Print this page
Saturday, 20 July 2013 11:19

‹‹silent killer (ዝምተኛው ገዳይ)...>>

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(2 votes)

<> ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ ከላይ ያነበባችሁት ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ ለዚህ አምድ አዘጋጅ ከሰጡት ማብራሪያ የተወሰደ ነው፡፡ ዶ/ር ሙሁዲን የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት ሲሆኑ የሚሰሩት በኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል እንዲሁም ሀያት እና ቅዱስፓውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ በአስተማሪነት ነው፡፡የደም መርጋትን እንደበሽታ ከመቁጠር አስቀድሞ ተፈጥሮአዊውን ሁኔታ ኢንካርታ 2009/ እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡ Thrombocytes, ወይም platelets በሚባል የሚታወቁ ትናንሽ እና ቀለም የሌላቸው ክብ ቅርጽ የሆኑ ህዋሳት በደም ውስጥ በብዛት ይገኛሉ፡፡

እነዚህ አካላት በማንኛውም ጊዜ የደም ስር በሚቆረጥበት ወይንም ደም በሚፈስበት ጊዜ ደምን ከመፍሰስ ለማዳን እንዲረጋ የማድረግ ስራ ያላቸው ናቸው፡፡ቅቁሮ..ስቁስ..ቋ ደም ቅዳና ደም መልስ የተባሉት የደም ስሮች ጉዳት እንደደረሰባቸው ሲያውቁ ወዲያውኑ እርስ በእርሳቸው በመጣበቅ ወይንም አንዳቸው በአንዳቸው ላይ በመውጣት ወደተቆረጠው የደም ስር በመሄድ አካባቢውን ይዘጋሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ ደም እንዳይፈስ በርከት ያሉ መሰሎቻቸውን ወደ አካባቢው እንዲመጡ እና መፍሰስን እንዲያቆሙ እገዛ እንዲያደርጉ በደም ውስጥ መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡ ይህ ጤነኛውና የሚፈለገው የደም መርጋት ሲሆን ጤነኛ ያልሆነውና በበሽታ መልክ የሚገለጸው የደም መርጋት በዶ/ር ሙሁዲን አብዶ እንደሚከተለው ተገልጾአል፡፡

ደም በደም ስሮች አማካኝነት የፈሳሽ ቅርጽ ይዞ እንደልብ እየተዘዋወረ መደበኛ ስራውን መስራት የሚገባው ሲሆን ያ ሳይሆን ሲቀርና ወደ መርጋትና አንዳንዴም ጠጥሮ የደም ስሮችን ሲያውክ እንዲሁም ሂደቱን ወይንም ዝውውሩን ሲያስተጉዋጉል የደም መርጋት ተከሰተ ይባላል፡፡ ማስተጉዋጎል ብቻም ሳይሆን ሕመም የሚፈጥር ሲሆን በተለይም የደም መልስ በሚባለው የሰውነት ክፍል ውስጥ መርጋት ሲፈጠር በተለያየ ምክንያት ከንቅላት ወይንም ሳንባ አካባቢ ከሚገኙ ትናንሽ የደም ስሮች በማለፍ እስከሞት የሚያደርስ ከፍተኛ አደጋ ይፈጥራል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች እናቶችን ለሞት የሚያበቁ ከሚባሉ መካከል የሚጠቀስ ሕመም ነው፡፡ ይህ በሽታ ባደጉት አገሮች በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ በመሆኑ ለሞት ምክንያት መሆኑም እንዲሁ ወርዶ ይገኛል፡፡

እንደኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ግን በሆስፒታል ውስጥ ከሚሞቱ እናቶች በሚወሰደው መረጃ መሰረት እስከ 20 ኀየሚሆነው የእናቶች ሞት በደም መርጋት በሽታ ምክንያት በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ለእናቶች ሞት ምክንያት የተባሉት መድማት፣ መመረዝ፣ከወሊድ ጋር የምጥ መርዘም፣ ከውርጃ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችና የመሳሰሉት በምእተ አመቱ የልማት ግብ ትኩረት እንዲደረግባቸው አጽንኦት ቢሰጣቸውም የደም መርጋትም አንዱ በከፍተኛ ሁኔታ እናቶችን ለሞት የሚያበቃ እና ትኩረትን የሚሻ በሽታ ነው፡፡ የደም መርጋት ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር የመከሰቱ ሁኔታ ቀደም ባሉት ዘመናትም የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን ካለው የአኑዋኑዋር ዘዴ ጋር በተገናኘ እጅግ ተስፋፍቶ እና ለብዙዎች ታማሚነት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ምክንያቶቹም የሚታወቁ ናቸው፡፡ የደም ዝውውርን የሚያስተጉዋጉሉ ተብለው የሚጠቀሱት ምክንያቶች በዋናነት በሶስት ይከፈላሉ፡፡

* የደም ዝውውሩ በትክክለኛው መንገድ መሆን ሲገባው ነገር ግን ሲገታ፣

* በደም ውስጥ የደም መርጋትን አጋጣሚ የሚጨምሩ ነገሮች በሚጨምሩበት ጊዜ፣

* በደም ስር ውስጥ ያሉ ተፈጥሮአዊ አካላት በሚጎዱበት ወይንም አደጋ በሚደርስባቸው ጊዜ፣ ከላይ የተጠቀሱት ሶስት ምክንያቶች እርስ በእርሳቸው በሚደጋገፉበት ጊዜ ውጤቱ የደም መርጋት በሽታ ይሆናል፡፡ በተለይም በእርግዝና ወቅት ተጠቃሾቹ ምክን ያቶች እንዲከሰቱ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ በርካታ አጋጣሚዎች የሚኖሩ በመሆኑ በበሽታው ለመያዝ ቀላል ይሆናል፡፡ አንዲት ሴት በእርግዝና ላይ ከሆነች እና በወሊድ ወቅት ሊያጋጥሙዋት ከሚችሉ የጤና እክሎች አንዱ የደም መርጋት ነው ፡፡ በዚህ ወቅት የደም መርጋት በሽታ እንዲከሰት የሚያደርጉ የተለያዩ አጋጣሚዎች በመኖራቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡

•በእርግዝና ጊዜ ሰውነት በራሱ ደም እንዳይፈስ ለመከላከል ሲል የሚያዘጋጃቸው የደም መርጋት ተፈጥሮአዊ ሂደቶች ይጨምራሉ፡፡

•እርግዝናው ጊዜውን እየጨመረ በሚመጣት ጊዜ ጽንሱ በማደጉ ምክንያት በሚፈጠረው ጭነት ምክንያት ደም መልስ የሚባለው አካል በትክክል ስራውን እንዳይሰራ የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖራል

•በእርግዝና ወቅት በምጥ ሰአት ወይንም በውርጃ ጊዜ በተለይም ደግሞ ከወሊድ በሁዋላ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የደም መርጋት ሂደቱን የሚያባብሱ ነገሮች አሉ፡፡ በተለይም...

•ከምጥ ጋር በተያያዘ የደም ስሮች መጎዳት፣

•በኦፕራሲዮን መውለድ ፣ •የሰውነት ውፍረት፣ •ተገቢውን አካላዊ እንቅስቃሴ ካለማድረግ ...ወዘተ ጋር በተያያዘ ወላድዋ የደም መርጋት ሕመም ሊገጥማት ይችላል፡፡ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ እንዳብራሩት በአብዛኛው ጊዜ የደም መርጋት በሽታ ምክንያቱ የሚታወቅ እና ሊከላከሉት የሚቻል ሲሆን ከጥንቃቄ ጉድለት በርካታ እናቶችን ለጉዳት ሲዳርግ የሚታይ በእንግሊዝኛውም Silent killer (ዝምተኛው ገዳይ) እስከመባል የደረሰ ነው፡፡ በሽታው የሚከሰተው በአብዛኛው ደም መልስ በሚባለው የሰውነት ክፍል ሲሆን በይበልጥ የሚጀምረውም ከታችኛው የሰውነት ክፍል ከእግር አካባቢ እንዲሁም በማህጸን ዙሪያ አካባቢም የሚጀምር ሲሆን በተለይም ሂደቱ ወደሳምባ ወይንም ወደጭንቅላት በማለፍ በትናንሽ የደም ስሮች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እና የመተንፈስ ችግር ብሎም የሞት አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በማህጸን ውስጥ እና ዙሪያውን ባሉ አካላት ላይ በሚፈጠርበት ጊዜ ወደ እንግዴ ልጅ በማለፍ ጽንስንም ሊጎዳ የሚችልበት አጋጣሚ ይስተዋላል፡፡ የደም መርጋትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ምክንያቶች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ውፍረት ፣እንቅስቃሴ አለማድረግ ፣መተኛት የመሳሰሉት ከላይ ተገልጸዋል፡፡ አንዲት ሴት በተለይም በኢትዮጵያ ስትወልድ ከሚደረግላት እንክብካቤ መካከል ምግብ ከለመደችው መጠንና አይነት በላይ መስጠት እና ለእረፍት መተኛት እንዳለባት ይነገራል፡፡ ይህንን ዶ/ር ሙሁዲን ይቃወሙታል፡፡ ‹‹...እንደባህል ሆኖ በኢትዮጵያ የወለደች ሴት መታረስ አለባት ከሚል አስተሳሰብ ብዙ እንድትተኛ ቅባት ያላቸውን ምግቦች ከመጠን በላይ እንድትመገብ ይደረጋል፡፡ በተለይም መኝታው እንደእረፍት የሚቆጠርበት መንገድ ትክክል አለመሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ እረፍት ማለት መኝታ አይደለም፡፡ ማረፍ ማለት ሰውነት እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ ለተለያዩ በሽታዎች እንዲጋለጥ ማድረግ ተብሎ ሊተረጎም አይገባም፡፡

ማረፍ ማለት ቀደም ሲል ከነበረው አስጨናቂ ነገር አእምሮን ገለል አድርጎ ጥሩ ጥሩ ነገር እያሰቡ አዲስ ስላገኙት ነገር በተለይም ስለወለዱት ልጅ ምቹ ነገርን እያሰቡ ቀድሞ ከነበረው ውጥረት የበዛበት የኑሮ እንቅስቃሴ እራስን ገለል አድርጎ በመጠኑ እየተንቀሳቀሱ ለተወሰነ ጊዜ እራስን ማደስ ተብሎ ቢታሰብ ይበጃል፡፡ ከወለዱ በሁዋላ መተኛት የሚለው እጅግ ጎጂ የሆነና የተሳሳተ አስተሳሰብ መሆኑን ሁሉም ቢረዳው መልካም ነው፡፡ ስለዚህ አንዲት ሴት ከወለደች በሁዋላ ለተወሰነ ጊዜ እረፍት አድርጋ በየአንድ እና ሁለት ሰአቱ ልዩነት ለአስራ አምስት እና ሰላሳ ደቂቃ ያህል ከአልጋ እየተነሳች ብዙ ሳትርቅ ከክፍል ክፍል ዞር ዞር ማለት እና አቅሙዋም በጨመረ ጊዜ በደንብ በቤቷ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ማለት ይጠበቅባታል፡፡

ወደምግቡ ሁኔታ ስንመለስም... በወለዱ ጊዜ የሚመገቡት ምግቦች ስብ እና ጣፋጭ የበዛባቸው እንዲሆኑ አይመከርም፡፡ ይልቁንም በፈሳሽ መልክ የተዘጋጁ ምግቦችን እንዲሁም መጠጦችን እየወሰዱ በወለዱ ጊዜ የሚሰሩ የአካል እንቅስቃሴዎችን በየደረጃው በባለሙያ ምክር መስራት ሊከሰት የሚችለውን የደም መርጋት ሊያስቀር ይችላል፡፡ በተለይም ኦፕራሲዮን ሆነው የወለዱ ሴቶች ከቁስሉ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ምክንያቶችን ለራሳቸው እየፈጠሩ ፍርሀት ሰለሚያድርባቸው እራሳቸውን ከእንቅስቃሴ ሊገድቡ ስለሚችሉ የደም መርጋት ክስተቱን ሊያባብሱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ማንኛዋም ወላድ የመጀመሪያዎቹን ስምንት ሰአታት ካረፈች በሁዋላ በየደረጃው የሰውነት ክፍሉዋን ማንቀሳቀስ ይጠበቅባታል...›› ብለዋል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ፡፡ ይቀጥላል

Read 5244 times