Print this page
Saturday, 27 July 2013 13:42

“ለውይይት የተዘጋ በር የለም፣ መንግሥት በሩ ክፍት ነው”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በቅርቡ በደሴ ከተገደሉት የሃይማኖት አባት ጋር ተያይዞ መንግስት በተደጋጋሚ መግለጫዎችን እያወጣ ሲሆን ተቃዋሚዎች በበኩላቸው መንግስት ከሃይማኖት ጉዳዮች እጁን እንዲያወጣ እየጠየቁ ነው፡፡ በሃይማኖትና በአክራሪነት እንዲሁም በተቃዋሚዎች አቋም ዙርያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ጋር የሚከተለውን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

መንግስት በተከታታይ ከሀይማኖት አክራሪነት ጋር የተያያዙ መግለጫዎችን መስጠቱ ለምን አስፈለገ? ጉዳዩን የበለጠ ማጋጋል አይሆንም?
ጥሩ ነጥብ ነው የተነሳው፡፡ በሃገራችን፣ ሁሉም አይነት የእምነትና ሃይማኖት ችግሮች የተከሰቱባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ አሁን ከሃይማኖትና እምነት ጋር ተያይዞ ያለንበት ምዕራፍ አዲስ ነው፡፡ እነዚያ ችግሮችም አሁን የሉም ብለን ነው የምናስበው፡፡ ህገ መንግስታችንም የሚለው ይህን ነው፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት መሪ ድርጅቱም ይሁን ተጨባጭ ተግባሩ ይሄው ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ሁላችንም እንደምናውቀው የሃይማኖቶች አብሮ በሰላም ተቻችሎ የመኖር እሴት ያለን ሃገር ነን፡፡ የተዛቡ ግንኙነቶች በህገ መንግስታችን የተስተካከሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እንዲህ አብሮ በሰላም የመኖር እሴት ባለበት ሃገር ላይ የሚመጡ ዝንባሌዎች ሃይማኖታዊ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በሌላ በኩል ግን የሃይማኖት አጀንዳ በሚነሳበት ጊዜ ሚዛናዊ የሆነ አረዳድ ለመያዝ ሰው ሊቸገር ይችላል፤ ምክንያቱም ከሃይማኖቱ ጋር ተጣብቆ ሊነሳ ስለሚችል፡፡

ትክክለኛ መረጃ ሳይያዝ በእርግጥም በሃይማኖታችን ላይ ያነጣጠረ ሰው አለ የሚል አይነት አዝማሚያና ዝንባሌ ሊፈጥር ይችላል፡፡ አክራሪነት አንዱ ጥቅም ላይ የሚያውለው ይህንን ነው፡፡ ይህ ደካማ ጎን ነው እኛን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችለው የሚል አመለካከት ነው የሚኖረው፡፡ እኛ አክራሪነትና ፅንፈኝነትን ከህገ መንግስታችን ተነስተን ነው የምንፈርጀው ብለናል። ከመፅሃፍት ወይም ከመዝገብ ቃላት ተነስተን አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም ደጋግመን እንደምናነሳው የዜጎችን የእምነት ነፃነት ህገ መንግስታችን ሰጥቷል። እንደዚህ ያልኩት በአንዳንድ ሃገሮች የተወሰኑ ሃይማኖቶች ተዘርዝረው ከዚህ ውጪ የምናውቀው ሌላ ሃይማኖት የለም ይባላል፤ እንዲያም ሆኖ ነፃነት አለ ተብሎ ይወሰዳል። የሃይማኖት እና የእምነት ነፃነት የተከበረና የተጠበቀ ነው ተብሎ ሲባል ዋነኛ መስፈርቱ ሁሉም የሚፈልገውን የኔ ነው የሚለውን እንዲያመልክ ሊፈቀድለት ይገባል፡፡ ተፈጥሮአዊ ስለሆነ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡
የአክራሪነትና ፅንፈኝነት ሂደት ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ እኛ ትክክለኛ ነው ያልነውን ብቻ ከመከተል ያለፈ ሌላ አማራጭ የለም ብሎ የሚዘጋ ነው፡፡ ሌላው የሃይማኖት እኩልነትን መቃረን፣ መንግስታዊ ሃይማኖትን መፈለግ የሚሉት ናቸው፣ የአክራሪነትና የሃይማኖት ፅንፈኝነት ማጠንጠኛ ነጥቦች፡፡
ለምንድነው ተከታታይ መግለጫዎች በሼህ ኢማም ኑር እና በአክራሪነት ዙሪያ ላይ እንዲሰጥ የተፈለገው የሚለውም ይህን ጉዳይ ግልፅ ለማድረግ ነው፡፡ መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ሲባል፣ ዜጎች በሃይማኖት ምክንያት በደል ሲፈፀምባቸው ምናልባትም አሁን እንዳየነው አይነት ግድያ ሲፈፀምባቸው ዝም ብሎ ያያል ማለት አይደለም፡፡ መንግስት እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ህዝቡን መጀመሪያ በደንብ ማስተማር አለበት፡፡ ይህ ጉዳይ ሃይማኖታዊ አይደለም፤ ህገመንግስታችንን የሚጥስ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ስንለው የነበረው በተጨባጭ እየመጣ ነው የሚለውን በተደጋጋሚ መግለጫዎች ማሳየት ከዚህ አንፃር ተገቢ ነው፡፡
እነዚህ አካላት ከኔ ሌላ መኖር የለበትም በሚለው አመለካከታቸው የራሳቸውን ሃሳብ በሌሎች ላይ በግድ ለመጫን የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ይህን ለማስፈፀም ከሚጠቀሙት ስልት አንዱ እንግዲህ የሰሞኑ የሼክ ኢማም ኑሩ ግድያ ማሳያ ነው፡፡ አልፎ ተርፎ መንግስት ነው የገደላቸው እያሉ እያስወሩም ነው፡፡ እንግዲህ ይህ የከፋ ህዝብን የመናቅ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ነው የሚያሳየው፡፡ ህዝቡን በተለይም ለሃይማኖቱ ቀና የሆነውን ወጣቱን ህብረተሰብ እንደፈለግን እናሽከረክረዋለን ከሚለው አመለካከት የመጣ ነው፣ ገድለው ሲያበቁ “ይህን ድራማ የሰራው መንግስት ነው” ያሉት፡፡ መንግስት እዚህ እንካ ሰላንቲያ ውስጥ የሚገባበት ምክንያት የለም፡፡ በማህበራዊ ድረገፆችም ሆነ በተለያዩ መድረኮች ይህ ያልተገባ እንካ ሰላንቲያ እንዲካሄድ እየፈለጉ ነው፡፡ ይህን ብዥታ ለማጥራት ደግሞ… በመንግስት በኩል ህዝባችን ግልፅና የጠራ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ጉዳዩን አጉልቶ ማሳየትም አስፈላጊ ነው፡፡
የምናምነው ደግሞ አክራሪነትና ፅንፈኝነት መጨረሻው አሸባሪነት መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ነው ስንለው የነበረው፤ በተጨባጭም የታየው ይሄው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉንም ህዝበ ሙስሊምም ሆነ የሀገራችንን ህዝቦች የሚወክል አይደለም፡፡ ዝም ብሎ ቢተውም ድራማውን እውነተኛ አድርገው ማስወራታቸው ስለማይቀር ነው አጉልቶ ማውጣት ያስፈለገው፡፡ ለምንድን ነው መንግስት ልዩ ትኩረት የሰጠው ለሚለውም፣ በጉዳዩ ላይ መንግስትም ሆነ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን እጅግ የሚፈታተን ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ የህግ የበላይነትንና ህገ መንግስታዊ ስርዓትን የማፃረር ስራ ነው የተሰራው። ህገመንግስታዊ ስርዓታችንን የሚፃረር ስራ በሚሰራበት ጊዜ መንግስት ዝም ብሎ ቀላል አድርጎ ሊያይ አይችልም፡፡
አሁን ሼህ ኢማም ኑሩ የመኖርና፣ በፈለጉት ሴክት የእምነት ክፍል ውስጥ የመሆን መብታቸው ተደፍሯል፡፡ መንግስት እንዲህ አይነት ህገመንግስታዊ የመብት ጥሰት በሚያጋጥምበት ጊዜ፣ የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅና ጥቃቶችን የመከላከል ሃላፊነት አለበት፡፡ በአንድ የሃይማኖት ምሁር/አባት/ የተፈፀመው ብቻ አይደለም መታየት ያለበት። በዚህ አይነት መንገድ የተሟላ የህግ የበላይነት ሳይከበር ቢታለፍ፣ የዚህ አይነት ነገሮች ይለመዳሉ። በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች እንደገለፁትም፣ በብዙ ሰዎች ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ሊፈፀም ሲቀነቀን ነበረ፡፡ በዚህ ዙሪያ ላይ ለህብረተሰቡ የተሟላ መረጃ አቅርቦ፣ በቂ ግንዛቤ ፈጥሮ፣ ህዝቡ በደንብ ተወያይቶ፣ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ መድረሱ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
እንደዚህ ጉዳይ ለምን ይጦዛል የሚሉ አካላት ሁለት አይነት መልክ ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ። አንደኛውና የመጀመሪያው በአክራሪነት ላይ የተሟላ ግንዛቤ አለመያዝ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁንም ከሃይማኖት አጥባቂነት ጋር አያይዘው እያዩ፣ ሃይማኖትን ባጠበቁት ላይ እየመሠላቸው፣ በቅንነት “መንግስት ለምን በእዚህ መልኩ ይሄዳል” የሚሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሁለተኛው ክፍል ግን ሆን ብሎ እና አውቆ አሁንም የተሰራውን እና ያጀበውን ስራ በማድበስበስ እንዲታለፍ ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ዋና አላማቸው ጉዳዩ ተሸፋፍኖ እንዲታለፍ የሚሹ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ከህገመንግስታዊ ስርዓታችን ጋር የማይታረቅ ቅራኔ ያላቸው ናቸው፡፡
መንግስት ጉዳዩን በጥንቃቄ አልያዘም፤ ወደ አንድ ወገን ያደላ አቋም አለው ይባላል፡፡ በዚህ ላይ የመንግስት ምላሽ ምንድነው?
በጥንቃቄ መያዝ አለበት የሚሉ ወገኖች አገላለፃቸው ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ እኛም አክራሪነትና ፅንፈኝነት በጥንቃቄ ነው መያዝ ያለበት ብለን፣ ላለፉት ሁለት አመታት ከሃምሌ 2003 ጀምሮ በሰፊው ህገ መንግስታችንን ለማስተማር፣ የሃይማኖት ተቋማትን በክርስትናውም በእስልምናውም ከራሳቸው ቅዱሳን መፃህፍት መነሻ አድርገው፣ ሃይማኖቶቹ ስለምን እንደሚሰብኩ ለማስተማር ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡ በጥንቃቄ መያዝ አለበት ሲባል እንግዲህ ይሄ ነው፡፡ ሌላው የማይመለከታቸው ሌሎች ወገኖች በዚህ ጉዳዩ ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በጥንቃቄ መያዝ አለበት ሲባል፣ በምንም አይነት መንገድ ከዚህ ተግባር የማይመለሱ መንግስታዊ ሃይማኖት ለመመስረት አቅደው የሚንቀሳቀሱትን ለይቶ ማስቀመጥ ነው፡፡ በዚህ ላይ ከህዝባችን ጋር ሆነን እኛም ሰዎች በአዕምሯቸው ላይ ባሰቡት ሳይሆን በተጨባጭ የሚገኝ ማስረጃን ይዘን ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ ሰዎች እንደቀድሞ ስርዓት ስለተጠረጠሩ ብቻ አይፈረድባቸውም። ይህ አይነቱ ስርአት ዛሬ የለም፡፡ ሠዎች ፍትህን ከትክክለኛው የፍትህ አደባባይ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በጥንቃቄ መያዝ ሲባል አንዱ ማስተማርና ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ላለፉት ሁለት አመታትም ይሁን አሁን የተኬደበትና እየተኬደበት ያለ ነው፡፡ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ሲከናወን ግን መንግስታዊ ስርአት በስርአት አልበኞች እንዲጣስ እየተፈቀደ በሄደ ቁጥር፣ ስርአት አልበኝነት አንደኛው አንደኛውን እየወለደ የሃገራችንን ሠላምና መረጋጋት አደጋ ውስጥ የሚከትበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ የሆነ ቦታ ላይ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራ ሲሠራ ጥንቃቄ የጐደለው ነው ተብሎ ሊፈረጅ አይችልም፡፡
መንግስት በጥንቃቄ ጉዳዩን አልያዘውም ከሚያስብሉት አንዱ ወሃቢያን በግልፅ እንደሚቃወም መግለፁ ነው፡፡ በእርግጥስ ይህ ውሣኔ ወገንተኛ አያስብለውም?
የመንግስት ፍረጃ መስፈርቱ አንድ ነው። ህገ መንግስታዊ ስርአትን ተቀብሎ የሚሄድ ነው አይደለም ነው፡፡ ወሃቢያ ነው፣ ሠለፊያ ነው የሚለው አገላለፅ ምናልባት በዚህ ውስጥ ተደራጅተናል የሚሉ ሠዎች በአዕምሯቸው ውስጥ ስለያዙ አይደለም፡፡ በተጨባጭ ከላይ ያስቀመጥነውን ነጥብ ሠዎች ሲጥሡ፣ የዚያ ሃይማኖት ወይም (ሴክት) አባላት ስለሆኑ ሣይሆን ህገ መንግስትን እየጣሱ ስለተገኙ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ይህ መንግስት አንዱን ሴክት ደግፎ ሌላውን ተቃውሟል የሚያሠኝ ነገር ሊያመጣ አይችልም፡፡ መንግስት ሃይማኖቱን ወይም ሴክቱን አይደለም የሚቃወመው፤ ድርጊቱን ነው፡፡ ድርጊቱ ህገ መንግስቱን የሚቃረን ሆኖ እስካልተገኘ ድረስ መንግስት አይመለከተውም፡፡ ለምሣሌ ሠዎች “ወሃቢያ ነኝ” “ሠለፊያ ነኝ” ብለው ቢያምኑ ለምንድን ነው ወሃቢያ የሆናችሁት የሚል ክርክር አናነሣም፡፡ ሠዎች የፈለጉትን የማመን መብታቸው የተረጋገጠ ነው” ለእርምጃዎቻችን መነሻ የምናደርገው ፀረ-ህገ መንግስት የሆነን አክራሪነት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ለሁሉም ሃይማኖቶች ሲባል ነው፡፡ በእነዚህ ሴክቶች ለሚያምኑት ጭምር፡፡
ማንኛውም ዜጋ ህገ መንግስቱን ማክበርና ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ህገ መንግስት አለማክበርን አንዳንዴ የደረቅ ውይይት አካል ያደርጉታል፡፡ ህገ መንግስት ባይከበር እኮ ሁላችንም በሠላም መኖር አንችልም፡፡ የእለቱ ጐበዝ በመጣ ቁጥር ሊያስተዳድረን ይሞክራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የወሃቢያን አስተምሮ መንግስት ይቃወማል ለሚለው የምንቃወመውን ክፍል እንቃወማለን፤ የማንቃወመውን ክፍል ግን አንቃወምም፡፡ በወሃቢያ ውስጥ ሆኖ ህገ መንግስቱን ለመናድ የሚሄድ አካል ካለ፣ ወሃቢያ በመሆኑ ብቻ ሣይሆን እያራመደ ያለውን አስተሣሠብ እንቃወማለን፡፡ ያ ፀረ-ህገ መንግስት ነው፡፡ ስለዚህ ተቋሞቹ የፈለገ ስም ቢኖራቸው እኛ ጉዳያችን አይደለም፡፡ ተቋማቱ ውስጥ ሆነው ፀረ-ህገ መንግስት ተግባር የሚፈፅሙ ካሉ፣ መንግስት ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን የማስጠበቁን ሃላፊነት እንዲወጣ ይገደዳል፡፡ ህዝቡ እኮ መንግስት አድርጐ ሲመርጠው፣ ህግና ስርአትን ያስከብርልና ብሎ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በእስልምና ውስጥ ብቻ ያለ ተደርጐ መወሠድ የለበትም፡፡ በክርስትና ውስጥም ተመሣሣይ ነገሮች ይካሄዳሉ፡፡

ሌላውን እምነት “እምነት አይደለም” ብሎ የመፈረጅ፣ “ከኔ ጋር እኩል የሆነ ሃይማኖት መኖር የለበትም” የሚሉ አመለካከት ያላቸው አሉ፡፡ “መንግስታዊ ሃይማኖት ካልሆንን፣ ሃይማኖታችን ተዋርዷል፤ ክብርና ሞገሡ ቀንሷል” የሚሉ በክርስትና ሃይማኖት ሽፋንም አለ፡፡ ፍረጃው ተመሣሣይ ነው፡፡ በአንዳንድ የክርስትና ማህበራት ጥላ ስር ያሉ ግለሠቦች ተመሣሣይ አላማና ፍላጐት አላቸው፡፡ ይህን ፍላጐት ለማሣካትም ግንባር ሲፈጥሩም ይስተዋላል፡፡ አንደኛው እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም ሲፈልግ፣ አንደኛው ክርስቲያናዊ መንግስት አቋቁማለሁ ነው የሚለው፤ ግን ግንባር ፈጥረው ለመንቀሣቀስ ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ ይህ እንግዲህ ለሠሚው ግራ ነው። እንዴት አድርጐ ነው የጋራ አላማ ሊኖራቸው የሚችለው፡፡ የጠላቴ ጠላት ጠላቴ ነው በሚል አይነት ፍረጃ የሚሄዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የመንግስት አቋም ሃይማኖቶቹ ምንድናቸው ሣይሆን፣ በነዚህ ተጠልለው ከህገ መንግስቱ የተቃረነ ድርጊት ይፈፅማሉ አይፈፅሙም የሚለው ላይ ትኩረት ማድረግ ነው፡፡ በሞት የተለዩን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፤ በተወካዮች ምክር ቤት በግልፅ ተናግረዋል፡፡ እኛ እያልን ያለነው እንዲከበርላቸው የሚሹትን መብት ለሌላውም እንዳይነፍጉ ነው፡፡ እነሡ ግን እያሉ ያሉት ከዚህ መርህ የተቃረነ ነው፡፡ እስቲ አሁን በኛ ሃገር የትኛው መብት ነው የተከለከለው? መፀለይ ነው? የሃይማኖት ተቋም መገንባት ነው? ሃይማኖት ማስፋፋት ነው? የፈለከው ቦታ ተንቀሣቅሠህ አጀንዳህን ማሣካት ነው? የትምህርት ተቋማት እየገነባህ የሃይማኖት ትምህርት ህፃናትና ወጣቶችን ማስተማር ነው? የትኛው ነው የተከለከለው ተብሎ ሲጠየቅ መልስ የለውም፡፡
አንዳንድ ተቃዋሚዎች ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማንሳታቸው “በእሣት መጫወት” ነው ተብሏል፡፡ መንግስትስ በግልጽ አቋሙን ለይቶ በማስቀመጥ እንዲህ አይነት እንቅስቃሴዎችን ማድረጉ ተገቢ ነው?
አንዱ ህገመንግስታችን ላይ በግልጽ የተቀመጠው፣ ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ ናቸው የሚለው መርህ ነው፡፡ በህገመንግስቱ አንቀጽ 11 ላይ ይህ በማያወላዳ መንገድ የተቀመጠ ነው፡፡ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚል ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ከሚያነሷቸው ነጥቦች መካከል አንደኛው፣ “መንግስት በሃይማኖት ላይ ጣልቃ ገብቷል፤ እጁን ያውጣ” የሚል መፈክር ነው፡፡ ሁለተኛው፣ “የታሰሩ ይፈቱ” የሚል ነው፡፡ እንግዲህ ፓርቲዎች መንግስት ለመሆን ነው የሚወዳደሩት፡፡ መንግስት ሲሆኑ የመጀመሪያው ተልዕኮ፣ ህገመንግስትን ማክበርና ማስከበር ነው፡፡ ይህ ማለት ለአንድ ሀገር ህልውና በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ነው በሚባለው በህገመንግስት ማዕቀፍ ውስጥ የሚታይ የህግ የበላይነት ነው፡፡ ተቃዋሚዎች እያደረጉ ያሉት ለነዚህ ሃይማኖቶች ተቆርቋሪ በመምሠል፣ በሃይማኖቶቹ ተሸፍነን የፖለቲካ ፍላጐታችንን እናሣካለን የሚል ነው፡፡ ትልቅ ስህተት እየሠሩ ነው፡፡ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ ቢረጋገጥ፣ ይህን የሚያርመው ራሱ መንግስታዊ ስርአቱ ነው። ገዢው ፓርቲ ለምሣሌ እከሌ ጣልቃ ገብቷል ብሎ ሲያስብ፣ የሌላ ሠው አስታዋሽ ሣይፈልግ ራሱን በራሱ ነው የሚያርመው፡፡ መንግስት ህገ መንግስቱ ተጥሷል ብሎ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ያ ፀረ-ህገ መንግስታዊ የሆነ እንቅስቃሴ ሃይማኖታዊ አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግስት ጣልቃ ገብቷል የሚለው አገላለፅ አንድም ተራ የሆነ ተወዳጅነትና ተቀባይነት እናተርፋለን ተብሎ የሚቀርብ ዜና ነው፤ በሌላ በኩል የህግ መሠረት የሌለውና እነዚህ ፓርቲዎት መድረሻቸውም መነሻቸውም ህገ መንግስታዊ ስርአትን የማክበርና የማስከበር ሣይሆን ሌላ ፍላጐት እንዳላቸው የሚያሣይ ነው፡፡
እዚህ ላይ የሚታየው አንዱ “የታሠሩ ይፈቱ” የሚለው መፈክር ነው፡፡ በመግለጫችንም በተለያዩ አጋጣሚዎችም አንስተነዋል “የታሠሩ ይፈቱ” የሚል ፍላጎት በግለሠቦቹ አዕምሮ ውስጥ ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን አባባሉ በቀጥታ ከህግ የበላይነት ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ “የሠማያዊ ፓርቲን” አጅበውና አሣጅበው ይህን ጥያቄ ለተወሠኑ አካላት አቅርበው ሲሄዱ፣ በቀጥታ እንዳሉት በዚህች ሃገር ውስጥ የዳኝነት ስርአት የሚባል ነገር በግለሠቦች ቅስቀሣ ይደፈቃል ማለት ነው፡፡ ለዚህም ሊያደራጅ የሚችል በሙሉ “ይፈታ” እያለ የሚያስፈታ ከሆነ፣ የህግ የበላይነት በአጃቢው ፅንፍ የሚወድቅበት ሁኔታን ነው እያሣዩ ያሉት፡፡ ስለዚህ ፓርቲዎች ህገመንግስታዊ ስርአቱንም ህጋዊ ስርአቱን እንዲሁም የዳኝነት ስርአቱንም ጭምር የሚጥስ ስራ ላይ ነው የገቡት፡፡ እነሱ ፓርቲ እንዲሆኑ በር የከፈተላቸውን ህገመንግስት ጭምር ነው እየደፈቁ ያሉት፤ በዚህ አይነት መንገድ ፓርቲ ሊሆኑ አይችሉም ማለት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ለመሄድ የሚያስቡት ሙከራም እግሩ በጣም አጭር ነው፡፡ በራሳቸው ህልውናም ጭምር ፈተና የሚደቅንም ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ከሃይማኖቶቹ ገለጥ አድርገህ ስታያቸው ባዶ ናቸው ማለት ነው፡፡ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከአክራሪና ከጽንፈኛ ሃይሎች ጋር አብረው የሚሰለፉ ከሆነ የመጀመሪያው ጉዳይ የሚሆነው አክራሪነትንና አሸባሪነትን እየደገፉ ነው ማለት ነው፡፡ ሰውን በእምነቱ ምክንያት በጠራራ ፀሐይ ከሚገድሉ ጋር ፓርቲው የሚያብር ከሆነ፣ በአለማቀፍ ህግም በሃገራችን ህጐችም፣ በፀረ ሽብር ህጉም ጭምር እነዚህ ሰዎች የማይጠየቁበት ምክንያት የለም፡፡ አሸባሪነትን “ጐሽ፤ አይዞህ በርታ” ማለት በፀረ ሽብር ህጉ የሚያስጠይቅ ነው፡፡
ተቃዋሚዎች “የፀረ-ሽብር ህጉ አፋኝ ነው” በሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ አንዳንዶችም ለማሰረዝ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ መንግስት በህጉ ላይ ለምን ከተቃዋሚዎች የሚቀርቡለትን ማስረጃዎች ተመልክቶ በጉዳዩ ላይ ከነዚህ አካላት ጋር አይወያይም?
በፀረ-ሽብር ህጉ ላይ በአመለካከት ምክንያት የሚጠየቅ ሰው የለም፡፡ የአመለካከት ነፃነት በህገመንግስታችን ዋስትና የተሰጠው ተፈጥሯዊ እውነት ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው፡፡ በአመለካከት ምክንያት ተጠያቂ ሆነናል የሚሉ ሰዎች አቀራረብ አታላይነት ነው፡፡ በየመጽሔቱ፣ በየጋዜጣው ስንት ነገር ይባላል እኮ፤ ግን እንደዚህ አይነት አመለካከት ይዘሃል ተብሎ የሚጠየቅ ሰው የለም። ሆኖም በየትኛውም መንገድ ህዝብን ወደ ሽብርና አለመረጋጋት እንዲሁም እምቢተኝነት መምራት የተከለከለ ነው፡፡

ይሄ ሃገራችንም ከተቀበለቻቸው አለማቀፍ ህጐች ጋርም ተያይዞ የሚታይ ነው፡፡ ፀረ ሽብር ህጉ ሰውን ተጠያቂ የሚያደርገው፣ በተግባር በዚህ ውስጥ ግለሰቦች ተሳትፈው ሲገኙ ነው፡፡ በሀገራችን በየቀኑ ቦምብ ስለማይፈነዳና ሠላማዊ ዜጐች ሰለባ ስለማይሆኑ፣ ይህን ሃሳብ የሚያቀርቡ ግለሰቦች ጭምር በሰላም ውለው ስለሚገቡ፣ ምንም ስራ ሳይሰራ እንዲሁ መሽቶ እንደሚነጋ ስለሚያስቡ ነው፡፡ ይህን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ብዙ የሀገራችን ዜጐች ሌት ተቀን እንደሚሰሩ አይገነዘቡም ማለት ነው፡፡ የሽብርን አደጋ ቀድሞ የመከላከል ስራ በመሠራቱ፣ ሠላም ማግኘታቸውን አይረዱም ማለት ነው፡፡
ስለዚህ የፀረ ሽብር ህጉ፣ በተለየ መንገድ ሰዎችን ለማጥቃት የተዘጋጀ ነው የሚሉ ሰዎች መጀመሪያውኑ በሽብር ላይ ለመሳተፍ ካላቸው ፍላጐት የሚመነጭ ካልሆነ በስተቀር፣ የሚጠብቃቸው ህግ እንጂ ሽብርተኛ ሆናችኋል ብሎ የሚያስራቸው ህግ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጐት አይደለም፡፡ ይህ ህግ እኮ ደጋግመን እንደምንለው አሉ ከተባሉ አለማቀፍ ህጐች የተቀዳ ነው፡፡ በሌላ በኩል የአንድ ሚሊዮን ሰዎችን ፊርማ እናሰባስባለን ብለው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች በአደባባይ ከአክራሪነትና ጽንፈኛነት መፈክሮች ጀምሮ፣ በአሸባሪዎች ይፈፀሙ የነበሩ ድርጊቶችን ሳያወግዙ ግን በሌላ በኩል የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ተዋንያኖች ሆነው ታይተዋል፡፡ ስለዚህ እነሱ በዚህ አይነት ሲንቀሳቀሱ ህዝባችን ይዳኛቸዋል ብለን እናስባለን፡፡ ዙሪያችን በሙሉ ምን እንደሆነ እናውቃለን ግን ከውጭ ፖሊሲያችን ተነስተን፣ ጨለማ ነው ብለን አናስቀምጥም፤ ብርሃን ነው ብለን ነው የምናስቀምጠው፡፡

ግን ጥንቃቄ የሚሻ ብርሃን ነው ያለው፡፡ ሶማሊያ ያለውን እናውቃለን፣ በኤርትራ ገዢ ፓርቲ በኩል ያለውን ፍላጐት እናውቃለን፤ ሌሎችም በተለያዩ ምክንያቶች የጀመርናቸውን ልማቶች ለማደናቀፍ ምን አይነት ስልቶችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። እነዚህን እኩይ ስልቶችን ለማክሸፍ የውስጥ ተጋላጭነትን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ድህነትን ማጥፋት ዋናው ተግባር ነው፡፡ በሚገባ የሚበላ የሚጠጣ ሰው በትንሹ አይደለልም። ኋላ ቀርነታችን ለእንደዚህ አይነት ጉዳይ ተጋላጭ ያደርገናል፡፡
የራሳቸውን ሃገር መልሰው የሚወጉ ባንዳዎችም አይጠፉም፡፡ መንግስት ለምንድን ነው ማሳያዎችን አምጡ ብሎ ጉዳዩን የማያጤነው ለሚለው፣ በእርግጥም የተወሰኑ ብዥታዎች ላላቸው ሰዎች እንደዚህ አይነት አገላለጽ ሊጠቅም ይችላል። ለህዝባችን በዚህ ዙሪያ ላይ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ አካላት ግን ኑ ተብለው ብታስረዳቸውም የሚቀበሉ አይደሉም፡፡ መነሻቸውን ስለሚያውቁ የሚያመቻቹት የገቡባትን ቀዳዳ መሸፈኛ የሚሆናቸውን ብቻ ነው፡፡ በዚህም ውይይት እየተደረገ ቢዋል ቢታደር አሳምነው ወይም አምነው የሚሄዱ አይደለም፤ ስለዚህ ጉዳዩን በተለያዩ ብዥታዎች ተሸፍኖ እንዳይሄድ በውይይት ግልጽ መደረግ አለበት የሚለው ሊያስኬድ የሚችል ቢሆንም፣ እነዚህ ሃይሎች ለዚህ ያላቸው ፍላጐት አነስተኛ ነው፡፡
መንግስት፤ ለምን አስቀድሞ አክራሪዎች የሚላቸውን ወገኖች ጥያቄ በአደባባይም ይሁን በሌላ መንገድ ነፃ ሆነው እንዲያቀርቡ እድል አልሰጣቸውም? ለምንስ አይሰጣቸውም?
እንደዚህ አይነት ሃሳብ የሚያቀርቡ ወገኖች ካሉ መረጃ ስለሌላቸው ነው፡፡ አስቀድሜ ሳነሳው እንደነበረው፣ አክራሪዎቹና ጽንፈኞቹ ባለፉት 30 እና 40 አመታት የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ስራ ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ አክራሪነትና ጽንፈኝነትን ሲያስተምሩ በነበረበት ወቅት “ለምን ይህን ታደርጋላችሁ” ብሎ ያስቆማቸው ሰው አልነበረም። አሁን ለምንድን ነው ጉዳዩ ገንፍሎ የወጣው ሲባል፣ የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት ይህን አክራሪነትና ጽንፈኝነት ማጋለጥ የሚችልበትን ትምህርት ማስተማር መጀመሩ ነው፡፡ ይህን ትምህርት “መንግስት ከመጅልሱ ጋር ሆኖ መበቲ ሃይማኖትን አምጥቶብናል” በሚል በከፍተኛ ደረጃ አብጠልጥለውት ነበር፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይም “አህባሽ የሚባል ሃይማኖት መንግስት አምጥቷል” በሚል ሰፊ ቅስቀሳ ተደርጓል፡፡ ህገመንግስታችን ማንም የፈለገውን ማስተማር እንደሚችል በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ አክራሪው ሃይልም ባለፉት 30 እና 40 አመታት የፈለገውን ትምህርት ሲያስተምር ቆይቷል። ለዚያ የሚሆኑትን ተቋማት ሲገነባ ቆይቷል፡፡ ሃምሌ 2003 ዓ.ም አካባቢ መጅሊሱ ትክክለኛው የሃገራችን የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ምንድን ነው በሚል ማስተማር ሲጀምር፣ የአክራሪውና የጽንፈኛው ቡድን ማንነት መጋለጥ ጀመረ፡፡ ይህ መጋለጥ ሲጀምር እጅግ በሰፊ መንገድ መጅሊሱን መቃወም ጀምረዋል፡፡ መጅሊሱ የሚወክለን አይደለም፤ በበር ሳይሆን በመስኮት ነው የመጣው በሚል ማለት ነው፡፡ በዚህ እንግዲህ አክራሪነቱ በግላጭ እየመጣ ሄደ፡፡
የመጅሊሱ አስተምህሮ በዚህ ከቀጠለ የኛን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፤ ስለዚህ በምንችለው ሁኔታ ይህ እንዳይሆን መፍጨርጨር አለብን የሚል ሃሳብ አመጡ፡፡ ይህን ሲያነሱ የተለያዩ የራሳቸውን አደረጃጀት እየፈጠሩ በተለይ አርብ ጁምአ በመጣ ቁጥር፣ እጅግ በጣም ሰፊ የሚባል ህዝብን እያንቀሳቀሱ ለመሄድ ይሞክሩ ነበር፡፡ ይህን ሲያደርጉ በጣም ብዙ መድረኮች ተከፍተው “ጥያቄያችሁ ምንድነው” ተብለው ተጠይቀዋል። ስለዚህ መንግስት በተለይም አስተባባሪዎችና መፍትሔ አፈላላጊዎች ነን የሚሉ ቡድኖችን ከሦስት ጊዜ በላይ አግኝተን አነጋግረናቸዋል፡፡ የተለያዩ መዋቅሮቻችንም በየራሳቸው አግኝተው አነጋግረዋቸዋል፡፡ በራሳችን መዋቅር ግን መፍትሔ አፈላላጊ የተባሉትን ቡድን ለማነጋገር ተሞክሯል፡፡ “ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ትሠራላችሁ፤ ከኦነግ ጋር ከአልሸባብ፣ ከግንቦት 7 ጋር ትሠራላችሁ፤ የናንተን ድምጽ እነዚያ ያስተጋባሉ፤ የእነሱን ድምጽ እናንተ ታስተጋባላችሁ፤ ይህ ሃይማኖት ጥያቄ አይደለም” ብለናቸዋል፡፡ መጨረሻ አካባቢ እንደውም ከአልሸባብና ከአልቃኢዳ ህዋስ ጋር የመተሳሰር ነገርም ነበር፡፡

ያም ሆነ ይህ ሃይማኖታዊ ጉዳይ የምትሏቸውን አምጧቸው፤ እኛ እንደመንግስት የሚያገባን ነገር ካለ እንወያይባቸው ብለን ነበር። አንደኛው ያነሱት የስልጠና ጉዳይ ነው፡፡ አህባሽ የሚባለው ስልጠና ላይ የተነሳ ጥያቄ ነው፡፡ እኛ የትኛውም አስተምህሮ ይቅረብ፤ ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል እስካልሆነ ድረስ ግድየለንም፣ ስለዚህ ማን ምን አስተማረ የሚለው ህገመንግስትን የሚጥስ ነው የማይጥስ ነው በሚለው መስፈርት ነው፣ የሚጥስ ትምህርት ስታስተምሩ እንኳ አቁሙ አልተባላችሁም ብለናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ በግልጽ ተወያይተናል፡፡
ሁለተኛው መጅሊሱ የሚወክለን ተቋም አይደለም የሚለው ነው፡፡ መጅሊሱ የማይወክላችሁ ከሆነ የሚወክላችሁን ተቋም ማቋቋም የእናንተ መብት ነው፡፡ በዚያ ጉዳይ ላይ የምናግዛችሁ ካለ እናግዛችሁ፡፡ ለምሣሌ አዳራሾችን በመፍቀድ ፀጥታና ሠላም በማስጠበቅ ልናግዛችሁ እንችላለን፡፡ ይህን ስታደርጉ ደግሞ ብይን የሚሰጠው የኢላማ ምክር ቤት በሚሠጠው ውሣኔ መሠረት መሄድ አለብን በሚል ተነጋገርን፡፡ ምርጫው ተካሄደ፡፡ ከ8 ሚሊዮን በላይ መራጭ የተሣተፈበት ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሃይሎች ይህንንም ምርጫ የማብጠልጠል ነገር ውስጥ ተዘፍቀው ተገኙ፡፡ እንግዲህ የዚህ ሁሉ ምክንያት ሠዎች መነሻቸውን ስለሚያውቁ፣ የሌላው ማብራሪያ ስለማያሣምናቸው ነው፡፡ መሃል ላይ ተግባብተናል ብለው በተግባቡት መንገድ ለመሄድ አይፈልጉም፡፡ ሌላው ከአውሊያ ትምህርት ቤት ጋር ተያይዞ የተነሣው ነው፡፡ አወሊያ ት/ት/ኮሌጅ በውጭ የእስልምና እርዳታ ተቋማት ድጋፍ የተቋቋመ ነው፡፡ መነሻው ላይ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለበጐ ጉዳይ አቋቋሙት ነው የሚባለው። ኋላ ግን አንዳንድ ነገር ማስኬድ ሲቸግራቸው ይመስለኛል እነዚህ አለማቀፍ ተቋማት ይገባሉ። ይገቡና አጠቃላይ ከሚመለምሏቸው መምህራን ጀምሮ፣ በአረቢኛ ቋንቋ ሽፋን የሚያስተምሩት ትምህርት የአክራሪነት እና ፅንፈኛነት ትምህርት ነው፡፡ ይህንንም ለማስተካከል ተሞከረ፤ እንደዚህ እያለ ይቀጥልና መጨረሻ ላይ የተነሣው “የታሠሩ ይፈቱ” ነው፡፡ “የታሠሩ ይፈቱ” የሚለው ከህግ የበላይነት ጋር የሚፃረር ነው፡፡ እንግዲህ በእነዚህ ጉዳዮች ሁሉ ይመለከታቸዋል ከተባሉት ጋር ሁሉ ውይይት ተደርጓል፡፡ ስለዚህ መንግስት በር ዘግቶ፣ “ከእናንተ ጋር ውይይት አላደርግም” አላለም፡፡ የአክራሪው ቡድን ግን ለምሣሌ የዛሬ አመት እንደ ነገ የአፍሪካ ህብረት ስብሠባ ሊካሄድ ሆኖ እያለ፣ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ሠልፍ ጠርተናል ብሎ አዲስ አበባን ለማመስ ተንቀሣቅሠዋል፡፡ እኩለ ለሊት ላይ የአዛን ደውል አስደውለው፣ “አሁን እያንዳንድህ ጐረቤትህን ማጥቃት ያለብህ ጊዜ ነው” የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ይህ ማለት በጣም አደገኛ ሴራ ማለት ነው፡፡ እዚህ አይነት ደረጃም ደርሠው ነበር። ኋላ ላይ ግን እነዚህ ሠዎች ፍላጐታቸው የህዝብ መተላለቅ መሆኑን ህዝብ ሙስሊሙ እየተረዳ ሲመጣ፣ ባዶአቸውን ትቷቸው ሄዷል፡፡ አሁን የእነሡ ደጋፊዎችና አጫፋሪዎች ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ሣይሆን ከኢትዮጵያ ውጪ ናቸው። በማህበራዊ ሚዲያዎች (ፓልቶክ፣ ፌስቡክ) ብዙ ሲያወሩና ሲያስወሩ ይሠማል፡፡ አሁን ላይ እንደውም ኢትዮጵያ ውስጥ የአርብ ፀሎት የለም የሚል እያስወሩ ነው፣ ሴቶች ሃይማኖቱ የሚያዘውን አለባበስ ተከልክለዋል፣ የስግደት አካሄድ ተቀይሯል የሚሉ የፈጠራ ወሬዎችንም እያስወሩ ነው፡፡ የእነዚህ ሠዎች አላማ እንግዲህ በሃገራችን የታየውን ብርሃን መልሶ የማጨለም ነው፡፡ እንግዲህ አስቀድሜ እንዳልኩት፤ በፌደራል ጉዳዮች ለውይይት የተዘጋ በር የለም፡፡ ሁለት አመት ሙሉ የውይይት ጊዜ ነበር፤ አሁንም መንግስት በሩ ክፍት ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሠዎች የማይታረቅ ቅራኔ ነው ያላቸው፡፡

ባለፈው ደሴ ላይ ሠው ተገድሏል፡፡ ባሌ ውስጥም የአንደኛው የታወቁ አሊም መቃብር ቆፍረው አስክሬናቸውን ሲያቃጥሉ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ከነዚህ ግለሠቦች አንዳንዶቹ በዚህ ሽፋን ምንም ሣይኖራቸው በማግስቱ ሚሊየነር የሆኑ ናቸው። ስለዚህ ይህ አጀንዳ ተዘጋ ማለት፣ ለአንዳንዶቹ የመኖር ህልውናቸው አከተመ ማለት ነው፡፡
እርሶም እንዳሉት በአንድ በኩል በማህበራዊ ድረገፆች የሚካሄዱ ቅስቀሣዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ከተቃዋሚዎች ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሣ አለ፡፡ በአንድ ወገን ደግሞ የመንግስት አቋም አለ፡፡ እነዚህ ሶስት አካላት የያዙት የተካረረ የሚመስል አቋም የዚህችን ሃገር መፃኢ እድል አስጊ አያደርገውም? መጨረሻውስ ምንድን ነው የሚሆነው?
የሚሆነው የሚመስለኝ ውሸት እግሩ አጭር ነው፡፡ የአንድ ሠሞን ግርግር አካል ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚያ ባለፈ ግን ለህዝባችን ህይወቱን የሚቀይር ነገር እንደሌላቸው በሂደት እየተጋለጡ ነው፡፡ ህዝባችን ከማህበራዊ ድረ ገፅም ከተቃዋሚ ፓርቲም የሚፈልገው፣ “እንዴት ሆኖ ከድህነት እንወጣለን” የሚለውን የሚያሣየውን እንጂ የተመለሡ ጥያቄዎችን ያልተመለሡ አድርገው ከበሮ መምታትን አይደለም፡፡ ለዚህም ተባባሪ አይሆንም፡፡ በመጨረሻ ፈራጅ የሚሆነው ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ ከበሮ ስለተመታ ይሁንታ አይሰጥም፡፡ ማነው ለልማት ደፋ ቀና እያለ ያለው? ማነው ልማትን ለማደናቀፍ የሚተጋው? የሚለው ሁሉም ሠው እየለየው ሊሄድ ይችላል፡፡ ሁሉንም ተቃዋሚዎች የሚመለከት ባይሆንም፣ የተቃዋሚዎች በዚህ አይነት መሄድ ግን መጨረሻቸው የማያምር ነው፡፡ እነዚህ ሃይሎች መንግስት ለመሆን ፍላጐት የላቸውም ማለት ነው። አንዳንድ ልሂቃን የሚያስቀምጡት ነገር አለ። አንድ ሃይማኖት ሲኖር አምባገነንነት ነው፣ ሁለት ሃይማኖት ሲኖር ጦርነት ነው፣ ብዙ ሃይማኖት ሲኖር ሠላም ነው፤ የኛን ሃገር የሚገልፀው ሶስተኛው ነው። በዚህች ሃገር ውስጥ አንደኛው ካለ አንደኛው እኖራለሁ ብሎ የሚያስብበት ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ አካላት የሃሣብ ልዩነት ቢኖራቸው እንኳ የህዝባችንን ይሁንታና ፍርድ አክብረው መሄዳቸዉ የሚመከር ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ያለፈው ትውልድ ድህነትና ኋላቀርነት እንዳስተላለፈልን ሁሉ ይሄኛው ትውልድ ደግሞ አክራሪነትንና ፅንፈኛነትን ለቀጣዩ ትውልድ ሊያስተላልፈው ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ያ እንዳይሆን ሁላችንም በየራሣችን ድርሻ መጪውን ጊዜ ከግምት ያስገባ ስራ መስራት አለብን፡፡
የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ የሠጠውን መግለጫ ጨምሮ ከተለየዩ አለማቀፍ ተቋማት እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች ኢትዮጵያ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ የመብት ጥሠት ትፈፅማለት የሚሉ ናቸው፡፡ ሚ/ር መስሪያ ቤቱ እነዚህን ሪፖርቶች እንዴት ነው የሚገመግማቸው በሃገራችን ገፅታ ላይስ አሉታዊ አስተዋፅኦ አይኖረውም?
የአውሮፓ ህብረት እንዲህ ያለ መግለጫ መስጠቱን አልሠማሁም ሠጥተው ከሆነ ሃገራችንን የማይገልፅ ነው፡፡ ስለ ሃገራችን ሃይማኖቶች እና እምነቶች ባለፉት 20 አመታት የነበሩ ተጨባጭ እውነታዎች የሚመክሩት ነው፡፡ ሌላ መስካሪ ሣያስፈልገን የኛ ዋነኛ መስካሪ ህዝባችን ነው። ይህ ደግሞ በየእለቱ በሚያከናውነው ተግባሩ የሚገለፅ ነው፡፡ በየአርቡ፣ ቅዳሜ እና እሁድ በየራሱ አምልኮ ላይ በነፃነት የሚሣተፈው ህዝብ ነው የሚመሠክረው፡፡ መናገርና ሆኖ መገኘት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ የራሣቸውን ፍላጐት ለማሣካት ካልሆነ በስተቀር የሃገራችንን ነባራዊ ሁኔታ የሚገልፅ አይደለም፡፡

 

Read 5778 times
Administrator

Latest from Administrator