Saturday, 10 August 2013 10:38

ወደ አረብ አገራት የሚጓዙ ሴቶች ሌላው ፈተና!

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(18 votes)

ፍቅረኛ በምትልከው ገንዘብ ሌላ ትዳር መመስረት ተለምዷል
ፍቅረኞቻቸው በሚፈፅሙባቸው ክህደት ለሞትና ለእብደት የተዳረጉ ሴቶች አሉ

ትዕግስት ገብሬ የሰላሳ አመት ወጣት ሳለች ነበር ወደ ቤሩት ያቀናችው- በ1997 ዓ.ም፡፡ ግድ ሆኖባት ነው እንጂ ለአምስት ዓመት አብራው የዘለቀችውን የትምህርት ቤት ፍቅረኛዋን ሚካኤል ሃይሉን ትታ መሄድ አልፈለገችም ነበር፡፡ “በምድር ላይ እንደሱ የማፈቅረውና የማምነው ሰው አልነበረም” ትላለች፡፡ ለነገሩ ወደ ቤሩት የሄደችውም ትንሽ ሰርታ ጥሪት በመቋጠር ከሚካኤል ጋር ትዳር ለመመስረት ነበር፡፡ በቤሩት በቆየችባቸው ሁለት ዓመታት ቢያንስ በሳምንት ሁለት ጊዜ፣ ሚካኤል ጋር በመደወል ናፍቆቷን ትወጣለች፤ ወደፊት ስለሚመሰርቱት ትዳርም በሰፊው ያወራሉ፡፡
ትዕግስት በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ እየሰራች የምታገኘውን ደሞዝ፣ አብዛኛውን ለሚካኤል እየላከች፣ ጥቂቱን ለቤተሰብዋ ትልክ ነበር፡፡ የሁለት አመት የስራ ኮንትራትዋ ሲያልቅ ፍቅረኛዋ ጋ ደውላ “ልመጣ ነው” አለችው፡፡ ሚካኤል ደነገጠ፡፡ በዚህ ፍጥነት ትመጣለች ብሎ አላሰበም፡፡ እናም ማግባባት ያዘ - እዚያው እንድትቆይለት፡፡ “አንዴ በደንብ ስሪ እና ደህና ገንዘብ አጠራቅመን እንጋባለን” አላት፡፡ የሱ ነገር ሆነባትና ሃሳቡን ተቀብላ ፣ ኮንትራትዋን ለሁለት ዓመት አደሰች፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን የፍቅረኛዋ ባህርይ እየተለወጠባት መምጣቱን ትዕግስት ታስታውሳለች፡፡ እንደ በፊቱ ስትደውል አታገኘውም፡፡

አንዳንዴ ስልኩ ዝግ ይሆናል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ አይነሳም፡፡ ያነሳላት ጊዜ “ምን ሆነህ ነው?” ስትል መጠየቋ አልቀረም፡፡ ሰበብ አያጣም፡፡ ወይ “ተኝቼ ነበር” አለያም “አልሰማሁትም” ይላታል፡፡
ትዕግስት ጆሮ አልሰጠቻቸውም እንጂ ቤተሰቧ ፍቅረኛዋን በተመለከተ አንዳንድ ጥርጣሬያቸውን ነግረዋታል፡፡ ግን እንዴት ብላ የአምስት ዓመት የፍቅር አጋሯን ትጠርጥረው! ትዕግስት በአጠቃላይ ለአራት አመት ያህል ከሰራች በኋላ “አሁንስ በቃኝ” ብላ ወደ አገሯ ለመምጣት ቆረጠች፡፡ ፍቅረኛዋ ግን አሁንም መመለሷን አልፈለገውም፡፡ እዚያው ትንሽ እንድትቆይ ሃሳብ አቀረበ፡፡ እሷ ግን አገሯ መጥታ ከምትወደው ፍቅረኛዋ ጋር በትዳር ለመተሳሰር ቸኩላለች፡፡ እናም ዝም ብላ ወደ ሀገሯ ተመለሰች፡፡ትዕግስት አገሯ እንደመጣች ፍቅረኛዋን አላገኘችውም፡፡ “ለንግስ ወደ አንድ ገዳም ሄጃለሁ” የሚል መልዕክት ትቶላት ነበር፡፡ የናፈቃትን የወደፊት ባሏን ያገኘችው ከሳምንት በኋላ ነበር፡፡ በተገናኙ ሰዓትም ተቃቅፈው መላቀሳቸውን ታስታውሳለች - በናፍቆት፡፡
ሚካኤል ትእግስትን ካገኛት ቀን ጀምሮ “ኢንተርኔት ቤት ከፍተን እንስራ” እያለ ይወተውታት እንደነበር ትናገራለች፡፡ ይሄኔ ነው ስትልክ የነበረውን ገንዘብ የት እንዳደረገው የጠየቀችው፡፡ “ላስደስትሽ ብዬ ቤት መስራት ጀምሬአለሁ” ሲል መለሰላት፡፡ በደስታ ጮቤ ረገጠች፡፡ ወዲያው የጠየቃትን ኢንተርኔት ቤት ለመክፈት አስር ሺህ ብር ሰጠችው - ቤት እንዲከራይ፡፡ ገንዘቡን እጁ እንዳስገባ ተጣድፎ መውጣቱን የምትናገረው ትዕግስት፤ ከጥድፊያው የተነሳ ሞባይሉን እንኳን ይዞ አልሄደም ትላለች፡፡

ይሄ ሞባይልም ነው ጉዱን ያወጣበት ፡፡ ትዕግስት ሞባይሉ ስክሪን ላይ አንድ ፎቶ አየች፡፡ ህፃን ልጅ ያቀፈች ሴት ናት፡፡ ታውቃታለች፡፡ የገዛ ጓደኛዋ ቤቴል፡፡ እንዴት ፍቅረኛዋ ሞባይል ላይ የጓደኛዋ ፎቶ እንደተገኘ የሚነግራት ሰው ግን አላገኘችም፡፡ ቤሩት እያለች ስለ ቤቴል ስትጠይቀው “አንገናኝም፤ አግብታ ሌላ ቦታ ነው የምትኖረው” የሚል ምላሽ እንደሰጣት ታስታውሳለች፡፡ ቤቴልም ራሷ የትዕግስትን ስልክ ማንሳት ካቆመች ሶስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በጥያቄና ግራ በመጋባት ብዙ ዋለለች፡፡ በዚህ መሃል የሚካኤል ስልክ ጠራ፡፡ “my love” ይላል - ጥሪው፡፡ በደመነፍስ ስልኩን አነሳችው፡፡
“ሄሎ”
“ሄሎ ማን ልበል?” ደዋይዋ ናት
“ሞባይሉን ቻርጅ እያደረገው ነበር… ማን ልበል?” ትዕግስት የቤቴል ድምፅ መሆኑ አልጠፋትም፡፡
“ባለቤቱ ነኝ፤ ገዳም በሰላም መድረሱን ለማወቅ ነው” የደዋይዋ ምላሽ ነበር፡፡
“እኔም ባለቤቱ ነኝ አንቺ ማነሽ?” አለች ትዕግስት ለቅሶ በተቀላቀለበት ድምፅ፡፡
ከዛ በኋላ ያደረገችውን አታውቀውም፡፡ ግን ታማ ለአስር ቀን ፀበል ተመላልሳለች፡፡ ለካ ፍቅረኛዋ ከገዛ ጓደኛዋ ወልዷል፡፡ ትዕግስት በምትልከው ገንዘብም ትዳር መስርቶ አዲስ ህይወት ጀምሯል፡፡ ቤት እየሰራሁ ነው ያላትም ውሸቱን እንደሆነ ገባት፡፡ ትዕግስት ከሁለት ያጣ ሆነች፡፡ ገንዘቧንም ፍቅሯንም ተነጠቀች፡፡ ጊዜዋ በከንቱ መባከኑ አበገናት፡፡ ከዚህ በኋላ እንደ አዲስ ፍቅረኛ ይዛ፣ ወደ ትዳር ለመግባት የእድሜዋ ጉዳይ አሳስቧታል፡፡ መውለድ ባልችልስ? እድሜዬ ቢያልፍስ? … ትብሰለሰላለች - በቁጭት፡፡
ሚካኤል ያንን ሁሉ በደል ፈፅሞባት አሁንም መደወሉን አላቆመም፡፡ “ከፈለግሽ ከእኔ መውለድ ትችያለሽ፤ ቤሩት ሄደሽ ሰርተሽ ነይ እንጂ እሷን ፈትቼ አገባሻለሁ” እያለ ይጨቀጭቀኛል ትላለች - በሃዘን ተውጣ፡፡
ደብረዘይት ተወልዳ ያደገችው ሰናይት ሃይሉ፤ ከፍቅረኛዋ ከወርቁ ጋር በ1999 ዓ.ም መጨረሻ ላይ እንደተጋቡ ትናገራለች፡፡ በቂ መተዳደርያ ገቢ ግን አልነበራቸውም፡፡ ለዚህም ነው ባለቤቷ፣ ቤሩት ሄዳ በመስራት ትንሽ ገንዘብ ይዛ እንድትመጣ ሃሳብ ያቀረበው፡፡ ቤተሰቦቿ ሃሳቡን ባይደግፉትም ሠናይት ግን በባሏ ምክር ተሸንፋ ወደ ቤሩት ተጓዘች፡፡
ቤሩት ከገባች ጀምሮ በየሳምንቱ እየደወለች ባለቤቷን ታገኘው ነበር፡፡ ሙሉ ደሞዟን የምትልከውም ለእሱ ነበር፡፡ አንድ ዓመት ከሶስት ወር ከሰራች በኋላ ግን ያልታሰበ ነገር ተፈጠረ፡፡ አሰሪዎቿ ለእረፍት ወደ ሌላ አገር ሲሄዱ አብራ መሄድ አልፈለገችም፡፡ ስለዚህ እሷም ድምጿን አጥፍታ ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ መጣች፡፡ ቤቷ ግን ኦና ነበር፡፡

ወርቁ የለም፡፡ ቤተሰቧን ጠየቀች፡፡ የሄደበትን አውቃለሁ የሚል ጠፋ፡፡ እሷ ግን ፍለጋዋን አላቆመችም፡፡ የማታ ማታ ወርቁ በጓደኞቹ በኩል ደብዳቤ ላከላት፡፡“አትረብሺኝ፤ እኔ አግብቻለሁ፤ የራስሽን ኑሮ መምራት ትችያለሽ፤” ይላል የደብዳቤው መልዕክት፡፡ ሠናይት የምትሆነውን አጣች፡፡ ድንጋጤ፣ ዱብዕዳ፣ ሀዘን፣ ፀፀት፣ እልህ… በየተራ ተፈራረቁባት፡፡ በመጨረሻ ወርቁ የሚኖርበትን አካባቢ አጠያይቃ በመሄድ በጩቤ እጁ ላይ ወጋችው፡፡ ጉዳቱ ብዙ ባይሆንም መደንገጡና መፍራቱ አልቀረም፡፡ የመኖሪያ አካባቢውን ቀየረ፡፡ የዕረፍት ጊዜዋ ቢያልቅም ወደ ቤሩት መመለስ አልፈለገችም፡፡ ከሁሉም በላይ ሰው ቤት ሰርታ ያመጣችውን ገንዘቧን መብላቱ እንደሚያንገበግባት ትናገራለች፡፡ በቤተሰብና በጓደኞቿ ምክርና ግፊት ወደ ቤሩት ተመልሳ የሄደችው ከአንድ አመት በኋላ ነበር፡፡

አሁን ከቤሩት መጥታ የስጦታ እቃዎች መሸጫ ሱቅ ከፍታ እየሰራች ነው፡፡ ሰናይት፤ ቤሩት የምታውቃት አበራሽ የተባለች ወጣት የገጠማትን ተመሳሳይ አሳዛኝ ታሪክ አውግታናለች፡፡ አበራሽ እዚህ ሳለች ከፍቅረኛዋና ከአንድ ልጃቸው ጋር ነበር የሚኖሩት፡፡ ዘውዲቱ የተባለችውን የአገርዋን ልጅም አስጠግታት አብራት ትኖር ነበር፡፡ ለሰናይት እንደነገረቻት፤ ወደቤሩት ስትሄድ የልጅዋን ነገር አደራ የሰጠችው ለዚህችው አብሮ አደጓ ነበር፡፡
አበራሽ ስለ ፍቅረኛዋ አውርታ አትጠግብም የምትለው ሰናይት፤ እየሰራች ደሞዟን ለፍቅረኛዋ ትልክ እንደነበር ታውቃለች፡፡ ቤሩት በመጣች በስምንተኛ ወሯ ግን ዘውዲቱ ከፍቅረኛዋ ማርገዟን ሰማች፡፡ ፍቅረኛዋ የጋራ ልጃቸውን ለእናቷ ሰጥቶ ከአገርዋ ልጅ ጋር ትዳር መስርቷል፡፡ አበራች የሰማችውን መርዶ መቋቋም አልቻለችም፡፡ ህሊናዋን ሳተች፤ ጨርቋን ጥላ አበደች፡፡ በቤሩት ጐዳናዎች ራቁቷን መታየት ጀመረች፡፡ ሀገሯ እንድትመለስ ኤምባሲውን ማነጋገራቸውን የጠቀሰችው ሰናይት፤ ከኤምባሲው መፍትሄ አለመገኘቱንና ኋላም ሆስፒታል ገብታለች መባሉን እንደሰማች፣ ከዛ በኋላ ግን ያለችበትን እንደማታውቅ ትናገራለች፡፡
የሳዕዳ ታላቅ እህት ሃቢባ ጀማል፤ ወደ ሳውዲ አረቢያ የሄደችው ባለፈው አመት ነበር፡፡ ከመሄዷ በፊት ግን እቤታቸው ተከራይቶ ከሚኖረው ፍቅረኛው ጋር ኒካ (ቀለበት) ማሰሯን እህቷ ሰዓዳ ትናገራለች፡፡ ፍቅረኛዋን እንደነፍሷ ትወደው ነበር የምትለው ታናሽ እህቷ፤ አንድ አመት ሙሉ የሰራችበትን ገንዘብ ለእሱ እንደላከችለት ትገልፃለች፡፡
የሃቢባ ፍቅረኛ እነሱ ጋ ቤት ተከራይቶ ቢኖርም ከቤተሰቡ ጋር ብዙም እንደማይቀራረብ የምትናገረው ሳዕዳ፤ ከክፍለአገር የመጣች የአክስታቸው ልጅ ከእሱ ጋር በጣም ተቀራርበው እንደነበርና ይህንንም ቤተሰቡ ለሃቢባ መግለፁን ታወሳለች፡፡ በሰማችው የደነገጠችው ሃቢባ፤ ወዲያው ፍቅረኛዋ ጋ ትደውልና “እሷን ልጅ ብዙ አትቅረባት፤ ክፍለሃገርም ስሟ ጥሩ አይደለም” በማለት ቤተሰቡ ከጠረጠራት ዘመዷ ልታርቀው ሞከረች፡፡ ግን አልተሳካላትም፡፡ “ከዚህ በኋላ የሚያገባሽ ነገር የለም፤ አንቺን እንደውም አልፈልግሽም፤ ማግባት የምፈልገው እሷን ነው” ሲላት ከምትሰራበት ቤት አራተኛ ፎቅ ላይ ስልኩን ጆሮዋ ላይ እንደያዘች ወድቃ፣ ህይወቷ ማለፉን እህቷ በእንባ እየታጠበች ነግራናለች፡፡
እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ የሴት እህቶቻችን ታሪኮች ጥቂት አይደሉም፡፡ የሚያሳዝነው ወደ አረብ አገራት የሚጓዙ ሴቶች እዚያ በሚያዩት በደልና ስቃይ ሳያንሳቸው እዚህም ሌላ ፈተና መጋፈጣቸው ነው፡፡ የሴት እህቶቻችን መከራ የሚቆምበት ጊዜ ይናፍቃል፡፡

Read 5637 times