Saturday, 31 August 2013 12:14

ህይወት ለመስጠት ህይወትን ማጣት!

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(3 votes)

ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በየቀኑ 68፣ በየሰዓቱ 3 ሴቶች ህይወታቸው ያልፋል
በአገራችን ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በየቀኑ 68 ሴቶች በየሰዓቱ ደግሞ 3 እናቶች ህይወታቸው ያልፋል፡፡ የአብዛኛው እናቶች ሞት ደግሞ የሚከሰተው በደም መፍሰስ፣ በተራዘመ ምጥና በከፍተኛ የደም ግፊት ሳቢያ ነው፡፡ ለዚህ ችግር ዋንኛው ምክንያትም የጤና ተቋም በአካባቢ አለመኖር፣ የትራንስፖርት ችግርና ህብረተሰቡ በጤና ተቋማት መውለድ እንደሚገባው በቂ ግንዛቤ አለመኖር መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡
                                          .=========.
ከምዕተ አመቱ ግቦች አንዱ የሆነውን የእናቶችና ህፃናት ሞት ለመቀነስ በየክልሉ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ቢነገርም ችግሩ ግን እምብዛም መሻሻሎችን አለማሳየቱንና በተያዩ ክልሎች ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች የሚሞቱ እናቶችና ህፃናት ቁጥር አለመቀነሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአገራችን በየአመቱ 2.8 ሚሊዮን እናቶች የሚያረግዙ ሲሆን ከእነዚህ እናቶች መካከል በሰለጠነ ባለሙያ ታግዘው የሚወልዱት 10% የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 90% የሚሆኑት እናቶች ዛሬም የሚወልዱት ያለማንም እርዳታ በቤታቸው ውስጥ ነው፡፡ በአገራችን ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በየቀኑ 68 ሴቶች በየሰዓቱ ደግሞ 3 እናቶች ህይወታቸው ያልፋል፡፡ የአብዛኛው እናቶች ሞት ደግሞ የሚከሰተው በደም መፍሰስ፣ በተራዘመ ምጥና በከፍተኛ የደም ግፊት ሳቢያ ነው፡፡
ለዚህ ችግር ዋንኛው ምክንያትም የጤና ተቋም በአካባቢ አለመኖር፣ የትራንስፖርት ችግርና ህብረተሰቡ በጤና ተቋማት መውለድ እንደሚገባው በቂ ግንዛቤ አለመኖር መሆናቸውም ተጠቅሷል። እናቶች ወደ ጤና ተቋማት ሄደው በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዳይወልዱ ያደርጓቸዋል ከሚባሉት ጉዳዮች መካከል “ሶስቱ መዘግየቶች” እየተባሉ የሚገለፁት ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መዘግየቶች መካከል የመጀመሪያው በምጥ የተያዘችው ሴት ወደ ጤና ጣቢያ (ጤና ተቋም) ለመሄድ በመወሰን ላይ የሚኖረው መዘግየት ነው፡፡ በምጥ ላይ ያለችው እናት ወደ ጤና ተቋማት ሄዳ እንድትገላገል ውሳኔ የሚተላለፈው በአብዛኛው በባል ወይም በባል ቤተሰቦች ይሆናል፡፡ ይህም ሴቲቱ በጊዜ ወደ ጤና ተቋማቱ እንዳትሄድ ያዘገያታል፡፡ ሁለተኛው መዘግየት የምንለው ደግሞ ከውሳኔው በኋላ እናቲቱን ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ የሚወሰደው መዘግየት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በትራንስፖርት አለመኖር፣ በመንገድ ችግር እና መሰል በሆኑ ምክንያቶች የሚፈጠረው መዘግየት ነው፡፡ ሶስተኛው መዘግየት እናቲቱ ጤና ጣቢያ ከደረሰች በኋላ የሚፈጠርና በጊዜውና በወቅቱ እርዳታ ማግኘት ባለመቻልዋ ምክንያት ለጉዳት የምትዳረግበት መዘግየት ነው፡፡ እነዚህ 3 መዘግየቶች በርካታ እናቶችን ያለ አግባብ እንድናጣቸው ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ተቋቁመው እርጉዝ እናቶች በጤና ተቋማት ውስጥ እንዲወልዱ በተለያዩ መንገዶች ጥረት የሚያደርጉና ለውጥ እያመጡ ያሉ ቦታዎች ናቸው ከተባሉ አካባቢዎች ጥቂቶቹን ሰሞኑን ለማየት እድል አግኝቼ ነበር፡፡
ቦታው ከአዲስ አበባ በ620 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ስፍራው በትግራይ ክልል ውስጥ ማይጨው እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ወደዚህ ስፍራ ለመምጣቴ ዋንኛው ምክንያቴ ደግሞ የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም (IFHP) ከዩኤስ ኤይዲ (USAID) ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ፣ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በእናቶችና ህፃናት ጤና ዙሪያ እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት ለማየት ነው። የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም በአሜሪካው አለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የገንዘብ ድጋፍ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ፕሮግራም ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም በቤተሰብ እቅድ፣ በእናቶችና ህፃናት ጤና ዙሪያ፣ በኤችአይቪ ኤድስ፣ በስርዓተ ፆታ እና መሰል በሆኑ የጤና ዘርፎች ላይ ከተለያዩ ክልሎች ጋር በጋራ የሚሰራ ነው፡፡ ፕሮግራሙ በዋናነት በፓዝ ፋይንደር ኢትዮጵያና በGSI የተቀናጀ ድጋፍ በጋራ የሚሰራ ሲሆን በትግራይ፣ በአማራ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉልና በሶማሊያ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ በ301 ወረዳዎች ውስጥ ይንቀሳቀሳል፡፡ ፕሮግራሙ በሚሰራባቸው ክልሎች ውስጥ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉና እንዴት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የሚከታተል የቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴ በአገር አቀፍ ደረጃ አቋቁሞ በየሶስት ወሩ ስራዎቹ ባሉባቸው አካባቢዎች እየተዘዋወር ይጐበኛል፡፡
ወደ ስፍራው ያቀናውና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መ/ቤቶች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም የሥራ ኃላፊዎችና የ(USAID) ተወካዮችን ያካተተው ቡድን፤ ጉብኝቱን የጀመረው ከታሪካዊቷ የማይጨው ከተማ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው መስዋእቲ ጤና ጣቢያ ነው፡፡ ስፍራው ጣሊያን አገራችንን ወርራ አብዛኛውን የትግራይ ክልል በተቆጣጠረችበት ወቅት ከፍተኛ የሞት ሽረት ትግል ተካሂዶ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ከፍተኛ መስዋእትነትን ከፍለው በርካታ ጣሊያኖች በመደምሰስ አካባቢውን ነፃ ያወጡበት ስፍራ በመሆኑ መስዋእቲ የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ይነገራል፡፡ በአካባቢው ለአገራቸው ክብርና ነፃነት ሲሉ ህይወታቸውን ላሳለፉት ኢትዮጵያውያን የመታሰቢያ ሐውልትም ተሰርቶላቸዋል፡፡
የመስዋእቲ ጤና ጣቢያ ሰናይ፣ ስምረት፣ ተ/አያና፣ መሆኒ ለተባሉ ቀበሌዎች ጭምር አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ አካባቢው ለጉዞ እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ቀበሌዎችም የሚገኙበት ሲሆን በእነዚህ ስፍራዎች የሚኖሩ እርጉዝ እናቶችን ወደ ጤና ጣቢያው ለማምጣት የአካባቢው ወጣቶች እየተደራጁ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እርጉዝ እናቶች የወሊድ ጊዜያቸው ከመድረሱ በፊት ወደ ጤና ጣቢያው በመምጣት እስኪወልዱና ከወለዱም በኋላ እስኪጠነክሩ ድረስ የሚቆዩበት ቤት ይዘጋጅላቸዋል፡፡ ማህበረሰቡ “አንድ ጣሳ ለአንዲት እናት” በሚል መርህ እያዋጣ ለወላዷ ሴት ገንፎና አጥሚት እንዲዘጋጅላት ያደርጋል፡፡ በአንዳንድ ስፍራዎችም ከተለያዩ ድርጅቶች በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የዱቄት፣ የስኳርና የአልባሳት ድጋፍ እንዲሰጥ ይደርጋል፡፡ ይህ አሰራርም ወደ ጤና ጣቢያው በመምጣት የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ለመጨመር እንዳስቻላቸው በመስዋእቲ ጤና ጣቢያ ውስጥ ያገኘናቸው የጤና ባለሙያዎች ገልፀውልናል፡፡
በመኸን፣ በኩኩፍቶና በሰመር መለስ ጤና ጣቢያዎችም በተመሳሳይ መንገድ ወደ ጤና ተቋማት እየሄዱ የሚወልዱ እርጉዝ እናቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተነግሮናል፡፡
በአካባቢው ባሉ አንዳንድ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በመግባት ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሩንም፤ አሁን አሁን ወደ ጤና ተቋማት እየሄዱ መውለድና የህክምና እርዳታ ማግኘት የተለመደ ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ እርጉዝ ሚስቱን ወደ ጤና ተቋም በመውሰድ እንድትገላገል ያላደረገ አባወራ፤ በአካባቢው እንዲወገዝና እንዲገለል በማድረግ እናቶች በእርግዝናና በወሊድ ጊዜ ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄዱ የመቀስቀሱን ስራ የአካባቢው የልማት ሠራዊትና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እየተገበሩት ያለ ጉዳይ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ጤና ጣቢያዎች ከእርግዝናና ከወሊድ አገልግሎት በተጨማሪ የፌስቱላ ችግር ያጋጠማቸው ሴቶች ህክምና እንዲያኙ በማድረግ ወደቀድሞ ጤንነታቸው የመመለስ ተግባሩንም እየከወነ ይገኛል። በመኸን ጤና ጣቢያ አግኝተን ያነጋገርናትና ቀድሞ የፌስቱላ ችግር ተጠቂ አሁን ደግሞ የፌስቱላ አምባሳደር በመሆን እየሰራች ያለችው ስንዳዮ ዳርጐ አንዷ ነች፡፡ የፓዝ ፋይንደር ኢትዮጵያ ተጠሪና የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም ኃላፊ ዶ/ር መንግሥቱ አስናቀ እንደገለጹት ከ66 ሚ.ዶ በላይ ተመድቦለት በሚንቀሳቀሰው በዚህ ፕሮጀክት በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ በሥርዓተ ፆታ፣ የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ እና በወባ በሽታ ላይ እንደሚሰሩና የፌስቱላ ችግር የገጠማቸው ሴቶች ህክምና የሚያገኙበትንና ወደቤታቸው ተመልሰው የቀድሞ ህይወታቸውን የሚመሩበትን መንገድ እንደሚያመቻች ተናግረዋል።
የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እየተከናወኑ ባሉት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ከፍተኛ ለውጥ እየታየ መሆኑን የነገሩን የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ የዓለም ፀጋይ፤ መንግሥት ፕሮግራሞቹን የማስቀጠልና ለውጤታማነታቸው ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡ በክልሉ አሁንም በቤት ውስጥ የሚወልዱ እናቶች መኖራቸውንም ጠቁመው፣ በቤታቸውም ሆነ በጤና ተቋማት ውስጥ በሚወልዱበት ወቅት የሚሞቱ እናቶች እንዳሉም ገልፀዋል፡፡
የ2005 DHS (የሥነ ህዝብና ጤና ቅኝት) እንደሚያመለክተው ከአንድ መቶ ሺህ ወላድ እናቶች ውስጥ 673 የሚሆኑት ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ይህችን ዓለም ይሰናበታሉ፡፡ ይህ አሀዝ በ2011 በተደረገው የ DHS (የሥነህዝብና ጤና ቅኝት) ቁጥሩ ወደ 676 አሻቅቧል፡፡ የጥናቱ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ አሀዙ በእናቶችና ህፃናት ሞት ላይ ይህንን ያህል የጐላ ለውጥ አለመታየቱንና ዛሬም በርካታ እናቶችና ህፃናት ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ህይወታቸው እያለፈ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚያወጣቸው መረጃዎች በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታየው የእናቶችና ህፃናት ሞት ቁጥር መቀነስ እያሳየ ነው። ሚኒስትር መ/ቤቱ ከምዕተ አመቱ ግቦች መካከል የሚጠቀሰው የእናቶችና ሕፃናት ሞት መቀነስ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነና አንዲትም እናት ከወሊድ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች መሞት የለባትም በሚል መሪ ቃል እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ በተደጋጋሚ ቢገለፅም፣ ዛሬም በርካታ እናቶች ከወሊድ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች እየሞቱብን ነው።
የDHS ጥናቱን መሰረት ብናደርግ እንኳን አንዲትም እናት እየተባለ መፈክር በሚነገርባት አገር፣ ዛሬም ከ100ሺ እናቶች 676 ያህሉ ህይወት ለመስጠት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ የእነዚህን እናቶች ሞት ለመታደግ ይረዳሉ ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል የህክምና ተቋማት በሌሉባቸው ወይንም አገልግሎቱን ለማግኘት አስቸጋሪ በሆኑባቸው አካባቢዎቹ ተቋማቱ እንዲቋቋሙ ማድረግ፣ በሙያው የሰለጠኑ ባለሙያዎች በስፋት እንዲኖሩና ባለሙያዎቹ የሙያ ሥነምግባራቸውን ጠብቀው ለህብረተሰቡ ተገቢውን ግልጋሎት እንዲሰጡ ማድረግና አገልግሎቶቹ ለሁሉም ማህበረሰብ ተደራሽ የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። እናቶች ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ እንዲወልዱ በመቀስቀስ ብቻ (አገልግሎቶቹን ዝግጁ ሳያደርጉ) በእርግዝናና በወሊድ ሳቢያ የሚሞቱ እናቶችንና ህፃናትን መታደግ አይቻልምና !

Read 3805 times Last modified on Saturday, 31 August 2013 12:23