Saturday, 17 August 2013 11:30

“እውነተኛ ሽብርተኝነትን አጥብቀን እንቃወማለን”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)
  • የፀረ ሽብር ህግ ጭራሽ አይኑር የሚል አቋም የለንም 
  • በፀረ ሽብር ሕግ ሰበብ ዜጐች እንዳይደራጁ እየተደረገ ነው
  • መተካካት የኢህአዴግ አጀንዳ ነው፤ እኛ የወጣቶች ማህበር አይደለንም

አንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ የሦስት ወር መርሃ ግብር ቀርፆ፣ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎችን እያደረገ ነው፡፡ “የሚሊዮኖች ድምፅ” በሚልም የፀረ ሽብር ህጉን ለማሰረዝ ፊርማ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ፤ አክራሪነትና ሽብርተኝነት በሚሉት ጉዳዮች የአንድነት አቋም ምንድነው? የፀረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ ለምን ተፈለገ? በእነዚህና ተያያዥ በሚሉና ተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች ዙርያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከፓርቲው ሊ/መንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡

 በአሁኑ ሰዓት አንድነትን ጨምሮ የተቃዋሚዎች ተከታታይ ሰልፍ መጥራት የ8 አመቱን እገዳ ማካካስ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

እርግጥ ከ97 በኋላ ትላልቅ ሰላማዊ ሰልፎች አልተካሄዱም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ከ97 በፊት የነበሩትን ሰላማዊ ሰልፎች ያደራጅ የነበረው ፓርቲ (ቅንጅት) መከፋፈል ነው፡፡ ያ ክፍፍል ከተፈፀመ በኋላ ቅንጅትን እንደገና ማደራጀት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ሁሉም በራሱ አካሄድ እንደገና መደራጀት ውስጥ ገባ፡፡ ሰፊውን ጊዜ የወሰደው በቅንጅት የነበረውን መንፈስ ይዞ መቀጠል የሚያስችል አደረጃጀትን የመፍጠር ጉዳይ ነበር፡፡ እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ በዚህ አካሄድ ከቆየን በኋላ ምርጫ መጣ፡፡ በምርጫው ተሳተፍን፡፡ ቀጥሎም ምርጫውን መገምገም ነበረብን፡፡ ምርጫውን ከገመገምን በኋላ ከዚያ ተነስተን የ5 አመት ስትራቴጂ ማውጣት ነበረብን፡፡

በትክክል እኛ ስራ ጀምረናል የምንለው በ2004 ዓ.ም ነው፡፡ የትግል ስልታችን ሰላማዊ ነው፡፡ ሌላ የትግል ስልት የለንም፡፡ የዚህ የትግል ስልት አንዱ መገለጫው ደግሞ ህዝባዊ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን ማካሄድ ነው፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በወጡት አዋጆችና የተለያዩ ክልከላዎች ሳቢያ እነዚህን ስልቶች ተግባራዊ ለማድረግ ፈታኝ ሆኖብን ነበር፡፡ በሌላ በኩል ፓርቲው አዳዲስ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ሂደት ውስጥ ነበር፡፡ ለአባላቱም ስለ ሰላማዊ ትግል ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከዚያ በኋላ በስፋት ህዝባዊ ንቅናቄዎችን መፍጠር ጀመርን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ለማካካስ ሳይሆን በእቅዳችን ነው ስንጓዝ የነበረው፡፡ እዚህ ላይ ለማስታወስ የምፈልገው ትላልቅ ሰላማዊ ሰልፎች ባይካሄዱም ቀደም ብሎ ወ/ት ብርቱካን እንድትፈታ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገን ነበር፡፡
አሁን እያካሄዳችሁት ያለው ሰላማዊ ሰልፍ በትክክል የታቀደበት ነው?
አዎ! እቅዱን የነደፍነው ከሚያዝያ 2005 ጀምረን ነው፡፡ እቅዱን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል ስንወያይ ቆየን፡፡ ከዚያም እንቅስቃሴውን ለሦስት ወራት እናካሄዳለን ብለን ፕሮግራም አወጣን፡፡ ሰኔ፣ ሐምሌ እና ነሐሴ ወር ላይ ለማካሄድ ወሰን፡፡ በሁለት ምክንያቶች ነው ይህን ወቅት የመረጥነው፡፡ አንደኛ የአመቱ ማጠቃለያ ስለሆነ በአመቱ አንዳች ስራ ለመስራት ሲሆን ሌላው ቀጣዩ ጠቅላላ ጉባኤ የሚካሄደው በመስከረም ወር ነው፡፡ ስለዚህ ከዚያ በፊት የሦስት ወር ፕሮግራም ነድፈን በደንብ የተዘጋጀንበት እንጂ ዝም ብለን የጀመርነው አይደለም፡፡
የሰልፉ አላማ ወይም ከሠልፉ የሚጠበቀው ውጤት ምንድን ነው?
ከሰልፉ ብቻ ሳይሆን ከእቅዳችን የምንጠብቀው፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመፈፀሚያ አመቺ የሆነው ወይም አሁን እንደምናየው ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን እና ሌሎች የህብረተሰቡ አካሎችን ለማጥቂያ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ እንዲሻሻል ወይም ከነጭራሹ እንዲሰረዝ የሚል ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ህጉ ምን አይነት እንደሆነ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ምን አይነት ጉዳት እያደረሰ እንዳለ ህዝቡ እንዲረዳው እንፈልጋለን፡፡ ከሰልፉ ባሻገር የህብረተሰቡን ድጋፍ አሰባስቦ ለሚመለከተው አካል ህጉ ወይ ይሻሻል አሊያም ይሰረዝ የሚል ማመልከቻ ማቅረብ ነው፡፡ ይህን ህግ በመቃወም ሚሊዮኖች ከፈረሙ ተሰሚነት ያገኛል በሚል ነው እንቅስቃሴውን የጀመርነው፡፡ በዚህ ብቻ አናበቃም፡፡ ስለፓርቲውም ስለ ህጉም የተለያዩ መረጃ ሰጪ በራሪ ወረቀቶች እንበትናለን፡፡ ሌላው በእንቅስቃሴ ውስጥ አባላትን ማፍራት ይቻላል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ልናተርፈው የምንችለው እንግዲህ እነዚህ ናቸው፡፡
የምታካሂዱት እንቅስቃሴ በመንግስት ላይ ጫና ፈጥሮ ህጉን የማስቀየር አቅም ይኖረዋል? ወይም የዚያን ያህል አቅም እንዲኖረው አድርጋችሁ ነው እየተንቀሳቀሳችሁ ያላችሁት?
መንግስትም፣ ዜጐችም፣ የአለም ማህበረሰብም እንዲያውቅ የምንፈልገው በዚህ በፀረ ሽብርተኝነቱ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኑሮ ጉዳዮችም ህዝቡ መተንፈሻ ይፈልጋል፡፡ በየጊዜው በሚደረጉት ሰልፎችና ስብሰባዎች የሚወጣው ህዝብ ምን ያህል እንደሆነ በሚያይበት ጊዜ በሚዲያም ሲስተጋባ በሚመለከተው አካል ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል፡፡ በአንድ በኩል ህዝቡ የታመቀ ብሶቱን እንዲገልጽ ያስችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይሄ ጉዳይ ለካ የህዝብም ጥያቄ ነው ብሎ መንግስት ቆም ብሎ እንዲያስብ ይረዳል፡፡ ሌሎችም የመንግስት የገቢ ምንጭ አካላትም በመንግስት ላይ ተጽእኖ እንዲፈጥሩ ይረዳል፡፡ መንግስት ግትርነቱን ትቶ የህዝቡን ድምጽ መስማት ይጀምራል ወይ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ በመሠረቱ ይህን እንቅስቃሴ ስናደርግ መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆኖ አይደለም፡፡ ሌሎች አካባቢዎች በብዙ ውጣውረድ ፍቃድ አግኝተን አላማችንን ብናሳካም በትግራይ መቀሌ እና በወላይታ ሶዶ ከአስተዳደሩ ጀምሮ እስከታች ወረዳ ድረስ ያሉ አመራሮች እርስ በእርስ በመጠላለፍ በሰሩት ስራ ያሰብነውን ማካሄድ አልቻልንም፡፡
ምን ነበር በሁለቱ ቦታዎች ያሰባችሁት?
መቀሌ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር ያቀድነው፡፡ ወላይታ ሶዶ ደግሞ ህዝባዊ ስብሰባ ነበር፡፡ ሁለቱም ተጨናግፈውብናል፡፡ ከላይ ጀምሮ እስከታች ድረስ በነበረው አሻጥር እቅዳችን ሊሣካ አልቻለም፡፡
አክራሪነትና ሽብርተኝነት በሚባሉት ጉዳዩች ላይ “አንድነት” ያለው ጥርት ያለ አቋም ምንድን ነው?
እኛ ሽብርተኝነትን በጥብቅ እንቃወማለን፡፡ ሽብርተኝነት ምን ማለት ነው በሚለው ላይ በህገመንግስቱ መሠረት ነው የምንሄደው፡፡ በአንቀጽ 29 መሠረት ሰዎች የፈለጉትን ሃሳብ መያዝ ይችላሉ፡፡ በሚዲያ አማራጮችም መግለጽ ይችላሉ፡፡ ይህ መብት በህገመንግስቱ ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ የፀረ ሽብር ህጉ ይህንን አንቀጽ የሚጥስ ነው፡፡ ገና አስበዋል ተብሎ በተግባር ያልፈፀሙ ወይም ለመፈፀም ዝግጅት ባላደረጉ ሰዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ሁለተኛ በህገ መንግስቱ በአንቀጽ 30 ላይ ማሰብ ብቻ ሳይሆን ህዝባዊ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን በማድረግ ያልመሰለህን ነገር መቃወምና እንዲሻሻል ለመንግስት ማመልከቻ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህም መብት እየተጣሰ ነው፡፡ ሌላው በዚህ የፀረ ሽብር ህግ በማሳበብ ዜጐች እንዳይደራጁ እየተደረገ ነው፡፡ እነዚህን ህገመንግስታዊ የመብት ጥሰቶች እኛ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ በዚህ አካሄድ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱም ነው እንቅስቃሴ የምናደርገው፡፡ አስረግጬ መናገር የምንፈልገው እኛ እውነተኛ ሽብርተኝነትን አጥብቀን እንቃወማለን፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሽብርተኝነት ስጋት አለ ብላችሁ ታምናላችሁ?
በምንድን ነው የምናረጋግጠው? መንግስት በሚለው ብቻ እንጂ የምናውቅበት መንገድ የለም፡፡
ለምሣሌ አዲስ አበባ ውስጥ የደረሱ የቦንብ ፍንዳታዎች በማሳያነት ይቀርባሉ?
እሱ ቆይቷላ! እንደዚያ አይነት ነገር በ2004 ዓ.ም የታለ? የዚያ አይነት ፍንዳታ አላየሁም፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች በሰዎች አለመግባባት ግጭቶች ተፈጥረው ሊሆን ይችላል እንጂ ሽብርተኝነት በጉልህ ለመኖሩ እኛ መረጃ የለንም፡፡
መንግስት፤ የሃይማኖት አክራሪነት የሃገሪቱ ስጋት ነው ሲል ይገልፃል፡፡ በእናንተ በኩል ይህን እንዴት ነው የምትመለከቱት?
አክራሪነት አንድ ሰው አንድ ሃሳብን ይዞ የማክረር ጉዳይ ነው፡፡ እኛ በግምገማችን ሰዎች ስለመብታቸው መከበር እየጠየቁ መሆናቸውን፣ ይህን በማድረጋቸው መታሰራቸውን ደርሰንበታል፡፡ ይህን በማድረጋቸው ደግሞ መታሰር የለባቸውም፡፡ ለምሣሌ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተማረኝ እንደዚህ ነው፣ ይሄ መሆን አለበት ብሎ በሌሎች ላይ ጫና የመፍጠር ሁኔታ እኔ አላየሁም፡፡ የግራ ፊትህን ለመታህ ቀኝህንም ስጠው በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መርህ የሚሄዱ አሉ፤ ቁርአን ይሄን ይሄንን ነው የሚለው ስለዚህ በዚህ መንገድ ነው መሄድ ያለብን ብሎ የሚያስተምርም አለ፡፡ ያንን ሃሳብ የመያዝና የማስተማር መብቱ በአንቀጽ 29 እና 31 (በህገ መንግስቱ) የተጠበቀ ነው፡፡
መንግስት፤ አንዳንድ ተቃዋሚዎች “እስላማዊ መንግስት” እንዲመሠረት ከሚሹ አክራሪ አካላት ጋር እየሰሩ ነው ይላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእናንተ አቋም ምንድነው?
የእስላማዊ መንግስት ቢቋቋም ጥሩ ነው የሚል ካለ፣ ያንን ለምን አሰብክ ብሎ መጋፋት ትክክል አይደለም፡፡ መብቱ ነው፡፡ ያንን በተለያዩ መንገዶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ነው ችግሩ፡፡ ምክንያቱም የሌሎቹን መብት እየተጋፋ ነው ማለት ነው፡፡ እኛ እስካሁን ድረስ ይሄን አላየንም፡፡ እስላማዊ መንግስት በኢትዮጵያ ይቋቋም የሚል ጥያቄ አንስቶ የሚንቀሳቀስ ስለመኖሩ እኔ እስካሁን አልሰማሁም፡፡
አንድነት የፀረ ሽብርተኝነት ህግ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለው?
በአንድ በኩል ወንጀሎች ናቸው እየተፈፀሙ ያሉት፡፡ ለዚያ ደግሞ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አለ፡፡ እዚያ ላይ የሚጐድል ነገር ካለ ማሻሻል ይቻላል፡፡ እንዳልኩህ ሽብርተኝነትን እንቃወማለን፡፡ በዚያ አካሄድ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን እንቃወማለን፡፡ ካስፈለገ ህግ ሊወጣ ይችላል፡፡ እኛ የፀረ ሽብርተኝነትን ህግ ጭራሽ አይኑር የሚል አቋም የለንም ግን የሚወጣው ህግ ዜጐችን መልሶ የሚጐዳ መሆን የለበትም፡፡
ይሄን ጥያቄ ያነሳሁት አሁን ከጀመራችሁት እንቅስቃሴ አንዱ የፀረ ሽብር አዋጁን ማሠረዝ ስለሆነ ነው?
አዎ እኛ የፈለግነው በ2003 የወጣው አዋጅ እንዲሠረዝ ነው፡፡ ያ አዋጅ በዜጐች ላይ መልሶ ጥቃትን የሚፈፅም አዋጅ ነው፡፡ ጥሩ አይደለም፡፡ ይሄ የ2003 አዋጅ ወይ ይቀየር ወይም ተሻሽሎ ይውጣ ነው እንጂ ያልነው የፀረ ሽብር ህግ ከነጭራሹ አያስፈልግም አላልንም፡፡
አንድነትን ጨምሮ የሃገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የአመራርነት ቦታ ለተተኪ ወጣቶች እድል የሚሠጥበት አይደለም ይባላል፡፡ በዚህ ላይ የእርሶ አቋም ምንድነው?
መተካካት የኢህአዴግ አጀንዳ ነው፡፡ እኛ የፖለቲካ ፓርቲ እንጂ የወጣቶች ማህበር አይደለንም፣ ወይም ደግሞ የሴቶች ማህበር አይደለንም፡፡
ወጣቶችም ይሁኑ ሽማግሌዎች ወይም ሴቶችና ሠራተኞችም ይሁኑ ዋናው ቁም ነገር የፖለቲካ ጉዳይ ነው፡፡ አላማችንን አይቶ በፍላጐት ለመታገል የመጣን ሰው ወጣት አይደለህምና አይሆንም ብለን አናገልም፡፡ የአመራር ብቃት የሚታየው በእንቅስቃሴ ውስጥ ነው፡፡ በተጨባጭ ግን እንደማየው የአንድነት ፓርቲ አመራር በአብዛኛው በወጣቶች የተደራጀ ነው፡፡ እኔና አቶ አስራት ብቻ ነን ወደ 70 የተጠጋነው (እየሳቁ) የተቀረው ከዚያ በታች ነው፡፡
በእርግጥ የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤም ሰሞኑን በ89 ዓመታቸው ለ7ኛ ጊዜ በምርጫ ተወዳድረው ማሸነፋቸውን ሰምተናል…
ጥያቄው ሰውየው መንቀሳቀስ ይችላል ወይ ነው፡፡ ማሰብ ይችላል ወይ ነው፡፡ ወይስ አርጅቶና ጃጅቶ የማይሆን ተግባር ይፈጽማል ወይ ነው መሆን ያለበት፡፡ ለመምራት እውቀቱ ያስፈልጋል፣ ጤንነት ያስፈልጋል፡፡ በአካል የመንቀሳቀስና በአዕምሮው በሚገባ ማሰብ የሚችል ሰው መሆን አለበት፤ ያ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ አንድ መሪ ብቻውን አይደለም ሀገር የሚመራው፡፡ ስለዚህ የግድ ወጣቶች ብቻ መሆን የለበትም፡፡
ከመኢአድ ጋር ውህደት ለመፍጠር በድጋሚ እንቅስቃሴ መጀመራችሁ እየተነገረ ነው፡፡ ምን ላይ ደረሳችሁ?
በ2004 ዓ.ም ኮሚቴ አቋቁመን ነበር፡፡ እኛ ከመድረክ ጋር አስቀድመን ግንባር ፈጥረናል፤ ይሄን በማይነካ መልኩ ከመኢአድ ጋር ውህደት ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ የነበረ ኮሚቴ አቋቁመን መነጋገር ጀምረን ነበር፡፡ ግን በአንድ ጉዳይ ምክንያት መስማማት አልቻልንም፤ መኢአድ የብሔር ድርጅቶችን የጐሣ ድርጅቶች ናቸው ይላል፡፡ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር ለመስራት አልፈልግም የሚል አቋም አለው፡፡ አንድነት መድረክ ውስጥ እስካለ ድረስ ውህደት ሊኖር እንደማይችልም አቋሙን አስረግጦ ገልጿል፡፡ እኛ ደግሞ መድረክ ውስጥ የገባንበት ምክንያት አለን፡፡ ስለዚህ ከእናንተ ጋር ለመዋሃድ ብለን ከመድረክ የምንወጣበት ምክንያት የለም ብለናቸዋል፡፡ ምርጫ 2005 የፈጠረው የ33 ፓርቲዎች ትብብር ውስጥም ሁለቱም ፓርቲዎች አሉ፡፡ በዚያ በኩል አብሮ ተባብሮ ለመስራት የተፈረመ ስምምነት አለ፡፡ ከዚያ ውጪ በተናጠል የጀመርነው ነገር የለም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ውይይቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በመዋቅር ደረጃ ግን በ2004 ተሞክሮ አልተሳካም፡፡
በሌላ በኩል ከመድረክ ጋርም ግንኙነታችሁ እየሻከረ መሆኑ እየተነገረ ነው…
ግለሰቦች ነፃነት አላቸው፡፡ አንዳንዴ ችግር የሚፈጠረው በፓርቲ ውስጥ ያለ ግለሰብ በግሉ ሃሳብ በሚያቀርብበት ጊዜ የፓርቲው አቋም ነው ብለው የሚወስዱ አሉ፡፡ ለምሣሌ እነ አቶ ቡልቻ በግለሰብ ደረጃ የሚናገሩት አለ ያ ማለት የመድረክ አቋም አይደለም፡፡ ፕ/ር በየነ በአቶ ግርማ ላይ ይጽፋሉ፤ አቶ ግርማም ይመልሳሉ፣ ይሄ የግለሰቦች ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባት አንድነት የ4 አመት ጉዟችንን ገምግሞ ነበር፡፡ ከመድረክ ጋር ያለን ግንኙነት እንዴት ነበር? አብሮ በመስራት ምን ውጤት ተገኘ? የሚል ግምገማ አካሂደን ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት በአካሄድ ጉዳይ ላይ ንግግሮች ነበሩ፡፡ ከዚህ ውጪ በአንድነትና በመድረክ መካከል ምንም ችግር የለም፡፡ ችግርም ካለ በህገ ደንባችን መሠረት የሚፈታ ይሆናል፡፡
በውጭ አገር ያሉት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እና አቶ ስዬ አብርሃ አሁንም የአንድነት አባል ናቸው?
አቶ ስዬ ከዚህ ሲሄድ አባል ነበረ፡፡ አሜሪካን ከሄደ በኋላም አለቀቀም፤ ሲረዳን ነበር፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ፓርቲውን ለቋል የሚሉ ሃሜታዎች ይሰማሉ፡፡ ነገር ግን ከአቶ ስዬ በኩል በዚህ ምክንያት ፓርቲውን ለቅቄያለሁ የሚል ደብዳቤ አልደረሰንም፡፡ እንደሚወራው ከሆነ በፖለቲካ ስራ ላይ እንዲሳተፍ የማይፈቅድለት ስራ ውስጥ ተቀጥሯል፡፡ ይሄንን ግን አሜሪካ ቦስተን ያለው ወኪላችን አላረጋገጠልንም ወይም አቶ ስዬ ራሱ ምክንያቱን አስረድቶ አላሳወቀንም፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ስለሱ ምንም ማለት አልችልም፡፡ ወ/ት ብርቱካንን በተመለከተ ግን አባላችን ብቻ ሳይሆን ሊቀመንበራችንም ነበረች፡፡ ወደ አሜሪካ ከመሄዷ አንድ ቀን በፊት በአንተ በኩል መልዕክት እንዲደርስልኝ እፈልጋለሁ ብላኝ ተገናኘን፡፡ በእስር ቤት ከደረሰባት ጫና ለማገገምና ለትምህርት እንደምትሄድ አስረድታኝ የአንድነት ፓርቲ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ከእንግዲህ አልኖርም ብላ በግልጽ ነግራኛለች፤ ስለዚህ አባላችን አይደለችም፡፡
አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ በ2007 ፓርላማ ለመግባት እንደሚወዳደርና በቀጣይም ፕሬዚዳንት ለመሆን እንዳሰበ በይፋ ተናግሯል፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት? በሁለቱም ሂደቶች ያለፉ ስለሆኑ ነው ጥያቄውን ያነሳሁት…
እዚህ ላይ ወይ የሱ አሊያም የሰዎች የግንዛቤ ችግር አለ፡፡ የፓርላማ ምርጫ በ2007 ነው፡፡ አዲስ ፕሬዚዳንት የሚሾመው በ2006 መስከረም ወር ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ከፈለገው ፓርላማ ሳይገባ ከውጪ ለፕሬዚዳንትነት እጩ አድርጐ ሊያስመርጠው ይችላል፡፡ ህገመንግስቱ አንድ ፕሬዚዳንት ተደርጐ የተመረጠ ሰው የፓርላማ አባል ከሆነ ወንበሩን መልቀቅ አለበት ይላል፡፡ ያ ማለት ከፓርላማም ከውጪም ሊመጣ ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ፕሬዚዳንት መሆን ከፈለገ አሁን ነው እጩ መሆን የሚቻለው፡፡

Read 2320 times