Print this page
Saturday, 20 July 2013 10:20

የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ተናጋሪዋ ምድር
ትግራይ የትራጀዲና ኮሜዲ መድረክ ናት!
ከክርስቶስ ልደት 2006 ዓመት በፊት “አልሙጋህ” የተባለ ጣኦት ይመለክበት የነበረውን አዲአካውህን ጐብኝተን ውቅሮ ስንገባ ነው ጽሑፌን በይደር የቋጨሁት፡፡
ውቅሮ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ የተመሰረተች ዘመናዊ ከተማ ናት፡፡ ከዚያች ውብ ከተማ ዳር እንደደረስን የከተማዋ ከንቲባና ነዋሪዎችዋ እንደሌሎች ከተሞች ነዋሪዎች ሁሉ በጭፈራ፣ በሆታና በዕልልታ ነው የተቀበሉን፡፡ ደመቅ ያለ ቁርስም ከቡና ጋር ጋብዘውናል፡፡ እንግዳን በክብር መቀበልና መጋበዝ የትግራዮች ባህል መሆኑን በተደጋጋሚ ስላየን ብዙም ላይደንቅ ይችላል፡፡ ግን የውቅሮ ከተማ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሊወደሱበት የሚገባ አንድ እንግዳ ነገር ተገንዝበናል፡፡ በውቅሮ ቅዳሜ የሥራ ቀን ነው፡፡ ህዝቡን ለማገልገል ሲባል ሠራተኛው በሙሉ ፈቃደኝነት ቅዳሜን በሥራ እንደሚያሳልፍ ተነግሮን “ይበል በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችም ይለመድ” ብለናል፡፡
የውቅሮ ቆይታችንን በአጭሩ አጠናቀን መጓዝ ስላለብን፣ ወደ አውቶቡሳችን መሰባሰብ ጀምረናል፡፡ ጊዜውም የተሳፈርንበት አውቶቡስም እሽቅድምድም የያዙ ይመስል በየፊናቸው ይከንፋሉ፡፡ አውቶቡሳችን ሲከንፍ ተናጋሪዋን ምድር እየቃኘን፣ በአየነው ተራራ፣ ወይም የተፈጥሮ ጥበቃ እየተደመምን ስንጓዝ ሌላ አስደናቂ ነገር ሲቀበለን፤ በቃ ትግራይ ማለት ቢገልጧት፣ ቢገልጧት ተነብባ የማታልቅ ግዙፍ መጽሐፍ ትመስላለች፡፡
በዚህ አይነት ስንጓዝ ቆይተን በአገራችን ታሪክ የመጀመሪያው ውቅር ቤተክርስቲያን ከሚገኝበት አብርሃ ወአጽብሃ ቀበሌ ደረስን፡፡ አብርሃ በአራተኛው መቶ ክፍለዘመን የአክሱም ንጉሥ የነበረና ክርስትና መንግሥታዊ ሃይማኖት እንዲሆን የደነገገ ነው፡፡ የአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ በስሙ የተሰየመውም በዚሁ ታሪካዊ ምክንያት ሲሆን መቃብሩም በዚሁ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይገኛል፡፡
ስለቤተክርስቲያኑ የአሰራር ጥበብና በውስጡ ስለሚገኙት ቅርሶች፣ ስለ ሶስቱ ቤተመቅደሶች፣ ስለ ቦታው አቀማመጥ፣ ወዘተ ብዙ እጅግ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ግን ቦታም ጊዜም የለም፣ እንደ ጉብኝታችን ሁሉ ጽሑፌንም ፈጠን ማድረግ አለብኝ፡፡ አለዚያ ጋዜጣችን ትግራይ ላይ ብቻ ቢከርምም ስለ ትግራይ ምስጢር፣ ስለ ትግራይ ተአምራዊነት ጽፎ መጨረስ አይቻልም፡፡ የገደላትና ተአምራት ፀሐፊዎች እንዲህ አይነቱ እጹብ ድንቅ የሆነ ጉዳይ ሲገጥማቸው “ሰማዩ ሰሌዳ ወይም ብራና፣ የክረምቱ ዝናም ቀለም ቢሆኑም ጽፌ መጨረስ አልችልም” ይላሉ፡፡ የትግራይ ጉዳይ ያለምንም ማጋነን ለእኔ እንዲያ ነው፡፡
አብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ከታሪካዊው ቤተክርስቲያኗ በተለይ የምትደነቅበት አጋጣሚም ተፈጥሯል፡፡ ቀበሌዋ እጅግ ከተራቆቱት የክልሉ ቀበሌዎች አንዷ ነበረች፡፡ ግን በህዝቡ እንደ ብረት የፀና ትግስትና ጥረት ዛሬ ተቀይራለች፤ ተራሮችዋ በተፈጥሮ ደን እየተሸፈኑ ናቸው፡፡
የአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ስም ሲነሳ የአንድ ጀግና አርሶ አደር ስም አብሮ መወሳቱ ግድ ነው፡፡ ስሙ “አባ ሐዊ” ይባላል፡፡ በትግርኛ “አባ እሳት” ማለት ነው፡፡ ትክክለኛ ስሙ ግን ገብረሚካኤል ዓደይ ይባላል፡፡ “አባ ሐዊ” የሚለው ቅጽል ስም የወጣለት በግብሩ ነው፡፡ ሲናገር እሳት ነው፤ ሲሰራ ደግሞ የበለጠ ነበልባል ነው፡፡ ኃላፊዎች ከቢሮአቸው ቁጭ ብለው ወይም ህዝብን ሰብስበው “እንዲህ ብታደርጉ የተሻለ ምርት ታገኛላችሁ፤ ወይም ምርታችሁ እንዲያድግ ይህን ፍጠሩ ማለት የለባቸውም፡፡ እንዲህ ብለው ሲያዝዙ ህዝቡ “የምትነግረን እውነት ከሆነ ለምን አንተ አልከበርህም?” የሚል ጥያቄ ቢያነሳ መልስ የለውም፡፡ ስለዚህ መሪዎች ሠርቶ በማሳየት አርአያዎች እንጂ የወሬ ጀግኖች መሆን የለባቸውም” ብሎናል በኩራት፡፡
አብርሃ ወአጽብሃ ቀበሌ እጅግ ዘግናኝ ከሆነ ድህነትና መራቆት የተራቀቀችው በአባ ሐዊ ፋና ወጊነትና አመራር ሰጭነት መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ አባ ሐዊ በዚህ የልማት ጀግንነቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ አንድ ጊዜ፣ በአገር አቀፍ ደግሞ 15 ጊዜ ተሸልሟል፡፡ የአባ ሐዊ የአመራር ጥበብ ቀድሞ ሠርቶ በማሳየት በመሆኑ፣ በህዝቡ ዘንድ ትልቅ አመኔታና ከበሬታን አግኝቷል፡፡
ከአባ ሐዊ ጓሮ ተገኝተን በአይናችን አይተን ያረጋገጥነው እውነትም ይኸው ነው፡፡ ያ አስፈሪ የነበረ ራቁት መሬት በደን ከመሸፈኑም በላይ ልዩ ልዩ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ተንዠርግገው ይታያሉ፡፡ የሰው ልጅ ከፈለገ አጥፊ ከፈለገ ደግሞ ተፈጥሮን ከነሙሉ ለዛዋና ክብሯ ሊመልሳት እንደሚችል መልካም አብነት ነው፡፡
ከአባ ሐዊ ጓሮ የተንዠረገጉትን ልዩ ልዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በአድናቆት ከጐበኘን በኋላ ወደ እንግዳ መቀበያው ወሰደን፡፡ የእልፍኝ ቅርጽ ካለው እንግዳ መቀበያ ቤቱ ቁጭ እንዳልን፣ በሚያስገርም ፍጥነት ሻሽ የመሰለ ማር በዳቦ እያደረገ ለእያንዳንዱ ተጓዥ አደለ፡፡
ጠንክረው ከሰሩ ጣፋጭ ውጤት እንደሚገኝ ከአባ ሐዊ ተምረን፣ አመስግነንም ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ አክሱም ገብተን ማደር ስላለብን እንጂ ልክ እንደ ማሩ ሁሉ ያንን የሚጣፍጥ አንደበቱን እያዳመጥን ትንሽ ጊዜ ብንቆይ ደስታውን አንችለውም ነበር፡፡
የጥበብ ተጓዦች ጉዞ ከጀመሩበት ዕለት አንስተው በአውቶቡሱ ውስጥ መዝፈን፣ ማቅራራትና መዘመር ወይም ግጥምና ዜና በማንበብ ራሳቸውን ማዝናናት የተካኑበት ቢሆንም ከአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ጉብኝታቸው በኋላ ግን የሆነ ህመም የያዛቸው ይመስል እየፈዘዙ መጡ፡፡
እርግጥ ነው ትግራይ ግራ ታጋባለች፤ ትግራይን ከራስ እስከ እግሯ ሳይጐበኙ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ማለትም ይከብዳል፡፡ ወይም ያሳፍራል፡፡ ትግራይ ተራራዋ ሁሉ፣ ከርሰምድሯ ሁሉ፣ ገዳሟ መስጊዷ ሁሉ የአገሪቱን ወይም የመላ አፍሪካን ምስጢር ደብቀው ይዘዋል፡፡
ጉዟችን ቀጥሏል፡፡ መንገዱ ገና እየሰፋ ስለሆነ ኮረኮንች ነው፡፡ በአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ህዝብ ጥንካሬ፣ በአባ ሐዊ የአመራር ስልት፣ በገዳሙ ጥንታዊነት ድንቅ ጥበብ እየተደነቅን ስንጓዝ በስተግራ በኩል እውቅ ቀራጺ ተጠንቅቆ ያዘጋጀው የሚመስሉት የገርዓልታ ሰንሰለታማ ተራሮች ከፊት ለፊታችን ድንቅ አሉ፡፡ ተራሮቹ እንደ ማንኛውም ተራራ የድንጋይ ቁልሎች አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከአፍ እስከ ገደፋቸው የአገራችን የሥልጣኔ፣ የታሪክ፣ የሥነ ጥበብ፣ የሥነ ሕንፃና የሥነ ፈለክ ምስጢሮች የታጨቁባቸው የምስጢር ጐተራዎች ናቸው፡፡
አስደናቂውን የአባ ቶምዓታን ቤተክርስቲያን ጨምሮ በአብዛኞቹ ተራሮች ላይ ከ34 በላይ ከአንድ አለት የተፈለፈሉ አብያተክርስቲያናት አሉ፡፡ እያንዳንዳቸውን ጐብኝቶ ለመጨረስ ቢያን ለአንዱ ቤተክርስቲያን የአንድ ቀን ቆይታን ይጠይቃል፡፡
በገርዓልታ ተራሮች ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ፣ በውስጣቸው ስላሉ ምስጢራት እየተደነቅን በመጓዝ ላይ ሳለን ከፊት ለፊታችን፤ ግን በርቀት አስደናቂው እና በር አልባው የደብረዳሞ ተራራ በኩራት ተጀንኖ ታየን፡፡
ደብረ ዳሞ በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አባ አረጋዊ የሚባሉ መነኩሴ የመሠረቱትና እንደ ግዑዝ ነገር በመጫኛ ብቻ እየተጐተቱ የሚወጡበት ታላቅ ደብር ነው፡፡ የመጐብኘት ዕድሉ ስላልነበረን ውስጤ እያዘነ ግን ደግሞ በካሜራዬ ምስሉን ለማስቀረት እየሞከርኩ ማለፍ ግድ ሆነ፡፡ ጥላሁን ገሠሠ “በዓይን እየተያዩ የመናፈቅ ጣጣ…” ያለው እንዲህ አይነቱ የውስጥ ስቃይ ገጥሞት ይሆን?
ትግራይ የሃይማኖት፣ የስልጣኔ፣ የፍልስፍና፣ የዕውቀትና የማንነት ምስጢራት ዋሻ ብቻ ሳትሆን የትራጄዲና ኮሚዲ መድረክም ናት፡፡ አሁን ደግሞ ሐውዜን ገባን፡፡ ሐውዜን መራራ ትራጄዲ ከተተወነባቸው መድረኮች አንዷ ናት፡፡ በቀድሞው መንግሥት የጦር አውሮፕላኖች በአንድ የገበያ ቀን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጐች እንደ ቅጠል ረግፈውባታል፡፡
የትራጄዲውን መድረክ ሐውዜንን በሀዘን ተሰናብተን ወደፊት እየተጓዝን ነው፡፡ ትግራይ ክልል ውስጥ ተራራ ላይ ቢወጡ አስደናቂ ጥበብ ይነበባል፤ መሬቱን ቢቆፍሩ እጅግ የሚገርም ምስጢር ይገኛል፡፡ ስለሆነም ማየት ያለብን ብዙ ነገር ቢኖርም በጊዜ አክሱም ለመግባት መፍጠን ይጠበቅብናል፡፡ ግን ደግሞ ውቧን ከተማ አድግራትን ማግኘት አለብን፡፡
አድግራትም የተለመደው ህዝባዊና ደማቅ አቀባበል ከምሳ ግብዣ ጋር ተደረገልን፡፡ ምሳው ደግሞ ከሚጣፍጠው የትግራይ ባህላዊ ምግብ “ጥህሎ” እና ከንፁህ የማር ጠጅ ጋር ነበር፡፡ በነገራችን ላይ “አድግራት” ማለት “አድገራሕት” ማለትም “የእርሻ አገር” ማለት መሆኑን አቶ ከበደ አማረ አስረድተውናል፡፡ ለጥ ካለ ሜዳ ላይ የተመሰረተች በመሆኗ እውነትም ለእርሻ ምቹ የነበረች መሆኗን መገንዘብ አያዳግትም፡፡
አድዓራት ውብ ከተማ ናት፡፡ የዩኒቨርሲቲው መመሥረት ከሻዕቢያ ጦርነት በኋላ ተቀዛቅዛ የነበረችውን ከተማ አነቃቅቷል፡፡ የአድግራት ከተማ ባለሥልጣናትና ነዋሪዎችን ግብዣ አጠናቀን በምስጋና ተሰነባበትንና ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ የእኛ ነገር መሄድ፣ ማየት፣ ባየነው ነገር መደነቅ ነው፡፡ ድካም የሚባል ነገር የለም፡፡ ከሁሉ የሚገርመኝ የ78 አመቱ አዛውንት አቶ አስፋው ዳምጤ የእግር ጉዞን የሚጠይቁ ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጐብኘት ከወጣቶች እኩል፤ ብዙ ጊዜ ግን ቀድመው ሲራመዱ ማየት የትግራይ መስህብ ቦታዎች ምን ያህል ጉጉት ፈጣሪዎች እንደሆኑ ያስረዳል፡፡
ወደፊት እየገሰገስን ነው፡፡ ከፊትለፊታችን ደግሞ የዓለም ጥቁር ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው ጣሊያኖች በወርቅ ቀለም ብዙ እጅግ ብዙ ቁምነገሮችን የጻፉለት አድዋ ይጠብቀናል፡፡ ጊዜው ግን ከእኛ ፈጥኖ እየተጓዘ ነው፡፡ የአክሱም ከተማ ከንቲባ አቶ አበራም ህዝቡን አሰልፈው እየጠበቁን ነው፡፡ ስለዚህ ዝነኛዋን አድዋን በዝምታ አልፈን፣ ስንመለስ በደንብ ልንጐበኛት ቀጠሮ ይዘን ወደ አክሱም ገሰገስን፡፡
ጉዞ ወደ አክሱም ማለት ደግሞ ወደ ጥንተ ታሪክ፣ ወደ ማንነታችን መፍለቂያ በከፍተኛ ጉጉት መጓዝ ማለት ነው፡፡ በተለያዩ ጽሑፎችና ምስሎች አይተን የምንጓጓላትን አክሱምን ልናያት፣ አይተንም በአግባቡ ልናውቃት ነው፡፡ ግን ጊዜው ከእኛ ጋር እልህ የተጋባ ይመስል ይከልባል፤ እነሆ 1፡30 ሆነ፡፡
እናም የናፈቅናትን አክሱምን ሌባ ይመስል በጨለማ ገባንባት፡፡ ለብዙ ሰዓታት ሲጠብቁን የቆዩት የከተማዋ ባለሥልጣናትና ህዝቡም እስከዚህ ሰዓት ድረስ በከፍተኛ ትዕግስት ሲጠብቁን አምሽተው ነበርና በክብር ተቀበሉን፡፡ ሞቅ ያለ ራት ከጋበዙን በኋላ ወደተያዙልን ሁለት ሆቴሎች አመራን፡፡ በየደረስንበት ቦታ ሁሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ “እኔም ከጥበብ ተጓዦች ጐን አልለይም” ብሎ ሲከተለን እንደነበር በዚህ አጋጣሚ መግለጽም ማመስገንም እፈልጋለሁ፡፡ አክሱምን ሲነጋ በደንብ እናያታለን፡፡

 

Read 4834 times
Administrator

Latest from Administrator