Saturday, 31 August 2013 11:52

በገቢዎችና ጉምሩክ ተጠርጣሪዎች ላይ 8 የክስ መዝገቦች ተከፈቱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(18 votes)

አቶ መላኩ ፋንታ እና አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ በ3 መዝገቦች ተከሰዋል
ሶስት ተጠርጣሪዎች በነፃ ተለቀዋል

የፌደራሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ፤ ከ40 በላይ በሚሆኑ የገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ባለስልጣናት እና የቅርንጫፉ ጽ/ቤት ሠራተኞች እንዲሁም ከባለስልጣናቱና ሠራተኞች ጋር ተመሳጥረው ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በተባሉት ባለሀብቶች ላይ 8 የክስ መዝገቦች አደራጅቶ ከፈተ፡፡ በምርመራ ቀጠሮ ላይ የቆዩ 3 ተጠርጣሪዎች በነፃ ሲለቀቁ፣ ቀደም ሲል በዋለው ችሎት ምርመራቸው አልተጠናቀቀም ተብለው እንደገና ወደ ምርመራ ቀጠሮ የተመለሱት ተጠርጣሪዎች ባሉበት ሆነው እስከ ጳጉሜ 1 ቀን 2005 የምርመራ ስራው እንዲቀጥል ተብሏል፡፡
የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ የከፈታቸው 8 መዝገቦች በሚኒስትር ማዕረግ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፋንታ እና አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ በሶስት መዝገቦች ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆች በየደንበኞቻቸው ላይ የቀረበው የክስ ጭብጥ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ቢሆንም ፍ/ቤቱ እስከቀጠሮ ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲደርሳችሁ ይደረጋል የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾችም በቀጣይ ቀጠሮ ሲቀርቡ የክሱ ጭብጥ እንደሚነበብላቸው ተገልጿል፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን፤ የባለስልጣኑ ሠራተኞች በነበሩት በአቶ ንጉሴ ክብረት፣ አቶ ጌታቸው አሰፋ እና አቶ ምሣሌ ወ/ስላሴ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ በማጠናቀቁና ክስ እንደማይመሰረትባቸው በማረጋገጡ በነፃ እንዲለቀቁለት ጠይቆ፣ ፍ/ቤቱ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል በእነ አቶ ገ/ዋህድ መዝገብ ተካተው ምርመራ ሲካሄድባቸው የነበሩት አቶ ሙሌ ጋሻው በመሃንዲስነት ሲሰሩ በነበሩበት የኦሮሚያ ክልል ፍ/ቤት ጉዳያቸው እንዲታይ አቃቤ ህግ አመልክቷል፡፡ ተጠርጣሪውም ፈቃደኛነታቸውን በመግለጻቸው ፍ/ቤቱ የአቃቤ ህግን ጥያቄ ተቀብሎ ጉዳያቸው በክልሉ ፍ/ቤት እንዲታይ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል የኦዲት ምርመራው ባለመጠናቀቁ አቃቤ ህግ፣ በአቶ ተክለአብ ዘረአብሩክ፤ አቶ ምህረተአብ አብርሃ፣ አቶ በእግዚአብሔር አለበል እና አቶ ፍፁም ገ/ማርያም ላይ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀ ቢሆንም ፍ/ቤቱ ከተጠየቀው ጊዜ ቀጠሮ 8 ቀን ብቻ በመፍቀድ ተጠርጣሪዎች ባሉበት ማረፊያ ቤት ቆይተው ለጳጉሜ 1 ቀን 2005 እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የክስ መዝገብ የተከፈተባቸውን ተጠርጣሪዎች በ15ኛ ወንጀል ችሎት በኩል ክሳቸው እንዲታይ ለጥቅምት 11 እና 12 ቀን 2005 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 22176 times