Saturday, 07 September 2013 09:57

በከሰል ጭስ ታፍነው ሦስት ሴቶች ሞቱ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

ከሐምሌ ወዲህ 11 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በጭስ ሞተዋል
አዲስ አበባ ቦሌ መንገድ አካባቢ ሦስት ወጣት ሴቶች በጭስ ታፍነው የሞቱ ሲሆን፤ ባለፈው ሃምሌ 9 ሰዎች በተመሳሳይ ምክንያት ህይወታቸው እንዳለፈ በመግለጽ፣ የከሰል አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ፡፡
ቦሌ መንገድ የአውሮፓ ህብረት ቢሮ አካባቢ በወጥ ቤት ተቀጥራ ለ5 ወር ስትሰራ የቆየችው ይርጋለም ሀጐስ ብቻዋን አልነበረችም፡፡ በሶስት ወር የምትቀድማት የጽዳት ሰራተኛ ጽጌረዳ ደምሴና በሞግዚትነት የመጣችው ውቢት ደበበ አብረዋት ነበሩ፡፡ ውቢት ከተቀጠረች ገና ሁለት ቀኗ ነው፡፡ ተቀራራቢ እድሜ ያላቸው ሦስቱ የስራ ባልደረቦች በስራ የደከመ ሰውነታቸውን ለማሳረፍ የጋራ መኝታ ክፍላቸው ገብተው ጋደም ያሉት ከምሽቱ 4 ሰዓት ተኩል ገደማ ነው፡፡ ምሽቱን አጥንታቸው ድረስ ከዘለቀው ብርድ ለመገላገል የከሰል ማንደጃ አስገብተዋል፡፡
ከዚያ በኋላ ድምፃቸው አልተሰማም፡፡ ጥዋትም ያለወትሯቸው ከእንቅልፍ ሳይነሱ አረፈዱ ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡ በሞግዚትነት የተቀጠረችው ውቢት፣ የህፃናቱን ልብስ እንድትቀይር ስትፈለግ ነው፣ የጥበቃ ሰራተኛው ሂድና ጥራት ተብሎ የተላከው፡፡ ሰዓቱ ረፍዷል፤ የመኝታ ክፍላቸው ግን አልተከፈተም፡፡ ፖሊስ መጠራት ነበረበት፡፡ ከካራማራ ፖሊስ ጣቢያ የመጡ ፖሊሶች መኝታ ክፍሉን ከፍተው ሲያዩ ሦስቱ የስራ ሰዎች በድን ሆነዋል፡፡ የወጣቶቹን ሴቶች ህይወት የቀጠፈው የከሰል ማንደጃም በከፊል አመድ በከፊል ያልተቀጣጠለ ከሰል ይዞ ይታያል፡፡
በእርግጥ ፖሊስ በችኮላ ምርመራውን አልደመደመም፡፡ ሌላ ችግር ይኖር እንደሆነ አስሷል፡፡ ሴቶቹ የሞቱት ከተቀጣጣይ ከሰል በሚወጣ ጋዝ እንደሆነ የተረጋገጠው፣ በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ ነው፡፡
በክረምት እና ብርድ በሚበረታባቸው ወራት፣ በጭስ ታፍኖ የመሞት አደጋ እንደሚበራከት የተናገሩት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን መሪ ም/ኢንስፔክተር ዘውዴ አሸናፊ፣ ብርድ ለመከላከል ቤት ዘጋግቶ ከሰል ማቀጣጠል አደገኛ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ከሚቀጣጠል ከሰል የሚመነጨውና ካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ ተብሎ የሚታወቀው ጋዝ ቀለም ወይም ሽታ ስለሌለው ብዙ ሰዎች ምንም ሳይታወቃቸው እንደሚሞቱ ም/ኢን ዘውዴ ገልፀው፤ የጭሱን ገዳይነት አለመገንዘብ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል፡፡
በአንድ ቤት ውስጥ በርካታ ሰዎች ሲሞቱ ይታያል በማለት የአደጋውን ክብደት የገለፁት ም/ኢ ዘውዴ፣ በተለይ የቤት ሰራተኞች ጭሱ ያልወጣ ከሰል ክፍላቸው ውስጥ አስገብተው ሲሞቁ እዚያው በተኙበት ህይወታቸው እንደሚይልፍ ጠቁመዋል፡፡እነ ውብሸት ታዬ በድጋሚ ይቅርታ ሊጠይቁ ነው
ሰላም ገረመው
የይቅርታ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ ረቡዕ የተነገራቸው የአውራምባ ታይምስ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና የኢብአፓ ፓርቲ አመራር አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚያብሄር፤ በየአመቱ የይቅርታ ጥያቄ ማቅረብ ስለሚቻል በድጋሚ እንደሚሞክሩ ቤተሰቦች ተናገሩ፡፡
በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አመፅ የሚያስነሳ ፅሁፍ አቅርባችኋል በሚል የ14 እና 17 አመት እስር እንዲሁም ከ30ሺ ብር ያላነሰ ቅጣት እንደተፈረደባቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ለይቅርታ ቦርድ በደብዳቤ ጥያቄ ያቀረቡት ከአንድ አመት ከአራት ወር በፊት እንደሆነ የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ባለቤት ወ/ሮ ብርሃኔ ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ ይቅርታ እንደሚያገኙ ጠብቀን ነበር የምትለው ወ/ሮ ብርሃኔ፤ በተመሳሳይ ጉዳይ ሁለት የስዊድን ዜጐችም ይቅርታ ተደርጐላቸው ከእስር እንደተፈቱ በማስታወስ፣ በኢትዮጵያዊነታቸው አዎንታዊ ምላሽ እንደሚያገኙ ተስፋ ነበረን ብላለች፡፡
የይቅርታ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ ሲነገራቸው በጣም ደንግጠናል ያለችው ወ/ሮ ብርሃኔ፤ በህጉ መሠረት ዘንድሮም የይቅርታ ጥያቄያቸውን እንደገና ለማቅረብ አስበዋል ብላለች፡፡
ከጋዜጠኛ ውብሸት እና ከአቶ ዘሪሁን ጋር የተከሰሱት ሂሩት ክፍሌ ያቀረቡት ተመሳሳይ የይቅርታ ጥያቄ ውድቅ እንደተደረገ በደብዳቤ የተገለፀላቸው ከሦስት ሳምንት በፊት እንደነበር ይታወሳል፡፡
የ14 አመት እስርና የ30ሺህ ብር ቅጣት ተፈርዶባት ይግባኝ ያቀረበችው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ቅጣቱ ወደ 5 ዓመት ዝቅ እንደተደረገላት ይታወሳል፡፡

Read 14451 times