Saturday, 24 August 2013 10:32

“የማያውቁት አገር…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ዝናቡን አሳንሶ ውርጩን ላከብን አይደል! አየሩ ውርጭ፣ ኑሮው ውርጭ…
እትቱ በረደኝ ብርድ ይበርዳል ወይ
የማያውቁት አገር ይናፍቃል ወይ?
የሚሏት ዘፈን አለች፡፡ አዎ እንደ ዘንድሮ ሁኔታችን ከሆነ…አለ አይደል… የማያውቁት አገር እንክት አድርጎ ይናፍቃል! ነገሮች ሁሉ ግራ ሲገቡ፣ “የእኔ ጓዳ ከሞላ የሌላው ዳዋ ይምታው…” አይነት አስተሳሰብ ሲበዛ፣ በ‘ማስተዳደር’ እና በ‘መግዛት’ መካከል ያለው ቀጭን መስመር ሲጠፋ፣ አቤቱታ አቅራቢ እንጂ አቤቱታ ተቀባይ ሲጠፋ፣ “የወሎ ህዝብ መሰደድ ልማዱ ነው…” እንዳሉት የድሮ ባለስልጣን… “የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶት ማቅረብ ልማዱ ነው…” አይነት ‘ወንበሬም እኔም አንገለበጥም’ አይነት ‘ቦስነት’ ሲበዛ…“እኔን ተከተል…” እንጂ “ጎን ለጎን እንጓዝ…” ማለቱ ለአንደበት ሲጎመዝዝ…ያኔ እንክት አድርጎ የማያውቁት አገር የማይናፍቅሳ!
ስሙኝማ…ሰሞኑን ቢቢሲም አልጀዚራም ስለ ወገኖቻችን ስደት ‘ጉዳችንን’ አደባባይ ሲያወጡብን አያችሁልኝ አይደል! እናማ…አንድ ሆድ ለመሙላት ያን ሁሉ መከራ መጋፈጥ የ‘ጥጋብ’ ሳይሆን ነገርዬው ሁሉ “አገሩ ለባለ አገሩ” አልሆን ብሎ…የማያውቁት አገር እየናፈቀ ነው፡፡
ከዚህ በፊት የጠቀስናትን እንድገማትና… ልጅቱ ዓረብ አገር ለመሄድ ደፋ፣ ቀና ትላለች.. እና ሀሳቧን እንድትለውጥ ሊመክሯት ያስቡና…“እነኚ ሁሉ ሲሞቱ እየሰማሽ ቢቀርብሽ ምን አለ!” ምናምን አይነት ነገር ይሏታል፡፡ ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው…“እዚህም ያው ሞት ነው፡፡”
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይሄ ሰሞኑን ብዙ የግል ትምህርት ቤቶች እያደረጉ ያሉት ጭማሪ…“እዚህ አገር ‘ሰበብ’ እየተጠበቀ ‘ቆዳ ገፈፋ’ ላይለቀን ነው!” ያሰኛል። ወላጆች አምስት ሳንቲም ተጨማሪ ‘ፈረንካ’ ባላገኙበት፣ ‘ጤፉም ጧፉም’ በየጊዜው ሽቅብ እየተሰቀለ ባለበት ወቅት በአንድ ልጅ የወር ሂሳብ ላይ እስከ ሺህ ብር መጨመር…አለ አይደል… “ኸረ ውሎ አድሮ ጡር ይኖረዋል!” ያሰኛል፡፡ እንደውም “ከፈለጋችሁ ሌላ ረከስ ያለ ትምህርት ቤት ውሰዱ…” አይነት ቃና የሚሰማባቸው አሉ ይባላል፡፡ እናማ…ልጆችን በመልካም መንገድ አንፆ ለማሳደግ ሲያቅት…የማያውቁት አገር የማይናፍቅሳ!
የልጆች ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ትንሹ ልጅ አስቸጋሪ ነው፡፡ እናላችሁ… ብቻውን አውቶብስ ይሳፈርና ከሾፌሩ ጀርባ ይቀመጥና መጮህ ይጀመራል፡፡ “አባዬ በሬ ሆኖ እናቴ ላም ብትሆን ኖሮ እኔ ሚጢጢ በሬ እሆን ነበር!” ሾፌሩ በጣም ይናደዳል፡፡ ልጁም መጮሁን ይቀጥልና… “አባዬ ዝሆን ቢሆንና እናቴ ሴት ዝሆን ብትሆን ኖሮ እኔ ሚጢጢ ዝሆን እሆን ነበር!” ልጁ እንዲህ፣ እንዲህ እያለ መጮሁን ይቀጥላል፡፡
ሾፌሩ በጣም ይናደድና አፉን ለማዘጋት እንዲህ ይለዋል…“አባትህም እናትህም ወፈፌ ቢሆኑ ኖሮስ!” ይለዋል፡፡ ልጁ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“የአወቶብስ ሾፌር እሆን ነበር፡፡” ቂ…ቂ…ቂ…
ደግሞላችሁ…ካነሳነው አይቀር፣ በከተማችን እየተከፈቱ ያሉ አንዳንድ ሬስቱራንቶች…አለ አይደል…ግራ ያጋቧችኋል፡፡ እንዴ… አንዳንዴ እኮ ለአንዲት ‘ስኒ’ ሻይ በፋይቭ ስታር ሆቴል ከሚጠየቀው ሂሳብ እጥፍ የሚደርስ ይጠይቋችኋል፡፡ ሻይ (ያው ሙቅ ውሀና ሻይ ቅጠል!) ሦስትና አራት ባውንድ ሲሆን፣ እንዲህ የሚያደርገው…አለ አይደል… የ‘ማርኬቲንግ ጥበብ’ ሳይሆን የአልጠግብ ባይነት አባዜ…ነው። ሚጢጢዎቹ ቦታዎች ብትሄዱም በሸራፋ ብርጭቆ፣ ስኳሩ ‘ቀበቶን በማጥበቅ’ አይነት ቁጠባ የተጨመረበት ሙቅ ውሀ…ሰባትና ስምንት ብር ይባላል፡፡ እናማ በሰበብ አስባቡ ሁሉም ዋጋ ጭማሪ ሲሆንና፣ ምናምን ማድረግ የማትችሉ ‘ምስኪንነት’ ስሜት ሲያድር …የማያውቁት አገር የማይናፍቅሳ!
የምር ግን… እዚህ አገር የ‘ሴልፊሽነት’ መጠኑና ስፋቱ ለመግለጽም የሚያስቸግር ደረጃ እየደረሰ ነው! ብቻ ምን አለፋችሁ ሁሉም… ከቦሶች እስከ ታች ድረስ ደግሞ “በየት በኩል የቀረችውን ሳንቲም እናራግፋቸው?” እያሉ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ አይመስላችሁም!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ለምሳሌ በእኛ አገር ‘ቦተሊካ’ ላይ ‘ሰበብ’ ሲገኝ…አለ አይደል… “የጫማህ ማስቀመጫ ያድርገኝ!” አይነት ይል የነበረው ሁሉ… “ከእነ እንትና ጋር አረቄ እንደምትጠጣ የማናውቅ መሰለህ!” አይነት ‘ቆዳ ገፈፋ’ ይጀመርላችኋል፡፡
ደግሞላችሁ…ምሁራን አካባቢ ካያችሁ “እሱ እኮ የአይንስታይን ደቀ መዝሙር መሆን የሚችል ነው…” ለማለት ጥቂት ይቀራቸው ያልነበረውን ሰው…አለ አይደል…‘ሰበብ’ ሲገኝ ምን አይነት ‘ቆዳ ገፈፋ’ ይጀመር መሰላችሁ… “እኔ’ኮ ልደርስበት ያልቻልኩት ዶክትሬቱን ፎርጅድ ያሠራው የት እንደሆነ ነው እንጂ ወረቀቷማ ፌክ ነች!” ይባላል፡፡
አሪፍ የነበረችው እንትናዬ አለችላችሁ…“ልቅም ያለች ልዕልት ዲያናን የምታስንቅ ቆንጆ…” ስተባል የነበረችው ፈዘዝ ስትልና ‘ሰበብ’ ሲገኝ ያው አድናቂ ሰራዊት ምን ማለት ይጀምራል መሰላችሁ…“ድሮም እኮ ዕድሜ ለሜክ አፕ ትበል!” አይነት ነገር ይመጣል፡፡
እናማ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲበዙ፣ ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት ማለት ሲያቅተን…ምነው የማያውቁት አገር የማይናፍቅሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እዚቹ ከተማችን ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ ነገሮች…አለ አይደል…አያሳስቧችሁም? እንዴት ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉም ነገር እስከ ጽንፍ እየሄደ የሚበላሸው ያሰኛል፡፡ እናላችሁ…መጪ ትውልዶች ላይ እንደ ዴሞስቴን ሰይፍ የተንጠለጠሉ ችግሮች እንዲህ ሲከማቹ…የሚጨንቃቸው ቦሶች የማንሰማሳ! …“ለምንድነው ደግ፣ ደግ ነገሮችን መያዝ ያቃተን!” የሚል የአገር አለኝታ ምነው ጠፋሳ! ሁሉም ነገር የ‘ቦተሊካ ቲራቲር’ እየሆነ ምድር ለምድር እየተስፋፉ ትውልድ እየበከሉ ያሉ ነገሮች ችላ ሲባሉ…አለ አይደል...የማያውቁት አገር የማይናፍቅሳ!
አንዳንድ ጊዜ ወላጆች…አለ አይደል… “እንደው ልጆቼ እንደምንም ብለው ከዚህ አገር ቢወጡልኝ…” ሲሉ…ልጆቻቸው ‘የውጪ ዜጋ’ እንዲሆኑላቸው የመመኘት ጉዳይ ሳይሆን “ዓይኔ እያየ ገደል ሲገባ ዝም ብዬ አላይም…” በሚል በየቦታው ከሚገማሸሩ የጥፋት ማዕበሎች ሊከላከሏቸው ነው፡፡
ታዲያላችሁ…‘የማያውቁት አገር የሚያስናፍቁ’ ነገሮች ሲበዙ…ይመለከተኛል ባይ ሲጠፋ የምር ጥሩ ምልክቶች አይደሉም፡፡ እናማ… የ‘መምራት’ ትልቁ እሴት… ዲስኩርና በባንዲራ ያሸበረቀ ስብሰባና ‘ሬሴፕሽን’ (ቂ..ቂ…ቂ…) ማብዛት ሳይሆን ‘መሬት ወርዶ’ ሥራ መሥራትና ከሁሉም በላይ ትውልዶችን መንገዶች ላይ የሚኖሩ እንቅፋቶች መቀነስ መሞከር ነው፡፡
የእንቅልፍ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው እልም ያለ እንቅልፍ ወስዶታል፡፡ እናላችሁ…የሆነ ጓደኛው ይመጣና ወዝውዞ ይቀሰቅሰዋል፡፡ ከዛ ምን ይለዋል…“እንቅልፍ ወስዶህ ነበር እንዴ!” ይለዋል፡፡ ይሄኔ ተኝቶ የነበረው በጣም ይናደድና ምን ቢል ጥሩ ነው…“አይ ኮማ ውስጥ ነበርኩ…ህይወቴን ስላተረፍክልኝ አመሰግናለሁ፡፡”
እናማ…ድፍን አገር እንቅልፍ ሲያበዛ ጥሩ ነገር አይደለም፡፡ ‘የማናውቀውን አገር የሚያስናፍቁን’ ነገሮችን ይቀንስልንማ!
በፊት ጊዜ ልጆች ለቡሄ ጊዜ ሲጨፍሩ የሚሏት ስንኝ ነበረች፣
ቡሄ ቡሄ በሉ… ልጆች ሁሉ
የቡሄን አደራ… አንቺ አሞራ
እናላችሁ…“ሀገሬን አደራ…” የምንላት ‘አሞራ’ ነገር ይላክልንማ!
መልካም የበዓል መዳረሻ ሰሞን ይሁንላችሁማ!
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 2949 times