Saturday, 20 July 2013 10:34

ዘቢብ

Written by  ዋሲሁን በላይ (አዋበ)
Rate this item
(3 votes)

(የሰባ መስዋዕት)

ሐበሻ ሽፍታ ይወዳል፡፡
በዝምታ የተኳለ መልከመልካምነት አይመስጠውም፡፡
የቁጣ ዝናሬን ታጥቄ…ምንሽሬን ወልውዬ…ግስላ መሆን ነው፡፡
የገዛ ህሊናው ነበር እንዲህ እያለ ልቡ ውስጥ ነጋሪት እየጐሰመ ፋኖ ያደረገው፡፡
እንየው፤ ቀጠሮው ቀፎታል፡፡
የልጅነት ጊዜውን በዘርዛራ ወንፊት አንገዋሎ፣ አንገዋሎ፣ የትዝታውን ውጤት እንቅጥቃጭ አድርጐበታል፡፡
እጁ ላይ “ቴስቲ” የሆነ ነገር ነበረው፡፡
ኩርፊያ ስመጥሩ ጥል መሆን የለበትም ባይ ነው፡፡ ግን የታጠቀውን የኩርፊያ ድግ መተርተር አልቻለም፡፡ በልብ አቂሞ ትዳር መምራት ከንቱነት ነው፡፡ ሐገርንም እንደዛው፡፡
በዛች የጐሽ ግምባር በምታክል ቤት ውስጥ …ከመጠን በላይ ተንጐራደደ …እስኪያልበው…የፍርሃቱን ግዳይ ለመጣል ይመስል፡፡ ይወራጫል፣ ፀጉሩን ይነጫል፣ እጁን በቡጢ ይነርታል…የገዛ ራሱን ምን ፍጠር እንደሚለው አይታወቅም፡፡
ጠረጴዛው ጫፍ ላይ የተቀመጠው የውኃ መጠጫ ብርጭቆ፣ የተወለወለው ወለል ላይ “ዋይ” ብሎ ላመ፡፡ “መጪው ጊዜዬ ይሄ ይሆን…” ተጨነቀ፡
እንደ ውኃ የፈሰሰውን ብርጭቆ ለመሰብሰብ አልፈለገም፡፡ የከበረ መዋረድ ስለሌለ …በገዛ እጁ ውዱን ፈትቶ ለቋል…አርዝሞ ማሰር… አለችኝ ብሎ ለመኩራራትም ሆነ ለመኮፈስ አያስደፍርም፡፡
ሴት ልጅ አፍቅራው ከልቡ ደጅ ተመላልሳ፣ ሳያስበው የራቀችው ወንድ ሲባንን እሱ…የወፍጮ ቤት ጣራና ግድግዳ ነው፡፡ በተሰጠው ልክ መስጠት ካቃተው…ባዶነቱን መሙያ ዘመኑን ሙሉ ኳታኝ ነው፡፡ መሐል ላይ ገመዱ የተጠመጠመበት ስፍራ መልኩን ቀይሮ ወደነበረበት ለመመለስ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ውዶች…ዋጋ ያስከፍላሉ!
በአፍ መጠን የሚጐረስ የፍቅር ጉርሻ ከልብ ሆድ መድረሱ፣ በእጅ ምጣኔና ልኬት ላይ ተወስኖ ይኖራል፡፡ “የትም አይሄድም” ያልነውና የተመጻደቅንበት ፍቅርም ሆነ ሌላ ነገር ሳናስበው ባልተረዳነው አኳኋን ካጠገባችን ይርቃል፡፡
ፈትቶ መልቀቅም፣ አስረዝሞ ማሰርም፣ ሁለቱም ከጥርጣሬ ድር የተሰራ አንድ አለኝነት ነው፡፡
እንየው፤ በቅጡ ያልተረዳው ሥጋት ከመጠን በላይ ሲጮህ ጆሮው ውስጥ ይሰማዋል፡፡ ተረብሿል፡፡
አይኑ እምባ ማቅረሩን ያስተዋለው…የመስኮቱን መጋረጃ መንጭቆ ሲገልጠው ነው፡፡ የገዛ ፊቱን ተጠራጥሮ ተመለከተው…በእንዲህ አይነት ስሜት ውስጥ ፊቱ የተቃጠለ ከተማ ነው የሚመስለው፡፡ ከንፈሩን በጥርሱ አላመጠ፣ ትኩሳቱ የፈጠረለት ህመም፣ ከንፈሩ ላይ አሻራ ስሏል፡፡ የሆነ ስስ ላስቲክ የመሰለ ቆዳ በጥርሱ እንደክር መዘዘ፡፡ ህመም ተሰማው፡፡ ልቡ በስሱ ልቧን ታንኳኳለች ”ማነው…” የሚላት ባታገኝም፡፡ አናቱ ላይ ክምብል ሊል የደረሰ በሚመስለው ጣሪያ በኩል ዝናቡ እኝኝ የሚል ለዛቢስ ዲስኩር ይደሰኩራል፡፡ ጣሪያው ማሳበቁ ይገርማል፡፡
እነዚህን ሁሉ የድብርት ጥርቅም በአለባበሱ ለመደለል ያደረገው ጥረት፣ ከግማሽ በላይ ሚዛን ደፍቶለታል፡፡ ልክ ህዝቦቿ በርሃብ ኩል ጠልሽተው፣ በሆነ አሀዝ እድገታችን ከፍ ብሏል ብላ እንደምታቅራራ ሃገር ተሽሞንሙኗል፡፡
እንየው…በመኮሳተር መስመር ውስጥ ተጨማዶ ፊቱን ደጋግሞ ተመለከተው፤ የገዛ ፊቱን ተጠራጠረው…የሌላ አስቀያሚ ሰው ፊት አምጥተው የለጠፉበት ይመስል…በዛ በከሰለው መልኩ ድራቢ…ውዳሴ እየሳቀች ተመለከተ፡፡ ሳቋ…ማህሌታይ ያሬድ የፈጠረውን “ኖታ” ተመርኩዞ የሚዘምር አይነት ነበር፡፡
የመስኮቱን መስተዋት ላለማየት መጋረጃውን በእልህ ደረገመው፡፡
ሮጦ መኝታ ቤት ገባ፡፡
ተመልሶ ለመውጣት ቃጣ…
እያደረገ ያለው ድርጊት ተቆጪ እንዳጣ ሞልቃቃ ህፃን መንቧቸት ሆነበት፡፡
(ቁንጮዎቻችን እንኳ እንደፈለጉ ሲሆኑ “ለምን?!” ማን ብሎ ያውቃል፡፡)
የውዳሴ መኳኳያ መስተዋት ከአልጋው በስተቀኝ በኩል በቁመቱ ዠቅ ብሎ እንደ መልከመልካም ልጃገረድ አምሮ ተሰይሟል፡፡ አሁን ሙሉ እሱነቱን በደንብ አተኩሮ ተመለከተው፡፡ ህሊና ሲበረበር ይሄንን ይመስላል፡፡ በቀፈፈው ስሜት ፊቱን ሲመለከተው፣ የጠፋ አመድ ላይ የተንከባለለ ሙሽራ መስሏል፡፡ የለበሰው ሙሉ ልብስ ግን “ሰው” የሚለውን ስም ለጥፎለታል፡፡
“እመቤት ለምን ዛሬ ቀጠረችህ?” መስተዋቱ ውስጥ ያለውን እንየው ጠየቀው፡፡
በቀለም ያበደውን ፀጉሯን እየቆነጠረች፣ በሳቅ ቀምማ የትምህርት ቤት ፍቅራቸውን ከትረካ ማህደሯ መዝዛ ስትተርክለት፣ ብብቱን እንደተኮረኮረ ህፃን እሚጥም ሳቅ እየረጨ ሰማት፡፡ ስስ ብልቱ እንደተነካ ተመጽዋች ፍቅረኛ ፍርክርክር አለላት፡፡ ቀድሞም ስለምታውቀው ሳያስበው መዳፏ ውስጥ ያስዋኘላትን አጋጣሚ የማምለክ ያህል ተንበረከከችለት፡፡ ሴት ልጅ የመረቧ ውል ጠፍቶባት አያውቅም፣ አውቃ ካልረሳችው በቀር፡፡
መስተዋቱ ውስጥ…ውዳሴ እና እመቤት አጠገብ ላጠገብ ሆነው…ውዳሴ በንጽህና እንደተሰጠ የቤተክርስቲያን እጣን ቀጥ ብላ ስትጐን…መዓዛዋ ደረሰው፤ ነፍሱ ውስጥ የሸሸገውን እውነት አወደበት፡፡
እመቤት ግን ሳቋ ንፍሮ እንደሚቀቅል ውሃ ወይቦ ሲንተከተክ ታየው… ከጀርባቸው… ያ… ተሸናፊው እንየው፤ ጥሬ ትዝብቱን እየቆረጠመ የሚሆነውን በአግራሞት ኩል እየኳለ ተገትሯል፡፡ አንድ የሆነ ሁለትነት…በአንድ ግማሽነት የጅል አድራጐት ግራ መስመር ላይ እየተጠጋ አፋፉ ጋ ነው፡፡ (መሪም ግራ ሲገባው የህዝቡን ጣት ይጠባል!)
የእመቤት ሳቅ የጆሮውን እምብርት ሲደቃው አመመው፡፡
ከውዳሴ ጋር በማይረባ ነገር ተኳርፈው ከቤት ሲወጣ…ጭር ያለው ጐዳና ላይ ያለ ገላጋይ በመኪናዋ እየፈሰሰች…እሱም እሷም ባላሰቡበት ሁኔታ፣ የጊዜ አቃጣሪ ቀሽም ብልሃት መዞ፣ እንየው ስም እንደበዛበት ጧፍ እየነደደ እያለ ተያዩ…የመኪናዋን የድምጽ ርችት ሊንቀው ጉልበት አልነበረውም፡፡
“ብረትን መቀጥቀጥ እንዳጋለ ነው” ፍቃዱን ሳትጠይቅ ተንጠራርታ፣ ወዝ የጠገበ አብረቅራቂ መቋሚያ የመሰለውን እጇን ልካ በሩን ከፈተችለት፡፡ ገባ፡፡ ቀጥታ ለሠላምታ ጉንጯን አሞግጋ ላከችው - ከትኩስ ፈገግታ ጋር፡፡
እንየው፤ ከውዳሴ ጋር የተጋጨበትን ቀጭን ቅሽምና አምሮ ጠላው፡፡ አይወጣም ነበራ ከቤቱ…አያገኛትም ነበራ እመቤትን፡፡ ከስንት ዓመት በኋላ…
ሲሳሳሙ የከንፈሯ ወላፈን የከንፈሩን ጠርዝ በስሱ ገረፈው፡፡ ትዝታ ለመርጨት ነበር ስልቷ፤ ደግሞ እመቤት መሳም እንደተካነችበት አሳምሮ ያውቃል…እሷም ልሳም ብላ ከሳመች አቅልጤ መሆኗን አሳምራ ታውቃለች፡፡ ልቡ ነዳጅ መስጫው እግሯ ስር ሲወድቅ ታወቀው…ትረግጠው ይሆን…?
አይኑን ያገኛቸው፣ ዝገኑኝ ይመስል ከልብሷ አፈንግጠው ከወጡት ጡቶቿ ላይ ነው፡፡ “ተበልተሃል” ስትል በልቧ ያዜመችውን ልቡ ነገረው፡፡ የሆነው ሁሉ ሆነና…እማይሄድበት ቦታ ሸኝታው…የዛሬ ቀጠሮው ላይ ጥዳው ተለያዩ፡፡ ዘይቱ የጐደለበት ቀንዲል መስሎ በርቷል፤ ጭልጭል እያለ የኋላው ትዝታ፡፡
አሁንም ምስልና ሳቋ መስተዋቱ ውስጥ እየታየው ነው፡፡
ውዳሴ…ከደርባባ ፈገግታዋ ጋር የመልካምነት ነጠላ እንደለበሰች ከቅዳሴ እንደተመለሰች ሴት አምራ ታየችው…ከፊቱ በላቀ…አማረችው፣ አሳሳችው፣ ለመቅለጥ ጥግ ላይ ሆኖ አየው ራሱን፡፡ የትኛው ነው ዋናው እንየው…?
እዚህ በቆመበት የቆመው ወይስ ከእነዛ ሁለት ሴቶች ጀርባ የቆመው…?
(የብዙሃኖች ሃገርስ የቷ ናት…? አንገታቸውን የሰበሩት የሚኖሩባት ወይስ… ጥርሳቸውን እየሟጩ የሚያፋጩ… እሚፏልሉባት!)
በሁለት ነኝ ባይ አንድነት ውስጥ የጣሉትን አንስቶ የያዙትን መጣል ለማን ይበጃል…ውኃ የተሞላ የባሎን ላስቲክ እንደምን አየሩ ላይ ደረቱን ሰጥቶ መተኛት ይቻለዋል…? እንየው፤ ምርጫ የሌለው ምርጫ ውስጥ ተሸሽጓል፡፡ ትላንትናው በልጦ ዛሬውን ሊነጥቀው እየተሳለቀበት ፊት ለፊቱ ተገትሯል፡፡ እውነት ደግሞ ብርታቱ ከገዛ ልብ ሃገር ያሰድዳል፡፡
ውዳሴ…አኩርፋ ብትስቅ እንኳ የሳቋ እቅፍ ያሞቀዋል፤ ራቁት ነው ልቧ፡፡ ለሰከንድ እንየውን ተጠራጥራው አታውቅም፡፡ አንዲት የእሳት ፍንጣሪ አይኗ ውስጥ ዘልቃ አታውቅም፡፡ ለፍቅር ተፈጥራ አፍቅራ ማለፍ የምትችል ነጭ ላባ የሆነች ሴት ናት፡፡ ህዝቦቹን እንደሚፈራ መሪ እየባተተች አትኖርም፡፡ በህዝቦቿ እንባ ገላዋን እንደምትጐስም ሀገር ግን ፍቅር ተርባም ታምራለች፡፡
እመቤት…በሳቋ ኩርኩም የወንድን ልጅ የልብ ስስ ብልት እምታደማ፣ እንደጭቅና ሥጋ ስስ ማንነት የያዘች “ሲሆን ይሆናል ካልሆነ ምናባቱ”ን የተቃኘች ናት፡፡ ጠዋት በማመን እንቅፋት የፍቅሯ ጣት እንደቆሰለ እስካሁን አልዳነላትም፡፡ ያጣችውን ለመስረቅ፣ ለማካካስ የምትሮጥ አይደርሴ ሯጭ ሆናለች፡፡ እንየው፤ እቺን ያልተገረዘች ሴት አያውቃትም፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ የከንፈርም የአልጋም በረከት የተሸለመው፣ ድንግልና ወስዶ ያስወሰደውም ከእመቤት ነው፡፡ ያኔ በሽንገላ ሳቅ የታሸች ጨጨብሳ አልነበረችም፤ ጣፋጭ ጭኮ እንጂ፡፡ ስሟ ሲጠራ እና ሲያያት ውኃ ውስጥ እንደከረመ ተልባ ይማልጋል፣ ውኃው ሲናጥ ደግሞ አረፋው ተኩረፍርፎ ይቀራል፡፡
በመስተዋቱ ውስጥ ሶስቱንም ተመለከታቸው…ወንዱን ግን ጠልቶታል…እነቀው እነቀው የሚል ስሜት ተሰምቶታል! እንዴት ሰው በራሱ እግር መቆም ያቅተዋል…! ለዚህ ነው ወደ ውስጥ በተመለከትን መጠን ለራሳችን ያለን ግምት ሚዛን ላይ የሚወጣው… ራሱን ከራሱ ጋር ያልመዘነ “ሰውነት” ደግሞ አስጊ ነው!
ውዳሴ…አምሮባት…መታመን ግንባሯ ላይ ታትሞ…ቁንጅናዋ የለበሰችው ነጠላ ላይ ፈገግ ብሎ ተመለከተ፡፡ እምነት ለፈጣሪ የሚሰጥ የሰባ መስዋዕት ነው፡፡ (መታመን!) ውዳሴ ከሳቀች ደግሞ ቋንጣ ታቀልጣለች፡፡ እመቤትማ ሳቋ ለጠላት እንደተተኮሰ (ለወዳጅ ይተኮሳል እንዴ?) መትረየስ ሲንጣጣ…ጠመዳት!
ሙሉውን የመስተዋቱን ስፍራ ተንደላቀቀችበት…ልክ ለሀገሪቱ እናውቅላታለን እንደሚሉት አይነት፡፡ “እቺን ሴት አላውቃትም እንዴ”…? አለ ለራሱ፡፡
ከውዳሴ ጋር በምን ተዐምር ይመጣጠናሉ…የትኛውስ ሚዛን ነው ልኩን እሚያውቅ!፡፡
“ለምንድነው እንገናኝ ብትይኝ እሺ ያልኩሽ…?” አምባርቆ ጠየቃት፡፡
“ትወደኛለህ…አውቃለሁ…” የአመላለሷ ልስላሴ ከሃር ያይላል…ያንን እሚያመውን ሳቋን ሳቀችበት…የመድፍ ያህል ለቀቀችበት፡፡
“በእናትሽ ይሄ ልብ የሚገሸልጥ ሳቅሽን አቁሚና…ምን አስበሽ እንገናኝ አልሺኝ…?” መስተዋቱ ላይ አፈጠጠ…በቀኝ እጁ ግራ ጣቱ ላይ ያጠለቀውን የክብር ቀለበት እያሽከረከረ ነበር፡፡ ይሄ ሰው ሞኝ ነው እንዴ…
“ፍቅር እኮ የጥጥ ፍራሽ ነው መታደስ አለበት…” ቀስ ብላ ለጆሮው መጥና ነገረችው፡፡ ሳያስበው ከጣሪያ ስር ሳቀ…እንዲህ ስቆ አያውቅም፡፡
“እንሽዬ፤ ለእኔም የመጀመሪያዬ ላንተም የመጀመሪያህ ነኝ” ቀለበቷ እንዲታይላት ነው መሰል አፍንጫዋ ላይ ምንም ሳይኖር አበሰችው፡፡
“አውቃለሁ…” ደደብነሽ ይመስላል አመላለሱ፡፡
“እንደምታውቅ ይገባኛል…!” ወደፊት ተጠጋችው…ፍሬሙ ጠበባት መሰለኝ ለመውጣት ተቸገረች… “ምነው ፈራህ?” ሲያፈገፍግ አይታው ስታፈጥበት ተገርሞ ግምባሩን ቅጭም አድርጐ ተመለከታት…ራሷ ናት…ከንፈሮቿን ያውቃቸዋል፡፡ ለወራት ዋኝቶበታል…ዐይኖቿም የራሷው ናቸው…ጡቶቿ ግን በውበት ብዛት ልክ እንዳጣ ስዕል ሆኑበት፡፡ ውብ ናቸው ግን ለቴስታ የተመቻቸ ኳስ መሰሉት…ፈራት… የዛችን ሃገር ህዝቦች ማንም ታግያለሁ ባይ ከመሬት እየተነሳ እንደሚያስፈራራው አይነት ተሸማቀቀ…
“ለምን…? ትዳር እንዳለኝ እያወቅሽ ድክመቴን ተጠቅመሽ ትጥይኛለሽ…? በደካማ ጐኑ ሰውን መጣል ደግሞ ደፋር አያሰኝም…”
“ቆይ ተረጋጋ ምን ተፈጠረ…ለምን ሃገሩን እንደተቀማ ሽፍታ ትንጨረጨራለህ…”
“ያው ነው! ያው ነው!...ሚስትም ሃገር ናት፤ ሀገርም ሚስት ናት!...”
“ተሳስተሃል…ሃገር ሚስት ሳትሆን እናት ናት…ሚስትማ ብትሆን ይሄ ሁሉ ሞልፋጣ ስንት ራስ ወዳድ ያስቀፈቅፋት ነበር…”
“ወዴት ወዴት…ምንድነው ምትዘባርቂው!”
ያን ቀለሙ የተዘበራረቀውን ሳቋን ሰጠችው፡፡ እየተወራጨ አይኑን ጨፍኖ፣ ጆሮዎቹን በሁለት እጆቹ ግጥም ጭምቅ አድርጐ ይዞ፣ ለጥቂት ደቂቃ አጐንብሶ ቀረ፡፡
የውዳሴ እጆች እየዳበሱ ካጐነበሰበት ቀና ያደረጉት መሰለው…
ራሱን ቀጥ ብሎ መስታወቱ ፊት ለፊት አገኘው…እመቤት የለችም፡፡ ያኛው እንየው እና ውዳሴ አጠገብ ላጠገብ ቆመዋል፡፡ ያኛው እንየው የተረበሸና የተቃጠለው ገጹ የተወለወለ ባዶ የፎቶ ማስቀመጫ “ፍሬም” መስሏል፡፡ አጠገቡ ውዳሴ በመኖሯ የሆነ አበቦች መሃል የበቀለ ለአይን አያስጠሌ ነገር መስሏል፡፡
ዋናው እንየው… ልብሱን ማስተካከል ያዘ፡፡
ቀጥ ብሎ ቆመ፡፡
ብቻውን ነው፡፡
መስተዋቱ ውስጥም ከመስተዋቱ ሌላ ማንም የለም፡፡
ሰው ራሱን ከሆነ… ራሱን ብቻ ነው እሚመስለው!
ያልቆረጠው ልቡ የተቆረጠለትን ቀጠሮ እንደ ደጀሰላም ደወል ደወለለት፡፡ ከረባቱን አጠለቀ፡፡ ጥቁር ጣልጣል ያለበትን ቀይ መደብ ከረባቱን ዳበሰ፡፡ ግራ ደረት ኪሱ ውስጥ የተቀመጠችውን ቀይ መሃረብ እስካሁን አላያትም፡፡ ማነው ያስቀመጠው…? ማስታወስ አልቻለም፤ ግን ግን… የሆነ ቀን ይሄን ከረባት ውዳሴ ቦርሳዋ ውስጥ ስትከተው አይቷል፡፡ ላውንደሪ ልትሰጥለት ነው የመሰለው፡፡
መሀረቧን መዞ ሲያወጣት አንዳች መአዛ መንፈሱን አወደው… ለመጀመሪያ ቀን ውዳሴን አንገቷ ስር ሲስማት የሸተተው ሽቶ… ከገነት አበቦች ተቀምሞ የተሰራ ሽቶ… እድሜ ዘላለሙን ከህሊናው ጐታ የማይወጣ!
ጩህ! ጩህ! አሰኘው… አናወዘው… ዝቅ ሲል… የተጣጠፈች ወረቀት እግሩ ስር ለይቅርታ እንደተንበረከከ በዳይ ተንበርክካለች፤ ቀና ሲል ያኛው እንየው መስተዋቱ ውስጥ አፍጦ ቆሟል… ሳቀበትና “አንሳው እንጂ!” አለው፡፡
አሁን ይሄን ሰው ያምነዋል…
ዝቅ አለ፡፡
በዝቅታ ውስጥ ያለ ከፍታ ልዩ ስፍራ አለው፡፡
ይቅርታሽን ተቀብያለሁ ይመስል ወረቀቷን በሁለት እጁ ድምቡሽቡሽ ህፃን እንደሚስም አይነት በፍቅር አነሳት… ባለቀለም ወረቀት… አስተጣጠፏ በስርአት የተተኮሰ ሸሚዝ ይመስላል፡፡ ቀስ ብሎ ገለጠ… ምስሏ ከሩቅ… ከሰማየ ሰማያት የምትታይ የምትመስል የዋህና ታማኝ ሴት… ፈገግታዋን ቆጥባ የፈገገች ሴት ምስል ከፊደሎቹ ትከሻ ላይ ታየው፤ ፊደሎቹን ስለሚያውቃቸው ነው ምስሉ ቀድሞ የመጣለት… አጣጣሎቹ እንደ ውዳሴ የሳቁ ናቸው፡፡
“ውዴ” የሚለውን የተሰበረን የሚጠግን ቃል… ጐላ አድርጋ የምትፅፈው እሷ ናት፡፡ የተከረከመ የፅድ አጥር የመሰለው የእጅ ፅሁፍ ላይ አፈጠጠ…!
ሲጀምር… “ውዴ…” ይላል…
“ለምን ስትል ይከፋሃል… እኔ ሁልጊዜ አጥፊህ ነኝ… አንተ ደግሞ በይቅርታህ ላጲስ ስህተቴን ታፀዳልኛለህ… አውቃለሁ… ትወደኛለህ… አውቃለሁ እወድሃለሁ፤ እናውቃለን እንፋቀራለን… ስለምን ትከፋብኛለህ…? አንተን ከፍቶህ ከማይ… ለምን ቀኔን አይቀሙኝም! ያን ስላንተ እመርጣለሁ፡፡
ውዴ፡-
ስወድህ እኮ መጠንና ልክ የለውም… በወደድኩህ መጠን ሰፍሬ ሳስበው መልሼ እጥፉን እወድሃለሁ፡፡ መለኪያው ምንም ነው፡፡ ይሄ ነው አይባልም መጠኑ… ስትስቅልኝ እስቃለሁ… ሲከፋህ ግን ጨረቃ እግሬ ስር ተንበርክካ ብትለምነኝ እንኳ አልስቅም፡፡ ደስታ ከኔ ትርቃለች፡፡ አንተን ሲከፋህ እምነጠቀው ነገር ይበዛል፡፡ እየሆንኩ ያለውን ሳስበው… እማልሆንልህ እንደሌለ፣ ይበልጥና ላንተ ስል መራራውን ለማጣፈጥ እጥራለሁ፡፡ ደግሞ አብረኸኝ ካለህ ምንም ነገር ሊመረኝ አይችልም፡፡ ጣፍጠህ ታጣፍጠኛለህ፡፡
ውዴ፡-
አውቃለሁ… አስደስቼህ አላውቅም… አንተኮ ነህ የቀን ተቀን አረሜን ነቅለህ፣ እንክርዳድ አልባ መልካም ፍሬ ምታደርገኝ፡፡
አንተ’ኮነህ… አሸዋ ላይ ተተክዬ እምለመልም አበባ ምታደርገኝ…
አንተ’ኮነህ… ሳቄን እንደሚጣፍጥ ሙዚቃ እምትቀምምልኝ…
አንተ’ኮነህ… መኖሬን እንደውብ ግጥም በዜማ አሳምረህ ምጣኔውን አስተካክለህ… ስልት ባለው ክራር አጅበህ… ለነፍስ ጆሮ እንዲመጥን አድርገህ ምታነበኝ…
አንተ’ኮነህ… መውደቄን ወድቀህ ምታቆመኝ…
አንተ’ኮነህ… እንባዬን አብሰህ አይኖቼን ስመህ “እዪ” ምትለኝ…
አውቃለሁ… ታውቃለህ እንደምንፈቃቀር…፤ ስለምን ያ ሁሉ ጉልበትህ ዝሎ ትከፋብኛለህ…? ስትወደኝ መጠንና ልክ የለውም፡፡ በወደድከኝ መጠን ሰፍረህ ስታስበው መልሰህ እጥፉን ትወደኛለህ፡፡
አውቃለሁ፡፡
መለኪያህ ይቅርታ ነው፡፡
ስህተቴን በይቅርታህ መደምሰሻ አሻራው ሳይገኝ እንደምትደመስስልኝ…
ስለማውቅህ… አውቃለሁ፡፡
ውዴ…
ስለምን ሰዎች በፍቅር መኖር እየቻሉ በቁጣ ስለት አብሮ የመኖርን ገላ ቀርድደው ይጥላሉ…? ስለምን አንዱ ያንዱን ጉድፍ አያብስም…? የራሱ እንዳለ ሆኖ!
ስለምን እኔ ላንተ አንተ ስለእኔ አንኗኗርም… ሁለት የሆነ አንድነትን ስለምን በአጉል ሌላ መሻት እንደ ሰበዝ እንሰነጥቀዋለን… ስለምን…? ቀለም ያለን… አለላዋች መሆን አቃተን…፤
ውዴ፡-
እኔ አይደለሁ ደምቄ፣ አምሬ፣ እየታየሁ ህሊናህን በቅናት ጅራፍ ምገርፍህ… እመነኝ ካንተ ውጪ ለማንም አምሬ አልታይም፣ ቀድሞውኑም አንተኮ ነህ ማማሬና ውበቴ፡፡
ውዴ፡-
አንተ’ኮ ለእኔ ቤተክርስቲያን እንደሚሰጥ ከንፁህ ማሳ በቅለህ የተገኘህ ዘቢብ ነህ… “በቃሽ” ወረቀቱን ደረቱ ላይ አጣብቆ ውዳሴን ያቀፈ እስኪመስለው ተጠመጠመበት፡፡ “ለምን እናት…? ለምን…? የእኔን ቅጥ ያጣ ሃጢያት አንቺ ትሰሚያለሽ… ያንቺ ፍቅር እኮ እንደ ሞት የበረታች ናት… የእኔ ቅናት ግን እንደ ሲኦል የጨከነች ናት…! እኔ’ኮ ነኝ በዳይሽ… እኔ ነኝ ስቃይሽ… እኔ ነኝ ካስቀመጥሽኝ ቦታ በመንፈስ ተንሸራትቼ የወደቅሁት… አንቺ ምን አደረግሽ…?”
እንደረታችው ገባው… አንተ ነህ ጥፋተኛ ሳትል ፍቅሯን ፅፋ ሰጠችው… ስህተቱን መዞ አወጣ፡፡ ደብዳቤዋን ሳመው… እቅፍ አድርጐ ተንበረከከ… ደጋግሞ ደጋግሞ “ለምን…! ለምን…! ለምን…!” እያለ ጮኸ… ዘቢብነቷ ጣመው… ናፈቀችው… ስርዝ ድልዝ የበዛበትን ልቡን በንፅህናዋ አረመችው፡፡ እሷ ዘቢብ ነበረች… እንዳልበሰለ ኮሽም የሚኮመጥጥ ስሜቱን ያጣፈጠችለት… ባዶ እግሩን የደቀቀ ጠርሙስ ስባሪ ላይ ሲራመድ ተነጥፋ እሷን ተራምዶ ነው የቆመበት ቦታ ላይ የቆመው፡፡ እሷ ስለሆነች ነው አሁን የሆነውን የሆነው፡፡ አጥፍቶ ልሂድ ባይን “መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ” ሳይሆን፣ ተበዳይ በዳይ መስሎ ይቅርታ ሲጠይቅ፣ አስረዝመው ያሰሩትን በእምነት ይፈቱታል፡፡ ሐገርም እንዲያ ናት… እንደ ልባም ሴት… “ስለምን” እያለች እምትለምን፡፡ ስለ አንድ ልጇ መውደቅ እምትሰበር፣ በእንባዋ መሃል ሳቅ እምትፈትል… “ውዴ” እያለች ልጆቿን እምትጠራ…
እንየው፤ በሁለት እጁ ግጥም አድርጐ የያዘውን ደብዳቤ ተመለከተ… በእንባው በስብሷል… ታሪክ ነበር… ይብዛም ይነስ እያንዳንዱ ሰውና ሃገር ታሪክ አለው፡፡ ፊደሎች ጠቀሱት… ፈገገ፡፡ የምርም ይቅርታ ነበረባቸው፡፡ የምርም ሰው መሆን ነበረባቸው፡፡ የምርም ያዘመመ ጐጆን ቀጥ አድርገው የያዙ ባላዎች ነበሩ፡፡
ከአይኑ አቆማዳ የሚንጠባጠቡት እምባዎች መዳፉ ላይና ከበሰበሰው ደብዳቤ ላይ ባዶ ስፍራ መርጠው የሆነ ነገር እየፃፉ አያቸው…
መዳፉ ላይ፡-
“የጠቢባን ልብ በለቅሶ ቤት ነው፡፡ የሰነፎች ልብ ግን…በደስታ ቤት ነው፡፡ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሳፅ መስማት ይሻለዋል፡፡ በሰነፎች መካከል ከሚጮህ ከገዢው ጩኸት ይልቅ የጠቢባን ቃል በፀጥታ ትሰማለች፡፡ ከጦር መሳሪያዎች ይልቅ ጥበብ ትሻላለች… አንድ ኃጢያተኛ ግን ብዙ መልካምን ያጠፋል…” ይላል፡፡
ደብዳቤው ጐን ላይ ደግሞ፡-
“የእግዚአብሔር መስዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፡፡ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም፡፡”
***
“ሰው በልቡ አምኖ ይፀድቃልና… በአፉም መስክሮ ይድናልና…”
በሩ ተንኳኳ…
አይኖቹን በእንባ እንደ ኳለ… በሩ ላይ ወረወራቸው…
“ግቡ…”…
የልቡ በር ተከፈተ…፡፡

Read 4166 times