Saturday, 20 July 2013 10:11

የሼኩ ግድያና የሃይማኖት ጉዳይ ፓርቲዎችን እያነጋገረ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

“የትኛውም ፓርቲ ሙስሊሙን ብቻ የሚመለከት ስብሰባ ስለመጥራቱ አላውቅም” ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ የመድረክ አመራር አባልማንኛውም ፓርቲ ሁለት ነገር ተለይቶ መታየት እንዳለበት ነው እማምነው፡፡ አንደኛ ደሴ የተገደሉት የሃይማኖት አባት ጉዳይ የተፈፀመባቸው የነፍስ ግድያ ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ የህግ ጥሰት ነው፤ ስለዚህ የእሣቸው ጉዳይ በሃገሪቱ የህግ ስርአት መሰረት፣ ያለሰለሰ ጥረት ተድርጐ ገዳዮቻቸው ለፍትህ መቅረብ አለባቸው፡፡ እኚህ አባት በመሣሪያ ነው የተገደሉት የሚል መረጃ ነው የደረሰን፡፡ ልጆቻቸውም ቤተሰቦቻቸውም በሚዲያ ቀርበው ያረጋገጡት ነገር ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የፍትህ ስርአቱ ብቃት የሚታይበት ነው፡፡ የፖለቲካ አጀንዳነቱና ተገቢነቱ ለኔ አይታየኝም፡፡ እኔ መንግስት የእኚህን አዛውንት ሞት በቀላሉ ሳይመለከት ፍትሃዊ እርምጃ መውሰድ አለበት ነው የምለው፡፡ የመንግስትን ወገን በብዙ ነገር መጠርጠር ይቻላል ግን ሁሉም መረጃው ይፋ ከሆነ በኋላ የሚታይ ነው፡፡

“መንግስት የሠራው ድራማ ነው” የሚል ሃሳብ ከሠልፍ አድራጊዎቹም የሰማሁ መሰለኝ፤ ግን መንግስት ገዳዮቹን ይዣለሁ እያለ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በበቂ ማስረጃና በምስክር ነው የሚረጋገጠው፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሁሉም ሊታወቅ የሚችለው፡፡ “የፖለቲካ ሴራ እየተሰራ ነው፤ የመንግስት ድራማ ነው” የሚለውን ለማመን የሚያስችለኝ ማስረጃ የለኝም፡፡ ይህን የሚሉትን ወገኖች ሃሳብ የምጋራበትም በቂ ምክንያት አይኖረኝም ማለት ነው፡፡ መንግስት የዜጐችን ህገመንግስታዊ መብት እየተጋፋ ነው የሚለው ጉዳይ ለብቻው ነው መታየት ያለበት፡፡ በዚህ ጉዳይ መድረክም ቢሆን “መንግስት ፖለቲካና ሃይማኖትን አጣምሮ ከመንቀሳቀስ እጁን ይሰብስብ፤ ይሄ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው” የሚል መግለጫ አውጥተናል፡፡ የተገደሉት የሙስሊም መምህር ስለሆኑ ጉዳዩን ከዚህ ጋር ማገናኘት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ተቃዋሚዎች የሃይማኖት አጀንዳ ይዘው የተንቀሳቀሱበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም፡፡ መብት ይከበር፣ መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፣ በሁለቱም ተቋሞች አንዱ በሌላኛው አይገባም የሚል ህገመንግስታዊ ድንጋጌ አለ፡፡

የመንግስት ሚና ምናልባት የሚሆነው በሃይማኖቱ ሰበብ ህግና ስርአቱ ተጥሶ ወንጀል ከተሰራ አንዱ ሌላውን በማጥቃት ላይ ከተሰማራ፣ መቼም የሃይማኖት ተቋማት የራሳቸው ፖሊስ እና ደህንነት የላቸውም፤ ስለዚህ መንግስት ያንን ስርአት የማስያዝ ሃላፊነት ይኖረዋል፡፡ ያ ሃይማኖት ውስጥ ገባ አያስብለውም፡፡ ሆኖም “ይሄን ትመርጣላችሁ፤ ያንን ትጥላላችሁ፤ ይሄን እደግፋለሁ፤ ያንን እቃወማለሁ” ከሚላቸው ነገሮች እጁን መሰብሰብ ይገባዋል፡፡ አንዳንዴ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎችን ሃሳብ በመደገፍ ጉባኤዎችን እያደረገ፣ ሌሎች በመድረኩ እኩል ተሳታፊ አይሆኑም፡፡ መንግስት ራሱን ከዚህ አውጥቶ ሌሎችንም ያሳምን፡፡ አንዱን ወገን ለይቶ ከሌላው እንደማያስበልጥ በተግባር ያሳይ፡፡ ፓርቲዎችም የሚያነሱትና እያነሱት ያለው ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ የትኛውም ፓርቲ ሙስሊሙን ማህበረሰብ ብቻ የሚመለከት ስብሰባ፣ ስለመጥራቱ የማውቀው ነገር የለም፡፡ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጋ እንደመሆኑ፣ በአንድ አይነት ህዝባዊ ጥሪዎች ውስጥ እየተገኘ እግረ መንገዱን የራሱን ብሶቶች ቢያሰማ ተገቢ ነው፡፡

በዚህ ደረጃ ነው መታየት ያለበት እንጂ ከዚህ አልፎ ጉዳዮቹን ማጦዝ፣ በየትኛውም አቅጣጫ ቢሆን መግባባት ላይ የሚያደርስ ስለማይሆን፣ መንግስትም ሆነ ተቃዋሚዎች በጥንቃቄ ሊይዙት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ “ኳሱ ያለው በመንግሥት ሜዳ ላይ ነው” ዶ/ር መረራ ጉዲና - የፖለቲካ ሣይንስ ምሁርና የመድረክ አመራር አባል ሃይማኖት የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑ በዚህም ሆነ በዚያ ትክክል አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ማነው የጀመረው? ማንስ ነው ወደዚህ ያመጣው? የሚለው ነው፡፡ ለምሣሌ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ያን ያህል ችግር ሲደርስበት ተቃዋሚው የኢህአዴግን ጣጣ በመፍራት ዝም ቢል እነሱን እንደዜጐች ያለመቁጠርና ብሶታቸውን ለመስማት ያለመፈለግ ይሆናል፡፡ ተቃዋሚው ተቸግሮ ነው አንዳንድ ነገሮችን ማንሣት የጀመረው፡፡ መንግስት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እየገባ፣ ሰዎች ሲታሰሩና ሲደበደቡ ተቃዋሚው ዝም ቢል ያስወቅሰዋል፡፡ ኢህአዴግ ለምን ወደዚህ ነገር ውስጥ እንደገባ አልገባኝም፤ የሚያሳዝንም ነገር ነው፡፡ ጉዳዩን ለምን ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል እንደፈለገ አናውቅም፡፡ ይህን ጨዋታ የጀመረው ምርጫ 97 ላይ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ደግሞ ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ለየት ያለ ፍቅር አለኝ ይል ነበር፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደዚህ አይነት ነገር መጥቷል፡፡

መንግስት እንግዲህ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጁን አስገብቷል፡፡ ለምሣሌ የክርስትና እምነት ተከታዮች በቤተክርስቲያናቸው ጳጳሳቸውን መምረጥ ከቻሉ፣ ሙስሊሞች ለምን በመስጊዳቸው መሪያቸውን መምረጥ አይችሉም፡፡ ይሄ አጠያያቂ ነው፡፡ ይሄኛው በራሱ ቤተክርስቲያን ውስጥ ምርጫ እንዲያካሂድ ከተደረገ፣ እነዚያ ለምን በቀበሌ እንዲያደርጉ ይገደዳሉ፡፡ ይሄ እንግዲህ ኢህአዴግ የለመደውን የቀበሌ ጨዋታ እዚያም ለመድገም የመሞከር ይመስላል፡፡ ዋናው ጉዳይ በእኔ እምነት ኳሱ ያለው በመንግስት ሜዳ ላይ ነው፡፡ መነጋገርም፣ መደራደርም የሚችለው እሱ ነው፡፡ ዝም ብሎ ሁሉንም “ሽብርተኛ” ብሎ መክሰስ አያዋጣም፡፡ ከሱ ቁጥጥር ውጪ የሆኑና መብታቸውን የሚጠይቁትን ሁሉ “ሽብርተኛ” ማለት አይገባም፡፡ ይሄ ነው እንግዲህ ችግር የፈጠረው፡፡ እስካሁን ያለብንን የብሔረሰቦች ጣጣ በአግባቡ ሣንወጣው አሁን ደግሞ ሌላ ጣጣ እያመጣብን ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ቀላል አይደለም፤ እንደሌሎች የፖለቲካ ጥያቄዎችም አይደለም፡፡ እሱን ይዞ ጨዋታ መጀመር ኢህአዴግ ምን እንደሚጠቀምበትም ባናውቅም ውጤቱ ልንወጣው ወደማይቻለን አዘቅት ውስጥ የሚያስገባን ሊሆን ይችላል፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲፈጠሩ ደግሞ አንዳንዴ ሰው ያላሰበውን ነገርም ማሳሰብ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ በራሱ ላይ የማይሆኑ ቀዳዳዎችንና በሃገሪቱ ላይም ጣጣዎችን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ውጤቱ ኢህአዴግ እንደሚለው ቀልድ አይደለም፡፡ “የእኔ ጥያቄ መንግስት በዚህ መጠን ለምን ይጠረጠራል ነው” - አቶ ግርማ ሰይፉ ሰሞኑን ደሴ ውስጥ በተገደሉት የሀይማኖት አባት የተነሳ ሃይማኖትን አጀንዳ አድርጐ እየተንቀሳቀሰ ያለው መንግስት እንጂ ተቃዋሚዎች አይደሉም፡፡

እኛ እየጠየቅን ያለነው መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይግባብን፣ ህገ-መንግስቱ ይከበር ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ ላይ መንግስትና ሀይማኖት የተለያዩ በመሆናቸው መንግስት ጣልቃ ገብነቱን ያቁም ማለትና የመብት ጥያቄን ማንሳት በምንም መልኩ ሐይማኖትን አጀንዳ አድርጐ መንቀሳቀስ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም እኛ ሃይማኖትን አጀንዳ የማድረግ እቅድም ሃሳብም የለንም፤ በመርህ ደረጃም አንቀበለውም፡፡ የሃይማኖት መሪውን ሞት በተመለከተም መንግስት የፖለቲካ አጀንዳ አድርጐ ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም፣ እኔ ግን መንግስትን የሚሠማ ከሆነ ለመምከር የምሞክረው ለምሳሌ እኛ ደሴ ውስጥ ባካሄድነው ሠላማዊ ሰልፍ፣ የደሴ ነዋሪዎች መንግስት እንደሚለው ጥቂት ሳይሆኑ በርካቶች ናቸው፡፡ መንግስት እንደሚለው፤ መቶም ይሁኑ አምስት መቶም ይሁኑ አንድ ሺህ፣ መንግስት በሰውየው ግድያ እጁ አለበት እያሉ እየጠረጠሩ ነው፡፡ መንግስት እጁ አለበት የለበትም የሚለውን ማንም ከእኛ መጠበቅ የለበትም፤ ህዝቡ ራሱ ጥርጣሬ ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ማለት የምንፈልገው “መንግስት በዚህ ደረጃ ለምንድነው በህዝብ የሚጠረጠረው ነው” ለምንስ መንግስት በዜጐቹ አይታመንም እያልን ነው ያለነው፡፡ ወደራሱ በጥልቀት መመልከት አለበት የሚል ምክር አለን፡፡ መንግስት “ተቃዋሚዎች ሃይማኖትን አጀንዳ አድርገዋል፤ በእሳት እየተጫወቱ ነው” የሚለው ማስፈራራት ነው፡፡ ማስፈራራት ይቻላል፡፡ እኛ በመርህ ደረጃ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት፤ ሃይማኖትን አጀንዳ አድርገን አናውቅም፤ ወደፊትም አናደርገውም፤ ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መሠረት “ሀይማኖታዊ ነፃነት መከበር አለበት” የሚለው መርህ ግን ህገ-መንግስታዊ ነውና በዚህ ዙርያ ባሉት ችግሮች ላይ ሃሳባችንን እናሰማለን፡፡

ይሄ ማለት ግን መንግስት ጣልቃ የሚገባው በእስልምና ሃይማኖት ላይ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ በተለያዩ ሃይማኖቶች ጣልቃ ይገባል፡፡ መንግስት ጣልቃ አልገባሁም እያለ ነው፡፡ ግን አልገባሁም ብቻ ሳይሆን “ዜጐች ለምን በዚህ ደረጃ ይጠረጥሩኛል” ብሎ ራሱንም መፈተሽ አለበት። ለምሳሌ ቦስተን ላይ በደረሰው ፍንዳታና ጉዳት የአሜሪካ ህዝብ መንግስትን አልጠረጠረም፤ በቃ የሆነ አሸባሪ አድርጐታል እንጂ መንግስት አድርጐታል ብሎ አልጠረጠረም ታዲያ በእኛ አገር መንግስት ይህን ያህል ለምን በህዝቡ ይጠረጠራል ይህ በጣም ያሳዝናል፡፡ የ“ሃይማኖት ጥያቄ ስህተት የሚሆነው የመንግስትነት ጥያቄ ሲያነሳ ነው” አቶ ሙሼ ሰሙ የኢዴፓ ሊቀመንበር ይህን ነገር ከሁለት አቅጣጫ መመልከት አግባብ ነው፡፡ የመጀመሪያው ከህገመንግስቱና ከህገመንግስቱ ከሚመነጩ መብቶች አኳያ ሊታይ ይገባል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ከዚሁ ህገመንግስት ቢመነጭም እንደ መብት ለማስተናገድ በሚኖረን ዝንባሌ ላይ መመስረት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ደሴ ላይ የተገደሉትን የሃይማኖት አባት በሚመለከት ምንም ጥያቄ የለውም፤ ሰውን በማንኛውም መንገድ ከህግ አግባብ ውጪ መግደል ያስጠይቃል፡፡ በፍርድ ቤት ቀርቦ የሞት ቅጣት እስካልተፈረደበት ድረስ ማንም ሃይል ሰውን የመግደል ስልጣን የለውም፡፡ በዚህ ምክንያት የተፈፀመው ግድያ እጅግ የሚያሳዝንና አግባብነት የሌለው ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የሃሳብ፣ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ልዩነቱን ማስፈፀም የሚቻለው በህግ አግባብ ሊሆን ይገባል፡፡ የህግ ስርአትን መናድ ከተጀመረ፣ ማብቂያ የሌለው አዙሪት ውስጥ ነው የሚከተን፡፡ ሁለተኛው መንግስት ሌላ ፍረጃ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ሊጤኑ የሚገባቸው ነገሮች አሉ ፡- አንደኛ ጉዳዩ በሚገባ መጣራት አለበት፡፡ ይህ መረጃ ለህዝብ ባልደረሰበት ሁኔታ፣ “አሸባሪ ነው፤ የፖለቲካ ጥያቄ ነው፤ የሃይማኖት ጥያቄ ነው” የሚሉ ድምዳሜዎች ላይ ከመድረሱ በፊት አሁንም ጉዳዩን አጥርቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡

ይህ ባልሆነበት ከዋናው ስራ በፊት የህዝብ ግንኙነትና የፕሮፓጋንዳ ስራውን ማስቀደም አደጋ አለው፡፡ መንግስት አሁንም አጣርቶ የደረሰበትን መረጃ ግልጽ ያድርግ፣ ህዝቡ የራሱ ጉዳይ ስለሆነ በዚህ ላይ ደግሞ የራሱን አቋም እንዲወስድ ሁኔታውን ያመቻች፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በመርህ ደረጃ በህገመንግስቱ መሠረት የፖለቲካ ጥያቄዎች መፍትሔ የሚያገኙት በፖለቲካ መንገድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የሃይማኖት ጥያቄ ደግሞ ከፖለቲካ ጥያቄዎች ገለልተኛ ጥያቄ ነው፤ ይህ ማለት ግን የፖለቲካ እና የሃይማኖት ጥያቄን የሚያስተሳስራቸው ነገር የለም ማለት አይደለም፡፡ የሃይማኖት ጥያቄ ስህተት የሚሆነው የመንግስትነትን ጥያቄ ሲያነሳ ነው፣ የሃይማኖት ጥያቄው ስልጣንን ለመቆጣጠር የሚደረግ ከሆነ ህገወጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህገመንግስት መሠረት መንግስት ሴኩላር (አለማዊ) ነው፤ ሃይማኖት ውስጥ የማይገባ፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ የማይገባ ነው፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት ጥያቄዎች መስተናገድ ያለባቸው በሃይማኖት አጀንዳ ነው ብዬ አምናለሁ፣ የፖለቲካ ጥያቄዎች ደግሞ በፖለቲካ አጀንዳ ይስተናገዳሉ፡፡ ይህ አጋጣሚ በታሪክ የተፈጠረ ያልታሰበ፣ ያልተጠራ ሂደት ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የራሱ ጥያቄ ነበረው፤ ያንን ጥያቄ በተለያየ መንገድ ለመግለጽ በሚፍጨረጨርበት ጊዜ እነዚህ ፓርቲዎች ሠላማዊ ሠልፍ ተፈቅዶላቸው፣ ህጋዊ ሆነው ወጡ፡፡ ያንን አጀንዳ ህብረተሰቡ ከፖለቲካ ጥያቄ ጋር ደርቦ ይዞ ወጣ፤ ይህን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አልነበራትም፡፡

ግን ይሄን እንደ አንድ የታሪክ አጋጣሚ ወስደን፤ ለወደፊት እንዲህ አይነት መደበላለቅ እንዳይፈጠር መስራት ነው የሚያስፈልገው እንጂ ይሄ ነገር ያልተገባ ነው ብሎ ማውገዝ ተገቢ አይደለም፡፡ መንግስት የጉዳዩን አደገኛነት ከግምት ውስጥ አስገብቶ መስመር እንዲያዝ ማድረግ አለበት፡፡ የሙስሊሙ ማህበረሰብ የመብት ጥያቄ አላቸው፤ ያ መድረክ ተመቻችቶላቸው ጥያቄያቸውን የሚያቀርቡበት እድል ማመቻቸት፣ መደበላለቁ እንዳይፈጠር ይረዳል፡፡ ይህ ማለት ግን የሙስሊሞችም ሆነ የሌሎች እምነት ተከታዮች የመብት ጥያቄ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አይመለከታቸውም ማለት አይደለም፡፡ ጥያቄው ከመብት ጥያቄነት ካላለፈ ይመለከታቸዋል፡፡ የመብት ጥያቄን ሌላ ሃይል አይደለም ሊያስተናግድ የሚቻለው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ሃይል ብቻ ነው፡፡

Read 3529 times