Saturday, 10 August 2013 10:28

ለ120 ት/ቤቶች የወጣው የ200 ሚ ብር ጨረታ እያወዛገበ ነው

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

የፕላዝማ የትምህርት ስርጭት ችግሮችን ለማስተካከል የ120 ት/ቤቶች ፕሮጀክት በጨረታ ለዜድቲኢ የተሰጠው ከአመት በፊት ሲሆን፣ በአንድ ት/ቤት በተከናወነ ሙከራ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ፕሮጀክቱ ተቋረጠ፡፡ በአዲስ ከተማ ት/ቤት የተካሄደው ሙከራ እንዳልተሳካና በእቃዎች ላይ የጥራት ጉድለት እንደሚታይ የገለፁት የትምህርትና ቴክኖሎጂ ማዕከል፣ ዶ/ር ገበየሁ ወርቅነህ፤ የጊዜ ገደቡም ስላለፈ ጨረታውን እንደገና ማውጣት የግድ ነው ብለዋል፡፡ ዜድቲኢ በበኩሉ የጨረታው ህጋዊ አሸናፊ መሆኑን በመጥቀስ፤ በሙከራ ስራውና በእቃዎች ላይ ችግር እንደሌለና ሙሉ ፕሮጀክቱን ለማከናወን እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጿል፡፡

መንግስት ለጨረታ የሚያቀርባቸው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ፕሮጀክቶች ላይ የውጭ ኩባንያዎች ከፍተኛ ተቀናቃኝነት የሚታይባቸው ሲሆን፣ ለመላ አገሪቱ ተመሳሳይ የትምህርት ጥራት ለማዳረስ ያስችላል ተብሎ በከፍተኛ ወጪ የተጀመረው “የፕላዝማ የትምህርት ስርጭት” ፣ በአዲስ አበባ ከሚገኝ ማዕከል በሳተላይት አማካኝነት የተሚላለፍ በመሆኑ ለአስተማሪዎችና ለተማሪዎች አመቺ አልሆነም፡፡ ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ስለሆነ፣ በመሃል አስቁሞ አስተማሪው ማብራሪያ የመስጠት እድል የለውም በማለት ጉድለቱን የገለፁት ዶ/ር ገበየሁ፤ተማሪዎች ባይገባቸው ወደኋላ መልሶ መድገም አይቻልም ይላሉ፡፡

የስርጭት ብልሽትና የመብራት መቆራረጥ ካጋጠመም፣ ተማሪዎች ትምህርቱን ሳይከታተሉ ያልፋቸዋል፡፡ በፕላዝማ ቴሌቪዥን የሚቀርበው የቪዲዮ ትምህርት ተማሪዎችና አስተማሪዎች እንዳመቻቸው እንዲቆጣጠሩት ለማድረግም ነው አዲስ የማስተካከያ ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ ለጨረታ የቀረበው፡፡ በመጀመሪያው ዙር ለ120 ት/ቤቶች አምና በጥር ወር የወጣውን ጨረታ ያሸነፈው ዜድቲኢ የተሰኘው የቻይና ኩባንያ ሲሆን፣ በአዲስ ከተማ ት/ቤት የሙከራ ውጤት ለማሳየትና በ10 ወራት ውስጥ ሙሉ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ታስቦ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በሙከራው ውጤት ውዝግብ ስለተፈጠረ ፕሮጀክቱ በዚሁ ተቋርጦ ቆሟል፡፡ በቪዲዮ ተቀርፆ ከአንድ ማዕከል በሳተላይት አማካኝነት የሚሰራጨውን ትምህርት የሚቀበል የቪሳት ዲሽ በየትምህርት ቤቱ የተተከለው በቴሌ አማካኝነት እንደሆነ የገለፁት የትምህርትና የቴክኖሎጂ ማዕከል ሃላፊ ዶ/ር ገበየሁ ወርቅነህ በእያንዳንዱ ክፍል ከፕላዝማ ቴሌቪዥን ጋር የሚያገናኝ ኔትዎርክ የተዘረጋው በኛ በኩል ነው ይላሉ፡፡ የፕላዝማ ቴሌቪዥን ስርጭት ለመላ አገሪቱ ተመሳሳይ የትምህርት ጥራት ለማዳረስ የሚረዳ ቢሆንም በቂ እንዳልሆነና ጉድለቶች እንዳሉት እንገነዘባለን ያሉት ዶ/ር ገበየሁ፣ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል የተለያዩ ጥረቶችን አድርገናል ብለዋል፡፡

በአስር የትምህርት አይነቶች በፕላዝማ ቴሌቪዥን የሚቀርበውን ትምህርት በሲዲ አዘጋጅተን ለሁሉም ክልሎች ሰጥተናል የሚሉት ዶ/ር ገበየሁ፣ አስተማሪዎች የሲዲ ማጫወቻ ወይም ላፕቶፕ በመጠቀም ከፕላዝማ ቴሌቪዥን ጋር በማገናኘት ለተማሪዎቻቸው ማሳየት ይችላሉ ብለዋል፡፡ ሁነኛው መፍትሔ ግን ለትምህርት ስርጭት የተዘጋጁ ቪዲዮዎችን በሙሉ መያዝና ማከፋፈል የሚችል የኮምፒዩተር ማዕከል በየትምህርት ቤቱ ማቋቋም ነው የሚሉት ዶ/ር ገበየሁ፤ ይህንንም በኔትዎርክ ከእያንዳንዱ ክፍል ጋር ከፕላዝማ ቲቪ ጋር በማገናኘት አስተማሪዎች እንደ አስፈላጊነቱ እየተቆጣጠሩ ለተማሪዎቻቸው ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ይህንን የኮምፒዩተር ማዕከልና ኔትዎርክ በየት/ቤቱ ለመዘርጋት በመጀመሪያ ዙር ለ120 ት/ቤቶች የወጣው ጨረታ ዜድቲኢ አሸንፎ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት እንደነበር ሃላፊው አስታውሰው፤ በአስር ወራት ይጠናቀቃል የተባለው ፕሮጀክት ሳይካሄድ እንደተስተጓጐለ ይገልፃሉ፡፡

በጨረታው ሁለት ደረጃዎች ተጠቅሰዋል የሚሉት ዶ/ር ገበየሁ፤ አንደኛው ነጥብ ለፕሮጀክቱ ትክክለኛውን ጥራት ያሟሉ እቃዎች መቅረባቸውን ማረጋገጥ ነው፤ ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ በአንድ ት/ቤት የሙከራ ስራ ተከናውኖ ውጤቱ እንዲታይ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ ለሙከራ በተመረጠው አዲስ ከተማ ት/ቤትም ዜድቲኢ የኮምፒዩተር ማዕከል በማቋቋም ከመማሪያ ክፍሎች ጋር የሚያገናኝ ኔትዎርክ ዘርግቷል፡፡ የሙከራው ውጤት በባለሙያዎቻችን ታይቷል የሚሉት ዶ/ር ገበየሁ፤ በጨረታ ሰነዱ ላይ የተጠቀሱ መመዘኛዎች አያሟላም ብለዋል፡፡ የኮምፒዩተር ማዕከሉና ኔትዎርኩ ሁሉንም የመሣሪያ ክፍሎችን አያዳርስም፤ የእቃዎች ጥራት ችግርም አለበት ይላሉ ዶ/ር ገበየሁ፤ በኛ በኩል ሙከራው እንዳልተሳካና የእቃዎች ጥረት ጉድለት መኖሩን ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት አቅርበናል፤ ደንቡንና ስርዓቱን ተከትሎ ማድረግ የሚገባቸውን ያደርጋሉ ያሉት ዶ/ር ገበየሁ፤ በፕሮጀክቱ የተያዘው ጊዜ በማለፉና በጀቱ ስለተመለሰ እንደገና ጨረታ ማውጣት የግድ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ዜድቲኢ 120 ት/ቤቶች በርካታ እቃዎችን ከውጭ አስመጥቶ ማስገባቱንና ከጉምሩክ ለመቀበል ፈቃድ ለማግኘት መቸገሩን ምንጮች ቢገልፁም፤ ዶ/ር ገበየሁ ይሄንን እኛ አናውቅም ብለዋል፡፡ ዜድቲኢ በበኩሉ፣ የጨረታው ህጋዊ አሸናፊ መሆኑንና ካሁን በፊት በርካታ ፕሮጀክቶችን በጥራት እንደሰራ ገልፆ፣ አሁንም በጥራት ሙከራውን እንዳከናወነ ይናገራል፡፡ ስለ ፕሮጀክቱ ለሚነሱ ዝርዝር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚችለው የፕሮጀክቱ ባለቤት ነው የሚለው ዜድቲኢ፣ ሙሉ ፕሮጀክቱን ለማከናወን ዝግጁ ሆኖ እየተጠባበቀ መሆኑን ይገልፃል፡፡

Read 22120 times