Saturday, 24 August 2013 10:05

ሶኒ አዲስ የሞባይል ቀፎ ኢትዮጵያ ውስጥ አስገባ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ሶኒ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ የግማሽ ክፍለ ዘመን ጥረቴን ያንፀባርቃል ያለውንና አዲሱን “ኤክስፔሪያ ዜድ” የተሰኘ የሞባይል ምርት ወደ ኢትዮጵያ አስገብቷል፡፡ ሰሞኑን በይፋ ያስተዋወቀው ይሄው ምርት ወድቆ መከስከስ፣ ውሀ ውስጥ ገብቶ ስራ ማቆም አይነካካውም ተብሏል፡፡ አዲሱ ኤክፔሪያ ዜድ ሞባይል ዋጋው 18ሺህ ዘጠኝ መቶ ብር እንደሆነም የሶኒና የአከፋፋዩ የግሎሪየስ የስራ ሀላፊዎች ገልፀዋል፡፡ ምርቱ በአንድ ንክኪ የሚፈልጉትን ዘፈን ወደ ስፒከር የማዛወርና ከስፒከሩ ብቻ እንዲያዳምጡ የማድረግ አቅም እንዳለውም ተገልጿል፡፡ የሀምሳ አመት የስራ ዘመኑንና የቴክኖሎጂውን ምጥቀት እንደሚያሳይለት የገለፀው ሶኒ የጥገና ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ለመክፈት ዝግጅት ማጠናቀቁንም ይፋ አድርጓል፡፡
ኤክስፔሪያ ዜድ የምስል ጥራቱ ከ3D ቴሌቪዥን እኩል መሆኑን የገለፁት ሀላፊዎቹ ምርቱ ከድምፅ በተጨማሪ በንክኪ ምስልና ሌሎች አገልግሎቶችን ወደ ቴሌቪዥን የማሰራጨት አቅም እንዳለውም ተብራርቷል፡፡
ሰሞኑን በሂልተን ሆቴል በተካሄደው የምርቱ ይፋዊ ትውውቅ ስለ ሞባይሉ ማብራሪያ የሰጡት የግሎሪየት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ነዲብ አብዱልሰመድ እንደተናገሩት በሞባይሉ ራስን ከተለያየ አቅጣጫ ፎቶ ማንሳት የሚቻልበት ፈጠራም ታክሎበታል ብለዋል፡፡ የጨረር ጉዳቱ ከሌሎች በአለም ላይ ካሉ ሞባይሎች በጣም ያነሰ ነው የተባለለት አዲሱ “ኤክስፔሪያ ዜድ” የኔትወርክ ችግርን ለመቅረፍ ከሁለት ጂ በላይ ይዘት እንዳለው የተገለፀ ሲሆን ባለ አምስት ኢንች ሙሉ እውነታን ያሳያልም ተብሏል፡፡ የባትሪ አቅሙን በተመለከተ ከመደበኛዎቹ ባትሪዎች በአራት እጥፍ የላቀ አገልግሎት እንዳለውና ይህም ከሌሎች ሞባይሎች ተመራጭ እንደሚያደርገው ተጠቁሟል፡፡ አዲሱን ኤክፔሪያ ዜድ ከ30 አመታት በላይ የኩባንያውን ምርቶች እያስመጣ ሲያከፋፍል የኖረው ግሎሪየት እያስመጣ ለገበያ ያቀርበዋል ሲሉ ሀላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

Read 17857 times