይረሱ ጋር ተወል ደዋል፡፡ ከእነዚህ ህጻናት ውስጥ 90 % የሚ ሆኑት ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራትን ጨምሮ በ22/ ሀገሮች ውስጥ የተወለዱ ናቸው፡፡ ባደጉት ሀገሮች ውስጥ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈው የቫይረሱ ስርጭት ሙሉ ለሙሉ ተገትቶአል ማለት የሚያስችለው የ pepfar ጥናት በእርግዝና ጊዜ የጸረ ኤች አይቪ መድሀኒትን ትክለኛ የሆነ አጠቃቀምና ከወሊድ በሁዋላ ጡት ባለማጥባት ቀጥተኛ የሆነውን የቫይረሱን ስርጭት እስከ 5 % ድረስ መቀነስ ይቻላል ብሎአል፡፡ pepfar የዛሬ ሶስት አመት ባደረገው ዘመቻ መሰረት 9.8/ ሚሊዮን የሚሆኑ እር ጉዝ ሴቶች የኤችአይቪ ምርመራ እንዲያደርጉ ከእነዚያ ውስጥ 660,000/ያህሉ ቫይረሱ በደማ ቸው ተገኝቶ ነበር፡፡ እነዚህ እናቶች ቫይረሱን ወደልጆቻቸው እንዳያስተላልፉ ሲባል ART የጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት እንዲወስዱ ተደርጎአል፡፡

ይህ በመሆኑ ከ200,000/ (ሁለት መቶ ሺህ .. በላይ የሆኑ ሕጻናት ከኤችአይቪ ነጻ ሆነው እንዲወለዱ እድሉ ተፈጥሮአል፡፡ ከእናታቸው በቀጥታ ቫይረሱን የተቀበሉ ሕጻናት በሕይወት የሚቆዩት ቢበዛ እስከ ሁለት አመት እድሜያቸው ድረስ ነው፡፡ ከኤድስ ነጻ የሆነ ትውልድን ለማፍራት የሚደረገው እርብርብ አ.ኤ.አ በ2015/ ለታቀደው የሚሊኒየም ግብ 90% የሚሆነውን ከእናት ወደልጅ የሚተላለፈውን የቫይረሱን ስርጭት ይገታል የሚል ተስፋ አለ፡፡ ሕጻናት የኤችአይቪ ቫይረስን ከእናታቸው እንዳይወርሱ ከሚያስችለው አለምአቀ ፋዊ ጥረት መካከል እርጉዝ የሆኑ እናቶች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ከተገኘ በቀጥታ የጸረ ኤችአይቪ መድሀኒቱን እንዲወስዱ ማድረግ ይገኝበታል፡፡ ይህም በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በተግባር ላይ እንዲውል የሚያስችል አሰራር የተዘረጋ ሲሆን ይህንን በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡን የጋበዝነው ዶ/ር ታደሰ ከተማ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች ጤና አማካሪ ናቸው፡፡ ዶ/ር ታደሰ እንደሚገልጹት በኢትዮጵያ ላለፉት አስር አመታት በላይ ኤችአይቪ ከእናቶች ወደ ልጆች እንዳይተላለፍ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር በተግባር ውሎአል፡፡ አሰራሩን አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለመለወጥና ከኤችአይቪ ነጻ የሆነ ትውልድ ለማፍራት እንዲያስችል የተለየ አገልግሎት በየጤና ተቋማቱ እንዲሰጥ በመደረግ ላይ ነው፡፡ ይህ አገልግሎትም ከአሁን ቀደም ቫይረሱ ያለባቸውን እርጉዝ ሴቶች በመለየት ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ጸረኤችአይቪ መድሀኒት ይሰጥ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን የጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት ለእድሜልክ እንዲሆን ተወስኖአል፡፡

የዚህ አላማም ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ከማድረግ ባሻገር እናት ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ሌሎች ሕመሞችን እንዳትታመም እና የእራስዋን ጤንነት ለመጠበቅ እንዲያስችላት ነው፡፡ስለዚህም እናቶች ለእርግዝና ክትትል ወደጤና ተቋም በሚቀርቡበት ጊዜ ተመርምረው ፖዘቲቭ የሆኑት ወዲያውኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መድሀኒቱን አንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ እርጉዝ ሴቶችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች በደማቸው ኤችአይቪ ቫይረስ የሚገኝ ከሆነ የሰውነታቸው የመከላል አቅም እና በሰዎቹ ላይ የተከሰተውን የተለያየ ሕመም መሰረት በማድረግ ቫይረሱ ያለበት ደረጃ ከታየ በሁዋላ ጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት መውሰድ የሚገባቸውንና የማይገባቸውን በመለየት መድሀኒቱ ይሰጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን ግን እናቶቹ የሰውነት የመከላከል አቅማቸው ያለበት ደረጃ በምርመራ እንዲታወቅ የሚደረግ ሲሆን ያ የሚደረገው ግን ፀረ ኤችአይቪ መድሀኒቱን ለመጀመር ሳይሆን የጤንነታቸው ሁኔታ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ እና ክትትሉን ለማድረግ እንዲያስችል ሲባል ነው፡፡ ፀረ ኤችአ ይቪ መድሀኒትን ቀድሞ መጀመር ከኤችአይቪ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የተለያዩ በሽታዎችን እንዳይኖሩ ከማድረግ በተጨማሪ እናቶቹ ለረጅም ጊዜ ጤንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ፣የሚወልዱዋቸው ሕጻናትም ከቫይረሱ ነጻ ሆነው እንዲወለዱ ይረዳቸዋል፡፡ ዶ/ር ታደሰ ከተማ እንደገለጹት እናቶች የእድሜ ልክ የጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርገው አሰራር ኤችአይቪን በተመለከተ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል በተባሉ 22/ ሀገራት ተሞክሮ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን በተለይም ማላዊ የተሳካ ልምድ ያገኘችበት ነው፡፡

የአለም የጤና ድርጅት ለእናቶች ጤና ተገቢው እና ትክክለኛው ነው በሚል እንዲተገበር ብዙ አገራትን እያማከረ እና አቅጣጫን እያስያዘ ያለበት አሰራር በመሆኑ በኢትዮጵያም ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ የሚሰጠው አገልግሎት በደረጃ ሊከፋፈል የሚችል ነው፡፡ •በእርግዝና ወቅት እናቶች የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉ ማድረግ፣ •የኤችአይቪ የምክርና የምርመራ አገልግሎት መስጠት፣ •እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ማድረግ፣ •ከኤችአይቪ ፖዘቲቭ እናቶች የተወለዱት ሕጻናት ክትትል እንዲያደርጉ ማድረግ፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እናቶች የእርግዝና ክትትል የማድረጋቸው ሁኔታ ቀደም ካሉት ጊዜያት የተሸሻለ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ወደ 20 % የነበረው የእር ግዝና ክትትል ዛሬ ወደ 80% ደርሶአል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከ35 -45 % የማያንሱ እናቶች የኤችአይቪ የምክርና የምርመራ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ በአገሪቱ በአጠቃላይ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ይሆናሉ ተብሎ ከሚገመቱት ወደ 34000/ እናቶች ውስጥ 42 % የሚሆኑት ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ከተወለዱት ልጆችም የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙ የመኖራቸውን ያህል በተለይም ቤተሰቦች ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ የሚያቋርጡ በመሆኑ እንደ አንድ ችግር የሚታይ ነው፡፡ አንዳንድ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ የሆኑ እናቶችም የህክምና ክትትላቸውን በትክክል ሳያቋርጡ የማይከታተሉ በመሆኑ በዚህ ረገድ ገና ብዙ መሰራት የሚጠበቅበት ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ ምንም እንኩዋን ከነበረበት ሁኔታ የተሸሻለ ነገር ይታያል ቢባልም በአጠቃላይ አላማው ከቫይረሱ ነጻ የሆኑ ልጆችን ማዋለድ ሲሆን ይህንን ግን በትክክል ለማወቅ የሚያስችል አካሄድ እስከአሁን ማግኘት አልተቻለም፡፡ እ.ኤ.አ በ2011/ የተሰራ አገር አቀፍ ጥናት እንደሚጠቁመው በኢትዮጵያ ውስጥ ቀደም ሲል የነበረው የቫይረስ ስርጭት እየቀነሰ መምጣቱን ያመላክታል፡፡

በዚህም ጥናት መሰረት ቀደም ሲል ወደ 3% የነበረው አሁን 1.5% በሚል ሊጠቀስ እንደሚችል ጥናቱ ያሳያል፡፡ ቀደም ሲል ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱ እናቶች ቁጥር ወደ 80,000/ እና 90,000/ ገደማ የነበረ ሲሆን በዚህ ጥናት የታየው ግን ከ34,000 ብዙም የማይበልጡ እናቶች ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ይሆናሉ የሚል ግምት አለው፡፡ ይህም የግንዛቤ ማስጨበጥን ስራ እና በተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ ስራዎችን ውጤታማ አካሄድ የሚያ ሳይ ሲሆን እነዚህ አካላት ወደፊትም ብዙ እንዲሰሩ የሚጠበቅበት ሁኔታ መኖሩ ግልጽ ነው ብለዋል ዶ/ር ታደሰ ከተማ፡፡ በእርግዝና ክትትል ወቅት ኤችአይቪ በደማቸወ ውስጥ የተገኘባቸው እናቶች ቁጥር እና ጸረ ኤችአይቪ መድሀኒትን ተጠቃሚ የሆኑት ቁጥር በፊት ከነበረበት 25% አሁን ወደ 42% ደርሶአል፡፡ ስለዚህ እናቶች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ከተገኝ የእድሜ ልክ የጸረ ኤችአይቪ መድሀኒት ተጠቃሚ ይሁኑ ሲባል ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይ ተላለፍ እና እናቶችም ጤንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ለማስቻል መሆኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ውስጥ ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ ወይም መተላለፉን ለማጥፋት እቅድ ይዘው እየሰሩ ካሉ አገሮች ውስጥ አንዱዋ ነች፡፡ ስለዚህም ይህንን አለማ እውን ከማድረግ አንጻር ይህ የጸረ ኤች አይቪ መድሀኒት ለሁሉም ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ለሆኑ እርጉዝ ሴቶች በዘለቄታዊ መንገድ መስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ዶ/ር ታደሰ ከተማ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች ጤና አማካሪ እንዳብራሩት፡፡

Read 7685 times