Saturday, 03 August 2013 11:12

ዋልያዎቹ በ3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ትኩረት ይስባሉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ደቡብ አፍሪካ ላይ ሲሳተፍ በዚያው አገር በሚኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያገኝ ተጠብቋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ለምትሳተፍበት የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ CHAN ውድድር ያለፈው ከሳምንት በፊት በኪጋሊ ከተማ የሩዋንዳ አቻውን በመለያ ምት 5ለ6 በሆነ ውጤት በማሸነፉ ነው፡፡
የመጀመርያው ተሳትፎ በቻን
በ2014 እኤአ መግቢያ ለሚጀመረው 3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ 12 አገራት ከወዲሁ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ፤ ሊቢያ እና ጋና በቀጥታ ማለፋቸውን ሲያረጋገጡ ፤ ከመካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ ዞን ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ እና ኡጋንዳ፤ ከሰሜን አፍሪካ ዞን ሞሮኮ ፤ ከማእከላዊ አፍሪካ ዞን ኮንጎ፤ ከምእራብ አፍሪካ ዞን ናይጄርያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሞውታንያና ማሊ በመጨረሻ ዙር የማጣርያ ውድድር ያለፉት ሌሎቹ 9 አገራት ናቸው፡፡ በ2010 እኤአ ላይ 19ኛውን የዓለም ዋንጫ እንዲሁም በ2013 እኤአ ላይ 29ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያዘጋጀችው ደቡብ አፍሪካ በ2014 እኤአ ላይ 3ኛውን የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት የውድድሩ አዘጋጆች ከሰሞኑ ተናግረዋል፡፡ 29ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችበት ወቅት ስርዓቱን በሳተ የትኬት አሻሻጥና በስታድዬም ተመልካች ድርቅ የዝግጅት ድክመት ቢታይም ከውድድሩ እስከ 7.2 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ተችሏል፡፡
የአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን በ3ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ደማቅ መስተንግዶ ለማድረግ 50 በመቶ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀም ገልጿል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለዚሁ ውድድር በአራት ከተሞቿ የሚገኙ ስታድዬሞችን አዘጋጅታለች፡፡ የውድድሩን የመክፈቻ እና የመዝጊያ ጨዋታ የምታስተናግደው ኬፕ ታውን 64100 ተመልካች በሚይዘው የኬፕታውን ስታድዬም ፤ ፖልክዎኔ ከ1ሺ በላይ ተመልካች በሚይዘው የፒተር ሞኮባ ስታድዬም ፤ ብሎምፎንቴን እስከ 41ሺ ተመልካች በሚይዘው የፍሪስቴት ስታድዬም እና ኪምበርሌይ 18ሺ ተመልካች በሚያስተናግደው የሆፌ ፓርክ ስታድዬም የቻን ጨዋታዎችን ያስተናግዳሉ፡፡
በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን አማካኝነት የተመሰረተው ሻምፒዮናው በየአገሩ ሊጎች በመጫወት ለፕሮፌሽናል እድል ለመብቃት ያልቻሉ ተጨዋቾችን ወደ ገበያ ለማውጣት፤ የክለቦችን አህጉራዊ አስተዋፅኦ ለማሳደግ፤ የየአገራቱን የሊግ ውድድሮች ደረጃ እና የፉክክር ብቃት ለማጠናከር እንዲሁም በዋናው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር መሳተፍ ለማይሆንላቸው የአህጉሪቱ ቡድኖች የውድድር እድል ለመፍጠር አመቺ መድረክ መሆኑ ይገለፃል፡፡
የስደተኞቹ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ
ዋልያዎቹ የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ወይም ቻን ላይ በሚኖራቸው ተሳትፎ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን አስደናቂ ድጋፍ ስለሚገኙ ከፍተኛ ትኩረት መሳባቸው የማይቀር ነው፡፡ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደበት ወቅት ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ለዋልያዎቹ 12ኛ ተጨዋቾች እንደነበሩ የሚታወስ ነው፡፡ በዋና ከተማዋ ጆሃንስበርግ እንዲሁም ዋልያዎቹ የምድብ 3 ግጥሚያዎችን ባደረጉባቸው በኔልስፑሪቱ ሞምቤላ ስታዲየም እና በሩስተንበርጉ ሮያል ባፎኬንግ ስታድዬም በ50 ሺዎች የሚገመቱ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካ ዋንጫው ከፍተኛ ድምቀት ማላበሳቸው አይዘነጋም፡፡ በስደት፤ በትምህርት እና በስራ በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ግዛቶች የከተሙት ኢትዮጵያውያን በፍፁም የአገር ፍቅር መንፈስ እና አንድነት ለቡድናቸው ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የቻን ውድድር ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋፅጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡
ከአፍሪካ ዋንጫ ወደ ቻን ከዚያም ወደዓለም ዋንጫ…
በሌላ ዜና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ በ2014 ለሚዘጋጀው 3ኛው የአፍሪካ ሻምፒዮና ውድድር ማለፉን ካረጋገጠ በኋላ ለእረፍት የተበተነ ሲሆን ከ6 ሳምንታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ማጣርያ ለማለፍ በምድብ 1 የ6ኛ ዙር ወሳኝ ጨዋታ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ጋር ይገናኛል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን እና ፊፋ ይህ ወሳኝ ጨዋታ በኮንጎ ዋና ከተማ ብራዛቪል እንዲደረግ ሲወስኑ፤ ውድድሩን የሚመሩት ዳኞች ከአልጄርያ መመደባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ5ኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ለመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ማለፍ ትንቅንቅ ማለፋቸውን ያረጋገጡት 3 አገራት ኮትዲቯር ፤ ግብፅ እና አልጄርያ ናቸው በቀሪዎቹ ሰባት ምድቦች ምድባቸውን በመሪነት የሚያልፉትን ለመለየት የስድስተኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ይጠበቃሉ፡፡
ኢትዮጵያ በፊፋ ተገቢ ያልሆነ ተጨዋች በማሰለፍ ምክንያት በቅጣት ሶስት ነጥብ ከተቀነሰባት በኋላ ምድብ አንድን በ5 ጨዋታዎች ባስመዘገበችው 10 ነጥብ እና 1 የግብ ክፍያ ስትመራ፤ ደቡብ አፍሪካ በ8 ነጥብ እና በ4 የግብ ክፍያ፤ ቦትስዋና በ7 ነጥብ እና በ1 የግብ ክፍያ እንዲሁም ሴንተራል እፈሪካ ሪፖብሊክ በ3 ነጥብ እና በ6 የግብ እዳ እስከ አራት ያለውን ደረጃ አከታትለው ይዘዋል፡፡
በምድቡ የ6ኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው ሴንተራል አፍሪካ ሪፖብሊክ እና ኢትዮጵያ በገለልተኛ ሜዳ ኮንጎ ብራዛቪል ላይ ሲጫወቱ፤ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ በሜዳዋ ቦትስዋናን ታስተናግዳለች፡፡ በተመሳሳይ ቀን በተመሳሳይ ሰዓት በሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች በሚመዘገቡ ውጤቶች ኢትዮጵያ ካሸነፈች ብቻ በቀጥታ ለጥሎ ማለፉ ማጣርያ ማለፏን ታረጋግጣለች፡፡
ደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋና በበኩላቸው በመሸናነፍ፤ ከዚያም የኢትዮጵያ ነጥብ መጣል በመጠበቅ በያዙት የግብ ክፍያ ብልጫ ለማለፍ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ የጎል ድረገፅ አንባቢዎች በሰጡት የውጤት ትንበያ ኢትዮጵያ ምድቡን በመሪነት እንደምታጠናቅቅ ተመልክቷል፡፡
በኮንጎ ብራዛቪል በሚደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ሴንተራል አፍሪካን 31.77 በመቶው 3ለ1፤ 15.29 በመቶው 2ለ1 እንዲሁም 12.94 በመቶው 2ለ0 ታሸንፋለች ብለው ገምተዋል፡፡ በሌላው የምድቡ ጨዋታ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ቦትስዋናን 21.05 በመቶው 2ለ0 እንዲሁም 15.79 በመቶው 3ለ1 እንደምታሸንፍ ሲተነብዩ ያህሉ አንድ እኩል አቻ ይለያያሉ በሚል ገምተዋል፡፡
የዋልያዎቹ ዋጋ መጨመር
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ ትውልድ ያሉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ዘንድሮ በእግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ ላይ መሆናቸውን የተለያዩ ሁኔታዎች እያመለከቱ ናቸው፡፡
ዋልያዎቹ ኢትዮጵያ ለ31 አመታት የራቀችበትን ታሪክ በመቀየር ለ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ካበቁ በኋላ ለአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ የመጀመርያ ተሳትፎ የደረሱ ሲሆን አገራችን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ለምትበቃበት እድል ከፍተኛ የውጤት ተስፋ ይዘው ይገኛሉ፡፡ በዚሁ ታሪክ ሰሪ ትውልድ ሳቢያም በትራንስፈር ማርኬት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዝውውር ገበያ የዋጋ ግምት ላይ ጭማሪ እየታየም ነው፡፡ ከወር በፊት በአጠቃላይ ስብስቡ በዝውውር ገበያው የዋጋ ተመን 725ሺ ዩሮ የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እስከ 1 ሚሊዮን ዩሮ በመተመን ግምቱ ጨምሯል፡፡
ለዚህም አራት የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች ወደ ተለያዩ አገራት ክለቦች ዝውውር መፈፀማቸው ምክንያት ነው፡፡
ምንም እንኳን በትራንስፈርማርከት ድረገፅ የጌታነህ ዝውውር ሂሳብ እንደ አዲስ ተጨምሮ ብሄራዊ ቡድኑ በ875ሺ መተመኑ ቢገለፅም ወደ እስራኤል ክለብ አይሮኒ ኒር ራማት ሃሻሮን የሄደው አስራት መገርሳ 37.88 ሺ ዩሮ፤ ወደ ሊቢያው ክለብ አልኢትሃድ የሄደው ሽመልስ በቀለ 128.79 ሺ ዩሮ እና ወደ ሱዳን ክለብ አልሃሊ ሼንዲ የሄደው አዲስ ህንፃ 30.23 ሺ ዩሮ የዝውውር ሂሳብ በዝርዝር በትራንስፈርማርከት ውስጥ ሲገባ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዋጋ ተመን ከ1 ሚሊዮን ዩሮ በላይ መሆኑ አይቀርም፡፡

 

Read 5281 times