Saturday, 27 July 2013 14:17

‹‹የደም መርጋት በሽታ ...ሊድንም ላይድንም ...››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(5 votes)

ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ

‹‹... በደም መርጋት በሽታ ያለኝን ልምዴን ላካፍላችሁ፡፡ እኔ የምኖረው በአዲስ አበባ ነፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ሳሪስ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ነው፡፡ ልጅ ለመውለድ ብዙ ናፍቄ ፈጣሪዬን ስለምን... በጉዋደኞቼ ልጆች ስደሰት...ለእራሴም እንዲኖረኝ ስናፍቅ ኖሬ እድሜዬ አርባ አመት ከገባ በሁዋላ ወንድ ልጅ ወለድኩ፡፡ በእርግጥ የወለድኩት በኦፕራሲዮን ነው፡፡ የእኔም ሰውነት እጅግ ግዙፍ ስለነበር አስቀድሞውኑም የተለያዩ የጤና ችግሮች ...እንደ ደም ግፊት...ኩላሊት የመሳሰሉት አስቸግረውኝ ነበር፡፡ መውለዴ እውን ሆነና ልጄን ታቀፍኩ፡፡ እጅግ በጣም ደስ አለኝ፡፡ ከሆስፒታል ወጥቼ ወደቤ.. ስሄድ ሐኪሜ እንዲህ አለችኝ...
...የእኔ እመቤት...አንድ ነገር ልነግርሽ እፈልጋለሁ፡፡ አንቺ...
•ሰውነትሽ በጣም ወፍራም ነው፣
•የወለድሽበት እድሜም ገፋ ያለ ነው፣
•የወለድሽውም በኦፕራሲዮን ነው፡፡
...ስለዚህ መታረስ አለብኝ ብለሽ ዝም ብለሽ እንዳትተኚ፡፡ ...የምትመገቢያቸውን ምግቦችም በአበሻ ባህል መሰረት ቅቤና ስብ የበዛበት እንዳታደርጊ ተጠንቀቂ... የደም መርጋት የሚባል በሽታ እንዳይዝሽ በተቻለሽ መጠን ጥንቃቄ አድርጊ... ነበር ያለችኝ...፡፡ እኔም ወደእቤት ከገባሁ በሁዋላ ይህንኑ ለቤተሰቤ ስናገር... አረ አትስሚያት ...ደግሞ አራስ ከመቼ ወዲህ ነው ተኝታ አትታረስ የሚባለው? እያሉ በፈለጉት መንገድ መንከባከብ ጀመሩ፡፡ እኔም እንድ ልቤ ሐኪሜጋ..አንድ ልቤ ደግሞ ቤተሰቤጋ ሆኖ መታረሱን ቀጠልኩ፡፡ ልጄን በወለድኩ አንድ ወር ላይ የተለያዩ ህመሞች ይሰሙኝ ጀመር፡፡ ሰውነ.. ውስጥ እንደው ጋት...እንደመጉዋጎል... የመሳሰሉት፡፡ እና.. ሳትታክት ታሸኛለኝ፡፡ ብርድ ነው...መጉዋጎል ነው...የመሳሰሉትን ምክንያት እየሰጠችኝ ከሰል አጠገብዋ እያደረገች በቫዝሊን ታሸኛለች፡፡ እኔ ግን እየባሰብኝ ሄደ፡፡ ከአልጋ እምብዛም ያልወረደው እግሬ ውስጡን እንደቁስለት ስለተሰማኝ ያለእረፍት ይታሻል፡፡ በዚህ መሀል አንድ ቀን ከተኛሁበት ስነቃ የግራ እግሬ ከላይ እስከታች እንደድንጋይ ጠጥሮ በጣም አብጦአል፡፡ በእጅ ሲጫኑት ጭርሱንም ወደውስጥ አይገባም፡፡ ቆይ እስቲ ብዬ ከአልጋ ብወርድ ሊራመድ ቀርቶ ልጎትተው እንኩዋን አልቻልኩም፡፡ ጩኸ..ን ሳቀልጠው ...እና.. ልጄ ተለከፈች ብላ ፀበል ይዛ መጣች፡፡
‹‹...በቀጥታ ቁጣዬን እሱዋ ላይ ነበር ያሳረፍኩት፡፡ ...አንቺ ሴትዮ እንዳትጠጊኝ...ስል... እሱዋም ልጄ ተለከፈች በሚል ቄስ ጥሩልኝ ብላ ኡኡታዋን አቀለጠች፡፡ በዚህ መሀል ጎረቤት ሲሰበሰብ ...ስለእግዚሀር ...የእሱዋ ቄስ እስኪመጡ እኔን ሆስፒታል አድርሳችሁ መልሱኝ...ብዬ አለቀስኩ፡፡ አንድ ጎረቤ.. እስቲ ወይዱ ብሎ ጋጋታውን ካባረረ በሁዋላ በእርጋታ ምንድነው የሆንሽው ብሎ ሲጠይቀኝ...እግሬን ገለጥ አድርጌ አሳየሁት፡፡ ...እሱም እራሱን ይዞ ...ምንድነው የምትሉዋት...በቃ እኔ ሆስፒታል እወስዳታለሁ ብሎ ከመሃላቸው እየጎተተ አወጣኝ፡፡...ሆስፒታል ስደርስ ሐኪሜን ነበር መጀመሪያ ያገኘሁዋት...እሱዋም ...ያልኩት ነገር አልቀረም አይደል? ስትል ጠየቀችኝ፡፡ ምኑ? አልኩዋት ...የደም መርጋት አይደል የያዘሽ ? ...ስትለኝ እዬዬ ብዬ ነበር ያለቀስኩት፡፡ ...ልጄን ከቤት ጥዬ ወደሀያ ቀን ሆስፒታል ተኛሁ፡፡ ከዚያም እስከ አሁን ለሰባት ወር መድሀኒት እየወሰድኩ ነው፡፡ ከላይ እንደገለጽኩላችሁ እድሜዬ ከገፋ በሁዋላ ስለወለድኩ አንድ ልጅ መድገም እፈልግ ነበር ብዬ ሐኪሜን ሳማክር ... በሐኪም ክትትል ስር ሆነሽ ብትወልጂ ችግር የለም አለችኝ፡፡ ሌላ ሐኪም ሳናግር ደግሞ እንዲህ ብለሽ እንዳትሞክሪ...መጀመሪያ ለእራስሽ ሕይወት አስቢ አለኝ፡፡ የትኛውን እንደምይዝ ተቸግሬአለሁ...››
ቤተልሄም ተስፋዬ ከሳሪስ
የቤተልሔም ልምድ የብዙዎች ነው፡፡ ባለፈው እትም ለንባብ ያልነው የደም መርጋት ችግር በተለይም በእርግዝናና በወሊድ ወቅት ብዙ ሴቶች እንደሚደርስባቸው ማብራሪያውን የሰጡን ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ ከኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል ናቸው፡፡ እንደ ዶ/ር ሙሁዲን ምስክርነት፡-
‹‹... ቀደም ሲል በሕክምና ትምህርት ላይ በነበርንበት ጊዜ የደም መርጋት ሕመም የደረሰባቸው ሴቶች በተራራቀ ሁኔታ አልፎ አልፎ ነበር ወደሕክምናው የሚመጡት፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከተው ስንመለከተው ግን በርካታ ሴቶች ይህ ችግር ደርስባቸዋል፡፡ የደም መርጋት ችግር በዘር ሊመጣ የሚችል ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ግን ከአኑዋኑዋር ሁኔታ ጋር በተያያዘ ይከሰታል...›› ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ሲሆን በተለያዩ የህክምና ትምህርት ቤቶችም በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ ቤተልሔም ተስፋዬ በስተመጨረሻ ስለልጅ መውለድ ላነሳችው ጥያቄ የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል፡፡
‹‹... እርግዝናና መውለድ የደም መርጋትን ከሚያባብሱ ነገሮች መካከል ናቸው፡፡ በእርግጥ ከዚህም ውጪ ችግሩን እንዲከሰት የሚያደርጉ ምክንያቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የደም መርጋት ችግር በሕይወት ዘመኑዋ አንድ ጊዜ ማለትም በእርግዝና ወይም ወሊድ ወቅት ብቻ የተከሰተባት ሴት እና በሌሎች የጤና ሁኔታዎች ወይንም በዘር ምክንያት ችግሩ የተሰከተባት ሴት በእኩል አይን አይታዩም፡፡ ስለዚህ፡-
•ከእርግዝናው ወይንም ከመውለድ ጋር በተያያዘ ብቻ የደም መርጋት ሕመም የገጠማት ሴት ለዚህ ሕመም የዳረጉዋት ምክንያቶች ከተስተካከሉና ሕክምናውን በተገቢው መንገድ ወስዳ ለሚቀጥለው እርግዝና ብቁ መሆንዋን ሐኪም ካረጋገጠላት የሚቀጥለውን ልጅ ብዙም ሳትቆይ ማርገዝ ትችላለች፡፡
•የደም መርጋት ችግር በተለያዩ ምክንያቶች እና በዘር የወረሱ ወይንም በተደ ጋጋሚ የሚከሰትባት እናት ከሆነች ግን በቀላሉ ወደ እርግዝናው እንድትገባ አይፈቀድም ፡፡ ተከታታይ የሆነ የህክምና ክትትል አድርጋ የደም መርጋቱ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ መወገዱ ሲረጋገጥ እና ሐኪሞች ሲወስኑላት ግን ልጅ መውለድ ትችላለች፡፡
የህክምና አሰጣጡ ደረጃ እና ሕመሙ ያጋጠመበት ምክንያት ሁኔታውን ይወስኑታል እንጂ የደም መርጋት በሽታ የገጠማት ሴት እንዲያውም ልጅ መውለድ አትችልም የሚል ሳይንስ የለም፡፡ ነገር ግን የፕሮቲን እጥረት ያለባቸው ሴቶች ከሆኑ እርግዝናውን እስከመ ጨረሻው ድረስ ጠብቆ ልጅ መውለድ የማይችሉበት እና እርግዝናውም በመሀከሉ በውርጃ መልክ ሊወገድ የሚችል በመሆኑ ከእርግዝናው በፊት በእርግዝናው ወቅት ሊወሰዱ የሚችሉ መድሀኒቶችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል..›› ብለዋል፡፡ የደም መርጋት በሽታው በአብዛኛው የሚያጋጥመው በእርግዝናው ወቅት በተለይም እርግዝናው እየገፋ በሚመጣበት ጊዜ ነው፡፡ በእርግዝናው ወቅት ያጋጠመው የደም መርጋት ወደ ጽንሱ ተላልፎ በልጁ ላይ ችግር እንዳያመጣ ሲባል የሚደረገው የህክምና ሂደት ከሌላዋ እናት ከበድ ያለ ወይንም ደግሞ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ መድሀኒቶቹ በ3/ ደረጃ ይከፈላለሉ፡፡ የመጀመሪያው አራት ወር እርግዝና ላይ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከአራት ወር በሁዋላ እስከ ሰላሳ ስድስት ሳምንት ድረስ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ከዚያ በሁዋላ ደግሞ በወሊድ ወቅት ከመው ለድዋ 24/ ሰአት በፊት መድሀኒቱ ይቋረጥና ከወሊድ በሁዋላ ደግሞ እንደገና የሚቀጥልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡የደም መርጋት ችግር ከአመጋገብ ጋር ተያያዥነት ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌም... ከፍተኛ የስብ ክምችትን የሚያስከትሉ ወይንም የኮሎስትሮል መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦ ችን መመገብ ለዚህ በሽታ ተጋላጭ የሚያደርጉትን የደም ስሮች መዘጋት ወይንም ከፍተኛ ውፍረትን ስለሚያስከትሉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ እንደገለጹት የደም መርጋት በሽታ ምልክቶች አብዛኛውን ጊዜ አሻሚ ናቸው፡፡ ይህም ማለት አንዲት ሴት እንደዚህ ያለ ሕመም በሚሰማት ወይንም ምልክት በምታይበት ጊዜ የደም መርጋት በሽታ ምልክት ነው ለማለት የሚያስቸግር ነው፡፡ ምልክቶቹ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ግን በሳንባ የደም ስሮች ላይ ችግር ሲያስከትል ትንፋሽ የማጠር እራስን የመሳት የመሳሰሉ ከልብ ችግር ጋር ተመሳሳይነት ያለቸው ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በሽታው እንደጀመረ አካባቢ የሚታየው ምልክት በሁለቱ እግሮች የታችኛው ክፍል ላይ እንደእብጠት ያለ ነገር ሊታይ ይችላል፡፡ እንደቁስለት ህመም ይሰማል፡፡ በእርግጥ እነዚህ ስሜቶች የምን በሽታ ምልክት እንደሆኑ እንዲለይ ችላ ሳይሉ በአስቸኳይ ወደሆስፒታል መሄድ እና ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የደም መርጋት ሕመም በፍጥነት ካልታከመ የሚያመጣው አደጋ ከፍተኛ ስለሚሆን የሁሉንም ትኩረት ይሻል፡፡ የደም መርጋት በሽታ ሊድንም ላይድንም ይችላል፡፡ ...አንደ እርግዝና፣ በኦፕራሲዮን መውለድ ፣ረጅም ጊዜ መተኛት ፣ረጅም ጉዞ ተቀምጦ ማድረግ ...ወዘተ የመሳሰሉትን ጊዜያዊ አጋጣሚዎች ተንተርሶ የሚመጣው የደም መርጋት በሽታ ታክሞ መዳን ይቻላል፡፡ነገር ግን በተለይም በዘር በመተላለፍ የሚመጣ ከሆነ እስከመጨረሻው ማዳን ባይቻልም ነገር ግን ማከም ይቻላል፡፡ በአጠቃላይም የደም መርጋት በሽታን የሚያመጡ ምክንያቶችን መከላከል ይቻላል፡፡ ምክንያቶቹ ችላ ተብለው በሽታው ስር እስኪሰድ የሚቆይ ከሆነ ግን እንደተሰጠው ስያሜ (Silent killer) በመሆኑ ሕይወትን ይቀጥፋል ...ብለዋል ዶ/ር ሙሁዲን አብዶ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት፡፡

Read 11394 times