Print this page
Saturday, 31 August 2013 12:52

በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳካለት የኢትዮጵያ ቡድን መሸለሙ ይጠበቃል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

             በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሞላ ጎደል ስኬታማ የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቶች ቡድን በመንግስት እና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት በኩል መቼ እንደሚሸለም አልታወቀም፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የልዑካን ቡድኑን ወጤታማነት እና ድክመት በመገምገም በቅርቡ ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጥ የሚጠበቅ ሲሆን ለተገኘው ስኬት አስፈላጊውን የማበረታቻ ሽልማት ለማከናወን በዝግጅት ላይ እንደሆነ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው የሜዳልያ ደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ በሰበሰበቻቸው 10 ሜዳልያዎች ከዓለም 6ኛ እንዲሁም ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን ማግኘቷ ይታወሳል፡፡ ሞስኮ ላይ የኢትዮጵያ ቡድን በድምሩ 10 (3 የወርቅ፤ 3 የብርና 4 የነሐስ ) ሜዳልያዎች መሰብሰቡ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛው የሜዳልያ ብዛት ሲሆን አስሩ ሜዳልያዎች በ10 የተለያዩ አትሌቶች መገኘታቸው፤ በአዳዲስ የውድድር መደቦች ለመጀመርያ ጊዜ የተገኙ ሜዳልያዎች መኖርና ወጣት እና ተተኪ አትሌቶች በውጤታማነት መውጣታቸው የስኬቱን ታሪካዊነት አጉልቶታል፡፡ የኢትዮጵያን 3 የወርቅ ሜዳልያዎች በ10ሺ ሜትር ሴቶች ጥሩነሽ ዲባባ፤ በ800 ሜትር ወንዶች መሃመድ አማን እንዲሁም በ5ሺ ሜትር ሴቶች መሰረት ደፋር አስመዝግበዋል፡፡ ሶስቱን የብር ሜዳልያዎች ኢብራሂም ጄይላን በወንዶች 10ሺ ሜትር፤ ሃጎስ ገብረህይወት በወንዶች 5ሺ ሜትር እንዲሁም ሌሊሳ ዴሲሳ በወንዶች ማራቶን ሲጎናፀፉ አራቱን የነሐስ ሜዳልያዎች ደግሞ በ10ሺ ሜትር ሴቶች በላይነሽ ኦልጅራ፤ በ3ሺ መሰናክል ሶፍያ አሰፋ፤ በ5ሺ ሜትር ሴቶች አልማዝ አያና እንዲሁም በወንዶች ማራቶን ታደሰ ቶላ አግኝተዋቸዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ ውድድሮች ማግስት ውጤታማ ለሚሆኑ የአትሌቶች ቡድን አባላት እና ለአጠቃላይ ልዑካኑ በመንግስት እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት በኩል የገንዘብ፤ የማዕረግ እና ልዩ ልዩ የክብ ሽልማት ይሰጥ የነበረ ሲሆን ለአሁኑ ቡድን የሚደረገው ርብርብ ያነሰ መስሏል፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሜዳልያ ላገኙ አትሌቶች የህይወት ዋስትና በመግባት ማበረታቱን ጀምሯል፡፡
በተያያዘ ዜና በዓለም ሻምፒዮናው ለሜዳልያ አሸናፊዎች እና እስከ ስምንተኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች ከቀረበው እስከ 7 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የሽልማት ገንዘብ በ10 ሜዳልያዎች እና በወንዶች ማራቶን በቡድን ውጤት በተገኘው ተጨማሪ የወርቅ ሜዳልያ ኢትዮጵያ 330ሺ ዶላር ስታገኝ በአጠቃላይ 12 ሜዳልያ የሰበሰበችው ኬንያ ድርሻዋ 640ሺ ዶላር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሜዳልያ ተሸላሚዎች ከሰበሰበችው 330ሺ ዶላር ባሻገር እስከ ስምንት ባለው ደረጃ አራተኛ የወጡ 2 ፤ 5ኛ የወጡ 3፤ ሰባተኛ የወጡ 2 እና 8ኛ የወጡ 2 አትሌቶች በማስመዝገቧ በአጠቃላይ ከቀረበው የሽልማት ገንዘብ 408ሺ ዶላር ስታገኝ የኬንያ ድርሻ 891ሺ ዶላር ሆኗል፡፡
በሌላ በኩል የኬንያ ቡድን በሞስኮው የዓለም ሻምፒዮና አመርቂ ውጤት አላመጣም በሚል ከፍተተኛ ትችት ከሚዲያው እና ከአንዳንድ ባለሙያዎች እየደረሰበት ሰንብቷል፡፡ በወንዶች ማራቶን የኬንያ አትሌቶች በኡጋንዳ፤ በኢትዮጵያ፤ በጃፓንና በብራዚል ማራቶኒስቶች መበለጣቸው፤ በ3ሺ መሰናክል ከ1 እስከ 3 ደረጃ አለመገኘቱን የጠቀሱት ተቺዎቹ ሞስኮ ላይ የኬንያ ቡድን በቡድን ስራ እና በሚማርክ ቅንጅት አልሰራም በማለት ተቃውመዋል፡፡ የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት በዓለም ሻምፒዮናው ሜዳልያ ላመጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ሰሞኑን ያበረከቱ ሲሆን፤ ለወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዎች 11495 ዶላር ፤ ለብር ሜዳልያ 8621 ዶላር እንዲሁም ለነሐስ ሜዳልያ 5748 ዶላር ተሰጥቷቸዋል፡፡
በአጠቃላይ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው የሜዳልያ ስብስብ ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ 1ኛ ሆና የጨረሰችው ራሽያ በ7 የወርቅ፤ 4 የብርና 6 የነሐስ ሜዳልያዎች ሲሆን የደረጃ ሰንጠረዡን መሪነት ከአሜሪካ ስትነጥቅ ከ12 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ አሜሪካ በ6 የወርቅ፤ 14 የብርና 5 የነሐስ ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች፡፡ ጃማይካ በ5 የወርቅ፤ በ2 የብርና በ1 የነሐስ ሜዳልያ ሶስተኛ ፤ ኬንያ በ5 የወርቅ፤ በ4 የብርና በ3 የነሐስ ሜዳልያዎች 4ኛ እንዲሁም ጀርመን በ4 የወርቅ፤ በ2 የብርና በ1 የነሐስ ሜዳልያ አምስተኛ ሆነዋል፡፡ በሻምፒዮናው የአፍሪካ አገራት በነበራቸው ተሳትፎ 8 አገራት ብቻ የሜዳልያ ስኬት አግኝተዋል፡፡ ከአፍሪካ አህጉር ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃ የያዘችው ኬንያ ስትሆን ኢትዮጵያ ሁለተኛ ሆናለች፡፡ ሌሎች አፍሪካን የወከሉ አገራት ኡጋንዳ በወንዶች ማራቶን ባገኘችው ብቸኛ የወርቅ ሜዳልያ ሶስተኛ፤ አይቬሪኮስት በ2 የብር ሜዳልያዎች አራተኛ፤ ናይጄርያ በ1 የብርና በ1 የነሐስ ሜዳልያዎች አምስተኛ፤ ቦትስዋና በ1 የብር ሜዳልያ ስድስተኛ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ እና ጅቡቲ በእያንዳንዳቸው በወሰዷቸው አንድ ነሐስ ሜዳልያዎች ሰባተኛ ደረጃን ለማግኘት ችለዋል፡፡ በዓለም ሻምፒዮና በተሳተፉባቸው የውድድር መደቦች ከ1 እስከ ስምንት ባለው ደረጃ ባስመዘገቡት ውጤት በመመስረት በተሰራው ደረጃ ኬንያ 3ኛ ስትሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ስድስተኛ ነች፡፡ በሜዳልያ ስብስብ እና በአጠቃላይ ውጤት በወጣው ደረጃ አሜሪካ በ282 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ስታገኝ፤ ራሽያ በ83 ነጥብ ሁለተኛ፤ ኬንያ በ139 ነጥብ ሶስተኛ፤ ጀርመን በ102 ነጥብ አራተኛ፤ ጃማይካ በ100 ነጥብ አምስተኛ፤ ኢትዮጵያ በ97 ነጥብ ስድስተኛ፤ እንግሊዝ በ79 ነጥብ ሰባተኛ እንዲሁም ዩክሬን በ51 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የምንጊዜም የሜዳልያ ስብስብ የደረጃ ሰንጠረዥም ለውጦች ታይተዋል፡፡ በ14 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች የሰበሰበቻቸውን ሜዳልያዎች 300 (138 የወርቅ፤ 88 የብርና 74 የነሐስ) ያደረሰችው አሜሪካ አንደኛነቷን እንዳስጠበቀች ናት፡፡ ራሽያ 168 ሜዳልያዎች (53 የወርቅ ፤ 60 የብርና 55 የነሐስ)፤ ኬንያ 112 ሜዳልያዎች (43 የወርቅ፤ 37 የብርና 32 የነሐስ) ፤ ጀርመን 101 ሜዳልያዎች (35 የወርቅ፤ 28 የብርና 38 የነሐስ)፤ ጃማይካ 98 ሜዳልያዎች (24 የወርቅ፤ 42 የብርና 32 የነሐስ)፤ ሶቭዬት ህበረት 75 ሜዳልያዎች (22 የወርቅ፤ 25 የብርና 28 የነሐስ) እንዲሁም ኢትዮጵያ 64 ሜዳልያዎች (22 የወርቅ፤ 19 የብርና 23 የነሐስ) በ14 የዓለም ሻምፒዮናዎች የተሳትፎ ታሪካቸው በማስመዝገብ እስከ 7 ያለውን ደረጃ አከታትለው ይዘዋል፡፡

Read 6274 times
Administrator

Latest from Administrator