Saturday, 03 August 2013 11:06

ጊዮርጊስ የምድቡን መሪነት ለማጠናከር 2 የቱኒዚያ ክለቦችን ይፋለማል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

በ10ኛው የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ ቅዱስ ጊዮርጊስ የምድብ አንድን መሪነት ለማጠናከር በሁለት ሳምንት ልዩነት ከሁለት የቱኒዚያ ክለቦች ጋር ከሜዳው ውጭ ሊፋለም ነው፡፡ የጎል ድረገፅ አንባቢዎች በጨዋታው ላይ በሰጡት የውጤት ትንበያ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ውጤታማነት ያደሉ ግምቶችን ሰንዝረዋል፡፡ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ ከኤትዋል ደ ሳህል ጋር በሚያደርገው ጨዋታ 40 በመቶው 1ለ0 እንዲሁም 20 በመቶው 2ለ0 እንደሚያሸንፍ ሲገም/ ቀሪዎቹ 20 በመቶ ብቻ 3ለ1 እንደሚሸለፍ ተንብየዋል፡፡
በምድብ አንድ የመጀመርያ ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ የማሊውን ክለብ ስታድ ዴማሊዬን ከ2 ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስታድዬም በኡመድ ኡክሪ እና ፍፁም ገብረማርያም ጎሎች 2ለ0 ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡
ከዚህ ጨዋታ በፊት የጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ከካፍ ኦንላይን ድረገፅ ጋር ባደረገው ቃለምምልስ በምድብ ጨዋታዎች የመጀመርያ ጨዋታን ማሸነፍ በቀጣይ ለሚኖር ውጤታማነት ወሳኝ እንደሆነ ተናግሮ ነበር፡፡ ከምድብ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታዎች በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ3 ነጥብ እና በሁለት የግብ ክፍያ ምድብ አንድን ይመራል፡፡ የቱኒዚያው ክለብ ሲኤስ ኤስፋክስዬን ሌላውን የአገሩን ክለብ ኤትዋል ደ ሳህል በመጀመርያ ጨዋታ 1ለ0 በማሸነፉ በ3 ነጥብ እና በ1 የግብ ክፍያ ሁለተኛ ነው፡፡
ኤትዋል ደሳህል ያለምንም ነጥብ በ1 የግብ እዳ እንዲሁም የማሊው ስታድ ዴማሊዬን ያለምንም ነጥብ በሁለት የግብ እዳ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
በ10ኛው የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ ምድብ ሁለት ደግሞ ሁሉም ክለቦች በመጀመርያ ጨዋታቸው አቻ ውጤት በማስመዝገባቸው በ1 ነጥብ ያለምንም ግብ እዳ ከ1 እስከ 4 ያለውን ደረጃ ተጋርተውታል፡፡ በዚሁ ምድብ የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች የሞሮኮው ኤፍዩኤስ ራባት ከቱኒዚያው ቢዜርቴን እንዲሁም የአልጄርያው ኢኤስ ሴቲፍ ከዲ.ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ በተመሳይ 1ለ1 አቻ ተለያይተዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤትዋልደሳህል ጋር ዛሬ ለሚያደርገው የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ከትናንት በስቲያ ወደ ቱኒዚያ የተጓዘ ከሳምንት በኋላም ወደዚያው በመመለስ የምድቡን 3ኛ ዙር ጨዋታ ከሴፋክስን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህ ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች በኋላ በአራተኛ ዙር የምድቡ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ የቱኒዚያውን ኤትዋል ደሳህልን ይገጥምና ወደ ማሊ በመጓዝ ከስታድ ዴማሊዬን ጋር የምድቡን 5ኛ ዙር ጨዋታ አድርጎ በመጨረሻም ሴፋክስን አዲስ አበባ ላይ በ6ኛ ዙር ጨዋታው በማስተናገድ የምድብ ጨዋታውን ያጠናቅቃል፡፡
በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ሱፕር ስፖርት እንደዘገበው በቱኒዚያ ከሰሞኑ በተፈጠረው ሁከት ሳቢያ በአፍሪካ ደረጃ በውድድር ላይ የሚገኙ የአገሪቱ ክለቦች በሜዳቸው የሚያደርጓቸውን ግጥሚያዎች ላልተወሰነ ጊዜ በዝግ ስታድዬም እንዲያካሂዱ መንግስት እንደወሰነ ነው፡፡ የቱኒዚያ ክለቦች በዚሁ ውሳኔ ላይ አቋማቸውን እስከትናንት ያልገለፁ ቢሆንም ውሳኔው የክለቦቹን ውጤታማነት ሊጎዳ እንደሚችል እና እግር ኳስ አፍቃሪ በሆኑ ደጋፊዎቻቸው ላይ መጥፎ ስሜት መፍጠሩ እንደማይቀር በሱፕር ስፖርት ዘገባ ተገልጿል፡፡ ሁለቱ የቱኒዚያ ክለቦች በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ ውጤታማነት የሚታወቁ የሰሜን አፍሪካ ክለቦች ሲሆኑ ኤትዋል ደሳህል 1 ጊዜ እና ሲኤስ ሴፋክሴዬን ለ2 ጊዜያት ዋንጫውን የወሰዱ ናቸው፡፡
41 ተጨዋቾች የሚገኙበት የኤትዋል ደሳህል ስብስብ 10 የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ሲገኙበት ቡድኑ በትራንስፈርማርኬት የዝውውር ገበያ ተመን መሰረት 11.53 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚያወጣ ሲገመት ሌላው የአገሪቱ ክለብ ሲኤስ ሴፋክሲዬን 3 የውጭ ዜግነት ያላቸውን ተጨዋቾችን ጨምሮ በቡድኑ 25 ተጨዋቾች አስመዝግቦ 6.8 ሚሊዮን ዩሮ የተተመነ ነው፡፡ የማሊው ክለብ ስታድ ዴ ማሊዬን 2 የውጭ ዜግነት ያላቸውን ተጨዋቾችን ጨምሮ በቡድኑ 39 ተጨዋቾች አስመዝግቦ በትራንስፈርማርኬት የዝውውር ገበያ ተመን 650ሺሮ ሲገመት፤ የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 የውጭ ዜግነት ያላቸውን ተጨዋቾችን ጨምሮ በቡድኑ 26 ተጨዋቾች ያስመዘገበው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ125ሺ ዩሮ ተተምኗል፡፡

 

Read 3186 times