Saturday, 20 July 2013 10:46

ዊቴከር የሰራበት ፊልም በርእስ ኩረጃ ተከሰሰ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኦስካር ተሸላሚው ፎረስት ዊቴከር በመሪ ተዋናይነት የሰራበት አዲስ ፊልም ርእሱ ተኮርጇል በሚል መከሰሱን ሎስ አንጀለስ ታይምስ ገለፀ ፡፡ “ዘ በትለር” የተባለው የፊልሙ ርእስ እ.ኤ.አ በ1916 ዓ.ም ከተሰራ ድምፅ አልባ ፊልም የተወሰደ ነው የሚል ነው ክሱ፡፡ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም ለእይታ የሚበቃው ፊልሙ፣ በተመሰረተበት ክስ ከተሸነፈ ርእሱን ለመቀየር ይገደዳል፡፡ “በሲኒማው ኢንዱስትሪ ታሪክ ለ122 ጊዜያት ርእሶች ተደጋግመዋል፣ ተመሳስለው ተገኝተዋል” ይላል ፊልሙን የሰራው የዌይንስተን ኩባንያ ስራ አስኪያጅ - “ዘ በትለር” ፊልም ላይ የተለየ ነገር መነሳቱ አግባብ አይደለም በሚል ሲከራከር፡፡
በ25 ሚሊዮን ዶላር በጀት በዋርነር ብሮስ የተሰራው “ዘ በትለር”፤ ለስምንት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በአገልጋይነት ስለሰራ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ የህይወት ታሪክ ያሳያል፡፡ ፎረስት ዊቴከር በዚህ አዲስ ፊልሙ ለኦስካር የሚያበቃ የትወና ብቃት ማሳየቱን የጠቀሰው ሎስ አንጀለስ ታይምስ፤ በዚሁ ፊልም ላይ ኦፕራ ዊንፍሬይ፤ ሊያም ኔሰን እና ሮቢን ዊልያምስ መተወናቸውን አመልክቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 “ዘ ላስት ኪንግ ኦፍ ስኮትላንድ” በተባለው ፊልም ላይ የኢድ አሚንን ገፀባህርይ በመጫወት በምርጥ ተዋናይነት ኦስካር የተሸለመው ፎረስት ዊቴከር፤ በተመሳሳይ የጎልደን ግሎብ እና የባፍታ ሽልማቶችንም ወስዷል - በምርጥ ተዋናይነት፡፡ የ52 ዓመቱ የፊልም ባለሙያ ከተዋናይነቱ በተጨማሪ በፊልም ፕሮዱዩሰርነትና ዳሬክተርነትም ይታወቃል፡፡

Read 1387 times