Saturday, 03 August 2013 10:55

“የሽልንጓ ሴት” ግጥሞች ዳሰሳ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

           የክረምቱ ዶፍ ውስጥ ሆነን ሙሽራ ጀንበር የምንናፍቀው በተስፋ ነው፡፡ የብርሃን ቬሎ አጥልቃ ብቅ የምትለው የመስከረም ሰማይ ጀንበር - ከአደይ አበባ ጋር እየጠቃቀሰች መሣቅዋን የምናነብበው ዛሬ ለምቦጩን ከጣለው ሰማይ ሥር ተኮራምተን ነው። ግጥሞችም እንደ አበባ ናቸው፤ በተስፋ ይስቃሉ፣ በትካዜ ይጠወልጋሉ፡፡
ዛሬ የሰው ልጆች የገደል ማሚቱዎች ናቸውና በአብዛኛው እንደኛው ቀይ፣ ጥቁር፣ ጠይም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በቅርፃቸው ሳይሆን በይዘታቸው፡፡ እንደኛው ደም አላቸው፤ ይሞቃሉ፤ ይቀዘቅዛሉ። እንደኛው ልብ አላቸው፤ ይዘለልላሉ፤ ሕይወት ይረጫሉ፡፡ ምናልባትም በዚህ ዝምድና እንነፋፈቃለን፡፡ ሰው ከሌለ ግጥም የለም፤ ሰውም ያለ ግጥም ዝም ብሎ የተገተረ ጭራሮ ነው፡፡ በዜማ ያለቅሳል፣ በዜማ ይደንሳል፤ በዜማ ይተክዛል፣ በዜማ ይጽናናል፡፡ ይፈነጫልም! ሰውና ግጥም፣ ግንድና ሀረግ ናቸው ልበል? ማነው ሀረጉ? ቀን ይመልሰው፣ ብለን መዝለል አንችልም?...የጥያቄውን አጥር?...ሰውም ግጥምም ጥያቄ ነው፤ በጥያቄ የተጠቀጠቀ። በሃሳብ የሚነድድ እሳት! ታዲያ ሁለቱንም ችቦ አድርገን በአንድ ደመራ ስር ከምረን ሲነድዱ ይኑሩ ብለን እንተዋ!...አዎ!
አሁን የወጣቷ ገጣሚ ጽጌ ተምትም ግጥሞች መሠሉኝ ስሜቴን የቆሰቆሱት፣ የነካካቻቸው ነገሮች ደም አላቸው፤ ነፍስና ትንፋሻቸው፣ መዐዛና ዜማቸው ወደ ውስጥ ይዘልቃል!
ገጣሚዋ እኔ መግቢያዬ ላይ ስለተናገርኩት የአዲስ ዘመን መባቻ የምትለው ነገር መጀመሪያ ቀልቤን ሳበው፡፡ መጽሐፉን እንዳገኘሁ ማረፊያ ቦታ እስካገኝ ድረስ ያላቆዩኝ ግጥሞች ነበሩና አለፍ አለፍ እያልኩ ማየት ግድ ሆነብኝ፡፡ የጀርባው ግጥም ነው የልቤን ልብ ያንጠለጠለው፡፡
“መሬት ጥል ነጥፎባት፤
ጅብ በበቃው ሥጋ፤ ውሾች ሲራኮቱ ድምጽ ከተሰማ፣
ሊነጋ ነው ሌቱ ጐህ እየቀደደ፣ ሰማይ እየደማ፡፡” ይላል ግጥሟ፡፡
ጅብ እስኪበቃው ሲበላ፣ ጅብ ጠግቦ ሲተርፈው፣ ምን ያህል ጥንብ እንዳለ መገመት አያዳግትም፡፡ ማነው ግን ሟቹ? ብቻ እንዲህም ሆኖ በዚህ ሞት በገነነበት ፍርሀት ጉሮሮ ላይ ትንፋሽ ባሳጠረበት፣ ፀሊም ድባብ ውስጥ አሁንም ተስፋ አለ ትላለች። የሰው ልጅ ሕይወት ግዝፈቱ ምናልባት የተስፋ አቅሙ ሳይሆን አይቀርም ወደሚለው ድምዳሜ ትገፋናለች፡፡ ግን ደግሞ ጐህ ሲቀድ በነፃ አይደለም። ሰማዩ ስለ ብርሃን ደምቷል፡፡ ስለ ብርሃን ዋጋ ከፍሎዋል፡፡
ጨለማው የሚነጋው፣ እንቆቅልሹ የሚፈታው በዚህ ዋጋ በከፈለ ብርሃን ነው!
“ይነጋል?” ብላ ትተነብያለች ጽጌ!
ገጣሚ ጽጌ አሁንም “ትንቢት” በሚለው ግጥምዋ ታፏጭልናለች፡፡
ኑ…“ቃ” ቃ - እንጫወት
የቅጠል እንጀራ የጭቃ ዳቦ እንጋግር
ጠላ እንጥመቅ ከሳር፣ ቡና እናፍላ ከአፈር
ኑ…ቃ ቃ እንጫወት
ቆርኪ አለ ለስኒ፤ ጆግ አለ ለጋኑ
ኑ፡፡
ደረሰና ዛሬ - የልጅነት ትንቢት
ቢቸግረኝ የውነት ቁራሽ ባትኖር በቤት
የውሸት፣ የውሸት፡፡
ኑ… “ቃ” “ቃ” ንጫወት፡፡
የብዙዎቻችን የልጅነት ትዝታ ፊታችን ድቅን የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡ ጓደኞቻችን ይታሰቡናል፡፡ “ቡና ጠጡ” ተባብለን ከቆርኪ ከንፈር ጋር እየተሳሳምን አየር የሳብነው - ይታሰብናል፡፡ ደሞ እዚያው አንቀርም፤ ወዳነፀረችበት ሕይወት መጥተን በርካታ በሮችን እናንኳኳለን፡፡ መጨረሻችንም ከንፈር መምጠጥ ይሆናል፡፡
ጽጌ ልጅነትን ከነምናምኑ ፊታችን ደርድራዋለች። ደርድራ አልተወችም፤ ለዛሬ ሕይወታችን መልክ ማያ መስታወት አድርጋ አስቀምጣለች፡፡ ቅሬታ አላት፤ ለምን የሚል ጥያቄ ግጥሞችዋ ውስጥ ተገትረዋል፡፡ ለምን እንደ ልጅነታችን ጨዋታ የእውን ሕይወታችን ባዶ ሆነ? ለምን ጓዳችን አልሞላ አለ? ብላ አግድም እያወራች ነው - በዜማ!...አብረን እናጐራጉር ነው ነገሩ! መጀመሪያም ግጥም እየነደደ - ያነድዳል - ብዬ የለ! ..አንድ ደመራ ውስጥ ልንጣድ ነው፡፡
“ዝምድና 2” በሚል ርዕስ የተፃፈችው መንቶ ግጥም - ስለጊዜና ስለለውጥ ግዙፍ ሃሳብ የተሸከመች ይመስላል፡፡ እንዲህ ትላለች፡፡
እንኳንስ ለመንካት፣ ለእይታ ር….ቆ የተሰቀለ ሥጋ
ቋንጣ ሆኖ ይወድቃል - ቀን እየመሸ ሲነጋ፡፡
ይህች ግጥም ዜማ ትሠብራለች፡፡ ግጥሟ ምናልባት ሥጋዊ ውበትንም የምትወክል ይመሥላል። ጊዜ የሰውን ውበት ዘልዝሎ ቋንጣ ያደርገዋል፡፡ ከዚያም ይወድቃል፡፡ ብቻ የገጣሚዋ አይኖች ጠለቅ ያሉ ናቸው፡፡
“የሞት ስዕል 1” የሚለውን ግጥምዋን ደግሞ እንየው :-
“የእጆቼን አሻራ፤ የመዳፌን መስመር
ቀለሙን ጉዞውን “ባይኖቹ ቆምሮ
“ሞትሽ” ቀርቧል ያለኝ ቀኔን አሳጥሮ
ጥንቆላው ሰምሮለት - ሞቴን “ባይኔ አየሁት
እፀዳን አሳልፌ በ እንደሰጠሁት፡፡
ግጥሙ የመዳፍ ንባብን የቀጣዩን ዘመን ትንበያ በቀጥታ ቢያሳይም፣ በገፀ ባህሪዋ አንፃር ሲታይ አንደኛው ተባዕት ገፀ ባህሪ መዳፍዋን አይቶ፣ ሞትዋን ያሟረተባት ነገር እውን መሆኑ ያንገበገባት ይመስላል፡፡ ሞትዋ ደግሞ አፈር ገብቶ እስትንፋስን ዘግቶ መሰናበት ሳይሆን፣ በቁም ሳሉ መሞት ነው። የግጥሙ ተራኪ እንስት፣ ሞት በፍቅር እጅዋን እያሻሸ ያሟረተባት ተባዕት እጅ መውደቅዋ ነው። ግጥም ከዚህ በላይ ተርትሮ ገመናውን ባያሳይ ግድ አይባልምና “ከእጅ ያውጣት” ብሎ ደግ ደጉን መመኘት ነው፡፡
የጽጌ “ፀፀት” የተሰኘ ግጥም እስካሁን ስለፀፀት ካነበብኩዋቸው ግጥሞች በተለየና በሚገርም ሁኔታ የተገለፀ ነው፡፡
“በሞኝነት ብልጠት ስቶ፤ ሳያስቡት እንደቅዠት
የያዙትን ድንገት ሲያጡ
ብዙ ናቸው ቅጠሎቹ፤ ከሀዘን ልብ ተሸምጥጠው
በዓይኖች ላይ የሚረግፉ - በጉንጮች ላይ የሚሰጡ፤
የእምባ ግንድ ልብ ውስጥ ነው፤ ቅርንጫፉም ከዚያው ይመዘዛል፤ ቅጠሎቹ - የእምባ ዘለላዎች በሀዘን ተሸምጥጠው ጉንጭ ላይ ይሰጣሉ” ትላለች ግሩም ምሰላ፣ ግዙፍ ምናብ ነው፡፡
ግጥሞችዋ ብዙዎቹ ስሜት…የሚያስደምጡ ሌሪኮች ሆነው ለዛ ባላቸው ቃላት፣ በጥሩ ስነ ግጥማዊ አሰኛኘት ደርድራቸዋለች፡፡ አጫጭር ሆነው ዘለግ ያለ ታሪክና ሁነት የያዙ፣ ረዝመው የቃላት ትንፋሽ የማያጥራቸው ግጥሞች አሏት፡፡
ለምሳሌ ይህቺ አራቶ - ግጥም ታስደምማለች
ነፍሱ ስንፍናን ለለመደ
ኑሮውን ለቀኑ ለሚያማ
ህይወትን አትንገሩት
አያዳምጥም እየሰማ
በዚህች ግጥም - “ነፍስ” ውስጣዊ ማንነትን የምትወክል ናት፡፡ ስሜት፣ ዕውቀትና አእምሮ በእርሷ ይጠቀለላል የሚለው እምነትም የዘገየ ነው፡፡ ታዲያ ገጣሚዋ ስንፍና ኑሮዋ ስለሆነች ነፍስ ባለቤት በተባዕት ፆታ ታወራለች፡፡ ስንፍና እንደ ድንጋይ ተከምሮበት ሰበብ እየመዘዘ በየቀኑ ለቀን ጆሮ ኑሮውን ለሚያብጠለጥል ሰው፣ የሕይወትን ትርጓሜ በመተንተን፣ የውበትን ሥዕል ለማሳየት፣ አትድከም ብላ ሦስተኛ ሰው ትመክራለች፡፡ እያንዳንዱ አንባቢ ሦስተኛ ሰው ነው፡፡ ይተረክለታል፡፡ ምናልባት ደግሞ ሁለት ቦታ የሚገኝ ሰው ሊሆን ይችላል። ወይም እንችላለን፡፡ ሰነፍ ከሆንን በስንፍናችን ከምንቀምሳት ልምጭ ሌላ፣ እንደገና ሌላ የምክር ቃል ይጠብቀናል፡፡ “አትድከም ሰነፍ ይሰማል እንጂ አያዳምጥም፡፡ ለዚህ የሚሆን ቀልብ የለውም፤ ጊዜውን አባክኖ ያንተን ጊዜ እንዳያባክን ተጠንቀቅ…ነው ነገሩ፡፡
“ማነው ባለጋሪ?”ን ሳነብብ ሁለት የስነግጥም ምሁራን ትዝ አሉኝ፡፡ ኤስ ኤች በርተን፣ ለውረንስ ፔሪኒ “ስነግጥም በቀላል ቋንቋ ጠሊቅ ሃሳብ ሊይዝ ይችላል፤ ቃላት ብቻ ግጥም አይሰሩም” የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡ እንዲህ ትለናለች ገጣሚዋ ጽጌ :-
ላቡን አንጠፍጥፎ ሀገር እየዞረ
በእጅ እግሩ እየደቃ - ጋራ እየሾፈረ
ለሱ ባይከፈል፤ ባይደርሰው ስባሪ
ሰው ወይስ ፈረሱ …ማነው ባለጋሪ?””
ገጣሚ የሚደነቀው ይሄኔ ነው፡፡ ያነሣችው የፍትህ ጥያቄ ነው፡፡ ለመሆኑ ሰውን ባለጋሪ ያደረገው ማነው? ጋሪውን እርሱ አይጐትት፣ ብረትና እንጨቱን እርሱ አልተሸከመ! … ግን በብሩ ስለ ገዛ “አያ እገሌ … ባለጋሪው” ይባላል፡፡ ልብ ያላልነውን ልብ ብላለች፡፡ ነገሮችን ባልታዩበት መንገድ ማየት የገጣሚ አንዱ ብርቅ ተሰጥዖ ነው፡፡
“የዝንቦች ጨዋታ” ሌላኛው “የሽልንጓ ሴት” ግጥም ነው፡፡
በመሶብሽ ሞልተው ከእንጀራሽ ከወጡ
በእጃቸው በእግራቸው ባ’ፋቸው እያወጡ
ሲያሻቸው ሲበሉ፣ ሲያሻቸው ሲረግጡ
ጥጋባቸው በዝቶ ሌማትሽን አርክሰው በቆሻሻ ጩኸት
ወዲያ ወዲህ ሲሉ በመሶብሽ አናት
አይኖቼን አንስቼ የበለሉትን ባየው!?
እናት ሙች! ሙሽ!
ያው እንዳስቀመጥሽው አንዳ=U ሳይነካ፤
የዝንቦች ጨዋታ እንደዚህ ነው ለካ!
“የሽንልጓ ሴት” ውስጥ ጥቂት የማይባሉ ግጥሞች ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ባለ ሁለት መልክ መልዕክት የያዙ ይመሥላሉ፡፡ አሊጐሪ ሰምና ወርቅ ናቸው፡፡ እማሬያዊና ፍካሬያዊ እንደምንላቸው ዓይነት መልዕክቶች በውስጠ ወይራነት ሙሉ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ይሁን እንጂ ግጥም መልዕክት ማስተላለፍ ዋና ዓላማው አይደለም፡፡ በሚያስደንቅ መንገድ መኮርኮር ግን የላቀ ችሎታ ይጠይቃል ባይ ነኝ፡፡ ወጣት ገጣሚያን እንዲህ ሠርሠር አድርገው፣ አድማስ ዘልቀው ካዩ፣ ነገ ደግሞ ሌላ ውበትና ሌላ ልዕቀት ይመጣሉ፡፡ ሌላው እጅግ አይረሴ ነገር ግጥም የሙዚቃ ብልት መሆኑ ነው፡፡ ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነውና፣ በፈረሳይ በእንግሊዝ፣ በላቲን፣ በግሪክ ቢሆን ያለ ቃላት ትርጓሜ እንኳን ልባችንን ሊያስመታ፣ ስሜት በደማችን ጫንቃ ሊጋልብ ይችላል፡፡ ላምቦርን እንዲህ እንደሚሉት፤ “most fatal mistake we can make regard to poetry is to forget that poetry was born of music and is a form of music” ገጣሚት ጽጌ ተምትም በዜማ ግጥም ሸጋ ጅማሬ አላት፡፡ የነገዋ ብሩህ ሣቅም ደማቅ ሆኖ እንደሚመጣ ተስፋ አለኝ፡፡

Read 4528 times