Print this page
Saturday, 31 August 2013 11:48

አገሬ፣ እኔ እናሻማ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

መሸ
ቤቴ ገባሁ፡፡
ያው ደሞ እንዳመሉ
እንደባህሉ ሁሉ …መብራቱ ጨልሟል፡፡
እና ሻማ ገዛሁ
በሻማው ብርሃን፣ ልፀዳበት አሰብሁ፡፡
እና ሻማ ገዛሁ…ሁሉንም ባይሆንም
አንድ ሁለት አበራሁ
በሻማው ብርሃን …መንፈሴን አፀዳሁ
እንደ አያቴ መስቀል
እንደሼኪው ሙሰባህ
እንደ አበው መቁጠሪያ
እንደአገሬ ማተብ …እንዳገሬ ክታብ
አምኜ ጀመርኩኝ፣ ማስታወሻ መፃፍ
ህይወት ባገኝ ብዬ፣ ከጨለማው ደጃፍ፡፡

ከሐምሌ ጨለማ
ከጨረቃዋ ሥር፣ ጉም ከተናነቃት
ክረምቱ ዘንቦባት
ብርድ እንደዛር - ውላጅ፣ እያንቀጠቀጣት፤
አገሬ ጨልማ፤
በእንግድነት ቤቴ፣ መጥታ ልትጠይቀኝ
“መብራቴን ሸጫለሁ፣ ሻማ ለኩስልኝ”
ብላ ለመነችኝ፡፡
“የሸጥሽበት ገንዘብ፣ የት ደረሰ?” አልኳትኝ፡፡
(ይሄኔ ነጋዴ ኖሮ ቢሆን ኖሮ፤ “አትርፋለች?” ባለኝ፡፡
ይሄኔ አንድ ምሁር፣ ኖሮ ቢሆን ኖሮ
ማን ፈቅዶ ነው ይሄ፣ ምን ‘ማንዴት’ አላቸው?
ጉድ መጣ ዘንድሮ፤
ኖሮ ቢሆን ኖሮ፣ የጋዜጣ አንባቢ፤
“ህዝብ ያቃል ይሄንን?
ደባ ሲሰሩ ነው!” ባለ ነበር ምሩን
ሁሉን አስባበት፣ ሻማዊ ሳቅ ሳቀች
ሁሉን አስቤበት፤ ሻማዊ ሳቅ ሳኩኝ፡፡

ከነልብሴ ተኛሁ፣ ብርድ ልብስም የለኝ፡፡
እሷም ሌጣዋን ነች፤ ጐኔ ገለል አለች፡፡
ልክ ዐይኔን ስከድን፣ ቀና አለች ወደኔ
“ሻማውን አጥፋ እንጂ፤ ለነገ አታስብም?
የቁጠባ ባህል፣ ዛሬም አልገባህም?!”
ስትል ገሰፀችኝ፡፡

ሻማው ሰማ ይሄንን፣ ጣልቃ ገባ እንዲህ ሲል
“መብራት ከሄደበት፣ እስኪመለስ ድረስ
ዓመት ፍቃድ ላይ ነኝ፣ ይሁን ልሥራ ለነብስ
የበራሁ መስዬ፣ ተዉኝ ትንሽ ላልቅስ!
ብቻ ወዳጆቼ፤
እንሰነባበት፣ እንሳሳም በቃ፤
ስለማይታወቅ፣ ነግ ማን እንደሚከስም
ነግ ማ እንደሚነቃ!!”
(የነገን ማን ያውቃል ለሚሉ)
ከግንቦት 2004-2005 ዓ.ም

Read 3185 times
Administrator

Latest from Administrator