Saturday, 10 August 2013 10:26

በነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሥራዎች ላይ የባለቤትነት መብት አልቀረበም ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(3 votes)

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሸክላ 100ኛ አመት በዓል መሰረዝን አስመልክቶ በሰኔ 15 ቀን 2005 ዓ.ም እትማችን፣ ለመጀመርያ ጊዜ ድምፃቸውን በሸክላ ያስቀረፁትን ኢትዮጵያዊ የጥበብ ባለሙያ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የልጅ ልጅ የሆኑትን አቶ ታደለ ይድነቃቸውን በማነጋገር ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ሸክላዎቹን እንደገና በማሳተም ለምረቃ አዘጋጅተው የነበሩትንና የኢትዮጵያን የጥንት ሙዚቃዎች በዘመናዊ ዘዴ በማስቀረጽ የሚታወቁትን ፈረንሳዊ የሙዚቃ ሰው ሚስተር ፍራንሲስ ፋልሴቶ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ በአገር ውስጥ ባለመኖራቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ሚ/ር ፍራንሲስ ፉልሴቶ ዘገባውን ከተመለከቱ በኋላ ምላሻቸውን በጽሑፍ ልከውልናል፡፡ በሰኔ 5 ቀን 2005 ዓ.ም የጋዜጣችሁ ዕትም የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የልጅ ልጅ በሆነ ሰው የቀረበውን መሰረተ ቢስ ቅሬታ ተመልክቼዋለሁ፡፡ ዘገባውን ባዘጋጃችሁበት ወቅት በሲዲው ላይ ባለው የኢሜይል አድራሻ እኔን አግኝታችሁ ማነጋገር ነበረባችሁ፡፡ ወደ ጉዳዩ ስገባ፣ በአቶ ታደለ የቀረበው ቅሬታ መሰረተቢስ ነው ያልኩበት ምክንያት የተሰማ እሸቴ ሸክላዎች የህዝብ ሀብት ናቸው፡፡ ይህ ለክርክሩ ማብቂያ በቂ ነው፡፡ እኔም ሆንኩ አታሚው ኩባንያ በዚህ ሥራ ላይ ያቀረብነው ምንም አይነት የባለቤትነት መብት የለም፡፡ ይህንንም ደግሜ ሳረጋግጥ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ይህንን ቃል የተከበሩት የጋዜጣ አንባቢያን እንዲያውቁት እፈልጋለሁ፡፡
እንግዳው ነገር አቶ ታደለ የአያታቸውን ሸክላ በድጋሚ ለማሣተምና ለማስመረቅ ሣስብ፣ ከጐኔ በመሆን በቋሚነት ሲያማክሩኝና በቅርበት ሲተባበሩኝ መቆየታቸው ነው፡፡ ራሳቸው የአያታቸውን ታሪክ በመፃፍና ሰፊውን ክፍል የያዘውን ታሪካዊ ፎቶግራፎችና መረጃዎች በመስጠት ሲተባበሩኝ ነበር፡፡ ወደ ማተሚያ ቤት ከመሄዱ በፊትም የመጨረሻውን ፅሁፍ አይተውታል፡፡
ይህንን ስራ ለመጨረስ አራት አመታትን ፈጅቶብኛል፡፡ ማንም ሰው እነዚህን ፅሁፎች በጥንቃቄ ሊያስረክበኝ የሞከረ የለም፡፡ ማንም ሰው እንዲህ ያሉ ታሪካዊ ሥራዎችን በአንድ ምሽት አያገኛቸውም፡፡ ቡክሌቱ 32 ገፆች ያሉት ሲሆን ሁለተኛው ሲዲ ደግሞ 80 ገፆችን የያዘ ነው፡፡ የአቶ ታደለን አላስፈላጊና ከሥራው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ለማክበርና ለማሟላት ጥረት አድርጌአለሁ፡፡
ሌላው ላሰምርበት የምፈልገው ጉዳይ፣ የተሰማ እሸቴን ሥራዎች በድጋሚ የማሳተሙን ሥራዬን የአ.አ.ዩ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲቲዩት፣ የፈረንሳይ የጥናት ማዕከል፣ ገተ ኢንስቲቲዩትና ዩኔስኮ ድጋፍ አድርገውለታል፡፡ እነዚህ ተቋማት ደግሞ ዕውቅና ከሌላቸዉ ሰዎች ጋር አይተባበሩም፡፡
በሚያሳዝን ሁኔታ በርካታ ቅሬታዎችን በማንሳታቸው፣ በእኔ ሙሉ ስምምነት እ.ኤ.አ በመስከረም 2010 ተይዞ የነበረው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሸክላዎች ምረቃ እንዲሰርዝ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን የምረቃ ዝግጅት እንዳያይ በመነፈጉ ሁላችንም አዝነናል፡፡ ይህም በአቶ ታደለ የተፈፀመና በተሳሳተ መንገድ የተገኘ መራራ ድል ሲሆን ምንም ስሜት የማይሰጥ ነገር ነው፡፡
በድጋሚ ለማስታወስ የምወደው፣ እኔ የኢትዮጵያን ሸክላዎች የሰራሁት ማንም ኢትዮጵያዊም ሆነ ፈረንጅ ሲሠራው ባለማየቴ ነው፡፡ በሌላ ሰው የተሰሩ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን እንደማንኛውም ሰው ገዝቼ ብጠቀም ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በዚህ ሥራ በርካታ ችግሮችንና ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎችን አሣልፌአለሁ፡፡
በዚህ ጉዳይ ደስተኛ ያልነበረው ከተሰማ እሸቴ የልጅ ልጆች አንዱ፣ የአያቱን ዘፈኖች ራሱ ለማሳተም ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ እኔ ወጥቼ ጥረቱ እንዲሳካ ማድረጌ ስህተቱ ምን ላይ ነው? ስራው ከተሰራ በኋላ ያለምክንያት በእኔ ላይ ጥላቻ አሳደረ፡፡ ስራዎቹ በአግባቡ በመሠራታቸው ሊደሰት ሲገባው ቅሬታ ማቅረቡ መሰረተ ቢስ ነው፡፡ እንደገለፅኩት የተሰማ እሸቴ ሥራዎች ለሙዚቃ አፍቃሪዎችና ለሙዚቃ ሥራ ተመራማሪዎች የምዕተ ዓመቱ ቅርሶች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቃ አፍቃሪያን የኢትዮጲክስ ሲዲዎችን በቀላሉ ማግኘት እንደማይችሉ ተረድቻለሁ፡፡ ሙዚቃዎቹን አምጥታው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያከፋፍሉት ሰዎች ከአመት በፊት ማከፋፈል ማቆማቸውን አውቃለሁ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ጥራት የሌላቸው ቅጂዎች በአነስተኛ ዋጋ ለገበያ የሚያቀርቡ ሰዎች በመበራከታቸውና አስመጪዎች ከእነዚህ ሰዎች ጋር መወዳደር ባለመቻላቸው ነው፡፡ ለዚህም ነው ከፈረንሳይ አሳታሚ ኩባንያ ጋር “Ethiopiques for Ethiopia” ለተሰኘ ፕሮጀክት እገዛ በማድረግ ላይ ያለነው፡፡ ይህም በቅርቡ እንደሚጀመር ተስፋ አለኝ፡፡ ኢትዮጵክስ ሲዲዎች በኢትዮጵያ ውስጥ መመረትና በኢትዮጵያ የዋጋ ተመን መሸጥ ይኖርባቸዋል - ሚ/ር ፍራንሲስ ፋልሴቶ፡፡

 

Read 20284 times