Saturday, 03 August 2013 10:22

የተጠርጣሪ ባለሃብቶቹን ኩባንያዎች የማስተዳደር ጉዳይ እያከራከረ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

ፍ/ቤቱ በሁለት መዝገቦች ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የምርመራ ቀጠሮ ሰጠ
በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የከፍተኛ ባለሀብቶች ኩባንያዎችን የማስተዳደር ጉዳይ የፀረሙስና ኮሚሽን መርማሪዎችንና ተጠርጣሪ ባለሃብቶችን እያከራከረ ሲሆን ፍ/ቤቱም በጉዳዩ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለማክሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

ኮሚሽኑ የአምስቱን ኩባንያዎች ንብረት፣ ኮሜርሻል ኖሚኒስ እንዲያስተዳድርለት ለፍ/ቤቱ ማመልከቱ የሚታወስ ሲሆን ሃሙስ በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ በተመረጠው ድርጅት ኩባንያዎችን የማስተዳደር አቅም ላይ ጥያቄ አንስቷል፡፡ የኮሜርሻል ኖሚኒስ ልምድ በአብዛኛው ከገንዘብ መሰብሰብ እና ክፍያ መፈፀም እንዲሁም ከአክሲዮን ማሻሻጥና ከመሳሰሉት ጋር የሚገናኝ ሆኖ ሳለ፣ እነዚህን በተለያዩ የምርትና የአገልግሎት ስራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች እንዲያስተዳድር እንዴት ተመረጠ የሚል ጥያቄ ለኮሚሽኑ አቃቤ ህግ አቅርቧል፡፡ የኮሚሽኑ አቃቤ ህግም ኮሜርሻል ኖሚኒስ በተመሳሳይ የሚያስተዳድራቸው ሌሎች ኩባንያዎች መኖራቸውን በመግለፅ፤ የድርጅቱን የማስተዳደር ብቃት አጥንተንና አምነንበት ነው የመረጥነው ብሏል፡፡

አቃቢ ህግ አክሎም “የተሰጠን ቀን አጭር ስለነበር ኮሜርሻል ኖሚኒስን ሳናነጋግር ብቃቱን ካለፉት ልምዶቹ በማረጋገጥ ነው ያቀረብነው” ብሏል፡፡ ፍ/ቤቱም በድጋሚ የማስተዳደር ብቃቱ በሚገባ ተመርምሯል ወይ የሚል ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ በተሰጠን አጭር ጊዜ ስለ ድርጅቱ ብቃት ማስረጃ አሰባስበን አቅርበናል በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ከኩባንያዎቹ መካከል በእነ አቶ መላኩ ፋንታ መዝገብ ተካትተው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ከተማ ከበደ በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ኬኬ ሃላፊነቱ የተወሠነ የግል ማህበር፣ ግለሰቦችን ለአስተዳዳሪነት መርጦ ያቀረበ ሲሆን በተመሳሳይ ፍ/ቤቱም በነዚህ ግለሠቦች የብቃት ጉዳይ ላይ ጥያቄ አንስቷል፡፡ በእለቱ በችሎቱ የተገኙት የድርጅቱ ተወካይም ድርጅቱ ቡና ወደ ውጪ ከመላክ፣ ማሽነሪ ከማስመጣትና ከጨርቃጨርቅ ምርት ጋር የተያያዙ በርካታ ስራዎች ያሉት መሆኑንና የሰው ሃይሉ በርካታ በመሆኑ ይህን ሃላፊነት ወስደው ማስተዳደር ይችላሉ ብለን መርጠን አቅርበናል ብለዋል፡፡
ሌላው በእነ አቶ ገ/ዋህድ መዝገብ ስር ተካትተው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ነፃ ትሬዲንግ በራሱ በኩል ተመርጦ የቀረበ አስተዳዳሪ አለመኖሩን ፍ/ቤቱ አስታውቆ፤ ለጠበቆቹ “በምን አይነት ሁኔታ እንዲቀጥል ትፈልጋላችሁ?” የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ጠበቆቹ ቀደም ሲል በነበረው ችሎት ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ አጥንተን እንድንመጣ በታዘዝነው መሠረት ጉዳዩን በጋራ የተወያየንበት ቢሆንም ከተስማማንበት ውጪ ኮሚሽኑ ኮሜርሻል ኖሚኒስን መርጦ አቅርቧል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ከኮሚሽኑ ጋር የተነጋገሩበትም ችሎቱ ላይ ተለዋጭ ቀጠሮ እንጠይቃለን፤ ከዚያ በኋላ ተስማምተን እንሾማለን የሚል እንደነበር ለፍ/ቤቱ ያመለከቱት ጠበቆቹ፤ በኩባንያው በኩል በአጭር ቀን ውስጥ ብቃት እና ዋስትና ያለውን አስተዳዳሪ አካል አጣርቶ መርጦ ማቅረብ ከባድ ነው ብለዋል። በአሁን ሠአት ኩባንያው ወጥ የሆነ አስተዳደር እንዳለው የተናገሩት ጠበቆቹ፤ በቀጣይ ከየመስሪያ ቤቶቹ የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንዲያስተዳድር ሃሣብ አቅርበዋል፡፡
ፍ/ቤቱ እነዚህን አቤቱታዎች እና ምላሾች ካዳመጠ በኋላ “ለምንድን ነው ተነጋግራችሁ በጋራ መወሠን ያልቻላችሁት?” ሲል የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ ጠይቋል፡፡ አቃቤ ህግም ኬኬ ሦስት ግለሠቦችን መርጦ ያቀረበ ቢሆንም ያቀረቡት ግለሠቦች እዚያው በኩባንያው ሠራተኛ የነበሩ በመሆናቸው ገለልተኛ ሆነው ማስተዳደር እንደማይችሉ ስለሚታመን መስማማት አልቻልንም ብሏል፡፡ ነፃ ትሬዲንግን በተመለከተም በሃሣብ ደረጃ እንጂ በፅሁፍ ምርጫቸውን አላቀረቡልንም በማለት ገልጿል። ፍ/ቤቱም እነዚህን የግራ ቀኝ ክርክሮች ካዳመጠ በኋላ፣ ኮሚሽኑና የተጠርጣሪ ባለሃብቱ ኩባንያዎች ጠበቆች የመነጋገርና የማጥናት ስራውን በጋራ እንዲቀጥሉ በማሣሠብ እንዲሁም ፍ/ቤቱ ራሱ ጉዳዩን የማስጠናት አማራጭ እንዳለው በማስገንዘብ በጉዳዩ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለማክሠኞ ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም በድጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ ሠጥቷል፡፡
በሌላ በኩል በእለቱ ፍ/ቤቱ በእነ ተመስገን ስዩም እና በእነ መልካሙ እንድሪያስ መዝገብ ስር የተካተቱ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ የተመለከተ ሲሆን ለመርማሪ ቡድኑ በሁለቱም መዝገቦች ለመጨረሻ ጊዜ የስምንት ቀን የምርመራ ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በእነዚህ ሁለት መዝገቦች ላይ የተለያዩ የምርመራ ስራዎችን በተሠጠው 10 ቀን ውስጥ ማከናወኑን አመልክቶ፣ ይቀሩኛል ያላቸውን ተግባራት ከዘረዘረ በኋላ፣ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ቢሆንም የተጠርጣሪ ጠበቆች ከዚህ ቀደም የተሠጠው ቀጠሮ በቂ ስለሆነ ሊፈቀድለት አይገባም፣ የክስ መመስረቻ ጊዜ ብቻ ይሠጠው፣ ተጠርጣሪዎች ከ80 ቀን በላይ በእስር ላይ መቆየታቸው የፍርድ ያህል እየታሠሩ እንደሆነ ይቆጠራል የሚሉና ሌሎች ምክንያቶችን በማቅረብ ተከራክረዋል፡፡ ፍ/ቤቱም የመርማሪ ቡድኑ ይቀሩኛል ብሎ በዘረዘራቸው ስራዎች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡
የግራ ቀኝ የቃል ክርክሩን ሲያዳምጥ የቆየው ፍ/ቤቱም፣ በሁለቱም መዝገቦች ለመጨረሻ ጊዜ በማለት የስምንት ቀን ጊዜ ብቻ በመፍቀድ፣ መዝገቡን ለነሐሴ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

 

Read 2051 times