Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 19 November 2011 14:30

የኢህአዴግ ባለስልጣናት የሥልጣን ፈተና እየወደቁ ነው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የሃይማኖት ተቋማት ሃላፊነታቸውን ቢወጡ ፀረ - ሙስና ኮሚሽን አያስፈልግም ነበር 
በኢህአዴግ 20 ዓመት የስልጣን ዘመን “ስትሬት A” ያመጣው ባለስልጣን ይነገረን …
በባለስልጣናት ግምገማ ከ”A” በላይና ከ“C” በታች አይሰጥም …(ለተማሪ ዐ እና 100 አይሰጥም)
ከትላንትና በስቲያ ተሲያት ላይ ነው - አንድ ወዳጄ ቤት ተሰይሜአለሁ፡፡ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች እየተነሱ ይጣላሉ፡፡ ኢህአዴግ ይብጠለጠላል፡፡ ተቃዋሚዎች ይተቻሉ፡፡ ካፒታሊዝም ይነቀፋል፡፡ ሶሻሊዝም እርግማን ይወርድበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሥነፅሁፍ ይገመገማል፤ ይተነተናል፡፡ ግሽበቱ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ ባለ ሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ከሥልጣን የተነሱ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት … ምን ያልተነሳ አለ፡፡

የአገራችን ጉዳይ የመሰለንንና ያገባናል የምንለውን ጉዳይ ሁሉ ዳስሰነዋል - በስሱ፡፡ ማዶ ጥግ ላይ የተከፈተው አንዱ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ደግሞ ሌላ የአገር ጉዳይ ይዳስሳል - እንደኛ በስሱ ግን አይደለም፡፡ ጠበቅ አድርጐ ይዞ ነው፡፡ ለሬዲዮው ጆሮዬን ያዋስኩት መሃል ላይ ስለነበር ከየትኛው FM እንደሚሰራጭ አላውቅም፡፡ ተናጋሪውንም እንዲሁ፡፡ ብቻ የሃይማኖት መምህር (አዋቂ) እንደሆኑ ገብቶኛል፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስትያንን ወክለው የቀረቡ መሆናቸውን ተገነዘብኩኝ፡፡ የሰማሁት ጥቂት ነው - ከንግግራቸው፡፡ የቀሰምኩት ቁም ነገር ግን አንዳንድ ሰው ሙሉ ቀን ተናግሮም የማይገኝ ነው፡፡
ገና ማዳመጥ ስጀምር መምህሩ የሃይማኖት ተቋማትን እየወቀሱ ነበር፡፡ ከምዕመናን ገንዘብ አሰባስቦ እስር ቤት ውስጥ ቤ/ክርስትያን ለማሰራት ተፍ ተፍ የሚሉ የሃይማኖት ሰዎችን ክፉኛ ይተቻሉ - መምህሩ፡፡ እስር ቤት ውስጥ ቤ/ክርስትያን ከማሳነፅ ወደ ወህኒ የሚወርደውን የወንጀለኛ ቁጥር እንቀንስ የሚሉት መምህሩ፤ የወንጀለኞች ቁጥር መበርከት የሚያሳየው የሃይማኖት ተቋማት በአግባቡ ሥራቸውን እያከናወኑ አለመሆኑን ነው ብለዋል፡፡ ከሞራልና ሥነ ምግባር አኳያ ሁሉም ሃይማኖቶች ልዩነት እንደሌላቸው በመጥቀስም አማኞቻቸውን ከወንጀልና ከምግባረ ብልሹነት በመከላከል ወደ ወህኒ የሚወርዱ ወንጀለኞችን ቁጥር ለመቀነስ መትጋት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ የሃይማኖት ትምህርትን በአግባቡ ስላልሰጡና ምዕመናኑን ስላላስተማሩ እስር ቤቶች እንዲስፋፉ፣ የእስረኞች ቁጥር እንዲጨምር የራሳቸውን አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው ሲሉ ተቋማቱንና የሃይማኖት መሪዎችን ተችተዋል፡፡ በእኚህ መምህር አባባል የሃይማኖት ተቋማት የሃይማኖት አባቶች መነታረኪያ ሳይሆኑ የምዕመናን ሥነ ምግባር ማነፂያ ስፍራዎች ናቸው ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት በርትተው ሃላፊነታቸውን ቢወጡ ለወህኒ ቤቶችና ለፖሊስ ሃይል የሚመደበው ወጪ ይቀንስ ነበር ሲሉም አክለዋል - መምህሩ፡፡
በዓለም ደረጃ ኒውክሌር ለመገንባት የሚውለው ዕውቀትና ሃብት የስንት ሚሊዮን ህፃናትን ቀለብ ወይም የክትባት ወጪ ሊሸፍን እንደሚችልም በቁጭት ተናግረዋል፡፡ ከወዳጄ ቤት ወጥቼ ወደ ቤቴ ሳዘግም የሃይማኖት ሊቁ በኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ የተናገሩትን መሬት ጠብ የማይል ቁምነገርና ጠሊቅ ሃሳብ በአዕምሮዬ እያብሰለሰልኩ ነበር፡፡ እውነት እኮ የሃይማኖት ተቋማት የሥነ ምግባር ትምህርት የሚሰጡበት የተመቻቸ መድረክ ወይም ዝግጁነቱ ቢኖራቸው የወንጀለኞችን ቁጥር መቀነስ ብቻ ሳይሆን ብዙ የአገራችንን ችግሮች ይቀርፉ ነበር ብዬ ማውጠንጠን ጀመርኩ፡፡
ምን አልባትም አንዳንድ ከፍተኛ የመንግስት በጀት የሚመደብላቸው የመንግስት መ/ቤቶች ላያስፈልጉም ይችሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ የሙስና ወንጀል የሚፈፅሙ ዜጐች እንዳይኖሩ ተቋማቱ ታትረው ከሰሩ ሙስና ይገታል፡፡ ይሄ ማለት የሥነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አያስፈልግም ነበር፡፡ መቼም ሙስና ሳይኖር ወንጀሉን የሚመረምርና የሚያጣራ መ/ቤት አያስፈልግም አይደል!
ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ምዕመኑን በሚገባ ካስተማሩ ህዝባቸውን የሚዋሹ ፖለቲከኞች አይፈጠሩም፡፡ ምርጫ ማጭበርበር የሚሉት ነገር አይነሳም፡፡ በሥልጣን አላግባብ መጠቀም፣ ሰብዓዊ መብቶችን መጣስ፣ ሥልጣንን የሙጥኝ ማለት፣ ለፖለቲካ ሥልጣን ሲሉ ሴራ መጠላለፍ ወዘተ አይኖሩም ነበር፡፡
ክፋቱ ግን በተለይ የአንዳንድ ሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እንኳንስ ምዕመኑን በሥነ ምግባር ትምህርት ከጥፋትና ከክፋት ሥራ ሊያድኑ ቀርቶ ራሳቸውም ትምህርትና ምክር የሚሹ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ተግሳፅም ጭምር፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ከአገሬ ቋንቋዎች ውስጥ የምደፍረው ይሄን በየሳምንቱ “ፖለቲካ በፈገግታ”ን የምጽፍበትን የአማርኛ ቋንቋ ብቻ ነው፡፡ ዕድሜ ለምርጥ ወዳጄ ግን ሰሞኑን በቲቪ የትግርኛ ፕሮግራም አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ የተናገረውን ተርጉሞ ነገረኝ፡፡
ጋዜጠኛው የትግራይ እግር ኳስ የተዳከመበትን ምክንያቶች በተመለከተ ባለድርሻ አካላትን ካወያየ በኋላ ውይይቱን ሲቋጭ ዘርፉ የተዳከመው ልማታዊ እግር ኳስ ባለመኖሩ ነው እንዳለ ወዳጄ ቱርጅማን ሆኖ ነግሮኛል፡፡
መቼም የአገሪቱ ስፖርት የሰበብ እጥረት አጋጥሞት አያውቅም አይደል፡፡ እኔም እቺን ይዤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ2 ዓመት በላይ መንግስት አልባ ከነበረችው ሶማሌ ጋር ተጋጥሞ አቻ (ዜሮ ለዜሮ) የወጣው፣ እግር ኳሱ ልማታዊ ስላልሆነ ነው ብዬ አሰብኩ - በሆዴ በሌላ አባባል አሁን የምናየው የአገራችን እግር ኳስ “ኪራይ ሰብሳቢ” ነው ማለት ነው፡፡ ሌሎች ችግሮቻችንንም በዚሁ መነጽር ልንተነትን እንችላለን፡፡ መቼም የራሳችንን ችግር ኒዮሊበራሊስቶች እንዲተነትኑልን አንጠብቅም፡፡ ይሄማ ኪራይ ሰብሳቢ ከመሆን አይተናነስም፡፡ ለምሳሌ ከሰሞኑ ተመክሮዬ ተነስቼ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮችን ስተነትነው ዋናው እንከን ልማታዊ ፖለቲካ መፍጠር አለመቻላችን እንደሆነ ደርሼበታለሁ፡፡ በነገራችን ላይ እግር ኳሳችን ልማታዊ ባይሆንም በሌላ ወገን ግን አትሌቲክሱ ልማታዊ እንደሆነ የሰሞኑ ተመክሮዬ ይጠቁመኛል፡፡ ለዚህም ነው አትሌቶቻችን ሁሌም አሸናፊ የሚሆኑት፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ልማታዊ የምትለዋ ቃል ፍቺዋ እስካሁን በቅጡ እንዳልገባኝ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ ፍቺው ባይገባኝም ግን ቃሉዋ ደስ ስለምትለኝ ሁሌም እጠቀምባታለሁ!! ለነገሩ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች ኢህአዴጐችም የገባቸው አይመስለኝም፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም ከልማታዊነት ጋር የሚተዋወቁ እንዳልሆኑ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይፋ የሚደረጉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢህአዴግ ውስጥ ትንሽ የማይባሉ ኪራይ ሰብሳቢዎች ተሰግስገዋል፡፡ ይሄን ወቀሳ የሚያነቡ ሃሳዊ ኢህአዴጐች ግስላ እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ነው፡፡ ለምን ብትሉ … ነገርዬዋ እውነት ናታ!
ሃቀኞቹ ኢህአዴጐች ግን በሃዘን ጭንቅላታቸውን ደፍተው ያቀረቅራሉ፡፡ ኢህአዴግ በረሃ ለበረሃ የታገለው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው አባላት ለማፍራት ሳይሆን ልማታዊ ካድሬዎችን ፈጥሮ ልማትን ለማስፋፋት ነበር፡፡ (ነበር ባይሰበር!) ግን ከፓርቲው አቅም በላይ በሆነ ያልታወቀ ምክንያት ኪራይ ሰብሳቢዎች እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ሃሜት እንዳይመስልብኝ ግን መረጃዎችን ልጥቀስ፡፡ (በነገራችን ላይ እኔ ጋጠወጥ ጋዜጠኛ አይደለሁም)
በዚህ ሳምንት በወጣ ዜና “የአዲስ አበባ አስተዳደር 21 ሃላፊዎች በሙስና እንዲጠየቁ ተወሰነ” የሚል መረጃ ተሰራጭቷል፡፡ ይታያችሁ … ከመዲናችን አስተዳደር ብቻ 21 በኪራይ ሰብሳቢነት የተጠረጠሩ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት አሉ ማለት ነው! እንኳን ሃቀኞቹን ኢህአዴጐች ቀርቶ እኛ ሲቪሎቹንም የሚያስጮህ ነው .. እሪሪሪ .. የሚያስብል፡፡ “አስተዳደሩ ባካሄደው ግምገማ በሥራ አስኪያጅ መ/ቤት ሥር ባሉ መዋቅሮች ውስጥ ሲሰሩ የቆዩት 21 የሥራ ሃላፊዎች እንዲጠየቁ የስም ዝርዝራቸውን ለሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማስተላለፉን ምንጮች ገልፀዋል” ይላል ዜናውን የዘገበው አንድ የአማርኛ ጋዜጣ፡፡ ሃላፊዎቹ የት ሲሰሩ እንደነበር ስታውቁ ደግሞ የበለጠ ትገረማላችሁ፡፡ የከተማ ማደስና መሬት ባንክ ፅህፈት ቤት፣ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮና ክፍለ ከተሞች ናቸው ተብሏል፡፡
በአጭሩ ሁሉም ለስህተት የተዳረጉት ከመሬት ጋር በተገናኘ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመሬት ጉዳይ ጋር በተያያዘ በሙስና ተጠርጥረው ከሥልጣናቸው የወረዱ የመንግስት ባለስልጣናትን ብዛት ስትመለከቱ መሬት በእኛ አገር “ሃሺሽ” ነገር እየሆነ መምጣቱን ትረዳላችሁ፡፡ ይሄ ደግም እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ለአገርም ለዜጐችም፡፡
ሰሞኑን ለንባብ የበቃችው “ከፀሃይ በታች” የግጥምመድበል ላይ “ስህተትና ልክ” የምትል ግጥም አለች፡፡ እንዲህ ትላለች፡-
ተሳስቼ አውቃለሁ
ልክም ሆኜ አውቃለሁ
ልክ በመሆኔ ምን ተጠቅሜያለሁ?
ከመሳሳቴ ግን ብዙ ተምሬያለሁ
እቺን ግጥም እስቲ አንዴ ደግማችሁ አንብቧት፡፡ ከዛ ስለተሳሳቱት የኢህአዴግ ባለስልጣኖች ትንሽ አሰላስሉ፡፡ በሙስና የተሳሳቱት፣ በሥልጣን በመባለግ ወንጀል የፈፀሙት ሆን ብለው አይመስላችሁም? ከመሳሳት ብዙ ለመማር ፈልገው! ኢህአዴግ ነፍሴም ይሄ ስለገባው ይመስለኛል ጨክኖ የማይጨክንባቸው፡፡ እኔ የምለው ግን ከዚህ ቀደም ስለ ኢህአዴግ የግምገማ ሥርዓት ታውቁ ነበር? እውነቴን ነው የምላችሁ … እኔ ሃባ ነገር አላውቅም ነበር፡፡ ለካስ የኢህአዴግ ግምገማ ማለት ለ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና (ማርቲኩሌሽን) እንደመቀመጥ ዓይነት ነው፡፡ (ወይ ግሩም!) ቆይ ላስረዳችኋ … የከተማው አስተዳደር ከሰኔ 2003 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሂድ በቆየው ግምገማ ለተገምጋሚዎች እንደ ማትሪክ ውጤት A,B, እና C የሚሉ ውጤቶች አሽሯቸዋል፡፡ የግምገማውን ፈተና የወደቀ ባለስልጣን “C” ያገኘው ሲሆን በቀጥታ ከሥልጣን ይነሳል፡፡ “B” እና ከ“B” በላይ ያገኙ ካድሬዎችስ? በሥልጣን ይቆያሉ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ይዛወራሉ፡፡ የውጤት አሰጣጡ ግሩም ሆኖ ሳለ A+ B+ የተሰኙ ውጤቶች አለመኖራቸው ትንሽ ቅር አሰኝቶኛል፡፡ ወደ ታች ስንወርድም ለምን “D” እና “F” ውጤቶች እንደማይሰጡ ግራ ያጋባል፡፡ በእርግጥ የፈተና ውጤቱ አሰጣጥ ትንሽ ግልፅነትም ይጐድለዋል፡፡ ለምሳሌ በሥልጣን ዘመኑ ምን የፈፀመ ባለስልጣን ነው እንደ ሰቃይ ተማሪ “A” የሚያገኘው? “B” እና ”C” የተሰጣቸው ባለስልጣናት ምን በጐና ክፉ ተግባራትን አከናውነው ይሆን ይሄ ውጤት የተሰጣቸው? የአገር ደህንነትን ስጋት ላይ የሚጥል መረጃ ስላልሆነ እንደ ዜጋ ግልፅ ቢደረግልን አንጠላም፡፡ ህገ መንግስታዊ መብታችንም መሰለኝ!
የሆና ሆኖ ግን ከኢህአዴግ ግምገማ አንድ ነገር ገብቶኛል፡፡ ግምገማው የስልጣን Exam ወይም ፈተና ሊባል ይችላል፡፡ አንድ ባለስልጣን በግምገማው “C” ሲያገኝ ከሥልጣን ወደቀ ማለት ነው፡፡ “A” ያገኘው ደግም ሰቅሎ ሥልጣን ላይ ይቀራል፡፡
በግምት እንደገባኝ ከሆነ ግን ለኢህአዴግ ተገምጋሚ ባለሥልጣናት ምንም ቢሆን ከ“C” በታችና ከ “A” በላይ ውጤት አይሰጥም፡፡ ለተማሪ ዜሮ አይሰጥም እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ይሄ በዚህ እንዳለ ከሁለት ሳምንት በፊት በግምገማው “B” ያገኙት የከተማው ምክትል ከንቲባና የማስታወቂያ ቢሮ ሃላፊ አቶ ከፍያለው አዘዘ ከስልጣናቸው እንደ ተነሱ ሰምተናል፡፡ ያው “ቢ” ያገኘ ደግሞ አንድም ሥልጣን ላይ ይቆያል አሊያም ወደ ሌላ ቦታ ይዛወራል፡፡ በዚሁ መሰረት አስተዳደሩ አቶ ከፍያለው የከተማው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንዲሆኑ ጠይቆአቸው ነበር፡፡ የቀድሞው ምክትል ከንቲባ ግን አሻፈረኝ አሉ፡፡
አስተዳደሩ ግን ባለስልጣኑ በአሁኑ የሥልጣን ፈተና “B” ቢያመጡም ቀለሜዋ እንደሆኑ ያውቃል መሰለኝ ከዚህ በፊት ያልነበረ አዲስ መዋቅር በመፍጠር አቶ ከፍያለውን የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አድርጐ ሾሟቸዋል ተብሏል፡፡ ነገሩ አግራሞት የሚፈጥር ቢሆንም ለጐበዝ ተማሪ (የሥልጣን ተማሪ) የተደረገ ስለሆነ ብዙም አላስከፋኝም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለኢህአዴግ አመራሮች ጥቂት ጥያቄዎች ባቀርብ ደስ ይለኛል፡፡ ይሄ ግምገማ (የሥልጣን ፈተና) ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖችን ይመለከታል ወይስ አነስ ያሉትን ብቻ ነው? ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም ለግምገማ የሚቀመጡ ከሆነ ግን የእስከ ዛሬውን የጠ/ሚኒስትራችንን የፈተና (የግምገማ) ውጤት ባውቅ እወዳለሁ፡፡ መቼም ከ”A” በታች ከእሳቸው አልጠብቅም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል አንድም ጊዜ ወደየትም ቦታ ሳይዛወሩ በጠ/ሚኒስትርነት ለ20 ዓመት የዘለቁት፡፡ በ97ቱ ቀውጢ የምርጫ ወቅት የኢፌዲሪ ማስታወቂያ ሚ/ር የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን ከምርጫው በኋላ ከሃላፊነታቸው ተነስተው ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ የገቡት በሥልጣን ግምገማው “B” አግኝተው ይሆን ወይስ በሌላ ምክንያት? አያችሁ እንዲህ በግምት እንዳንናገር የባለስልጣኖቻችን የፈተና (ግምገማ) ውጤት ይፋ ቢደረግልን የተሻለ ይመስለኛል፡፡
በነገራችን ላይ ይሄን የኢህአዴግን የሥልጣን ግምገማ ውጤት አሰጣጥ ልምድ አሁን በህይወት ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎችም (እየከሰሙ ያሉትን አይመለከትም) ቢጠቀሙበት መልካም ሳይሆን እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡
እንግዲህ በማህበራዊም ሆነ በፍቅር ግንኙነታችንም እርስ በርስ እየተገማገምን ከA-C ያሉ ግሬዶችን መሰጣጠት ብንጀምር የሰለጠነ አካሄድ ይመስለኛል፡፡ እንዴት ማለት መሰላችሁ? ለምሳሌ በትዳር ህይወት ባል ሚስትን ወይም ሚስት ባልን ይገመግምና A ሲሰጡ ግንኙነቱ ይቀጥላል፡፡ C የተሰጠው ግን ከባልነቱ ወይም ከሚስትነቷ ትፈነገላለች፡፡
ውድ አንባብያን፡- የዛሬውን ፖለቲካዊ መጣጥፌን ገምግማችሁ ከA-C ካሉት ግሬዶች ይመጥነዋል ያላችሁትን ብታሽሩኝ እኔም ውለታዬን እመልስ ነበር፡፡ ወይም ወሮታሮውን እከፍል ነበር፡፡ ፅሁፌን የምቋጨው “ከፀሃይ በታች” ከተሰኘው የግጥም መድበል በጠቅላላው ለአፍሪካውያን የተገጠመች የምትመስል አንዲት ግጥም ለአንባቢ በመጋበዝ ነው፡፡ ”ሕልም እንኳ የታለ?” ይላል፡፡
በሕልሜ ተኝቼ፣
ሸጋ ህልም አይቼ፣
በአገሬ በአፍሪካ ዲሞክራሲ በቅሎ
ፍትህ - እኩልነት - መብቱ ተደላድሎ
ወገኔ ሲያጣጥም የሰላምን ፍሬ
ሽብር ተወግዶ በመላው አገሬ
ይህን እያለምኩኝ አልጋ ውስጥ አርፌ
ጥይት ቀሰቀሰኝ ከሞቀው እንቅልፌ
ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለአፍሪካ! ሰላም ለዓለም ህዝብ! መልካም ጊዜ!!

 

Read 5188 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 14:36