Saturday, 27 July 2013 14:15

ውሃ፤ ያድናልም ይገድላልም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
  • ሚሊዮኖች በንፁህ ውሃ እጦት ሳቢያ ለህልፈት ይዳረጋሉ 
  • የተበከለ ውሃ - ለታይፎይድ፣ ኮሌራ፣ የአንጀት ቁስለትና የጉበት ብግነት ያጋልጣል

ሰለሞን ፍቃዱ፤ በተደጋጋሚ እየተመላለሰ የሚያሰቃየው የሆድ ቁርጠት በሽታ፣ ቋሚ መፍትሔ ለማግኘት አለመቻሉ አሳስቦታል፡፡ በሽታው በተነሳበት ቁጥር የሚመላለስባቸው ክሊኒኮች ቁና ሙሉ መድሃኒት እያሸከሙት መመለሱን ለምዶታል፡፡ ታይፎይድ፣ ታይፈስ፣ የአንጀት ቁስለት፣ ጃርዲያና ባክቴሪያ ለበሽታው ከሚሰጡት ስሞች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የእነዚህ በሽታዎች መነሻ ምክንያቱ ደግሞ ንጽህናው ያልተጠበቀ ውሃና የተበከለ ምግብ እንደሆነ ሐኪሞቹ ደጋግመው ነግረውታል፡፡ በዚህ ምክንያትም በየሆቴሉና በየሬስቶራንቱ መመገቡን እርግፍ አድርጐ ከተወው ሰነባብቷል፡፡
ሆኖም በየጊዜው እያገረሸ አቅል የሚያሳጣው ህመሙ አልተወውም፡፡ ግራ ቢገባው ስለሚጠጣው ውሃ ማሰብ ያዘ፡፡ ከቧንቧ እየቀዳ የሚጠጣው ውሃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለየ ጣዕምና ሽታ ማምጣቱን ሲያስታውስ፣ ችግሩ ምናልባትም ከውሃው ሊሆን ይችላል ሲል አሰበ፡፡ ግን ደግሞ በቧንቧ የሚመጣው ውሃ የተጣራና ንጽህናው የተረጋገጠ እንደሆነ ሲነገር በተደጋጋሚ ሰምቷል፡፡ ታዲያ ውሃው እንዴት ሆኖ እሱ ለገጠመው ችግር መነሻ ይሆናል? ማሰብ ጀመረ፡፡ የአራትና የአምስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆቹም የተሟላ ጤና ካጡ ሰነባብተዋል፡፡ የህፃናቱ ችግር ንጽህናውን ያልጠበቀ ምግብና ውሃ ሊሆን እንደሚችል ሃኪማቸው ሲናገር ሰምቷል፡፡ ጥርጣሬው ከፍ ሲል ውሃውን በብርጭቆ እየቀዳ ማስተዋል ጀመረ፡፡ በብርጭቆ ውስጥ እየዘቀጡ የሚቀሩት ቆሻሻዎች ጥርጣሬውን አባባሱት፡፡ ስለጉዳዩ ለሃኪሙ መንገር እንዳለበት ወሰነና ነገረው፡፡ ሃኪሙም ውሃ በቧንቧ ስለመጣ ብቻ ንፁህ ነው ብሎ መጠቀሙ አደጋ እንዳለውና የቧንቧ ውሃም በተለያዩ ምክንያቶች ሊበከልና ለጤና እጅግ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል አስረዳው፡፡
ይህንን ችግር ለማስወገድም የመጠጥ ውሃን በሚገባ አፍልቶና አቀዝቅዞ መጠቀም እንደሚገባ፣ አለበለዚያም በተለያዩ የማከሚያ መድሃኒቶች በማከም መጠቀም ተገቢ እንደሆነ አብራራለት፡፡ በየጊዜው እየተከሰተ ለሚያሰቃየው የጤና ችግር መነሻው፣ የሚጠጣው ውሃ መሆኑን ማወቁ እፎይታ ቢሰጠውም የችግሩ ቋሚ መፍትሔ አለመገኘት አሳስቦታል፡፡ ለማን አቤት ይባላል? በከተማዋ እንዲህ አይነት ችግር ሲከሰት የሚቆጣጠረውና መፍትሔ የሚሰጠው አካል ማነው? ሰለሞን ይጠይቃል፡፡
ችግሩ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለከተማ፣ አለም ባንክ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነው የሰለሞን ፍቃዱ ችግር ብቻ አይደለም፡፡ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ በርካታ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ደንበኞች የሚያነሱት ችግር ነው፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች በአብዛኛው የሚጠቀሙበትን ውሃ የሚያገኙት ከቧንቧ ነው፡፡ የከተማው ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን 368ሺ ቆጣሪ ያላቸው ደንበኞች ያሉት ሲሆን ከገፈርሳ፣ ለገዳዲና ድሬ ግድቦችና የማጣሪያ ሥፍራዎች እንዲሁም 110 ከሚደርሱ ጉድጓዶች በቀን 374ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ እያመረተ ለነዋሪው እንዲሰራጭ ያደርጋል፡፡ ውሃው ለህብረተሰቡ ከመድረሱ በፊት በተለያዩ ዘመናዊ የውሃ ማጣሪያ መንገዶች ተጣርቶና በአስተማማኝ ሁኔታ ተዘጋጅቶ እንዲሁም በርካታ የማጣራት ሂደቶችን አልፎ እንደሚሰራጭ ቢነገርም አንዳንድ ጊዜ በቧንቧ የሚመጣው ውሃ የደፈረሰና ለጤና አደገኛ የሆነ ውሃ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ውሃውን ሳያፈሉ መጠቀም ለበርካታ የጤና ችግሮች እንደዳረጋቸው መሆኑንም የከተማ ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡ በቧንቧ የሚመጣው ውሃ የተጣራና ለጤና ጎጂ የሆኑ ባክቴሪያዎች እንዳይኖሩበት በቂ ማጣራትና ህክምና እንደሚደረግለት የሚናገሩ የባለስልጣን መ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ አንዳንድ ጊዜ የውሃ ቧንቧዎች ሲሰበሩና ጉዳት ሲደርስባቸው የቆሸሸና የደፈረሰ ውሃ በቧንቧ ሊመጣ እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡
በተለይ አሁን ከመንገድ ሥራ ግንባታው ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የውሃ ቧንቧዎች በመሰበራቸው ምክንያት በውሃው ንጽህና ላይ ችግር እያስከተሉ መምጣታቸውንም እነዚሁ ኃላፊዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ችግር በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን በግልጽ ተነግሮ፣ ሕብረተሰቡ ለመጠጥነት የሚጠቀመውን ውሃ በማፍላትና በማቀዝቀዝ ወይንም በተለያዩ የማከሚያ መድሃኒቶች አክሞ እንዲጠቀም ማድረጉ ተገቢ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶ/ር ታደሰ ተስፋዓለም ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገሩ፣ የተበከለ ውሃ ለታይፎይድ፣ ኮሌራ፣ የአንጀት ቁስለትና የጉበት ብግነት በሽታዎች እንደሚዳርግ ጠቁመው፣ እነዚህ በሽታዎች በቀላሉና በፍጥነት ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ለመተላለፍ የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ ህክምና ካልተገኘም ታማሚውን ለሞት የሚያበቁ ገዳይ በሽታዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ንጽህናው ያልተጠበቀና በሚገባ ተጣርቶ ያልታከመ ውሃን መጠቀም ለትንሹ አንጀታችን መቁሰልና ለተቅማጥ በሽታ እንደሚዳርገን የሚናገሩት የህክምና ባለሙያው፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ እጦት ሳቢያ የሚከሰተው የተቅማጥ በሽታ በህፃናት ላይ ጐልቶ የሚታይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የተቅማጥ በሽታ በወቅቱ ህክምና ካላገኘና በተቅማጥ መልክ የሚወጣውን የሰውነታችንን ፈሳሽ ሊተካ የሚችል ንጥረ ነገር ካላገኘ፣ታማሚውን ለህልፈት የሚዳርግ በሽታ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ታደሰ፣ እንዲህ እንደአሁኑ የክረምት ወቅት በሚሆንበት ጊዜ ውሃ በተለያየ መንገድ ሊበከል ስለሚችል፣ በተቻለ መጠን በቤት ውስጥ በማጣራት፣ በማፍላትና በማቀዝቀዝ እንዲሁም የውሃ ማከሚያ መድሃኒቶችን በመጨመር መጠቀሙ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡
በክረምት ወራት የሚከሰቱ የጤና ችግሮች በአብዛኛው ከውሃ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ናቸው ያሉት ዶ/ር ታደሰ፣ በአገራችን በየአመቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ በንፁህ መጠጥ ውሃ እጦት ሳቢያ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ለህልፈት እንደሚዳረግም ጠቁመዋል፡፡ ለመጠጥነት የሚውለውን ውሃ በማጣራት፣ በማፍላትና፣ በማከም በዚህ ሳቢያ የሚከሰተውን የጤና ችግርና ሞት ማስቀረት እንደሚቻልም ገልፀዋል፡፡ በቀላሉ ልንከላከለውና ልናስወግደው በምንችለው ችግር ሳቢያ፣ ለህመምና ለሞት ከመዳረግ መጠንቀቁ ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው ሲሉ የጤና ባለሙያው ያሳስባሉ፡፡

Read 4431 times