Saturday, 03 August 2013 10:47

ማስነጠስ እና መዘዙ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(9 votes)
  • ከባድ ማስነጠስ ለሞት ሊዳርግ ይችላል 
  • የኪስ ቦርሳዎች ለጀርባ ህመም ያጋልጣሉ

 በህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ውስጥ በጉንፋን፣ በቲቢና መሰል በትንፋሽ ሊተላለፉ በሚችሉ በሽታዎች የተያዘ ሰው ቢያስነጥስ የበሽታውን ጀርሞች በማሰራጨት ከሁለት እስከ አምስት ደቂቃ ጊዜ ውስጥ በመኪናው ውስጥ ያሉትን መንገደኞች ሁሉ በበሽታው ሊበክል እንደሚችል ይታወቃል፡፡ 

ይህንን የጤና ችግር ለማስወገድም የህዝብ ትራንስፖርቶች ሁልጊዜም መስኮታቸው ክፍት እንዲሆን የጤና ባለሙያዎች ሲመክሩ ይሰማል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቲቢ በሽታን ለመከላከል በሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫዎችም “መስኮት በመክፈት ቲቢን እንከላከል” በሚል መሪ ቃል በርከት ያሉ ማስታወቂያዎችንና ዘመቻዎችን ያካሂዳል። ከዚህ በዘለለ ዛሬ ዛሬ በማስነጠስ ላይ አዳዲስ ጥናቶች እና ምርምሮች እየተካሄዱ ውጤታቸውም ይፋ እየሆነ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረትም ማስነጠስ እጅግ ከፍተኛ ህመምና ስቃይ ላለው የአከርካሪ ዲስክ መንሸራተትና ለዲስክ መሰንጠቅ እንዲሁም ለአጥንት መሰበርና ለልብ ህመም ይዳርጋል እየተባለ ነው፡፡

የማስነጠሱ ኃይል እጅግ ከፍተኛ ከሆነም በጭንቅላት ውስጥ የሚገኙ የደም ስሮች እንዲበጠሱ በማድረግ፣ በጭንቅላት ውስጥ ደም ፈሶ የአንጣሹ ህይወት እንዲያልፍ ሊያደርግ ይችላል፡፡
በአገራችን ከሚታዩ የወገብ ህመሞች 80% በላይ የሚሆኑት መነሻቸው የዲስክ መንሸራተት ነው፡፡ የአከርካሪ አጥንት ህክምና ዶክተሩ (ካይሮ ፕራክተር) ዶ/ር ተስፋሁነኝ እንዳለ እንደሚናገሩት፤ በምናነጥስበት ወቅት የሰውነታችን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከቁጥጥር ውጪ ስለሚሆን ጅማቶቻችን ከልክ በላይ ይወጠሩና የጡንቻ መጋጠሚያና ዲስኮች አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡
የማንጠሱ ኃይል እጅግ ከፍተኛ በሚሆንበት ወቅት የአከርካሪ ዲስኮችን ሊሰነጥቅ፣ ጥርስ ሊያረግፍና ምላስንና የጉንጭ ውስጠኛው ክፍል ሊቀረጠፍ ይችላል፡፡ ችግሩ የጭንቅላት የደም ስሮች እንዲበጠሱ በማድረግ ደም በጭንቅላት ውስጥ ፈሶ የአንጣሹ ህይወት እንዲያልፍ ሊያደርገውም ይችላል፡፡
“በእያንዳንዱ የአከርካሪ አጥንቶቻችን መካከል የሚገኙትና ዲስክ እየተባሉ የሚጠሩት አካላት የተሰሩት ስፖንጅ መሰል ከሆነ የሥጋ ክፍል ነው። እነዚህ ዲስኮች ዋና ተግባራቸው የአከርካሪ አጥንቶችን ለመለያየት እና በአከርካሪዎች መካከል ጤናማ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ ነው። ህብለሰረሰር፣ አከርካሪ አጥንት፣ ዲስኮችና ጡንቻዎቻችን በቅንጅት የሚሰሩት ሥራ ጤናማ ሆነን ለመራመድና ለመቆም እንድንችል ያደርጉናል። እንደ ልባችን ጐንበስ ቀና እንድንል፣ አንገታችንን በፈለግንበት አቅጣጫ ማዟዟር እንድንችል፣ አቋቋማችንና አካሄዳችን የተስተካከለ እንዲሆን ዲስኮች ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ ዲስኮች በአደጋ፣ ከባድ ዕቃ በማንሣትና በኃይል በማስነጠስ ተፈጥሮአዊ ቦታቸውን ለቀው ሊንሸራተቱ ወይም ሊሰነጠቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ወቅትም ታማሚው እጅግ ከፍተኛ ለሆነ ስቃይ ሊዳረግ ይችላል” የሚሉት ዶ/ር ተስፋሁነኝ፤ ችግሩ እንደልብ ጐንበስ ቀና ማለት አለመቻል፣ አንገትና ትከሻን በፈለጉበት አቅጣጫ ለማዟዟር መቸገር፣ እንደ ኤሌክትሪክ የሚነዝር ህመም፣ የጡንቻዎች መወጣጠርና የአካል መዛልንም ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ማስነጠስ ድንገታዊና በቅፅበት የሚከሰት ነገር ሲሆን በዚህ ወቅት የሰውነታችን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከቁጥጥር ውጪ ይሆናል፡፡ ለማስነጠስ መነሻ የሚሆኑ ምክንያቶች እነዚህ ናቸው ብሎ መዘርዘሩ አስቸጋሪ ነው ያሉት ዶክተሩ፤ በአገራችን የተለመዱና የማስነጠስ ችግርን ሊያባብሱ የሚችሉ እንደ ሰናፍጭ ያሉ ምግቦች በድንገትና ሳይታሰብ የሚከሰቱ ማስነጠሶችን ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለጉንፋን፣ ለሳይነስና አፍንጫ ከርካሪ ለሆኑ ችግሮች ዳማከሴን ጨምቆ ውሃውን በአፍንጫ ውስጥ በመክተት እንዲያስነጥስ ማድረግ የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች በማንጠስ ምክንያት ሊከሰቱ ለሚችሉ ችግሮች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግባቸው ይገባል ሲሉ ይገልፃሉ፡፡
ማንጠሱ ጠንከር ያለና የሰውነት ኃይልን የሚያናጋ አይነት እንቅስቃሴን የሚፈጥር ከሆነ በጭንቅላታችን ውስጥ ያሉ የደም ስሮችና ጡንቻዎች እንዲናጉና እንዲበጠሱ በማድረግ ደም ወደ ጭንቅላታችን ውስጥ እንዲፈስ ያደርጋል፡፡

በዚህ ሣቢያም አንጣሹ ወዲያውኑ ህይወቱ ሊያልፍ ይችላል፡፡ ለማስነጠስ ፈልገን ማስነጠሱ እምቢ ሲለን ወይንም የመጣው ሲመለስ አሊያም እኛው እራሳችን ማንጠሱን ለመዋጥ ወይም ላለማስነጠስ ትግል በምናደርግበት ወቅት በጭንቅላታችን ውስጥ ከፍተኛ ግፊት ስለሚፈጠር ለጆሮ ታምቡር መቀደድ ችግር ሊዳርገን፣ ለደም ስሮችና ለጭንቅላታችን ጡንቻዎች መበጠስና ለጭንቅላት ደም መፍሰስ ምክንያት በመሆን ለሞት ሊያበቃን እንደሚችል ዶ/ር ተስፋሁነኝ ገልፀው፤ ይህንን ችግር ለማስወገድ በማንጠስ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ እንደሚገባን ተናግረዋል፡፡ “ልናነጥስ ስንሞክር ወይንም የማንጠሱ ስሜት ሲመጣ አስቀድሞ ይታወቀናል፡፡ በዚህ ጊዜም ቆመን ከሆነ ቀጥ ብለን በመቀመጥና የሆዳችንን ጡንቻዎት በማጠንከር ማስነጠሱ የሚፈጥረውን እንቅስቃሴ ወይም ንቅናቄ ልናቀዘቅዘው (ልናለዝበው) እንችላለን፡፡ ይህ ደግሞ በማንጠሱ ፍጥነትና ጥንካሬ የሚደርሰውን የመውደቅ አደጋ ሊያስቀርልን ይችላል ብለዋል፡፡
የአሜሪካ የስፓይናል ኦርቶፔዲክ ሰርጀኖች ምርምር ውጤት እንደሚያሣየው፤ የአከርካሪ ዲስኮቻችን በሁለቱ የአከርካሪ ቬርቴብራ መካከል የሚቀመጡ ለስላሣ ትራሶች ሲሆኑ እነዚህ ለስላሣ ትራሶች በወጣትነት ዕድሜ ዘመን ለስላሣና እንደ ልብ ተለጫጭ ሆነው ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ የመለጠጥ አቅማቸው እየቀነሰ መጥቶ ለአደጋ በቀላሉ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ወቅት የሚያጋጥም ድንገተኛና ጠንካራ ማስነጠስ እነዚህን ዲስኮች በቀላሉ ሊሰነጥቃቸው ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በማንጠሱ ወቅት ጥርሶች ከተጋጩ ሊረግፉ፣ አጥንቶች ሊሰበሩና ለልብ ህመምም ልንጋለጥ እንደምንችል ምርምሮቹ ያረጋግጣሉ፡፡
በማስነጠስም ሆነ በሌላ ጉዳት ሣቢያ የሚከሰቱ የዲስክ መንሸራተቶች፣ ጥመቶችና የዲስኮች ከተፈጥሮአዊ ቦታቸው መልቀቅ ችግሮች መኖራቸው ሊረጋገጥ የሚችለው ሆርሞግራፊ፣ ሲቲ ስካንና፣ ኤም አይ አር፣ በተባሉ የህክምና የምርምር ዘዴዎች ነው፡፡ በዲስኮች ላይ የሚከሰቱ ጥመቶች፣ መንሸራተቶችና መሰንጠቆች በተለያዩ የህክምና ዘዴዎች ማከምና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ይቻላል፡፡ መድሃኒቶች፣ ደረቅ መርፌዎችና የቀዶ ህክምና ዘዴዎች ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምና አይነቶች ናቸው። በዲስክ መሰንጠቅ ወይም መንሸራተት ሣቢያ የተከሰተን ህመም በማሣጅ ቴራፒ ወይም በሴራጂም ለማስወገድ መሞከሩ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል፣ በቅድሚያ የህክምና ባለሙያዎችን ማማከር እንደሚገባ ዶ/ር ተስፋሁነኝ ያሣስባሉ፡፡
በማስነጠስና በተለያዩ ጉዳቶች ሣቢያ ከሚከሰተው የዲስክ መሰንጠቅ ወይንም መንሸራተት ችግር በተጨማሪ በወንዶች የኋላ ኪስ ውስጥ እንደዘበት የሚቀመጡት የኪስ ቦርሣዎች (ዋሌት) በዳሌ አጥንት ላይ መዛባትን በማስከተል ለጀርባ ህመም እንደሚዳርግ ጥናቶቹ ይፋ አድርገዋል። ይኸው የወንዶች የኪስ ቦርሳ ዋሌት ክብደቱ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የሚያስከትለውም ችግር የዛኑ ያህል እየጨመረ እንደሚመጣና ከፍተኛ የአጥንት መዛባት በማስከተል ለጀርባ ህመም ያጋልጣል። እናም ጐበዝ ሁላችንም እንደ ቀላል የምናየውና ከምንም ሣንቆጥር በየዕለቱ የምናከናውነው ማስነጠስ እንዲህ ላለ ከባድ ችግርና ጉዳት ሊዳርገን ይችላል፡፡ እናስ ጥንቃቄ ማድረጉ ሳይሻል ይቀራል ትላላችሁ?

Read 6970 times