Saturday, 20 July 2013 09:57

የሙስና ተጠርጣሪዎች ምርመራ ለ6ኛ ጊዜ ተራዘመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

በተጠርጣሪዎች ላይ የ240 ምስክሮች ቃል ተቀብያለሁ…ፀረ ሙስና ኮሚሽን
በ5 ኩባንያዎች ላይ የተጀመረው የኦዲት ስራ እስከ ሐምሌ 30 ይጠናቀቃል
አቶ ገ/ዋህድ ከመንግሥት የተሰጣቸውን መኖሪያ ቤት በ20 ቀን እንዲያስረክቡ ታዘዋል

 በሙስና ተጠርጥረው በታሰሩ የጉምሩክና ገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊዎች ላይ ክስ ለመመስረት የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለስድስተኛ ጊዜ የምርመራ ጊዜ እንዲራዘምለት ያቀረበው ጥያቄ ከተጠርጣሪዎች በኩል ተቃውሞ ቢገጥመውም የ10 ቀን ቀጠሮ ተፈቀደለት፡፡ የጉምሩክና ገቢዎች ባለስልጣን ምክትል ዳሬክተር የነበሩት አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ከኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ የተሰጣቸውን መኖሪያ ቤት እንዲመልሱ ታዘዋል፡፡ ሰሞኑን ፍ/ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ከአቶ ገብረዋህድ ጋር በአንድ የምርመራ መዝገብ የተካተቱ 12 ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ፤ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአዳማ ቅርንጫፍ ኦፊሰር አቶ ያለው ቡለ እና የእንጀራ እናታቸው ወ/ሮ ሽቶ ነጋሽ በ13ኛ እና 14ኛ ተጠርጣሪ ሆነው እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

በተለያዩ የምርመራ መዝገቦች የተካተቱ ከ50 በላይ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ የ240 ምስክሮችን ቃል እንደተቀበለ የገለፀው የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በርካታ ሰነዶችን እንዳሰባሰበና በአምስት ኩባንያዎች ላይ ኦዲት እያካሄደ እንደሆነ ገልጿል፡፡
በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ከማቅረቤ በፊት ከተጨማሪ ምስክሮች ቃል ለመቀበል፣ ቀሪ ሰነዶችን ለማሰባሰብና የኦዲት ስራዎችን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለት ጠይቋል - ያስከስሳሉ የሚላቸውን ጭብጦችን በመጠቃቀስ፡፡ ቡድኑ ለጠቋሚ መክፈል የነበረበትን ገንዘብ አላግባብ ወስደዋል በሚል በአቶ ገ/ዋህድ እና በአቶ ጥሩነህን ላይ ባለፉት አስር ቀናት ተጨማሪ ሰነድ ሰብስቤያለሁ፣ የአምስት ምስክሮችን ቃል ተቀብያለሁ ያለው የፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል አላለም፡፡ ከቀረጥ ነፃ የገቡ መኪኖችን በሚመለከት ቀርቦ የነበረውን ክስ አላግባብ አቋርጠዋል በሚል በአቶ ገ/ዋህድ እና በሙሌ ጋሻው ላይ የአንድ ምስክር ቃል መቀበሉንና ከለገጣፎ የሰነድ ማስረጃ መሰብሰቡን ኮሚሽኑ ገልፆ፤ ከሦስት ተጨማሪ ምስክሮች ቃል ለመቀበል ጊዜ እንደሚያስፈልገው ጠቅሷል፡፡
ከውጭ የመጡ እቃዎች ሳይፈተሹ እንዲገቡ አድርገዋል ተብለው በተጠረጠሩት በአቶ ገ/ዋህድ፣ አቶ ነጋ፣ አቶ ሙሌ እና አቶ አሞኘ ላይ ተጨማሪ ሰነዶችንና ዲክለራስዮኖችን አሰባስቦ እንዳጠናቀቀና በአዳማ፣ በሚሌና ድሬዳዋ በተጀመረው ምርመራ የዘጠኝ ምስክሮችን ቃል እንደተቀበለ ኮሚሽኑ ለፍ/ቤቱ ገልጿል፡፡ ነገር ግን የአስር ተጨማሪ ምስክሮችና የአራት ባለሙያዎች ቃል ለመቀበል እንዲሁም መረጃዎችን ለማጠናቀር የጊዜ ቀጠሮ ያሰፈልገኛል ብሏል - ኮሚሽኑ፡፡
ወደ አዲስ አበባ በሚያጓጉዙት እቃ ላይ የታክስ ጉድለት የተገኘባቸው ኩባንያዎች ላይ በቃሊቲ ጣቢያ ድንገተኛ ፍተሻ እንዳይካሄድባቸው አድርገዋል ተብለው በተጠረጠሩት በአቶ ገ/ዋህድ፣ በአቶ ነጋ እና በአቶ አሞኘ ዙሪያም ምርመራውን ሲያካሂድ እንደሰነበተ የኮሚሽኑ ተወካዮች ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በዚሁ የፍተሻ ጉዳይ ከሰሞኑ የአራት ምስክሮች ቃል እንደተቀበለና ሰነዶች፣ እንደሰበሰበ ኮሚሽኑ ጠቅሶ፣ ቀሪ ምስክሮችና ሰነዶች እንዳሉ ገልጿል፡፡ ሁለት ተጠርጣሪዎች ተመሳጥረው የመንግስትን ታክስ አላግባብ ለራሳቸው ተጠቅመውበታል በሚል በአምስት በኩባንያዎች ላይ እንደተጀመረ የተናገሩት የኮሚሽኑ ተወካዮች፣ የሁለቱ ኩባንያዎች ኦዲት እንደተጠናቀቀና የሦስቱ ደግሞ እስከ ሃምሌ 30 ድረስ እንደሚጠናቀቅ ገልጿል፡፡
በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የተያዙ የኮንትሮባንድ እቃዎች አላግባብ እንዲለቀቁና ክስ እንዲቋረጥ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩት አቶ ገ/ዋህድ እና አቶ ጥሩነህ ላይ የሁለት ምስክሮች ቃል ተቀብሎ ሰነዶችንም እንዳሰባሰበ ኮሚሽኑ ጠቅሶ፤ የባለሙያዎችን ቃል ለመቀበልና ቀሪ ሰነዶችን ለማሰባሰብ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጿል፡፡
በፍራንኮቫሉታ እንዳይገባ የተከለከለ የውጭ አገር ሲሚንቶ አላግባብ እንዲገባ ተደርጓል በሚለው ጉዳይ ዙሪያ አምስት ሰነዶችን አሰባስቤያለሁ የሚለው ኮሚሽኑ፣ የእንግሊዝኛ ሰነዶችን ወደ አማርኛ ለማስተርጐምና ከሶስት ምስክሮች ቃል ለመቀበል ጊዜ ይሰጠኝ ብሏል፡፡ ይሄው የሲሚንቶ ጉዳይ አቶ ገ/ዋህድ፣ አቶ ነጋ እና አቶ አሞኘ እንዲሁም አቶ ተወልደን ይመለከታል፡፡
የፀረ ሙስና ኮሚሽን በማጠቃለያው በሁሉም ጉዳዮች ዙሪያ ምርመራዬን ለማጠናቀቅ የ14 ቀን ቀጠሮ ይሰጠኝ ብሏል፡፡ ተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻቸው ካሁን በፊት እንዳደረጉት የኮሚሽኑን ጥያቄ በመቃወም መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ የሚጠይቀው፣ ተሰርቶ ባለቀ ጉዳይ ላይ ነው ያሉት የአቶ ገብረዋህድ ጠበቃ፤ ካለፉት ቀጠሮዎች ያልተለየ ተመሳሳይ ምክንያት እያቀረበ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ብለዋል፡፡ ደንበኛቸው አቶ ገብረዋህድ ከባለቤታቸው ከኮ/ል ሃይማኖት ጋር መታሰራቸውን የገለፁት ጠበቃ፤ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ እያለ፣ ህፃናት ልጆቻቸው የሚኖሩበትን መኖሪያ ቤት በ20 ቀናት ውስጥ እንዲያስረክቡ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ደብዳቤ ተልኮላቸዋል ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብቶ እግድ ትእዛዝ ይስጥልን በማለት የአቶ ገብረዋህድ ጠበቃ ቢጠይቁም፣ ፍርድ ቤቱ ግን ጉዳዩ በሌላ የአቤቱታ አቀራረብ እንዲቀርብ አዟል፡፡
አቶ ገብረዋህድ በበኩላቸው፤ “በአሁን ሰዓት ለነዚህ ልጆች እናትና አባታቸው መንግሥት ነው፤ ፍርድ ቤቱ የልጆቼን የመኖር መብት እንዲያረጋግጥልኝ በትህትና እጠይቃለሁ” ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ የምርመራ ጊዜ እንዲራዘምለት የሚያቀርባቸውን ነጥቦች በየጊዜው እያደሰና እየጨመረ ስለሆነ ለክርክር አመቺ አይደለም በማለት የተከራከሩ ሌሎች ጠበቆች በበኩላቸው፤ ሰነድ ለማስተርጐም እንዴት የጊዜ ቀጠሮ ይጠየቃል ሲሉ ኮሚሽኑን ተቃውመዋል፡፡ አዳዲስ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎች ወደ መዝገቡ በገቡ ቁጥር የጊዜ ቀጠሮው መቋጫ አይኖረውም በማለት መከራከሪያቸውን ያቀረቡት የተጠርጣሪ ጠበቆች፣ ስለዚህ ውሳኔ የሰጥበት ብለዋል፡፡ የዋስትና መብታችን ይከበር፣ ካልሆነም የጊዜ ቀጠሮዎች በጣም አጭር መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል ተጠርጣሪዎች፡፡
የወ/ሮ ሽቶ ነጋሽ ጠበቃ የደንበኛቸው ጉዳይ ተለይቶ እንዲታይ ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ሲሆን፤ በዝዋይ ገጠር ውስጥ የሚኖሩት ታታሪ ገበሬ ናቸው ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ሽቶ በሚቀጥለው አመት ለሚደረገው የአርሶ አደሮች ሽልማት በእጩ ተሸላሚነት ተመርጠዋል ያሉት እኚሁ ጠበቃ፣ አሁን ግን የግብርና ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳልቻሉ ፍ/ቤቱ ተገንዝቦ በዋስ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ይፍቀድላቸው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው ችሎቱ፣ የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ፣ ከተጠየቀው የ14 ቀን ቀጠሮ ላይ 10 ቀን ብቻ በመፍቀድ ለሐምሌ 22 ቀጥሯል፡፡

Read 19980 times