Print this page
Saturday, 19 November 2011 14:13

የአዛውንቱ አባት ያልታበሰ እንባ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

ከወለዷቸው 13 ልጆች መካከል አምስቱን ሞት ነጥቆአቸዋል፡፡ ተደራራቢው የልጅ ሀዘንና የኑሮ ውጣ ውረድ ያጐሳቆለው ሰውነታቸው ችግራቸውን ለመናገር አቅም አለው፡፡ በትከሻቸው ላይ ባንጠለጠሏት አሮጌ የቆዳ ቦርሣ ውስጥ ስለልጃቸው አሟሟት የቤይሩት ዶክተሮች የላኩትን መረጃ ይዘዋል፡፡ ከሚኖሩባት ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ወሬሁላ ቀበሌ እዚህ አዲስ አበባ ከተማ ለዚሁ ጉዳይ ብቻ ከስድስት ጊዜ በላይ ተመላልሰዋል፡፡ ሃያኛ ዓመቷን እንኳን በቅጡ ያልደፈነችው ልጃቸው ወደ ቤይሩት በሄደች በአምስተኛ ወሯ ከፎቅ ላይ ተወርውራ መሞቷን የሚገልፀው የሐኪም መረጃ ተቀባይና ተመልካች አጥቶ እንደታጠፈ ተቀምጧል፡፡

“በሰው አገር ሰው ሆኜ ቤተሰቦቼን እረዳለሁ” በሚል ተስፋ ከአገሯ ወጥታ በድንገትና ባልታሰበ መንገድ ህይወቷን ያጣችው ልጃቸው ደም ደመከልብ ሆኖ መቅረቱ በቁጭት አንገብግቧቸዋል፡፡ ስለልጃቸው መናገር ሲጀምሩ እምባቸው መንታ መንታውን ይወርዳል፡፡ ለደቂቃዎች ጆሮውን ሰጥቶ ችግራቸውን የሚሰማና መቋጫ ያጣውና እንባቸውን የሚያብስ ሰው ጠፍቶ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው የአዲስ አበባን ጐዳናዎች ይንከራተቱባቸዋል፡፡
የትራንስፖርቱ ዋጋ ጣሪያ መንካት፣ የማረፊያ ማጣት የልጃቸውን አሟሟት ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት አልቀነሠውም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤትን ደጃፍ ጠዋት የተቀመጡበት ምሽቱ ይገላግላቸዋል፡፡
ችግራቸውን ለመረዳት የሞከረና እምባቸውን ያበሰ አንድም ሰው አለማግኘታቸው ተስፋቸውን የበለጠ ቢያጨልመውም ዛሬም የልጃቸውን አማሟት ቁርጥ ለማወቅ ሲሉ ይንከራተታሉ፡፡
ዛሬም አድማጭ ይፈልጋሉ፡፡ በሽማግሌ ጉንጮቻቸው የሚወርደው እምባ ዛሬም አልታበሠም፡፡
እኚህ አዛውንት ልጆቻቸውን በስደት ያጡ የብዙ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ተምሳሌት ናቸው፡፡ ልናነጋግራቸው ፈልገን አገኘናቸው፡፡ ረሃቡ፣ ድካሙ፣ ሀዘኑ፣ ተስፋ ማጣቱ ሁሉ ተደራርቦ አዛውንቱን አጐሳቁሏቸዋል፡፡ መረጃ የያዘችውን የቆዳ ቦርሳ ጠበቅ አድርገው ይዘው በከዘራ እየተረዱ ቢሮአችን ደረሱ፡፡ የሟች ታላቅ ወንድም የሆነው ልጃቸው ተከትሏቸዋል፡፡
ካጠላባቸው የሀዘን ድባብ ወጥተው ታሪካቸውን እንዲያጫውቱን ለማግባባት ሰዓታት ወስዶብናል፤ በሚናገሩት ዓረፍተነገር መካከል ሁሉ እንባቸው ይወርዳል፤ ሣግ ይተናነቃቸዋል፡፡ በጡት ማስያዣና በፓንት ብቻ ሆና በሳጥን ታሽጐ የተላከላቸውን እንቡጥ ልጃቸውን አስከሬን በዓይነ ህሊናቸው እያዩ ያነባሉ፡፡ ለቃለምልልስ በተቀመጥንባቸው ሰዓታት ስሜታቸውን አጋብተውብን ሀዘናቸውን አጋርተውናል፡፡
አቶ አዳሙ ተመስገን በሚኖሩበት አካባቢ ጥሩ ስምና አክብሮት ያላቸው ገበሬ ናቸው፡፡ ልጆቻቸውን አስተምረው ለወግ ለማብቃት ህልም ቢኖራቸውም የሚኖሩበት ገጠር መሆኑና የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ መሆኑ ህልማቸውን እንዲያሳኩ እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ በዚህ ላይ አንድ ልጃቸው የአእምሮ ህመምተኛ ሆኖባቸዋል፡፡ ልጃቸውን ይዘው በየፀበሉ ቢመላለሱም ተስፋ አላገኙም፡፡
እናም ህመምተኛ ልጃቸውን አዲስ አበባ በማምጣት አማኑኤል ሆስፒታል ለማስገባት ወሰኑና ለጉዞው ተነሱ፡፡ ትንሿ ልጃቸው ወርቅነሽ አዳሙ ተከትላቸዋለች፡፡ ጊዜው ከስምንት ዓመት በፊት ሲሆን፤ የልጃቸውን ህክምና አጠናቀው ወደ ትውልድ አገራቸው ሊመለሱ ሲሉ አንድ ሃሳብ መጣላቸው፡፡ ይህቺን ትንሿን ልጃቸውን ወርቅነሽን ከዚሁ አዲስ አበባ ለዘመድ ሰጥተው እንድትማርላቸው ማድረግ ነው የመጣላቸው ሃሣብ፡፡ ይሁንና ሃሣባቸው ሃሣብ ብቻ ሆኖ አልቀሩም፡፡ ሆዳቸው እየተንቦጫቦጨም ቢሆን ልጃቸውን ለዘመድ ሰጥታው ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ተመለሱ፡፡
ከዘመድ የተጠጋችው ወርቅነሽ የአዲስ አበባን ኑሮ እየተላመደች ብትሄድም ከዘመዶቿ ጋር አለመግባባቶች እየተፈጠሩ መጡ፡፡ እናም ሰው ቤት ተቀጥራ እየሰራች ልትማር ወስና ከዘመዶቿ ቤት ወጣች፡፡ ሁኔታው አባቷን ባያስደስታቸውም ትምህርቷን አለማቋረጧ አጽናናቸው፡፡ በየዓመት በአልና በተለያዩ አጋጣሚዎች ወላጅ ቤተሠቦቿ ወደሚኖሩበት ሥፍራ እየሄደች ስትጠይቃቸውና አልፎ አልፎም ስልክ ስትደውልላቸው ተስፋቸው እያደገ ሄደ፡፡ በሰው ቤት ሥራ በመሥራት ከምታገኘው ደመወዝ አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ ብላ አታውቅም፡፡ መውለድና የልጅ ሐዘን የጐዳቸው ወላጅ እናቷም ልጄ ደረሰችልኝ የሚለው ተስፋቸው ከቀን ወደቀን እያደገ ሄደ፡፡ በዚህ መሀከል ወደቤይሩት ለመሄድ እንደወሰነችና ገንዘብ ተበድረው እንዲሰጧት ወላጆቿን ጠየቀቻቸው፤ ይሁንና ለወላጆቿ ሁኔታው አስደንጋጭ ነበር፡፡ ኑሮ ለከበዳቸውና ከእጅ ወደአፍ በሆነ የገጠር የድህነት ኑሮ ለሚኖሩት ወላጆቿ ጥያቄው ዱብእዳ ሆነባቸው፡፡
አባቷ ስለጉዳዩ በጥልቀት ጠየቋት፡፡ “ልጄ አንቺ የገጠር ልጅ ነሽ፡፡ ሊያጐበርብሩሽ (ሊያጭበረብሩሽ) ይችላሉ” ቢሏትም በጄ አላለቻቸውም፡፡ አንተ የማትሰጠኝ ከሆነ ከሌላ ሰው ተበድሬ መሄዴ አይቀርም አለቻቸው፡፡ ሃሳቧን እንደማትቀይር ሲረዱ ገንዘቡን ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመሩ፡፡ 3 በሬዎቻቸውን ሸጠው ያገኙዋትን 3800 ብር እና ከወዳጅ ዘመድ አስቸግረው ያገኟትን ገንዘብ አሰባስበው 5ሺህ ብር ለልጃቸው ሰጧት፡፡ ዕዳዋን ከመክፈል ባለፈ ለቤተሰቦቿና ለታናናሽ እህት ወንድሞቿ ተስፋ ለመሆን ጉጉቷን ሰንቃ የካቲት 1/2003 ቤሩት ገባች፡፡ መግባቷን ለቤተሰቦቿ በ3ኛው ቀን ደውላ ከመንገሯ ውጪ በስልክም በደብዳቤም ከቤተሰቦቿ አልተገናኘችም፡፡ ቤተሰቦቿ የሚኖሩት በገጠራማ አካባቢ በመሆኑ ስልክ ለማግኘት የሰዓታት ጉዞ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
አባት ግን አልታከቱም፡፡ ከቤት ውስጥ የወላጅ እናቷን ልጂ ደወለች ወይ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በየዕለቱ ወደ ከተማ እየተመላለሱ ቢጠይቁም ምንም ነገር የለም፡፡ ቀናት ሣምንታትን ሣምንታት ወራትን እያስቆጠሩ፤ ልጃቸው ከተለየቻቸው አምስተኛ ወሯ ተጠጋ፡፡ አሁንም ምንም የለም፡፡ ሰኔ 29/2003 ዓ.ም ከዚህ ከአዲስ አበባ ወደ ደራ ወረዳ ወሬ ሁላ ቀበሌ የተደወለው ስልክ ግን የልጃቸውን አለሁላችሁ ብሥራት የያዘ አልነበረም፡፡ ልጃቸው በአደጋ መሞቷንና አስከሬኗን የሚረከብ ሰው አዲስ አበባ እንዲመጣ የሚያሳስብ ነበር፡፡ እናት ሀዘናቸው ቅጥ አጣ፤ አባት ተስፋቸው ጨለመ፡፡ በማግስቱ አስከሬኑን የተረከቡት የሟች ወንድምና አጐቷ በኮንትራት መኪና ይዘው ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ተጓዙ፡፡ ፓንትና ጡት ማስያዣ ብቻ በእርቃን ገላዋ ላይ የሚታየው ወርቅነሽ የፊት ገጽታዋ እንደመበለዝ ብሏል፡፡ የአሟሟቷን ሁኔታ የሚገልፁ መረጃዎችና ልዩ ልዩ የጉዞ ሰነዶቿ ከአስከሬኗ ጋር አብሮ መጥቷል፡፡
ከዚህ ውጪ ምንም ዓይነት ንብረትና የግል ቁሳቁሶቿ አልመጡም ወይም አልነበሩም፡፡ ሁኔታው ልብ የሚሰብር ነበር፡፡ ወላጆች ልጃቸውን አጣጥበው ከቀበሩ በኋላ ከአስከሬኗ ጋር የመጡትን ሰነዶች ይዘው አባት አዲስ አበባ መጡ፡፡ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት የተጀመረው የአባትየው እንክርት በየቢሮዎቹ ቀጠለ፡፡ የሟች ጓደኛ ናት የተባለች አንዲት ሴት እና በደላላነት ይሰራ የነበረ ወጣት ከኤጀንሲው ጋር እንዲያገናኟቸው አጥብቀው ጠየቁ፡፡ ነገር ግን ማንም አልሰማቸውም፤ እኛ እንደውልልዎት ነበር እርሶ ለምን መጡ አሏቸው፡፡ ልጄ ከፎቅ ላይ ተወርውራ ህይወቷ እንዳለፈ የሚገልጽ መረጃ በእጄ ይዤ እንዴት ዝም ብዬ እቀመጣለሁ፡፡ መረጃውን አይቶ መንግስት ለመንግስት ይነጋገርበት እንጂ አሉ፡፡ ልጃቸው ለአምስት ወራት የሰራችበት ደመወዝስ የት ገባ? አባት ጠየቁ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድና ከቀናት መመላለስ በኋላ የሠራችበት ደመወዝ ነው የተባለ 10.018 ብር በአንዲት ሴት አማካኝነት ተሰጣቸው፡፡ አሠራሩ ህጋዊነት የጐደለውና ውስጥ ለውስጥ የሚከናወን መሆኑ ያልተመቻቸው አባት ለምን አሉ፡፡
ገንዘቡንስ ከህጋዊ ቦታ በህጋዊ መንገድ ያልወሰኩበት ምክንያት ምንድነው ቢሉም ሰሚ አላገኙም፡፡ ከዚህ ውጪ የምናውቀው ነገር የለም አሏቸው፡፡ የአዛውንቱ ውትወታ ያሰለቻቸው ተጠያቂዎችም ስልካቸውን አጠፉ፡፡ በቃ ሊገልፁላቸው አልቻሉም፡፡
የእምቡጥ ልጃቸው ሀዘን ከልባቸው ያልወጣው አባት “ከሞቷ ያሟሟቷ” እንዲሉ - ሞቷ ሳይሆን አሟሟቷ ይበልጥ አሳዝኖአቸው ፍትህ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል፡፡ የውጪ ጉዳይ ሚ/ር ደጃፎች ዛሬም የአዛውንቱ ማረፊያዎች ናቸው፡፡
አንዳች ውጤት ሳይዙ ወደትውልድ ቀዬአቸው መመለስን ያልደፈሩት አባት፤ የቀን ሐሩርና የሌሊት ቁሩ እየተፈራረቀባቸው ዛሬም ጐዳና ላይ ናቸው፡፡ ሀዘንና ችግር ባጐሳቆለው ፊታቸው ላይ እምባቸው መንታ መንታውን ይወርዳል፡፡ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ልጆቻቸውን ወደ አረብ አገሮች የላኩ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ወላጆችን ህይወት ይመስላሉ ያልናቸው የእኚህ አዛውንት እምባ በምን ይታበስ ይሆን? የወጣቷ ስደተኛስ አሟሟት እንዴት ይገለጽ ይሆን? … በመፅሃፍ ቅዱስ ሚኪያስ 3፡4 ላይ እንደተፃፈው እግዚአብሔር አምላክ እንባን ሁሉ ከዓይን ያብሣል ሞትን ለዘላለም ይውጣል … እንዳንል ይሄኛውና ያኛው አካሄዱ ለየቅል ነው፡፡

 

Read 3235 times Last modified on Tuesday, 22 November 2011 14:18