Saturday, 10 August 2013 10:45

የፀረሙስና ኮሚሽን ምርመራውን በማጠናቀቁ ክስ እንዲመሰርት ታዘዘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

የአቃቢያን ህግ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ እሸቱ ወ/ሠማያትን ጨምሮ 10 ተጠርጣሪዎች በዋስ ተለቀዋል፡፡
የተጠርጣሪ ባለሃብት ኩባንያዎች አስተዳደር እስከ መስከረም ባለበት እንዲቀጥል ብይን ተሰጠ፡፡

የፌደራሉ የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርመሪ ቡድን ከኦዲት ስራ በስተቀር የ6 መዝገቦች ምርመራ አጠናቆ በማስረከቡ አቃቤ ህግ ክስ የመመስረቻ የ15 ቀን ጊዜ ተጠርጣሪዎቹ መካከል በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአቃቢያን ህግ ዳይሬክተር የነበሩትን አቶ እሸቱ ወ/ሰማያትን ጨምሮ አስር ተጠርጣሪዎች በዋስ ተለቀዋል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት በትናንት ከሰአት በኋላ ውሎው የገቢዎችና ጉምሩክ ዳሬክተር አቶ መላኩ ፈንታን እና ምክትላቸው አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስን ጨምሮ፣ በስድስት መዝገቦች የ47 ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ተመልክቷል፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ፍ/ቤቱ በሰጠው ጊዜ ውስጥ ከኦዲት ምርመራው በቀር ሁሉንም የምርመራ ስራዎች ማጠናቀቁን በመግለጽ፣ ተጠርጣሪዎች ከእንግዲህ ጉዳያቸውን ማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡ ከኦዲት ምርመራው ጋር በተያያዘ፣ የኢንተር ኮንቲኔታል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ፣ የኬኬ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ፣ የነፃ እና ባሰፋ ትሬዲንግ ኩባንያ ባለቤት አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር እንዲሁም ባለሃብቱ አቶ ምህረተ አብ አብርሃ እዚያው ባሉበት የፖሊስ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ መርማሪ ቡድኑ ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል አቶ እሸቱ ወ/ሰማያት እና ትዕግስት አለማየሁ፣ በእነ አቶ ገ/ዋህድ መዝገብ ተካተው የነበሩት አቶ ተወልደ ብስራት፣ አቶ ሙሉቀን ተስፋዬ፣ አቶ ዳኜ ስንሻው እና ወ/ሮ ፍሬ ህይወት ጌታቸው፣ አቶ ባህሩ አብርሃ እንዲሁም አቶ ስዩም ለይኩን፣ አቶ ሃይለማርያም አሰፋ እና ወ/ሮ አልማዝ ከበደ በዋስ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
ከኦዲት ስራ በስተቀር ምርመራው ተጠናቅቆ ከመርማሪ ቡድኑ መዝገቦቹን እንደተረከበ ያረጋገጠው የኮሚሽኑ አቃቢ ህግ፣ ተጠርጣሪዎቹ ባሉበት ሆነው ክስ የመመስረቻ የ15 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ በተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት ላይ አስተያየቱን እንዲያቀርብ የተጠየቀው አቃቢ ህግ፣ የተፈፀመው ወንጀል ከባድ የሙስና ወንጀል በመሆኑና ክስ ሲመሰረት የሚጠቀሰው አንቀጽም ከ10 አመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ስለሆነ የዋስትና መብት የሚያስከለክል ነው ብሏል፡፡
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው የተለያዩ የህግ መከራከሪያ አቅርበው የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት ተጠብቆ ጉዳያቸውን በውጭ እንዲከታተሉ ይደረግ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር ሲያደምጥ የቆየው ፍ/ቤቱም በእያንዳንዱ መዝገብ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን በእነ አቶ መላኩ ፋንታ እና አቶ ገ/ዋህድ እንዲሁም የእነ ተመስገን ስዩም እና መልካሙ እንድሪያስን መዝገብ ክሱ በ13 ቀን ውስጥ እንዲቀርብ አዟል፡፡
የእነ መሐመድ ኢሣ እና ጥጋቡ ዓይዳ መዝገቦች ላይ ደግሞ ለነሐሴ 15/2005 ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ለነሐሴ 16 ከሰአት በኋላ ቀጥሯል፡፡ በተጨማሪም ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ የተጠየቁት እንዲወርዱ እንዲሁም በማረፊያ ቤት እንዲያዩ ተጠየቁት በዚያው እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል የከባድ ሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ ባለሃብቶቹ ጠበቆች እና የፌደራሉ የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በኩባንያዎች አስተዳደር ጉዳይ ላይ ፍ/ቤቱ ባዘዘው መሠረት ተስማምተው፣ አስተዳዳሪ ባለማቅረባቸው ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 30 ቀን 2005 በዋለው ችሎት በድጋሚ ተስማምተው እስኪቀርቡ ድረስ የኩባንያዎቹ አስተዳደር አሁን ባለበት እስከ መስከረም 22ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ እንዲቀጥል ብይን ሰጠ፡፡
የተጠርጣሪ ባለሃብቶቹ ተወካዮችና ጠበቆች ለንብረቶቹ ገለልተኛ አስተዳዳሪ ሳይመደብ መቆየቱ ንብረቶች ያለ ባለቤት እንዲባክኑ ያደርጋል ብለው የተከራከሩ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ሁለቱ ወገኖች ከመስከረም 22 ቀን 2006 በፊት ተስማምተው በማመልከቻ የሚያቀርቡ ከሆነ በፍ/ቤቱ አሠራር መሠረት የተሰጠው ብይን ተሽሮ የሚታይበት ሁኔታ እንደሚኖር አስገንዝቧል፡፡
የፍርድ ቤት ሂደት እልባት እስኪያገኝ ንብረታቸው በገለልተኛ አስተዳደር እንዲተዳደር ጥያቄ ቀርቦባቸው የነበሩት አምስት ኩባንያዎች፣ ንብረትነታቸው የአቶ ስማቸው ከበደ የሆኑት ኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል እና ዲኤች ሰሜክስ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፣ የአቶ ከተማ ከበደ ንብረት የሆነው ኬኬ ኃ.የተ.የግ.ማህበር፣ ንብረትነታቸው የአቶ ነጋ ገ/እግዚአብሔር የሆኑት ነፃ ኃላ.የተ.የግ.ማህበር እና ባሰፋ ትሬዲንግ ናቸው፡፡

Read 2235 times